Wednesday, 03 June 2026 14:23

በአርሲ ለደረሰው ጥቃት አቡነ ማትያስ ለመንግሥት ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ አስተላለፉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በአርሲ ሀገረ ስብከት በኦርቶዶክሳውያንና በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ ጠንከር ያለ አባታዊ የኀዘንና የማሳሰቢያ መልእክት አስተላልፈዋል።
“የጸጥታ አካላትና ኃላፊዎች ከምንም በላይ በታሪክ የሚጠየቁት በሥልጣን ዘመናቸው ለዜጎች ደኅንነት በሚከፍሉት ዋጋ” መሆኑን ያስገነዘቡት ፓትርያርኩ፤ በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ፣ በዋቤ እና በሙኔሳ ወረዳዎች የተፈጸመውን ድርጊት በተሰበረ ልብ እንደሰሙት ገልጸዋል።
መቶ ዓመታት ያስቆጠረው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተቃጠለበት፣ እንዲሁም የካራ ኩፍቴና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተዘረፈበት በዚህ ክፉ ቀን፤ በርካታ ምእመናን በግፍ መሰዋታቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፓትርያርኩ አክለውም፣ ቤተ ክርስቲያን በምድራዊ መከራ ውስጥ ያሉትን ምእመናን በምታጽናናበት በዚህ ወቅት ራሷ በፈተና ውስጥ ሆና ከመቸገሯም በላይ፣ በአርሲ ምድር በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በደልና ግፍ በሁላችንም ልቡና ውስጥ “እስከ መቼ?” የሚል የቁጭት እና የኀዘን ጥያቄን መፍጠሩን አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያን ለሰላም፣ ለይቅርታና ለሰው ልጆች ክብር ሁል ጊዜ የምትቆም መሆኑን የገለጹት አቡነ ማትያስ፣ መላው ኢትዮጵያውያንና ምእመናን በወንድማማችነት መንፈስ ተጋግዘው የተፈናቀሉ ወገኖችን በቁሳቁስና በጸሎት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም ፈጣሪ ይህንን የኀዘን ሰዓት በምሕረቱ ያሳልፍ ዘንድ፣ በግፍ የሞቱትን ነፍሳት በመንግሥቱ እንዲቀበልና የተጎዱትንም በቸርነቱ እንዲያጽናና አባታዊ የጸሎት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
Read 1971 times