በምሥራቅ አርሲ ማንነትንና ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መገደላቸውን፣ ቤተክርስቲያን መቃጠሉንና ዜጎች መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አስታወቀ። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፣ ለዚህ ዓይነቱ ዘግናኝ ጥቃት ዋነኛው ምንጭ የአገሪቱ ፖለቲካ በማንነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ መሰል ጥቃቶችን የመከላከል ቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው የአካባቢው አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ተፈትነው መውደቃቸውን በጥብቅ ተችቷል።
ኢዜማ በዚህ ኢሰብአዊ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፣ መንግሥት በአስቸኳይ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ጥፋተኞችን ለይቶ አስተማሪና ሕጋዊ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል። አክሎም፣ በማንነት ላይ የተመሠረተው ፖለቲካ አገርን ጨርሶ አንድ በአንድ ሳይበትን ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀዳሚ የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ፓርቲው በብርቱ አስገንዝቧል።

