Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 08:27

ድንጋይ ፈጭቶና አቡክቶ ጂብሰም ቦርድ የሚጋግረው ፋብሪካ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለግንባታው 120ሚ. ያህል ብር ወጥቷል

* በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲሆን፤ በአፍሪካ 3ኛ እንደሆነ ይነገራል

* በዓመት 4ሚ ካ.ሜ ቦርድና 95ሚ. ኩንታል የጂፕሰም ዱቄት ያመርታል

“የድንጋይ ዳቦ ዘመን” ሲባል እርግጠኛ ነኝ የጥንቱን ደግ ዘመን ለመግለጽ እንጂ “ድንጋይ ዳቦ” ሆኖ አይደለም፡ዛሬ ግን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው “የድንጋይ እንጀራ” እየተጋገረ ነው ቢባሉ ምን ይላሉ?

እርስዎ ከሐሳብዎ ጋር ትንሽ ሲሟገቱ፤ እኔ ጉዳዩን ላጫውትዎት፡፡ ነገሩ ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው ወፍጮ ቋት ውስጥ ድንጋይ ይጨመርና በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተፈጭቶ ይደቃል፡፡ የሚገርመው ነገር ድንጋይ ቀርቶ እህል እንኳ ሲፈጭ ብናኙ አካባቢውን ያለብሳል፡፡ እዚህ ግን ፋብሪካው ድንጋይ ሲፈጭ አካባቢው እንዳይበከል የሚከላከል መሳሪያ ስለተገጠመለት እየተግተለተለና እየተጥመለመለ ወጥቶ በአየር ላይ የሚበተን ጪስ አይታይም፡፡ ምርቱና ተረፈ-ምርቱ በተለያዩ መስመሮች ነው የሚጓዙት፡፡

የድንጋዩ ዱቄት ጉዞውን ቀጥሎ ግማሹ በ50 ኪ.ግ ከረጢት እየተሞላ ይሰፋል፣ ጂፕሰም ዱቄት ማለት ነው፡፡ ቀሪው ጉዞውን ይቀጥልና ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር ይደበላቅና ይቦካል፡፡ ከዚያም ሊጡ ወደ መጋገሪያ ይሄዳል፡፡ መጋገሪያው ታዲያ ምጣድ እንዳይመስላችሁ፡፡ ምጣድና አክንባሎው ወፍራም የካርቶን ወረቀት ነው፡፡ ሊጡ ታዲያ የቀረበበት ትሪ ላይ ያለውን ሥዕል እንደሚያሳይ እንጀራ ቀጭን አይደለም ወፍራም ነው፡፡

ማዞሪያው ሁለት ጡት አለው፡፡ በመስመሩ የመጣለትን ወፍራም ሊጥ መጋገሪያው ካርቶን ላይ ያሰፋል፡፡ ከዚያም በካርቶኑ አክንባሎ ተከድኖ ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ሊጡ በተለያዩ ሂደቶችና የሙቀት ደረጃዎች ውስጥ አልፎ ደርቆ፣ የኩባንያው ስም ታትሞበትና ዙሪያው ታፍፎ (ተቆርጦና ተስተካክሎ) ጂፕሰም ቦርድ ሆኖ ይወጣል፡፡ ፋብሪካው የሥራ ሂደቱን የሚያከናውነው በተገጠመለት ሶፍትዌር በመሆኑ አጠቃላይ ሂደቱን አንድ ባለሙያ ነው በኮምፒዩተር የሚከታተለው፡፡

ይህ ጂብሰም ድንጋይ ፈጭቶ ጂፕሰም ዱቄትና ቦርድ የሚያመርተው ዘመናዊ ፋብሪካ የት አገር ነው የሚገኘው በማለት ፍለጋ እንዳትባዝኑ፡፡ እዚሁ በአገራችን በምሥራቅ ጐጃም ዞን አባይ ሸለቆ አፋፍ ላይ ጉብ ባለችው ደጀን ከተማ በአንድ ባለሀብት የተገነባ ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው የዛሬ ሁለት ሳምንት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ በተገኙበት፣ በአማራ ክልላዊ መንግሥት

ርዕሰ ብሔሩ በአቶ አያሌው ጐበዜ ተመርቋል፡፡

ባለሀብቱ አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ ይባላሉ፡፡ አቶ ጌታቸው ማን ናቸው? ይህን የጂፕሰም ፋብሪካ ለመገንባት ምን አነሳሳቸው? የዚህ ግዙፍ ፋብሪካ ካፒታል ምንጭ ምንድነው የሚለው ራሱን የቻለ አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡

አቶ ጌታቸው ደርግ ከሥልጣን እስከወረደበት 1983 ዓ.ም ድረስ ምስኪን የመንግሥት መ/ቤት ሾፌር ነበሩ፡፡ ሕይወታቸው መለወጥ የጀመረው በኢሕአዴግና በአንድ መቶ ብር በገዟት የሎተሪ ቲኬት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ስለ ቀሪ ታሪካቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

 

 

እንዴት ወደ ቢዝነስ ዓለም ገቡ? መነሻ ካፒታልዎስ ምን ያህል ነበር?

እኔ ወደ ቢዝነስ የገባሁት ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ ሥልጣን በያዘበት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ከዕዝ ኢኮኖሚ አላቅቆ በነፃ ገበያ መርህ እንዲመራ ያደረገው የመጀመሪያው ዘርፍ ትራንስፖርት ነበር፡፡ ደርግ ከሥልጣን ሲባረር ለቀድሞው ዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ለዛሬው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ) የገዛችው መቶ (100) ስካንያ መኪናዎች ነበሩ፡፡

ኢሕአዴግ እነዚያ መኪናዎች በትራንስፖርት ዘርፍ ለተሳተፉ ግለሰቦች በሎተሪ እንዲተላለፉ አደረገ፡፡ የዕጣው ዋጋ 100 ብር ነበር፡፡ ሁለት ሺህ ያህል ሰዎች ተወዳድረን የዕድል ነገር ሆነና ከመቶ ሰዎች አንዱ ሆኜ ዕጣው ደረሰኝ፡፡ ከዚያም 85 ከመቶ በዕርዳታ ማስተባበሪያ ዋስትና፣ 15 ከመቶውን ደግሞ ቤት ነበረኝ እሱን አስይዤ 753ሺህ ብር ይመስለኛል ሠርቼ እንድከፍል አንድ መኪና ከነተሳቢው ተሰጥቶኝ ሥራ ጀመርኩ፡፡

ይህን ሥራ ከመጀመርዎ በፊት ምን ይሰሩ ነበር?

ከዚያ በፊት በተለያዩ ሦስት መ/ቤቶች ሠርቻለሁ፡፡ መጀመሪያ በርታ ኮንስትራክሽን ከጅማ - ጭዳ ፕሮጀክት ከዚያም ሙገር ሲሚንቶ በመጨረሻ ደግሞ በግብርና ሚ/ር ምርት ማሳደጊያ ግብአት አቅራቢ ኮርፖሬሽን እየሠራሁ ነው ሎተሪው የደረሰኝ፡፡

ሎተሪው ሲደርስዎት ደሞዝዎ ስንት ነበር?

370 ብር

በግል መሥራት ሲጀምሩ አልከበደዎትም?

አልከበደኝም፡፡ ከዚያ በፊትም በሾፌርነት ስሠራ ስለነበር በዚያው ቀጠልኩበት፡፡ ምንም አልከበደኝም፡፡

ቀደም ሲል በደሞዝ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ አሁን የመኪናውን ዕዳ መክፈል ቤተሰብ ማስተዳደር ስላለ ማለቴ ነው፡፡

ያማ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ባለንብረት ነኝ ብዬ ገንዘብ አላባክንም ነበር፡፡ በደሞዝ ነበር የምተዳደረው፡፡ ባለንብረት ከሆንኩ በኋላ የገንዘብ ጥቅም በደንብ ስለገባኝ ጊዜዬን በከንቱ አላባክንም፤ ሌት ተቀን ነበር የምሠራው፡፡

ያኔ የት የት ነበር የምትሠሩት?

ጭነት በተገኘበት ሁሉ እንሄድ ነበር፡፡ አሰብ፣ ጅቡቲ፣ ጐንደር፣ ትግራይ…ሁሉም ቦታ እሄድ ነበር፡፡

ዕዳዎን በምን ያህል ጊዜ ከፍለው ጨረሱ?

በአምስት ዓመት ነው የጨረስኩት፡፡

ዕዳዎን ከከፈሉ በኋላ ሌላ መኪና አልጨመሩም?

ጨምሬአለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ የመስፍን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ከዚያም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና በኋላም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚ/ር ዴኤታ የነበሩት አቶ አርከበ ዕቁባይ በብድር እንድወስድ አመቻቹልኝና አራት መኪና ገዝቼ፣ ከበፊቱ ጋር አምስት አደረስኩት፡፡ እነዚህ ይበቁኛል ብዬ አልተቀመጥኩም፡፡ እየሠራሁና ዕዳዬንም በየአምስት ዓመቱ ከፍዬ እያጠና ሌሎች መኪኖችም ገዛሁ፡፡

አሁን ስንት መኪኖች አሉዎት?

አሁን 22 ቦቴዋችና አራት የጭነት መኪኖች (ከነተሳቢ) በአጠቃላይ 26 መኪኖች አድርሻለሁ፡፡

ሌላ የተሰማሩበት ሥራ አለ?

ለቡ አካባቢ በ1997 ዓ.ም መሬት ወስደን አንድ ባለ 4 ፎቅ ሕን ሠራን፡፡ እዚያ ግቢ ውስጥ የቅባት እህሎች እያበጠርን ወደ ውጭ እንልክ ነበር፡፡ ያንን ሥራ አሁን ትተናል፡፡

ከውጭ ምን ታስገቡ ነበር?

ከውጭ እንኳ ምንም አናስመጣም፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ለመኪኖቹ ጐማና አንዳንድ መለዋወጫዎች እናስገባለን፡፡

ከሚያውቁት የትራንስፖርት ሥራ ወደማያውቁት የኢንዱስትሪ ዘርፍ መግባት ከባድ ውሳኔ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ሐሳብ ከየት መጣ?

እውነቱን ለመናገር ከሆነ፣ ዘርፉ ልምድ ለሌለው ሰው በጣም ከባድና ፈታኝ እንደሆነ እናውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ለየት ያለ ነገርና በአካባቢያችን ታሪክ መሥራት አለብን በማለት ወሰን፡፡ ከዚያም ወደ ኢንዱስትሪ ሚ/ር ሄደን የሲሚንቶ ፋብሪካ ለማቋቋም ስንጠይቅ ካፒታሉ ከባድና የማይቀመስ ሆነ፡፡ ስለዚህ ሲሚንቶውን ትተን የጂፕሰም ድቄት ለማምረት ተነሳን፡፡

መቼ?

የዛሬ ሦስት ዓመት፡፡ ነገር ግን ያም ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀረ፡፡ በጣም አስቀያሚ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው፡፡ ምክንያቱም ፋብሪካውን የገዛንበት የቻይና ኩባንያ የተሳሳተ መሳሪያ ነበር የሸጠልን፡፡

ለምን? በዝርዝር መለያ (specification) አይደለም እንዴ የተዋዋላችሁት?

ነው፡፡ ግን በጣም በዝርዝር አላየንም፡፡ እኛ የጂፕሰም ዱቄት የሚፈጭ ፋብሪካ ነው የጠየቅነው፡፡ የተሸጠልን ፋብሪካም ጂፕሰም ድንጋዩን በሚፈለገው ደረጃም አልሞ (አድቅቆ) ይፈጫል፡፡

ነገር ግን በሚፈለገው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ስለማያሞቀው ከወፍጮው ላይ አይላቀቅም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ለማግባባት ብንሞክርም ስምምነቱ ላይ ችግር ቢፈጠር፣ በዚያ አገር (በቻይና) ሕግ ይዳኛል ስለሚል ቻይና እየተመላለሱ በማያውቁት ቋንቋ ዓለም አቀፍ ጠበቃ አቁሞ መከራከር ተጨማሪ ጊዜና ገንዘብ  ከማባከን በስተቀር የማያዋጣ ሆኖ ስላገኘነው ከአንድ ዓመት በኋላ ተውነው፡፡

ቻይናውያን ጓደኞቼ “አገራችሁ ጂፕሰም ድንጋይ ሞልቷል፡፡ ለምን የጂፕሰም ቦርድ ፋብሪካ አትሞክርም?” በማለት መከሩኝ፡፡

ከዚያ በኋላ ስለ ጂፕሰም ቦርድ አዋጪነት ጥናት አድርገን ስላመንበት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ውል ተፈራርመን፣ ይኼው ዛሬ ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም የጂ ኤች ኢንዱስትሪያል ማኅበር የጂፕሰም ዱቄትና ቦርድ ፋብሪካዎች ለመመረቅ በቅተዋል፡፡

ጂ ኤች ምን ማለት ነው? ሥራውስ?

የባለቤቴ ስም ሐና ነው፡፡ ጂ ኤች፣ ጌታቸውና ሐና ኃ.የተ.የግል ኢንዱስትሪያል ማኅበር ማለት ነው፡፡ ጂ ኤች፣ ጂፕሰም ዱቄትና ቦርድ የሚያመርት ፋብሪካ ነው፡፡

ለሁለቱ ፋብሪካዎች ምን ያህል ካፒታል ወጣ?

እዚህ ያልደረሱ መሳሪያዎች አሉ፡፡ ዶዘር፣ ስካቬተር፣ የመሳሰሉ መሳሪያዎች መንገድ ላይ ናቸው፡፡ እነሱን ጨምሮ 120 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡

ጂፕሰም ድቄትና ጂፕሰም ቦርድ ምንድነው ጥቅማቸው?

ጂፕሰም ቦርድ ዘመናዊ ግድግዳ ይሆናል ኮርኒስ የተለያዩ ጌጣጌጦች ይሠራል፡፡ ዱቄቱ ለብዙ ነገር ይውላል፤ ጄሶ ማለትኮ ነው፡፡ ለቤት ማስዋቢያ፣ ለግድግዳ፣ ለቾክ፣ ለሆስፒታል፣ ለሲሚንቶ ግብአት፣ ለማዳበሪያ ያገለግላል፡፡

የሙከራ ምርት ጀምራችኋል?

አዎ! ጂፕሰም ዱቄት ትናንት አምርተን 400 ኩንታል ወደ አዲስ አበባ፣ 400 ኩንታል ደግሞ ወደ ባህርዳር ጭነናል፡፡

ቦርዱስ?

ቦርድ ገና ጅምር ነው፡፡ በአገራችን ያልተለመደና በጣም እንግዳ የሆነ ነገር ነው፡፡

ለምን? ቦርድ የሚያመርት ፋብሪካ የለም?

አዎ! የለም፡፡ ይህ ፋብሪካ ጂፕሰም ቦርድ በማምረት በአገራችን የመጀመሪያው ነው፡፡ ስለዚህ ለማስተዋወቅና ለማስለመድ ብዙ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ወደ ገበያ ለመግባት በአገር ውስጥና በጐረቤት አገሮች በስፋት ማስተዋወቅ ይጠበቅብናል፡፡

የጐረቤት አገሮችን ገበያ እንዴት አሰባችሁት? እነሱ አያመርቱም?

ከአፍሪካ አገሮች ጂፕሰም ቦርድ እንደሚያመርቱ የሰማሁት ግብጽና ደቡብ አፍሪካን ነው፡፡ የሌሎቹን አገሮች አልሰማሁም፡፡

ጂ ኤች ታዲያ በአፍሪካ 3ኛው ጂፕሰም ቦርድ አምራች ፋብሪካ መሆኑ ነው?

የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

በአገራችን ጂፕሰም ቦርድ የሚጠቀሙ የ/ሰም ማለት ነው?

አሉ፡፡ ከውጭ እያስገቡ ነው፡፡ ከቻይና በብዛት ይገባል፡፡ ከማሌዢያና ኢንዶኔዥያ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች ይገባል፡፡ እስካሁን አንዳንድ በአሉሚኒየም ቦርድ የተሠሩ ቤቶች እንጂ በጂፕሰም ቦርድ የተሰሩ አላየሁም፡፡ ጂፕሰም ቦርድ በዓለም ደረጃ በጣም ተፈላጊና ታዋቂ ነው፡፡ እንደ እንጀራ ድንጋይ ተፈጭቶ ተቦክቶ፣ ተጋግሮ ማለት ነው፡፡ ወጪ የለውም፡፡ ለስኑኝ ቀለም ቀቡኝ …አይልም፡፡

ድንጋይ ስለሆነ፣ እሳትና ውሃ ይቋቋማል፡፡ ቀላል ስለሆነ፣፣ ለቤት መሥሪያም በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ አንድ ቤት ለመሥራት 6 ወር ቢፈጅ፣ በጂፕሰም ቦርድ ግን በ15 እና በ20 ቀናት ማጠናቀቅ ይቻላል፡፡ ለቤቱም ውበት ይሰጠዋል፡፡

ጂ ኤች በዓመት ምን ያህል ጂፕሰም ቦርድና ዱቄት ያመርታል?

ፋብሪካው በዓመት 4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦርድ፣ የዱቄቱ ደግሞ በሦስት ፈረቃ 24 ሰዓት ስለሚሠራ፣ በዓመት 95ሺህ ቶንስ ወይም 95 ሚሊዮን ኩንታል ያመርታል፡፡

ለወደፊት ምን አቅደዋል?

ርዕሰ መስተዳድሩ፣ እንደ ብሎኬትና ሸክላ ያለ ለግድግዳ የሚሆን ተገጣጣሚ ጂፕሰም ብሎክ ማምረቻ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ ዛሬ (ግንቦት 20) አኑረዋል፡፡

ሁለቱ ፋብሪካዎች ለምን ያህል ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል?

በአሁኑ ሰዓት 120 ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ ወደፊት እንደ ገበያው ሁኔታ የሠራተኞች ቁጥር ይጨምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አቶ ጌታቸው ጥር 24 ቀን 1984 ከወ/ሮ ሐና ጋር ትዳር መስርተው አምስት ልጆች አፍርተዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

Read 6367 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 08:29