Saturday, 16 June 2012 12:11

መንግሥት ያልሾማት የአገሯ አምባሳደር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ፈረንሳይ ነው የምትኖረው፡፡ በአንድ ሆቴል ሙዚየም ውስጥ ኮርስ እየተከታተለች ሲሆን፣ ለኮርሱ ተሳታፊዎች ምግብ በነፃ ይፈቃዳል፡፡ ስለዚህ የሙዚየሙ ሬስቶራንት ምግብ ያቀርባል፡፡አንድ ቀን የዕለቱ ምግብ ላዛኛ ነበር፡ የሬስቶራንቱ ባለቤት የሆኑት ሴት ምግቡን አቅርበውላት “አበላሉን ታውቂያለሽ” ሲሉ ጠየቋት፡፡ አገሯ ሳለች ብዙ ጊዜ የበላችው ምግብ ቢሆንም አጠያየቃቸው የቅንነት እንዳልሆነ ስለገባት “አይ፤ አላውቅም” አለቻቸው፡፡ ይኼን ጊዜ “የየት አገር ሰው ነሽ?” አሏት የሚከተላትን ሳትጠረጥር “የኢትዮጵያ” አለች በኩራት፡፡ “ኢትዮጵያማ ድሃ ናት” አሉ ሴትዮዋ፡፡ ነገሩ እውነት ቢሆንም በአገሯ ድህነት በመሰደቧና ክብሯ በመነካቱ ከመቅጽበት በንዴት ጦፈች፣ እርር - ድብን አለች፡፡ ነገር ግን ምንም ማድረግ ስላልቻለች “ከመሠሎት ይሁና!” አለች በለሆሳስ፡፡

ወደ ሬስቶራንቱ የሄደችው እርቧት ቢሆንም የረሃብ ፍላጐቷ ስለጠፋና ምግቡም ስላስጠላት ጥላው ልትወጣ አስባ ነበር፡፡ ነገር ግን የሌሎችን ትኩረት ላለመሳብ መቆነጣጠር ጀመረች፡፡ ትምህርቱ የግማሽ ቀን ስለሆነ ትንሽ ቆይታ ወደ ቤቷ ሄደች፡፡ ሌላ ጊዜ ጋደም ብላ ትንሽ ካሸለባትና ካረፈች በኋላ ነው የዕለት ተግባሯን የምትቀጥለው፡፡ ያን ዕለት ግን ጋደም ብትልም ማረፍ አልቻለችም፡፡

“እነሱ ሳይፈጠሩና ሰልጥነው እንደዛሬው ሰው የሚሰደድባቸው  ባልነበሩበት ዘመን አገሬ የራሷ ቋንቋ፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ባህል፣ የራሷ ታሪክ፣ ዓለም የሚያውቀው ሥልጣኔ ያሏት ነበረች፡፡ ስላለወቅንበት ነው እንጂ ኢትዮጵያስ ድሃ አይደለችም” አለች ለራሷ፡፡ ከዚያም አገሯ ድሃ አለመሆኗን በተጨባጭ በማሳየት ሴትዮዋን ለማስተማር ወሰነች በቃላት ሳይሆን በተግባር፡፡ አናም ምን ማድረግ እንዳለባት ማሰላሰል ጀመረች፡፡

በሦስተኛው ቀን “ድሃ” ያሏትን ሴት “ልደቴን እንዳከብርበት ይህን ክፍል ይፍቀዱልኝ” አለቻቸው፡፡ እውነተኛ ልደቷ አልነበረም - ለዘዴዋ ነው፡፡

ታዲያ ፈረንጅ ለልደት ልዩ ክብር አይደል ያለው - ፈቀዱላት፡፡ በባዕድ አገር ሁሉም ነገር እንደልብ ባይገኝም አገሯ ድሃ ያለመሆኗን ለማሳየት የሚገዛዙትን ገዛዝታ የሌላውን ከአገሯ ልጆች ተውሳ፤ በተቻላት መጠን ከፍተኛ ዝግጅት አደረገች፡፡

“ልደቴ ነው ባልኩበት ቀን፣ ሳር ጐዝጉዤ፣ የአገር ባህል ለብሼ፣ ባህላዊ ምግብ አዘጋጅቼ፣ ቡና ለማፍላት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ቡና፣ ቆሎ፣ ፈንዲሻ፣ ሰንደልና ዕጣን፣ ጀበና ከነሲኒው አቅርቤ፣ የጆሮ፣ ጌጤንና የአንገት ሐብሌን አድርጌ፣ ሌላም ወርቅ በግንባሬ አስሬ ከሚገባው በላይ ወርቁን በላዬ ላይ ደርድሬ፣ አምሬና አሸብርቄ ሬስቶራንቱ ከሰዓት በኋላ ዝግ ስለሆነ፣ ሠራተኞቹንና “ድሃ” ያለችኝን ሴትዮ “ልደቴን ላከብር ነውና ኑ!” ብዬ ጠራሁ፡፡ ቡናውን ቆልቼና ቆሎውን አቅርቤ፣ ምግቡን በመሶበወርቅ፣ ወጡን በሳህን ሁሉንም በአገራችን ባህል መሠረት አቅርቤ ከተበላና ቡናው ከተጠጣ በኋላ “አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ” አልኳቸው፡፡

“ኢትዮጵያውያን እንዲህ ከበላን፣ እንዲህ ከጠጣን፣ እንዲህ ካጌጥንና ከለበስን፣ (ይኼ ሁሉ ከአገራችን አፈር ነው የሚመረተው፡፡) በዚህ ላይ ደግሞ የምትቀጥራቸው ኢትዮጵያውያን ቆንጆዎች ናቸው፡፡ ባህላችን ይህን ከመሰለ፣ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ድህነታችን? ልደቴን ላከብር ነው ያልኳችሁ ውሸቴን ነው፡፡ ይህንን ያደረግሁት በቀደም “ድሃ” ያላችሁኝን “ድሃ” ያለመሆናችንን ላሳያችሁ ብዬ ነው፡ በዚህ ላይ አስተያየት ስጡ፡፡” አልኳቸው፡፡ ሰዎቹም በጣም ተገረሙ፤ አንዳንዶቹም የጥፋተኝነትና የሃፍረት ስሜት ይነበብባቸው ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነው እንግዲህ አገሬን ማስተዋወቅ የጀመርኩት” በማለት ታሪኳን አወጋችኝ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ፡፡

ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ንባበ ትባለች፡ አርቲስት (ሠዓሊ) ስለሆነች “አንቺ” አልኳት እንጂ በዕድሜም ሆነ በሰው አገርና በባዕድ ተከባ ብቻዋን አገሯን ለማስተዋወቅ በምታደርገው ትግልና ጥረት ትልቅ ክብርና “አንቱታ” ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም፡፡ ልብ በሉ! መንግሥት ያልሾማት፣ ደሞዝ ያልቆረጠላት በፈረንሳይ ብቸኛዋ የአገሯ አምባሳደር፣ ባለሟል፣ ተቆርቋሪ፣ ተሟጋች፣ አስተዋዋቂ፣…ሆና እየሠራች ነው፡፡

ወ/ሮ ዓለምፀሐይን ያነጋገርኳት ቦንጋ ከተማ ነው፡፡ እንዴት መሰላችሁ? ወደ ፈረንሳይ ልትመለስ ስድስት ቀናት ሲቀራት ማንኪራ ፕሮሞሽን የተባለው ድርጅት የቡና መገኛ መሆኗ የሚነገርላትንና በተፈጥሮ ቡና የተሸፈነችን ማኪራ ቀበሌ በጋዜጠኞችና አርቲስቶች ባስጐበኘበት ወቅት፣ እሷም በተጋባዥነት ወደ ስፍራው ተጉዛ፤ በካፋ ዞን ዋና ከተማ ቦንጋ ተገናኘን፡፡ እኔ ይህን ያህል ካልኩ ቀሪ ታሪኳን ከራሷ እንስማ፡፡

ሐረር ተወልደሽ የት አደግሽ?

ግማሽ የልጅነት ጊዜዬን በድሬዳዋና በሐረር ዙሪያ አሳልፌ፣ ቀሪውን አዲስ አበባ ኖርኩ፡፡

ወደ ፈረንሳይ መች ሄድሽ?

ከ18 ዓመት በፊት በ1986 ዓ.ም

ለምን?

ያላዩት አገር ይናፍቃል ይባል የለ? እንደዚያ ሆኜ ነው፡፡

ታዲያ እንደጠበቅሽው አገኘሽው?

ጥሩ ነው - በኑሮ ማለቴ ነው፡፡ ከአገሬ ግን ምንም የሚበልጥ ነገር የለም፡፡

አሁን በፈረንሳይ የት ከተማ ነው የምትኖሪው?

ቱር የምትባል ከተማ አለች፡፡ እዚያ ነው የምኖረው፡፡

ምንድነው የምትሠሪው?

ሻቶ ሎምባርዴ የተባለ በጣም ታዋቂ ሙዚየም ኃላፊ ነኝ፡፡

እዚያ ሠራተኞችን አሠለጥናለሁ ሙዚየሙን አስተዳድራለሁ፤ ወደ ሙዚየሙ የሚመጡ ቱሪስቶችን ተቀብዬ አስተናግዳለሁ፣ ገለፃም አደርጋለሁ፣

ሻቶ ሎምባርዴ ምንድነው?

ሻቶ የጥንት ንጉሣውያን ቤተሰቦች መኖሪያ የነበረና በፈረንሳይ አብዮት ጊዜ የቁስለኞች መታከሚያና መጠለያ የነበረ ትልቅ ቤት ነው፡ ሎምባርዴ፣ ቤቱን የገዛው ሰው ስም ነው፡፡

ሙዚየሙ ምን ይሠራበታል?

ብዙ ነገሮች ይሠራበታል፡፡ ሆቴልና ሬስቶራንት አለው፡፡ ስለአገሪቷ ጥንታዊ ታሪክ የተጻፉ መጻሕፍትና መግለጫዎች፣ ጥንታዊና ባህላዊ የወግ፣ የጦርነት ቁሶች የሚገኙት እዚያ ስለሆነ ብዙ ቱሪስቶች ይጐበኙታል፡፡

ሌላ የምትሠሪው ነገር አለ?

አዎ ሰዓሊ ነኝ - ሥዕል እሠራለሁ፡ አሳሳሌ ግን ከሌላው ሰዓሊ ይለያል፡፡ እኔ የምሥለው በአፈር፣ በድንጋይ፣ በጠጠር፣ በእህል፣ በተክል፣ በእጽዋት… ቀለም ነው፡፡

እንዴት? አልገባኝም?

ወደተለያዩ አገሮች ለጉብኝት ስዘዋወር ከባህር ዳርቻ ፣ ከተራራ፣ ከቮልካኖ ስፍራ የተለያየ ቀለም (ከለር) ያለውን አፈር፣ ድንጋይ፣ ጠጠር፣ አሰባስባለሁ፡፡ ከዚያም ድንጋዩን፣ ጠጠሩን፣ አፈሩን ወቅጨና ፈጭቼ…የሳልኩት ሥዓል በሚያስፈልገው ቀለም መሠረት፣ በጣቶቾ ቆንጥሬ፣ እንዳይበዛና እንዳያንስ ተጠንቅቄ እነሰንስበትና በብሩሽ አዳርሼና ጠርጌ እንዲደርቅ አደርጋለሁ፡ ለምሳሌ፣ ፊት ላይ ቀይ አፈር፣ ፀጉር ላይ ጥቁር አዝሙድ፣ ልብስም ቢሆን በሸሚዙ ፣ በጃኬቱ፣ በቀሚሱ፣ በሱሪው ፣ በጫማው… ቀለም መሠረት እሰንስበታለሁ፡፡ ጌጥና የተለያዩ ዕቃዎችም ቢሆኑ እንደዚያው ነው፡፡

ሌላም አለ፡፡ የተለያዩ እፅዋት፣ እህሎች፣ ተክሎችና ሥራ ስሮች ወቅጨ ቀለማቸውን እጠቀማለሁ፤ የተለያዩ ቀለማትን በማደባለቅም የምፈልገውን የተለየ ዓይነት ቀለም እፈጥራለሁ፡፡

ቡና፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ኑግ፣ ተልባ፣ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ፣ ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ እጠቀማለሁ፡በአጠቃላይ እንደሚያስፈልገኝ ቀለም ዓይነት የደቀቀ አፈር፣ ድንጋይ፣ አሸዋ፣ እህል፣ ተክል፣ እጽዋት ሥራ ሥር፣ እያደባለቅሁ እቀምማለሁ፡ በዚህ ዓይነት ነው ሥዕሎቼን የምሠራው፡፡

ሥዕል የት ተማርሽ?

እውነቱን ለመናገር ሆን ብዬና ሥዕል ት/ቤት ገብቼ አልተማርኩም፡፡ ግን ብዙ ኮርሶች ወስጄ ዲፕሎማና ሰርቲፊኬቶች አሉኝ፡፡ ለምሳሌ፣ አሜሪካ አጠገብ ወደምትገኘውና የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ወደነበረች ማርቲኒክ ደሴት ሄጄ ሁለት ዓመት ኖሬ ነበር፡፡ እዚያ ያለች ኤሊዛቤት የተባለች ፈረንሳዊት ጓደኛዬ፣ የሥዕል ት/ቤት አላት፡፡ ኤሊዛቤት ያለኝን የሥዕል ፍላጐትና ችሎታ አይታ ካደነቀች በኋላ ለአንድ ዓመት ተኩል አስተማረችን፡፡ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቄ በዲፕሎማ ተመርቃለሁ፡፡ ሌሎች ብዙ ኮርሶችም ወስጃለሁ፡፡

የሥዕል ፍላጐትና ችሎታዬ የመጣው ከተፈጥሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከልጅነት አንስቶ ሥዕል በጣም እወዳለሁ፡፡ ያየሁትን ነገር መሳል፣ ልብስ መስፋት፣ ቀለሞች ሣር ቅጠላቅጠልና አትክልት ጨቅጭቄ የተለያዩ ቀለሞች ማውጣት፣ ቀለሞቹን እያደባለቅሁ የተለየ አዲስ ቀለም መፍጠር፣ ቀለሞቹን ከአሸዋ ጋር እያደባለቅሁ የተለያዩ የጥንት ዕቃዎች ማስዋብ …በጣም እወድ ነበር፡፡ በአንዳንድ ኮርሶች ባዳብረውም ያ የልጅነት ፍላጐትና ሙከራ አብሮኝ  አድጐ ይኼው እያሳወቀኝ ነው፡፡

ስንት ሥዕሎች ሠርተሻል?

ከ200 በላይ ሥዕሎች አሉኝ፡፡

ኤግዚቢሽን አቅርበሽ ታውቂያለሽ?

አዎ! ለብቻዬም ከሌሎች ሰዓሊዎች ጋር በመሆን ብዙ ጊዜ አቀርባለሁ፡፡ (ወደ ፈረንሳይ ከተመለሰች በኋላ ከሌሎች ጋር ሆና ቨ3 ቀን ኤግዚቢሽን ማቅረቧና በዚህ ወር መጨረሻ አካባቢ ለብቻዋ ታላቅ የሥዕል ኤግዚቢሽን ለማቅረብ በጋዜጦች፣ በቴሌቭዥን በበራሪ ወረቀቶች፣ በሬዲዮ፣ በኢንተርኔት፣ እያስተዋወቀች መሆኑን ሰምቻለሁ)

ሌላም ትልቅ ኃላፊነት አለብኝ ስትይ ሰምቻለሁ፡ ምንድነው እሱ?

አዎ! አገሬን የማስተዋወቅ ከባድ ኃላፊነት አለብኝ፡ እዚህ በድህነት ነው የሚያውቁን፡፡ ስላላወቅንበት ነው እንጂ ድህነት የለብንም፡፡ ስለዚህ “ድሃ” የሚለውን ቅጽል ለመፋቅ፣ በቡናችን፣ በባህላዊ አለባበሳችንና፣ በመስተንግዶአችን እያስተዋወቅሁ ነው፡፡

ከዓለም ሁሉ በጣም ሀብታሞች ነን፡፡ ምክንያቱም የራሳችን ቋንቋ፣ የራሳችን ፊደል፣ የራሳችን ጽሑፍ፣ የራሳችን ሥልጣኔ፣ የራሳችን ታሪክ ያለን ነን፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት ነው፤ ድሃ ልንባል አይገባም፡፡ ስለዚህ ፊደሌን፣ ቋንቋዬን፣ ቡናዬን አመጋገቤን አለባበሴን፣ የሕዝቡን ኅብረት፣ ፍቅር፣ አስተምራለሁ፡፡

ቡናን ደግሞ እንዴት ነው የምታስተዋውቂው? የእኛ ቡና እዚያ አይታወቅም እንዴ?

ይታወቃል፡፡ በቡና መጋዘንም ውስጥ የእኛ ቡና ዋጋው ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ አቆላሉ ላይ ነው፡፡  የእኛን ቡና ከሌላ አገር ቡና ጋር አደባልቀው ነው የሚሸጡት፡፡ የእኛ ቡና ፍሬው ትንንሽ ስለሆነ ሲቆላ እኩል አይበስልም - ያርራል፡፡ ስለዚህ እንዴት እንደሚቆላ፣ እንዴት እንደሚፈላ፣ በስኳርና ያለስኳር እያቀመስኩ ጣዕሙ ከሌላው አገር ቡና የተለየ መሆኑን አስተምራለሁ፡፡ በዚህ በጣም ያደንቁኛል፡፡ ማስተዋወቅ ከጀመርኩ በኋላ አንዳንድ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ቡናችንን ቆልቼና አፍልቼ እንዳሳያቸው ይጠይቁኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቡና ጥቁር እንቁ ስለሆነ ፍሬው ብቻ ሳይሆን ከቅጠል እስከ ስሩ ምንም የሚጣል ነገር እንደሌለው አስተምራለሁ፡፡ ምክንያቱም የቡና ቅጠልና ገለባ እንደ ሻይ ይጠጣል፡፡ እንጨቱ ደግሞ ተወቅጦና ተፈልቶ ከአንድ ማንኪያ ማር ጋር ቢጠጣ ድካምና መጫጫንን አስወግዶ ዘና ያደርጋል፡፡

ሌላውና እኛም የማናውቀው የቡና ጥቅም ስሩ ያለው ምስጢር ነው፡፡ ስሩ፣ ከሽቶ ቅመሞች አንዱ መሆኑን ያወቅሁት ፈረንሳይ ነው፡፡ አግራፍ የምትባል ከተማ ሄጄ አንድ ታዋቂ የሽቶ ፋብሪካ ስጐበኝ ያየሁት ነገር በጣም የሚገርም ነው፡፡ በዚያ ፋብሪካ የቡና ስር፣ ከርቤና ዕጣን፣ ከጃርት በጠጥ (ካካ) ጋር ተደባልቆ ሲሠራ አለርጂ እንዳይፈጠር ስለሚከላከል ከሌሎች የሽቶ ንጥረ ቅመሞች ጋር ይቀመማል፡፡

ቡና፣ ለልብ ሕመም ጥሩ አይደለም ይባላል፡፡ ነገር ግን አንድ ስኒ ቡና ይታዘዛል፡፡ ሌላው የቡና አፈላል ሥርዓታችን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ነው የማስተምረው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሰፋ ባለ ሁኔታ የዓለም ሕዝብ የቋንቋ፣ የአኗኗር፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ…  ኤግዚቢሽን የሚቀርብበት አለ፡፡ ከበርካታ አገሮች ውስጥ እኔ የማቀርበው ዝግጅት ነው ተመርጦ በቴሌቭዥንና በጋዜጣ የሚቀርበው፡፡

እንዲህ እያዘጋጀሽ ማቅረብ ከጀመርሽ ስንት ጊዜ ሆነሽ?

ዘጠኝ ዓመት፡፡ በፊት በመንግሥት ደረጀ እውቅና አልነበረኝም ዝም ብዬ ነበር ስሠራ የነበረው፡፡ አሁን ግን የማስተዋወቅ ማኅበር አቋቁሜአለሁ፡፡ እዚያ ያሉ የአገሬ ሰዎች “የእኛ አገር ምግብ እዚህ የለም፡፡ ለምን ምግብ እየሠራሽ አትሸጪም?” ይሉኛል፡፡ በዚህ የተነሳ የኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች የሬስቶራንት ቦታ በነፃ ሰጥተውኝ ምግብ እየሠራሁ ማቅረብ ከጀመርኩ ሦስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በዚህ ዓይነት በአሁኑ ወቅት ምግቡ እየታወቀ ነው፡፡

ቱሪስቶችም ኢትዮጵያን እንዳሳያቸው እየጠየቁኝ ነው፡፡ አሁን ስመጣ እንኳ ሁለት ቱሪስቶች ይዤ መጥቼ፣ አስተናግጄና ኢትዮጵያን አይተው ተመልሰዋል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ 16 ቱሪስቶች እንዳመጣቸው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ እኔ ጊዜ ስላልነበረኝና ላመጣቸው ስላልቻልኩ፣ ራሳቸው መጥተው ሦስት ሳምንት ቆይተው ተመልሰዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያን ማየት የሚፈልጉ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

ብቻሽን ነው እየሠራሽ ያለሽው?

በፊት ብቻዬን ነበር፡፡ አሁን ግን አልቻልኩም፡፡ እኔ ምግቡ ጋ ስሆን ለኤግዚቢሽን የቀረቡትን ባህላዊ ዕቃዎች የሚጠብቅልኝና የሚያስተዋውቅልኝ ሰው ይቸግረኝ ነበር፡፡ አሁን ግን እዚህ ካለው ሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት የመጡ ተማሪዎች ስላሉ እነሱ ያግዙኛል፣ የማኅበሩ አባልም ሆነዋል፡፡

እዚያ የሚኖሩ ባለትዳሮችና ተማሪዎች፣ ማኅበር አቋቁመን ዝግጅቱን አስፍተን ከዚህ በምናገኘው ገንዘብ ለምን በኤችአይቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና አቅመ ደካማ አረጋውያንን አንረዳም? በሚለው ሐሳብ ተስማምተናል፡፡ ከአሁን በኋላ ሕፃናቱንና ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን ለመርዳት ዝግጁ ነን፡፡

ምግቡ እዚያ እየተለመደ ከሆነ ለምን በቋሚነት አታዘጋጂም?

ምግቡንማ እየደወሉ ሁሉ አዘጋጂልን የሚሉ አሉ፡፡ እኔም እያሰብኩበት ነው፡፡

አገርሽን በማስተዋወቁ ሥራ ለመቀጠለ ከዚህ ምን ያስፈልግሻል?

ከዚህ የሚያስፈልገኝ እዚህ ያለውንና ያየኋቸውን ነገሮች እዚያም እንዳሳይ ሕዝቡ እንዲረዳኝ እፈለጋለሁ፡፡ እዚያ ያለነውና ማኅበር የመሠረትነው፣ አንዳንድ ነገሮች ሠርተን እዚህ ያሉትን ችግረኞች ከረዳንና ካቋቋምን በኋላ የውጪ ዜጐች መጥተው እንዲጐበኙልን እፈልጋለሁ፡፡

===========================================================

መንግሥቱ ለማ በአንድ ወቅት በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያውያን አልተማሩም፣ አያውቁም፣ አልተማሩም…በማለት ለመሳለቅ፣

You Ethiopians, they tell us,

You pass the night on a tree.

How do you climb the tree every evening?

እንደምንሰማው ከሆነ እናንተ ኢትዮጵያውያን ሌሊቱን ዛፍ ላይ ነው አሉ የምታድሩት፡ለመሆኑ በየምሽቱ እንዴት ነው ዛፉ ላይ የምትወጡት? እንደማለት ነው፡፡

አምባሳደሩም “O! Don’t you know we use lifts!” በማለት መለሱላቸው፡፡

“ኦ! ሊፍት (አሳንሰር) እንደምንጠቀም አታውቁም?!” አሏቸው፡፡

በአገራችን ጉዳይ አለመበለጥ ታላቅ

የዜግነት ግዴታ ነው!

 

 

Read 4339 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:26