Saturday, 23 June 2012 07:32

“ጥረት” በአማራ ክልል ምን እየሰራ ነው?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አቶ ታደሰ ካሣ የ”ጥረት” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ “ጥረት” ከሚመራቸው ድርጅቶች አንዱ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አ.ማ ነው፡ ዳሽን ቢራ ባለፈው ሳምንት በደብረ ብርሃን ከተማ አዲስ ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ በዚያው ወቅት ከአቶ ታደሠ ካሣ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ:-

ጥረት ምንድነው?

ጥረት ኮርፖሬት በአማራ ክልል የሚካሄደውን የልማት እንቅስቃሴ የማገዝ ዓላማ ይዞ መሠረታዊ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል ውጤታማ ተግባራትን በመሥራት ላይ ይገኛል፡ ጥረት የልማት ድርጅት ሲሆን፣ ዓላማውም የአማራን ክልል ማልማት ነው፡፡ የአማራ ክልል ማልማት ማለት የኢትዮጵያን ክልል ማልማት ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ክልሎች እንዲለሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

የድርጅቱ ተቋማት በአማራ ክልል ብቻ አይደለም የሚንቀሳቀሱት - በመላው ኢትዮጵያ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ዳሸን ቢራችን በመላ ኢትዮጵያ ይጠጣል፡፡ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት በመላ አገሪቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አንባሰል የንግድ ሥራዎች፣ በመላ ኢትዮጵያ የኢምፖርት ኤክስፖርት (የገቢና ወጪ) እንቅስቃሴ ያካሂዳል፡፡ በአማራ ክልል የሚካሄድ የልማት እንቅስቃሴ ማለት በመላ ኢትዮጵያ የሚካሄደው የልማት እንቅስቃሴ አንድ አካል ስለሆነ የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ በተጨባጭ ማገዝ ማለት ነው፡፡

ከፍ ሲል ከተጠቀሱት በተጨማሪ በምን ዘርፎች ተሰማርቷል?

ድርጅቱ፣ በማኒፋክቸሪንግ፤ በእርሻ፣ በሰርቪስ፣… ዘርፍ ይሰማራል፡፡ በዚህ ረገድ በእርሻው ዘርፍ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ በማተኮር በአማራና ቤኒሻንጉል ክልሎች የእርሻ መሬቶችን የሚያለማ ድርጅት አለ፡ በለሳ ሎጂስቲክ የተባለ የሎጂስቲክ ኩባንያ አቋቁመን ለወጪና ገቢ ሎጂስቲኮች አስፈላጊ የሆነ ነገር እየሠራን ነው፡፡

ከዚሁ ጋር የቢራ ፋብሪካ ስናቋቁም አርሶ አደሩ ወደ ቢራ ገብስ ማምረት እንዲገባና ኮመርሻላይዝ ማድረግ ነው ዓላማችን፡፡ በዚህ ረገድ ጐንደር ላይ ያቋቋምነው ትልቅ የቢራ ብቅል ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ የመሳሪያዎች ተከላ እየተካሄደ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ክረምት የሚዘራውን የቢራ ገብስ መሸመት ይችላል፤ 200ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ ይፈልጋል፡፡

በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ አራት ፋብሪካዎችም አሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ ፕሮሰስ የሚያደርግ ፋብሪካ በወልዲያ ከተማ እየሠራን ነው፡፡ የማር ማቀነባበሪያም እዚያው ወልዲያ ይኖረናል፡፡ ትልቅ የቆርኪ ፋብሪካ ለመገንባት በሂደት ላይ ነው፡፡ እስካሁን በአገራችን ቆርኪ የሚያመርት ፋብሪካ የለም - ከቻይና ነው የምናስመጣው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር የሚቀርፍ ፋብሪካ በኮምቦልቻ ከተማ ለመትከል በሂደት ላይ ነን፡፡

የዋነኛ ትኩረት አቅጣጫችሁ ምንድነው?

አሁን እንግዲህ የትኩረት አቅጣጫችንን ለይተናል፡፡ የወደፊት ትኩረታችን እርሻውን ከማጠናከርና አርሶ አደሩን ከመደገፍ አኳያ አግሮ ፕሮሰሲንግ ነው፡፡ ሁለተኛው ትኩረታችን ቴክስታይል (የጨርቃ ጨርቅ) ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከእርሻው ጀምሮ እስከ መጨረሻው የልብስ ስፌት ድረስ ሁሉንም ሂደቶች የሚያጠቃልል ይሆናል ማለት ነው፡፡ አሁን ትልቅ የጥጥ ማዳመጫ ፋብሪካ መተማ ከተማ እየተከልን ነው፡፡ ይኼ ወደ አርሶ አደሩ የምንገባበት ነው፡፡ ከእኛ እርሻ ብቻ ሳይሆን ከአርሶ አደሩ ጥጥ እየገዛን የምንዳምጥበት ነው - በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራል፡፡ ከዚያም ደረጃ በደረጃ ፈትል፣ ጨርቅ፣ ምርት፣ ስፌት፣ … እያልን እስከ ኤክስፖርት እንዘልቃለን፡፡

ሦስተኛው ትኩረታችን ቴክኖሎጂ ነው፡ በዚህ ዘርፍ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ጣና ሞባይል ፋብሪካ በባህርዳር ከተማ አቋቁመናል፡፡ ይህ ፋብሪካ አሁን ሞባይልና ገመድ አልባ ቴሌፎን እያመረተ ነው፡፡ ወደፊት እያሻሻልን መካከለኛ ደረጃ ሞባይሎችን እናመርታለን፡፡ አሁን ባለው አቅም በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ሞባይሎች ማምረት ይችላል፡፡ ወደፊት ደረጃውን እያሻሻልንና አቅሙን እያሰፋን (እያሳደግን) ወደ ጐረቤት አገሮች ገበያ የመግባት ዕቅድ አለን፡፡

የሞባይሉ ጥራት እንዴት ነው?

እስካሁን ድረስ ባለን መረጃ መሠረት በጣም ጥሩ የጥራት ደረጃ ነው ያለው - ገበያ ላይ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ እኛ አምርተን ለቴሌ ነው የምንሸጠው፡፡ እስካሁን ከቴሌ ባለን ምላሽ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ተመሳሳይ ደረጃ ካላቸው ሞባይሎች በብዛት እየተሸጠ ያለው ጣና ሞባይል መሆኑን አውቀናል፡፡ በተለይ ለአርሶ አደሩ እንዲያመች ተደርጐ ስለተሠራና ጠንካራ ስለሆነ አርሶ አደሩ ይፈልገዋል፡፡ አራተኛው ትኩረታችን ማዕድን ቁፋሮ ነው፡ በአማራ ክልል እስካሁን ትኩረት ያልሰጠናቸው ማዕድናት ስላሉ ወደዚያ ለመግባት አቅደናል፡ ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች ብረታ-ብረትና ኬሚካል ነው፡፡ አሁን በአማራ ክልል ለመትከል ጥናቱን ያጠናቀቅነው ግዙፍና ትልቅ የወረቀትና ፐልፕ ፋብሪካ ነው፡፡ በዓይነቱና በትልቅነቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዛፎች አሉ - ባህር ዛፍ፣ ቀርከሃ፣ … ሌሎችም በብዛት አሉ፡፡ እነዚህን ዛፎች ወደ ወረቀት መቀየር ነው፡፡ ይህ ባህርዳር አካባቢ የሚሠራው የወረቀት ፋብሪካ አርሶ አደሩን በቀጣይነት ዛፍ እያመረተ እንዲሸጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢኮኖሚን በኅብረት የማሳደግ ዓላማ አለው ማለት፡፡

 

 

Read 5950 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:12