Saturday, 30 June 2012 10:56

የቤራ ቢር ድፍራት በሀዋሳ ተወዳጅ ሆኗል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ባለቤቱና የሥራ ኃላፊዎች ከአስተናጋጆች የሚለዩት ዩኒፎርም ባለመልበሳቸው ነው፡፡ በአጭር ታጥቀው በሁሉም አቅጣጫ በንቃት ይቃኛሉ፡፡ እንግዶች ገብተው እንደተቀመጡ፣ ለቦታው የተመደበ አስተናጋጅ፣ ቀድሞ የገባ እንግዳ እየታዘዘ ወይም ትዕዛዙን ለማቅረብ ሄዳ/ዶ ከሆነ እነሱ ጠጋ ብለው ፈገግታ ጋብዘው ትዕዛዝ ይቀበሉና  ለምድብተኛው አስተናጋጅ ቦታውን በማመልከት ትዕዛዙን ያስተላልፋሉ፡፡ ይህ ትዕይንት የሚስተዋለው ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ሀዋሳ ከተማን የረገጠ ሰው ከኃይሌና ከሌዊ ሪዞርቶች ቀጥሎ ከሚጐበኛቸው ስፍራዎች አንዱ በሆነውና ከአዲስ አበባ ውጭ የቢራ መጥመቂያ ጋኖች በግልፅ እየታዩ ትኩስ ድራፍት በሚጠጣበት ቤራ ቢር አዳራሽ ነው፡፡

“ሰው፣ ድራፍት በጣም ይፈልጋል፡፡ አቅርቦቱ ግን የተሟላ አይደለም፡፡ ዛሬ አንድ፣ ነገ ሦስት ወይም አምስት፣ ከነገ ወዲያ አንድ በርሜል ድራፍት … በቃ እንደተገኘ ይሰጡናል ሰው ደግሞ በአቅርቦት ማነስ ሲቸገር ብዙ ጊዜ አያለሁ፡፡ ይህን ችግር እንዴት መቅረፍ ይቻል ይሆናል? እያልኩ ሳሰላስል፣ “በውጭ አገር እንደ ጎጆ ኢንዱስትሪ ያለ፣ ድራፍት ቢራ መጥመቂያ አይኖርም ይሆን?” አልኩ - ለራሴ፡፡

“ይህን ጉዳይ በሥራ ለተዋወቅኋቸው የ”ሌንቦ” ብስኩት ባለቤቶች አጫወትኳቸው፡፡ እነሱም በመገረም ተያዩና፤ አንደኛው እኛም’ኮ በዚህ ላይ ልንሠራ ተዘጋጅተናል፡፡ ካታሎጉ (የአሠራር መግለጫው) እኔ ጋ አለ፤ እንዴት አሰብከው?” ብሎ ያሰብኩትን ዓይነት ካታሎግ ሲያሳየኝ የደስታ ስሜት ወረረኝ፡፡ “እኔም ያሰብኩት ልክ እንደዚህ ያለ ነው፡፡ በቃ! ቦታ ውሰድና አብረን እንሥራ አልኩት፡፡ እስከዛው እኔም የራሴን ሆቴል አጠናክሬ ስሠራ ቆየሁ፡፡ እነሱ በሌላ ሥራ ስለተወጠሩ ያ የተስማማንበት ሐሳብ ወደ ተግባር ሳይመነዘር ዓመት ሞላው፡፡ አንድ ቀን “ያሰብነው ነገር እንዴት ነው? ዓመት’ኮ ሆነው፡፡ ምንድነው ማድረግ ያለብን?” አልኩ፡፡ ሳቁና፣ “ማታ ቤት ና!” አሉኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ምሽት ላይ እነሱ ቤት ነው የምናሳልፈው፡፡

“ማታ ቤታቸው ሄድኩና አጀንዳው ተነሳ፡፡ አየህ! እኛ በዚህ ጉዳይ ትናንት ማታ ተነጋግረናል፡ ከአንተ ጋር በጋራ ለመስራት ባንጠላም፣ በተለያየ ምክንያት ለጊዜው  አብረን መሥራት አንችልም፡፡ ነገር ግን ላደረግህልን ቅን ውለታ ሁሉ፣ እኛ ማሽኑን ተክለን እንሰጥሃለን፤ ነገ-ዛሬ ሳንል መሳሪያዎቹን ከቻይናም ሆነ ከጀርመን በራሳችን ወጪ አስመጥተንና ተክለን እንሰጥሃለን” ብለው ፕሮሰሱ በ15 ቀን ውስጥ ተጀመረ” በማለት የቤራ ቢርን አመሰራረት ገልጸዋል - ባለቤቱ አቶ ጤናዬ ታደሰ፡፡ በሀዋሳ ከተማ፣ መናኸሪያው ፊት ለፊት፤ ከመንገዱ ዳር የተለያዩ ዛፎች ያሉት ቤት ይታያል፡፡ ከፊት ለፊት ባለው ስፍራ፣ በዛፎቹ ጥላ ስር ብዙ ጠረጴዛና ወንበሮች ተደርድረዋል፡፡ ሲገቡ በስተቀኝ ጥግ ላይ፣ ቡና የምታፈላ ወጣት (ኮፊ ገርል) ቄጤማዋን ጐዝጉዛ፤ በሰፊ ረከቦት ላይ በርካታ ሲኒዎች ደርድራና ምድጃው ላይ ጀበናዋን ጥዳ፣ ዕጣኑ እየጨሰ፣ ትታያለች፡፡ አቶ ጤናዬ እዚህ የደረሱት በቀላሉ እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከስረው፣ ብዙ ጊዜ ወድቀውና ተነስተው፣ ብዙ ጊዜ ተስፋ ቆርጠው፣ ብዙ ችግሮች ተጋርጠውባቸውና አልፈው እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ እዚህ ደረጃ እንዴት እንደደረሱ ሲያጫውቱኝ የፊልም ወይም የድራማ ታሪክ የሚተርኩልኝ ነበር የመሰለኝ፡፡ ይህን ጣፋጭ ታሪካቸውን ራሳቸው ቢያጫውቱን ይሻላል በማለት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

የት ተወለዱ? መቼ?

በቀድሞው አጠራር በሲዳሞ ክ.ሀገር በዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ አጠገብ ባለችና ቤራ በተባለች ቀ.ገማ ነሐሴ 13 ቀን 1949 ዓ.ም ተወለድኩ፡፡

የት አደጉ? የት ተማሩ?

ያደግሁትም ሆነ የተማርኩት እዚያው በትውልድ መንደሬ ነው፡፡ በተወለድኩበት መንደር በ1932 ዓ.ም የተመሠረተ ቤራ ጠዲቾ የተባለ ት/ቤት አለ፡፡ እዚያ እስከ 6ኛ ክፍል ተማርኩ፡፡ 7ኛ ክፍል የጀመርኩት ሻሸመኔ ከተማ ቢሆንም አልጨረስኩም - አቋረጥኩ፡፡

ለምን አቋረጡ?

በዚያን ዘመን እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ እንግሊዝኛ የምንማረው አንድ ክፍለ ጊዜ (ፔሬድ) ብቻ ነበር፡፡ ሌሎቹን ክፍለ ጊዜያት የምንማረው በተለያየ ቋንቋ ነበር፡፡ 7ኛ ክፍል ስገባ፣ ሁሉም ትምህርት በእንግሊዝኛ ሆነ፡፡ እንግሊዝኛ በጣም ከበደኝ፡፡ ስለዚህ የልጆች መሳለቂያና መቀለጃ አልሆንም ብዬ ተውኩት፡

ትምህርት ትተው ወደ ንግድ ነው የገቡት?

አይደለም፡፡ እኔ 7ኛ ክፍል ከመድረሴ በፊትም ልጅ ሆኜ ነጋዴ ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ አባቴ ጠጅ ቤት ነበራቸው፡፡ እዚያ ጠጅ እቀዳ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጠጅ የሸጥኩበትን ገንዘብ የሰፈር ልጆች ሰረቁኝና አባቴ ክፉኛ ገረፉኝ፡፡

ገንዘቡ ምን ያህል ነበር?

50 ብር ነበር፡፡ አንድ ማሰሮ ጠጅ ከ48-50 ብር ይጣራል፡፡ እናቴ አንድ ማሰሮ ጠጅ ሸጦ ገንዘቡን የት እንዳደረሰ ጠይቀው አለችው አባቴን፡፡ በዚህ የተነሳ አባቴ በጣም ስለገረፉኝ በማግስቱ የራሴን ስራ እሠራለሁ ብዬ ከቤት ወጣሁ፡፡ ከዚያም ከይርጋለም አራዳ (ይርጋለም አራዳና ስደተኛ የተባሉ ሰፈሮች አሉት) ለቤራ ቅርብ ከሆነው አራዳ ዳቦ እያመላለስኩ ገጠር እየሸጥኩ እማር ነበር፡፡

ከዚያም በ1966 ዓ.ም ከት/ቤቱ ጐን ምግብ ቤት (ሽሮ ቤት) ከፈትኩ፡፡ ከይርጋለም አንዱን እንጀራ በ0.5 ሳንቲም 20 እንጀራ በአንድ ብር ሂሳብ ከ50-60 እንጀራ እያመጣሁ በሽሮ ወጥ 10 ሳንቲም እሸጣለሁ፡፡ ዳቦም እያመጣሁ በየገበያው እያዞርኩ እሸጣለሁ፡ ያኔ እንደዛሬው ሻይ ቅጠል እንደልብ አልነበረም፤ አንበሳ ሻይ ብቻ ነበር ያለው፡፡ እሱ ውድ ስለነበር በእኔ አቅም አይሞከርም፡፡ ስለዚህ ስኳር በምጣድ አቀልጣለሁ፡፡ በዚያ ሻይ አፍልቼ ዳቦ በሻይ 10 ሳንቲም እሸጣለሁ፡፡

ት/ቤት ሲዘጋም አላርፍም፡፡ በቆሎ እጠብሳለሁ፡፡ በይርጋለም ከተማ በቆሎ ጠብሶ መሸጥ የጀመርኩት እኔ ነኝ፤ ከዚያ በፊት ማንም ሰው መንገድ ላይና ገበያ ውስጥ ጠብሶ ሲሸጥ አላየሁም፡፡ ከዚያ ደግሞ አህያ ገዝቼ ደረቅ በቆሎ ከአቦስቶ ከተማ እየገዛሁ በየገጠር ገበያው እየወሰድኩ እሸጥ ነበር፡፡

ንግድ ያለ ገንዘብ አይሞከርም፡፡ መነሻውን ካፒታል ማን ሰጠዎት? ምን ያህልስ ነበር?

መነሻ ካፒታል፣ አባቴም ሆነ ሌላ ሰው አልሰጠኝም፡፡ ቆቅ ይዤ ነው፡፡ እኛ አካባቢ ቆቅ በብዛት ነበር፡፡ እነሱን እየያዝኩ በመሸጥ ገንዘብ አገኛለሁ፡፡ ሰፈር ውስጥ “የቀቀቦ እናት” የተባሉ ሴት ዕቁብ ይሰበስቡ ነበር፡ “እቁብ አስገቡኝ” ብዬ ለመንኳቸው፡፡ “ከየት አምጥተህ ልትከፍል?” አሉኝ፡፡ “ግድ የለዎትም እከፍላለሁ፤ እርስዎ ብቻ ያስገቡኝ” በማለት ተማፀንኳቸው፡፡ “ምን ጨነቀኝ መጨረሻ ላይ እሰጥሃለሁ” ብለው አስገቡኝና ሁሉም ሰው በልቶ ካበቃ በኋላ ሰጡኝ፡፡

ምን ያህል ነበር?

47 ብር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አባቴ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ጠጅ ቤቱ እንዳልነበረ ሆኗል፤ ልብሶቻቸውን ለሰው እየሰጡ፤ (ነገሩ ብዙ ነው ስለማይጠቅመን ልተወው) ተቸግረው ነበር፡፡ አንድ ቀን መኝታ ቤት ስገባ፣ እናትና አባቴ ቀን በለበሱት ልብስ ብቻ ተኝተው አየሁና በጣም አዘንኩ፡፡ ከዚያም ቆላ ሄጄ በ37 ብር ቡሉኮ ገዝቼ አለበስኳቸውና 10 ብር ተፈረኝ፡፡ ወላጆቼ በጣም ደስ አላቸው፡፡

አባቴ ሰርዶ ነጭቶና እናቴን ከምታልብበት ጠርቶ አስቀምጧት፣ ሰርዶውን አናቴ ላይ አድርጐ ትኩስ ወተት እያፈሰሰበት፤ “ልጄ የማያልቅ ሀብት ይስጥህ፤ አንተ ክብር ልበስ፤ በሄድክበት ሁሉ እጅህ አይድረቅ፤ የሰው እጅ አያሳይህ፣ አበዳሪ ፊት አትቁም፣ አንተም ፊት ተበዳሪ አይቁም፣” እያለ መረቀኝ፡፡ የቀረችኝን  ብር ይዤ ነው እንግዲህ ንግድ የጀመርኩት፡፡

እኔ የማልነግደው ነገር አልነበረም፡፡ እኛ አካባቢ ብርቱካን በብዛት ነበር፡፡ ታዲያ ብርቱካን ስንገዛ በጆንያ ወይም በቅርጫት ተሞልቶ አልነበረም - ከነዛፉ ነው፡፡ ብርቱካኑን ይርጋለም ከተማ ወስደን ካልተሸጠ ቁልቁለት ላይ ደፍተን እንሄዳለን እንጂ ተሸክመን አንመለስም፡፡ እንዲያውም በ1969 ዓ.ም የገበሬ ማኅበር መኪና ለምኜ ብርቱካን አዲስ አበባ ወስጄ ሸጫለሁ፡፡ ደረቅ በቆሎ ወደ አንድ የገጠር ገበያ ወስጄ ካልተሸጠ በሌላ ቀን ወደ ሌላ ገበያ ወስጄ እሸጣለሁ፡፡ የበቆሎ ዱቄት፣ ደረቅም ሆነ እሸት በቆሎ፤ ብርቱካንም ሆነ ሌላ ነገር ሳይሸጥ ትንሽ ከቀረኝ ለእናቴ ይዤላት እገባለሁ፡፡

ዕንቁላልም እነግድ ነበር፡፡ ለኩ ከተማ በብር 36፣ ሃጣጤ ከሆነ በብር 40 ዕንቁላል፤ በ20 ብር 800 ዕንቁላል እገዛ ነበር፡፡ እኔ በብር 34 ሸጬ 6 ይተርፈኛል - ከ800 ደግሞ 120 ዕንቁላል አገኛለሁ፡፡ የተሰበረ ቢኖር ገዢው ጠብሶ ይሰጠኛል፡፡

ለምን?

እንደዚያ ካላደረገ ሌላ ጊዜ አላመጣለትማ! ለሌላ ነጋዴ አሳልፌ እንዳልሸጥበት ይንከባከበኛል፡፡ ዳቦ ለማምጣት ወደ አራዳ የምንሄደው ከሰፈር ልጆች ጋር ብዙ ሆነን ነው - ሌሊት በጭለማ፡፡ በቤራና በይርጋለም መካከል ደግሞ ዳማ የሚባል ወንዝ አለ፡፡ ድልድዩ ረዥም ነበር፡፡ እኔ ባትሪ ነበረኝ፡፡ እያንዳንዱን ልጅ ባትሪ እያበራሁለት ለማሳለፍ አምስት ሳንቲም አስከፍላለሁ፡፡ እንቢ ላለ አላበራለትም፡ ድልድዩን ስቶ ከወደቀ በሌላ በኩል ገብተን ነው የምናወጣው፡፡

ባለዳቦ ቤቱም ብዙ ልጆች ይዤለት ስለምሄድ፣ ለእኔ የሚጋግረው ዳቦ ተለቅ ተለቅ ያለ ነው፡፡ እንደዚያ ካላደረገ ልጆቹን ወደ ሌላ ዳቦ ቤት እወስዳቸዋለሁ፡፡ ዳቦውን ገጠር ስንወስድ የእኔ ከፍ ከፍ ያለ ስለሆነ ቶሎ ሸጬ እጨርሳለሁ፡፡ ልጆቹ ግን ባይሸጥም ግድ የላቸውም፤ ራሳቸው ይበሉታል፡፡ እኔ ጋ ግን ምንም የሚባክን ነገር አይኖርም፡፡ ገንዘብ ስለማጠራቅም ሀብታም ነበርኩ፡፡ በ1966 አካባቢ በ45 ብር የገዛሁት አዲስ ቀይ ሮመር ሰዓትና በ340 ብር የገዛሁት አዲስ የቻይና ብስክሌት ነበረኝ፡፡

በጭለማ ስትሄዱ ችግር አጋጥሟችሁ አያውቅም?

አንድ ቀን ጅብ ላይ ወጥቻለሁ፡፡ እኔ ከሌለሁ እነሱ በጭለማ መሄድ ስለሚፈሩ አይወጡም፡፡ እኔ ግን ሺ ጊዜ ቢጨልም አልፈራም- ሰንጥቄው ነው  የምሄደው፡፡ ጅብ ላይ የወጣሁ ‘ለታም ባትሪ ይዣለሁ፡፡ ነገር ግን ባትሪ ሁልጊዜ አይበራም፡፡ አንደኛ ድንጋዩ ቶሎ ቶሎ ያልቃል፤ ሁለተኛ በጭለማ ውስጥ መሄድ ደግሞ ጀግንነት ነው፡፡ ስለዚህ ሳላበራ ስሄድ ጅብ ላይ ወጣሁ፡፡

በእንዲህ ዓይነት ስሠራ ቆይቼ በ1969 ዓ.ም ጉድ መጣ፡፡ በማላውቀው ነገር “ኢሕአፓ ነህ” ተብዬ ታሰርኩና ክፉኛ ተገረፍኩ፡፡ ዕለቱ ኢሕአፓ ከነገሌ እስከ ሀዋሳ ወረቀት የበተነበት ቀን ነበር፡፡ ከእኔ ሻይ ቤት ጀርባ ቀለም በጥብጠው መልዕክታቸውን ጽፈው በየመንገዱ ሁሉ ወረቀት በትነዋል፡፡ እኔ ሶብሳብ ስር ነው የማድረው፡፡ በዚያን ዕለት በጧት ተነስቼ በብስክሌቴ አባቴ ወደ ላከኝ ስፍራ ሄድኩ፡፡ እኔ በብስክሌቱ ስበር፣ መንገድ ላይ የተበተነው ወረቀት በንፋስ ኃይል እየተነሳ ይበተናል፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች “የታደሰ ልጅ ነው የበተነው” ብለው ለሊቀመንበሩ ነገሩት፡፡

ከተላኩበት ስመለስ ሊቀመንበሩ ጠርቶ “የኢሕአፓ አደራጅ” ብሎ አሰረኝ፡፡ ከዚያም “በዚህ ዕድሜህ አዲስ ሰዓትና አዲስ ብስክሌት ከየት አመጣህ? ኢሕአፓን ለማደራጀት የተሰጠህ ነው አይደል?” በማለት ድንጋይ ላይ አንበርክኮ ገረፈኝና አሰረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ “ኢሕአፓ ናችሁ” ተብለው የሚያዙ ወጣቶች የሚታሰሩት ገጠር ነበር፡፡ እኛም አካባቢ አንድ እስር ቤት ነበር፡፡ እኔም የታሰርኩት ከእነሱ ጋር ስለነበር እነ መኮንን የተባሉት ልጆች የተገደሉ ዕለት ልንቀብራቸው ወጣን፡፡ እኔም “እስከመቼ ነው እዚህ የምስቃየው?” በማለት ጠፍቼ አጐቴ ወደነበረበት ሻሸመኔ ሄድኩ፡፡

ነገሩ ሲረጋጋ ወደ ሰፈሬ ተመልሼ፣ ጀንፈል ቡና (ያልተቀሸረ ቡና) ከገበሬዎች እየገዛሁ በየነ ፍላቴ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር ኮፌሌ፣ አሳሳ፣ ቆሬ፣ … ወደ ተባሉ ቦታዎች እየወሰድን እንሸጥ ጀመር፡፡ ገበሬዎቹ ያምኑኝ ስለነበር ቀፎ ሙሉ ቡና ይሰጡኝና ወስጄ እየሸጥኩ ገንዘባቸውን እሰጣቸዋለሁ፡፡ አሁን ከብድር ወጣሁ፣ ገንዘብ ያዝኩ፤ ራሴንም ቻልኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ስነግድ አንድ ቀን ቡናው በሙሉ ተወረሰብኝ፡፡

በስንት ብር የተገዛ ነበር?

በስምንት መቶ ብር የተገዛ ነበር፡፡ 800 ብር በዚያን ጊዜ በጣም ትልቅ ገንዘብ ነው፡  የመሬት ከበርቴዎች እንኳ ያን ያህል አይኖራቸውም ነበር፡፡

ከዚያስ ምን አደረጉ?

በዚያን ጊዜ አቶ በላይ የተባሉ ሻሸመኔ ይኖሩ የነበር ጠበቃ መኪና ነበራቸው፡፡ እሳቸው ጋ ሄድኩና አቶ በላይ በፈለጉት ገንዘብ በመኪና ረዳትነት ቅጠሩኝ” አልኳቸው፡፡ “ለምን?” አሉ፡፡ “እርሶ ጋ መቀጠር ስለፈለኩ ነው” አልኳቸው፡፡ “እሺ! በቀን አንድ ብር እከፍልሃለሁ” ብለው ጀመርኩ፡፡ ሰውዬው “ጐበዝ ልጅ አገኘሁ” ብለው እንዲያመሰግኑኝና ፍላጐት አለው ብለው እንዲወዱኝ፣ እንጨት ጠርቤ ታኮ ሠራሁና ወደ ቁልቁለት ከቆመ ከፊት፣ ዳገት ላይ ከቆመ ከኋላ ማስገባት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም መኪናው ሲቆም ፈጥኜ እወርድና የሚፈልጉትን ነገር እሰጣቸዋለሁ፡ በሦስተኛው ቀን “በቃ! አልፈልግህም፤ ሌባ መሰልከኝ” አሉኝ፡፡ “እኔ ሌባ አይደለሁም፡፡ ቡና ነጋዴ ነበርኩ፡፡ ቤተሰቦቼ ሲዳሞ አሉ፡፡ ቡናዬ ስለተወረሰና እዚሁ ቆይቼ መንጃ ፈቃድ ማውጣት ስለፈለኩ እንጂ ሌባ አይደለሁም” ብዬ አስረዳኋቸው፡፡ “አይይይ፤ በጣም ቸኮልክ፡፡ አልፈልግህም፡፡ ሁለተኛ መኪናዬ ጋ እንዳትጠጋ” ብለው አባረሩኝ፡፡

እንባ ቢያንቀኝም ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ሻሸመኔ የወህኒ ቤት አዛዥ የነበሩት ሻለቃ አበበ አደሩ አጐቴ ናቸው፡፡ እሳቸው ጋ ሄጄ የሆነውን በሙሉ ነግሬአቸው “ወታደር ቤት እቀጠራለሁ” አልኳቸው፡፡ “ምነው እንዲህ ተማረርክ?” ብለው ጠየቁኝ፡ “ታዲያ ምን ላድርግ? ገንዘቤ ተወረሰ፤ ረዳትነት ብቀጠር ሌባ ብለው አባረሩኝ፡ አንድ ሺህ ብር ካገኘሁ በቆሎ መነገድ እችላለሁ” አልኳቸው፡ “በቃ አንድ ሳምንት ብቻ ጠብቀኝ” ብለው በሳምንቱ የጠየኩትን ብር አምጥተው ሰጡኝና ማሞ ከተባለው አጐቴ ጋር በቆሎ ንግድ ጀመርኩ፡፡ ያኔ በቆሎ ወደ ነገሌና ሀገረማርያም በጣም ስለሚጫን ንግዱ ጥሩ ነበር፡፡ ከአጐቴ ጋር አንዱን ኩንታል በ15 ብር ገዝተን 25 ሳንቲም አትርፈን እንሸጣለን፡፡ እኔ በቆሎውን ከመሬት እየዛቅሁ በጆንያ እየሞላሁ ሰፍቼ እደረድራለሁ፡፡ ለዚያ ሥራዬ በኩንታል 10 ሳንቲም ይታሰብልኛል፡፡ በዚያን ጊዜ የሶማሌ ጦርነት ነበር፡ መኪኖች በግዳጅ ወደዚያ ስለሚሄዱ የትራንስፖርት እጥረት ነበር፡፡ በቆሎው ሳይጫን አንድ ወር ሊቆይ ስለሚችል እጠብቃለሁ፡፡ የጠበቅሁት መቶ ኩንታል ከሆነ፣ 10 ብር ይከፈለኛል፡፡ ሰውዬው ለጋስ ሆኖ 20 ብር ከሰጠኝ፣ ሎተሪ ደረሰኝ ማለት ነው - በደስታ ጮቤ እረግጣለሁ፡፡

በእንደዚያ ሁኔታ እየሠራሁ ጥሩ ገንዘብ አጠራቀምኩ፡፡ “እኔ ኩንታል እየተሸከምኩ ለምንድነው ለማሞ የማካፍለው? ለምንድነው የበቆሎ ንግድ ፈቃድ የማላወጣው?” አልኩና ማዘጋጃ ቤት ሄጄ ፈቃድ እንዲሰጡኝ ጠየኩ፡፡ አልተሳካልኝም፡፡ “የእህል ንግድ ፈቃድ ተከልክሏል” ተባልኩ፡፡

ወደ በቆሎው ንግድ ተመለሱ?

አልተመለስኩም፡፡ አንዲት ሴት አራዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብዙ ጊዜ አጠና ስታራግፍ አይ ነበር፡፡ አንድ ቀን ጠጋ አልኳትና “ወራጅ ስንት ነው? ጨፈቃስ? ተሸጋጋሪስ?” በማለት ጠየኳት፡፡ የሁሉንም ዋጋ ነገረችኝ፡፡ “ለመሆኑ ከየት እያመጣሽ ነው በውድ ዋጋ የምትሸጪው?” አልኳት፡፡ ከኮልፌ እንደምታመጣ ነገረችኝ፡፡ ይህቺን መረጃ ካገኘሁ በኋላ ማዘጋጃ ቤት ሄጄ “የእንጨት ንግድ ፈቃድ ማውጣት ይቻላል?” ብዬ ጠየኳቸው፡፡ “ይቻላል” አሉኝና ሰጡኝ፡፡ ፈቃዱን አውጥቼ አዲስ አበባ መመላለስ ጀመርኩ - በአጠና ንግድ፡፡ የኮልፌ ስፋትና የአጠናው ዋጋ ርካሽነት የሚገርም ነበር፡፡

ዋጋው ስንት ነበር? ያኔ ካፒታልዎ ስንት ደርሶ ነበር?

ዋጋው ሁለት ብርና 2.50 ነበር፡፡ ሙሉው መኪና 900 ብር ያህል ፈጀ፤ ለመኪናው ኪራይ ደግሞ 350 ብር ከፈልኩ፡፡ በዚህ ዓይነት ስመላለስ ቆይቼ፣ አንድ ቀን እዚያው ኮልፌ አካባቢ ስዘዋወር፣ አንድ ሰው ከንች (ለአጥር የሚሆን እንጨት)  ሲሸጥ አይቼ ዋጋውን ጠየኩት፡፡ 15 ብር መሆኑን ነገረኝ፡፡ “ባመጣልህ ትገዛኛለህ ወይ?” አልኩት፡፡ “አዎ” አለኝ፡ “በስንት ትገዛኛለህ?” ብዬ ጠየኩት “ገንዘብ ይዞ ብዙ ጊዜ ይቆያል፡ በዚያ ላይ ብዙ ተመርጦ የሚጣል አለ፡፡ በቃ 6 ብር እገዛሃለሁ” አለ፡፡ አልተከራከርኩም፡፡

ውስጤ በደስታ ስለተሞላ “እሺ!” ብዬ ተለየኋቸው፡፡ አጠናዬን አራግፌ፣ እያንዳንዱን ከንች በ90 ሳንቲም ሂሳብ 400 ብር ያህል አውጥቼ ሙሉ መኪና ወሰድኩላቸው፤ ሰውዬው አቶ ማሞ ይባላሉ፡፡ “አቶ ማሞ እንጨቱን አምጥቻለሁ” አልኳቸው፡፡ በዚያን ጊዜ እንጨት ማሳለፍ በጣም ከባድ ስለነበር በመገረም “እንዴት አሳልፈህ አመጣህ?” አሉኝ፡፡ “እንዴት እንዳለፈ ማወቅ ምን ያደርግሎታል? ቀርቦሎታል - ይግዙ” አልኳቸው፡፡ እንጨቱን ካዩ በኋላ፣ በ5.50 እንጂ በስድስት ብር አልገዛህም” አሉኝ፡፡ “ለምንድነው በስድስት ብር የማይገዙኝ? እኔ’ኮ ይህን እንጨት እዚህ ለማድረስ ብዙ አውጥቻለሁ፤ 5.50 አያዋጣኝም” ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡

እኔን ያስለቀሰኝ ደስታው ነው፡፡ አንዱን እንጨት 90 ሳንቲም ገዝቼ ለመኪና ኪራይና ለተለያየ ወጪ ሁለት ብር ባወጣ፣ ካንዱ እንጨት 3.50 አተርፋለሁ፡፡ በአንድ ጊዜ የማተርፈውን ብር እያሰብኩ ነበር የማለቅሰው፡፡ ኮልፌ፤ አጠና የሚሸጡልኝ ሰው አቶ ተማም ይባላሉ፡፡ በአጋጣሚያ በዚያ በኩል ሲያልፉ ሳለቅስ አዩኝና “አንተ፣ በቀደም አጠና የገዛኸኝ ልጅ አይደለህም እንዴ? ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ “አዎን አውቀውኛል፡፡ አቶ ማሞ ከንች አምጣ እገዛሃለሁብለው ካመጣሁ በኋላ ከእያንዳንዱ ላይ 0.50 ሳንቲም ቀነሱብኝ፡፡ እንጨቱን በ2.90 ነው የገዛሁት፤ ለመኪና ኪራይ ከፍዬ፣ መንገድ ላይ ብዙ ኬላ ስላለ በሁሉም ቦታ እየከፈልኩ ነው ያመጣሁት፤ 0.50 ሳንቲም እንኳ ባገኝበት ያልኩትን ይኼው ቀነሱብኝ” ብዬ ነገርኳቸው፡፡ “ማሞ የሚያድግ ልጅ ማስለቀስ ጥሩ አይደለም፡፡ አንተስ ቤት ልጅ አለህ አይደል እንዴ? በል ክፈለው፤ ከእኔ ጋር እንዳትቀያየም” ብለው ሄዱ፡፡ ሰውዬው የሚፈሩና የሚከበሩ ናቸው፡፡ አቶ ማሞም “እግዚአብሔር ረድቶሃል፤ አቶ ተማምን አመጣልህ” ብለው በስድስት ብር ሂሳብ አስበው ከፈሉኝ፡፡ እኔ ማመን አልቻልኩም፤ በአንድ ጊዜ ብዙ ብር አተረፍኩ፡፡

ስንት ብር አተረፉ?

ከሁለት ሺህ ብር በላይ ነው ያተረፍኩት፡፡ በዚያን ጊዜ ያ ገንዘብ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ገንዘቤን ከተቀበልኩ በኋላ “አሁንም ላምጣ?” አልኩ “አዎ! ግን በ5.50 ነው የምገዛው” አሉ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ምንም አላገኝም፤ በስድስት ብር ነው የምሸጠው” አልኩ፡፡ “እንግዲያውስ አልገዛህም” አሉ፤ “በቃ የእኔንም ወጪ አስበው አስተያየት ያደርጉልኛል” ብዬ ተለያየን፡፡

ከዚያ በኋላ ብዙ ጊዜ እያመላለስኩ ሸጥኩ፡፡ “ከየት እያመጣ ነው የሚሸጥለት?” እያለ የሚፈልገኝ ነጋዴ ስለነበር አቶ ማሞን ትቼ በሰባት ብር ሂሳብ እሸጥለት ጀመር፡፡

በዚህ ሁኔታ ስሠራ ቆይቼ በ1972 ዓ.ም 28ሺህ ብር ነበረኝ፡፡ አንድ ሺህ ብር የሰጡኝን አጐቴን “መኪና ልገዛ ነው?” ብዬ አማከርኳቸው፡፡ እሳቸውም፣ “ደርግ መኪና የሚወርስ አዋጅ ሊያወጣ ስለሆነ አትግዛ፡፡ ከዚህ ይልቅ በጋራ ወፍጮ ብንሠራ ይሻላል” አሉኝ፡፡ በዚህ ተስማምተን ወፍጮ ተኮናትረን መሥራት ጀመርን፡፡

ወፍጮ ቤት እያስፈጨሁና እየሠራሁ ሳለ “ካላገባ ገንዘብ ያባክናል” ብለው የልጆቼን እናት ወ/ሮ ስሜነሽ ኃይሉን ሚያዝያ 23 ቀን 1973 ዓ.ም ዳሩኝ፡፡ ወዲያው ደግሞ “ከአሁን በኋላማ ገንዘብ ወደቤቱ እንጂ ወዲህ አያስገባም” የሚል ሐሳብ አመጡና ከወፍጮ ቤት አባረሩኝ - አጐቴ፡፡ ሀብታም ሆኜ የነበርኩት ሰው ተመልሼ ደኸየሁ፡፡ ከወፍጮ ቤቱ ሲያባርሩኝ 2400 ብር ብቻ ነበረኝ፡፡

ከኮልፌ አጠና በምጭንበት ወቅት ሽንት ወጠረኝና ለአቶ ተማም ነገርኳቸው፡፡ “በዚያ በኩል ፎቅ ወጣና ሽና” ብለው አመላከቱኝ፡፡ ፎቅ ስወጣ በርከት ያሉ ሰዎች ከሞራ ሳሙና ሲሰሩ አየሁና ተገርሜ ማየት ጀመርኩ፡፡ ሰዎቹ “እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አሉኝ፡፡ ሽንት ወጥሮኝ እንደሆነ ነገርኳቸውና ወደ ሽንት ቤት እየገፈተሩ አስገቡኝ፡፡

ከሽንት ቤት ስመለስ፣ እንዴት እንደሚሠሩ በደንብ ቀርጫቸውና ኮፒ አድርጌ ወጣሁ፡፡ አጠናውን እንዳራገፍኩ ሀዋሳ መጥቼ “ሳሙና ፋብሪካ እከፍታለሁና ቦታ ይሰጠኝ” ብዬ ጠየኩ፡፡ ወዲያውኑ ከበቀለ ሞላ ሆቴል በታች ወንዙ አካባቢ ወደ 3200 ካ.ሜ ቦታ ተመራሁና 45 ብር ከፍዬ ቦታውን ያዝኩ፡፡

ከወፍጮ ቤት ስባረር የማደርገው ግራ ገብቶኝ፣ ተስፋ ቆርጬ፣ ሕይወቴንም ለማጥፋት ከጅሎኝ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኃይለኛ አፈሳ ነበር፡፡ ሌሊት ሌሊት መኪና አቁሙው ሥራ የሌለው ሰው እያፈኑ ጭነው ወደ ሁመራ ይወስዱ ነበር፡፡ ወደ ሁመራ ለመሄድ ወሰንኩና የመጀመሪያ ልጃችንን ፀንሳ ለነበረችው ባለቤቴ ነገርኳት፡፡ አንዱን ሺህ ብር ለራሴ አስቀርቼ የቀረውን አንድ ሺህ ብር ሰጥቼያት፣ ለሳሙና ፋብሪካ መስሪያ የተመራሁትን ቦታ ሸጣ ወደ ቤተሰቦቿ እንድትመለስ ነገርኳት፡፡ እሷም በጣም አዝና “አንተን አምኜ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ቆሎም ቢሆን ሸጠን እንኖራለን” በማለት ሐሳቤን እንድለውጥ እያለቀሰች ለመነችኝ፡፡

ለሳሙና መስሪያ የተመራሁትን ቦታ ሌላ ሰው ይጠይቃል፡፡ ማዘጋጃ ቤት በጣም ጥሩ ወዳጅ ነበረኝ፡፡ ሻሸመኔ መጥቶ “ቦታህ ሊወሰድ ነውና በጧት መጥተህ ግብር ክፈል” አለኝ፡፡ እኔም በጧት ሄጄ 45 ብር ከፍዬ ካርኒዬን ያዝኩ፡፡ ሰዎቹ ሦስት ሰዓት ላይ ሲሄዱ “ቦታውን አልተወም፡፡ ከእናንተ ትንሽ ቀደም ብሎ ግብር ከፍሎ ሄደ” አሏቸው፡፡ ሰዎቹም እኔ ጋ መጥተው ቦታውን እንድተውላቸው ጠየቁኝ፡፡ “ሳሙና ልሰራበት’ኮ ነው፡፡

እንዴት እተውላችኋለሁ?” አልኳቸው፡፡ ሰዎቹም “ይህ ሰው የነበረውን መኪና ሰለከሰረ ሸጠ፡፡ አሁን መኪና ማጠቢያ አቋቁመን ልንረዳው ስለፈለግን፣ እባክህን ተባበረንና እንደራደር” በማለት አጥብቀው ለመኑኝና በዋጋ ተደራድረን 2800 ብር ሸጥኩላቸው፡፡አቶ ጤናዬ ታሪካቸው ብዙ ነው፡፡ መሬት የሸጡበትን ብር በአጠቃላይ 4800 ብር ይዘው ከሌሎች ጋር በመሆን በምድር ጦር ሃይፋ መኪና ኮንትሮባንድ የቡና ንግድ ጀመሩና በአንድ ጊዜ 9 ሺህ ብር ሸጡ፤ ከዚያም ሌላ መኪና ፈልገው ቡና በኮንትሮባንድ እየነገዱ በ1974 ዓ.ም በ45ሺህ ብር የጭነት መኪና ገዙ፡፡ ለ11 ዓመት ከሰሩ በኋላ መኪናውን ሸጠው ከጓደኛቸው ጋር በሽርክና ዘይት መጭመቂያ እንዳቋቋሙና ቡና መፈልፈያ እንደተከሉ… በመጨረሻም ቤራ ቢርን እንደከፈቱ ገልፀው በአሁኑ ወቅት 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ቤራ ቢር መቼ ሥራ ጀመረ?

ከስምንት ወር በፊት ነው የጀመረው፡፡ መሳሪያውን የጀርመን ባለሙያዎች ናቸው ተክለውና ሠራተኞች አሰልጥነው የሄዱት፡፡ በየሦስት ወሩ እየመጡም ይቆጣጠራሉ፡፡

ገበያው እንዴት ነው? ሰውስ ምን ይላል?

ገበያው ጥሩ ነው፡፡ እያከሰረን ያለው ከውጭ የምናስገባው ጌሾ፣ ብቅል፣ ሌሎች ቅመሞች ናቸው፡፡ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ብርጭቆው ራሱ ውድ ነው፡፡ አንድ ብርጭቆ ከነቀረጡ 118 ብር ጨርሶ ነው የሚገባው፡፡ የሰው አስተያየትማ በጣም ጥሩ ነው፡፡   ሀዋሳን የረገጠ የውጭ አገር ሰው የእኛን ድራፍት ሳይቀምስ አይመለስም፡፡ የውጭ አገር ዜጐች፣ ከውጭ የሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊና እዚህ ያሉትም የቤቱን አሰራርና ዕቃዎቹን እየዩ የት አገር ሄደህ ነው የሰለጠንከው? እንዴት አሰብከው? እያሉ በጣም ነው የሚያመሰግኑኝ፡፡ እኔ ግን የትም አልሄድኩም፤ እዚሁ ሆኜ ነው፡፡

የድራፍቱ ዋጋ እንዴት ነው?

ለማስለመድ ብለን ነው እንጂ የሚገዛው ነገር ሁሉ ውድ ስለሆነ አያዋጣም፡፡ አዲስ አበባ አንድ ብርጭቆ ድራፍት 33 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ እኛ ግን ቀዩን ድራፍት 23፤ ነጩን 15 ብር ነው የምንሸጠው፡፡

የጥራት ደረጃውን ማነው የሚቆጣጠረው?

ጠማቂዎቹ ኬሚስቶች ናቸው፡፡ የአልኮል መጠኑንና የኬሚካል ይዘቱን በአጠቃላይ የጥራት ደረጃውን የሚቆጣጠረው የቢ ጂ አይ  ኬሚስት ነው፡፡

ለቤራ ቢር ምን ያህል ወጪ ሆነ?

ለመሳሪያዎቹ ግዢና ለቤቱ ግንባታ 11 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ ተደርጓል፡፡

የወደፊት ዓላማዎ ምንድነው?

በሀዋሳ፣ ድራፍት ቢራውን በጠርሙስ ለማሸግ፤ በአዲስ አበባ ደግሞ ሌላ ለመትከል አስቤአለሁ፡፡ ሌላ ደግሞ እንደ ድራፍት እየተቀዳ የሚጠጣ የጥራት ደረጃው ከፍተኛ የሆነ የቪኖ ፋብሪካ ለመትከል ከቤልጂየሞች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡

ድርጅትዎ ለስንት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል?

አሁን 92 ሠራተኞች አሉ፡፡ ወደፊት ያቀድናቸው ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሲሆኑ የሠራተኞቹም ቁጥር ይጨምራል፡፡

ሠራተኞቹ በሥራቸውና በአስተዳደሩ ደስተኞች ናቸው?

አዎ! በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ ተሯሩጠው ይሠራሉ፤ ጉርሻም ያገኛሉ፡፡ በተለይ ብዙ ሰው ሲያስተናግዱ ጥሩ ጉርሻ ያገኛሉ፡፡ በመስተንግዶአችን ደንበኞቻችንም ደስተኞች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መብራት ሲጠፋ በጀኔሬተር ነው የምንጠቀመው፡፡ ያኔ ድራፍቱ አልቀዳ ካለ ቅሬታ የሚሰማቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ በዚህ ጊዜ ተሯሩጠን እናስተካክላለን፡፡

እኔ ከሠራተኞቹ ጋር ዕኩል ነው የምሠራው፡ ሦስት ኃላፊዎች አለን፤ “አለቃ ነን” ብለን ቆመን የምናየውና የምናዘው ነገር የለም፡፡ እኔ  ስለምሠራ ሁሉም ይሠራል፡፡ እኔ አስተናግዳለሁ፤ ሁሉም ቦታ አለሁ፡፡ ሠራተኞችን አምኜ እስከመጨረሻው ሥራዬን አልለቅላቸውም፡፡ ደክሜ ከዘራ እስክይዝ ድረስ እኩል እሠራለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ስሠራ እንሱ ቆመው አይመለከቱም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ሥራዬ እንጀራዬ ነው” ብሎ በተነሳሽነትና በኃላፊነት ቢሠራ ኖሮ አገራችን ድህነትን ድል አድርጋ ትለማና ትበለፅግ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሰው የሚበላው እንጀራ ሥራው መሆኑን አያውቀውም፡፡

ሌላ የሚጨምሩት ነገር አለ?

አዎ! አንድም ደቂቃ ያለሥራ መባከን የለበትም፡ ደቂቃዎች በከንቱ በባከኑ ቁጥር በዚያው መጠን ዕድሜያችንም ይጨምራል፡፡ በልጅነት ባንኮኒ ላይ ከመሯሯጥ፣ በልጅነት ሠርቶ መጦሪያ መያዝ አማራጭ የሌለው የሰው ልጅ ግዴታ ነው፡ ያለበለዚያ ዕድሜ ሲጨምር፣ ጉልበት ሲደክም የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ልመናና የሰው ፊት ማየት፣ መዋረድና መናቅ ይመጣል፡፡

ጊዜና ኑሮ ተለዋዋጭ ነው፡፡ እንደ ድሮ መኖር የለም፡፡ እኔ 40 ዕንቁላል በአንድ ብር ገዝቻለሁ፡፡ ዛሬ አንዷ ዕንቁላል ወደ 3 ብር እየተጠጋች ነው፡ ነገና ተነገ ወዲያ ደግሞ ስንት ልትሰጥ እንደምትችል መገመት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሥራ የሁሉም ሰው መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አዝዞ መከበር የለም፡ መከበር የሚቻለው ሠርቶ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ለመበልፀግና ለመከበር ተግቶ መሥራት አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

 

,------------,,,,,

 

አዎ! አንድም ደቂቃ ያለሥራ መባከን የለበትም፡ ደቂቃዎች በከንቱ በባከኑ ቁጥር በዚያው መጠን ዕድሜያችንም ይጨምራል፡፡ በልጅነት ባንኮኒ ላይ ከመሯሯጥ፣ በልጅነት ሠርቶ መጦሪያ መያዝ አማራጭ የሌለው የሰው ልጅ ግዴታ ነው፡ ያለበለዚያ ዕድሜ ሲጨምር፣ ጉልበት ሲደክም የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ልመናና የሰው ፊት ማየት፣ መዋረድና መናቅ ይመጣል፡፡

 

 

 

 

Read 9911 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:17