Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 00:00

ከቡና ገለባና ከእንጨት ፍቅፋቂ ጢስ አልባ ብሪኬት የሚያመርተው ፋብሪካ ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከቡና ገለባና ከእንጨት ፍቅፋቂ ጢስ አልባ ብሪኬት የሚያመርተው ፋብሪካ ተመረቀ

ሁለት ዓይነት አገልግሎት አለው - በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው ጢስ አልባ ብሪኬት፡፡ አንደኛው፤ ብሪኬቱ ተሰባብሮ፣ ለዚሁ ተግባር ተብሎ በተሰራና “ሲላ” በመባል በሚጠራው አዲስ ዓይነት ምድጃ ተጨምሮ ሲነድ የሚፈጠረው ነበልባል የተፈለገውን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በከሰል ምትክ፣ ወጥ ይሠራበታል፣ ቡና ይፈላበታል፣…፡፡

የሚፈለገው ነገር ተሠርቶ እንዳበቃ፣ የብሪኬቱ ኃይል ስለማያልቅ የከሰለውን ፍም እንደከሰል በባህላዊ ምድጃ ጨምሮ በመጠቀም ወጥ ሊያሞቅ፣ ሻይ ሊያፈላ፣ ቡና ሊቆላበት፣… ይችላል፡፡ ወይም የሚፈለገው ነገር ተሠርቶ እንዳበቃ ፍሙን በውሃ አጥፍቶና በሌላ ጊዜ አድርቆ እንደገና መጠቀም ይቻላል በማለት አስረድቷል የአፍሪካ ብሪኬት ፋብሪካ የምርትና አቅርቦት ማናጀር አቶ ሮበል፡፡

ይህ ጢስ አልባ ብሪኬት፣ የማገዶ እንጨትን ተክቶ የሚሠራ ሲሆን፣ ከሰል ያልሆነ ማገዶ በሚጠቀሙ እንደ ምጣድ፣ ድስት ላሉ ቁሶች ያገለግላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብሪኬቱ ጥቅም እየሰጠ ያለው ድርጅቱ ባዘጋጀውና “ሲላ” በተባለ ልዩ ምድጃ ነው፡፡

የፋብሪካው ዓላማ ብሪኬትን ከቡና ገለባና ከእንጨት ተረፈ ምርት (ሰጋቱራ) በማዘጋጀት የማገዶ እንጨትንና ከሰልን መተካት ነው ያሉት የአፍሪካ ብሪኬት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ገርድ ላደሶተር፣ የደን ጭፍጨፋንና የአየር ብክለትን ለመከላከል ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ሲሉ ፋብሪካው በተመረቀበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ብሪኬት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከአራትና ከአምስት እንደማይበልጡ የጠቀሱት ሚ/ር ገርድ ላደሶተር፤ በጃፓን 200፣ በባንግላዴሽ 500 ተመሳሳይ ፋብሪካዎች መኖር፣ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያመለክት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተጨማሪ ፋብሪካዎች የማቋቋም እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ብሪኬቱን በእንጨት ጋዝ ቴክኖሎጂ ሲጠቀሙ ቤት የሚበክል ጭስ አለው ማለት ስለማይቻል ተጠቃሚዎች የተሻለ ጤና እንደሚኖራቸው፣ በምርት ሂደት ወቅት የታመቀ ሙቀት ስለሚጠቀጠቅ ንፁህና ጠጣር በመሆን ለአቀማመጥ ምቹ መሆኑን፣ ከፍተኛ የካሎሪ ይዘት ስላለውና ረዥም ጊዜ ስለሚነድ ብቃቱ አስተማማኝ እንደሆነና ከቡና ገለባ ስለሚሠራ የደን ውድመትን እንደሚያስቀር ተገልጿል፡፡

አፍሪካ ብሪኬት ፋብሪካ ጢስ የሌለውና ከፍተኛ ብቃት ያለው የተሻለ ምድጃ ለመሥራት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚያበረታታ ውጤት በማግኘቱ ምድጃዎች ሠርቶ ማከፋፈል መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ብሪኬቱ በመንደድ ሂደት ወቅት ከጋዝ ነፃ ነው ማለት ስለሚቻል የመርዛማነት ይዘቱ ከከሰል ጋር ሲነፃፀር 80 በመቶ ያነሰ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሕንድ የቴክኖሎጂ ተቋም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዳሽ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ላቦራቶሪ ድጋፍ ባደረገው ሰፊ ጥናት፣ ብሪኬቱ ከማገዶ እንጨትና ከከሰል ተመራጭ የሚያደርገው ግልጽ ውጤት እንዳለው አረጋግጧል፡፡  በአዲስ አበባ አካባቢ ለማገዶ የሚውለው እንጨት 3400 ካሎሪ ያለው ሲሆን የካሎሪ መጠኑ በማገዶው እርጥበት የሚወሰን ነው፡፡ የብሪኬት ካሎሪ ግን 4200 መሆኑን ብሔራዊ የጂኦሎጂ ተቋም ለክቶ ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ሰጥቶታል፡፡

ከአዲሱ “ሲላ” ምድጃ የሚወጣው የእሳት ነበልባል በዋት ተለክቶ ከሰል ከሚጠቀም ምድጃ ጋር ሲነፃፀር አቅሙ እጥፍ ያህል መሆኑን በውሃና ማዕድን ሚ/ር ላቦራቶሪ የተደረገ ውጤት አሳይቷል፡፡ የከሰል ምድጃና “ሲላ” በምን ያህል ጊዜ ውስጥ አንድን ነገር እንደሚያበስሉ በዚያው ላቦራቶሪ በተደረጉ 51 ሙከራዎች የከሰል ምድጃ በ44 ደቂቃዎች ያበሰለ ሲሆን “ሲላ” ግን 34 ደቂቃዎች ብቻ ነው የፈጀበት፡፡ በጥር 2004 ምርት የጀመረው አፍሪካ ብሪኬት ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በአንድ ፈረቃ 120 ኩንታል ምቹ ማገዶ ወይም ብሪኬት እያመረተ ሲሆን ምርቶቹንም በ10 እና 50 ኪሎ መያዣዎች ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የ “ሲላ” ምድጃ ዋጋ ውድ ነው፡፡ የአንዱ ዋጋ 480 ብር ሲሆን አነስተኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ ገዝቶ መጠቀም አይችልም፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ለትርፍ የቆመ ቢሆንም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ድጐማ በማድረግ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚገኙና ብቻቸውን ልጅ ለሚያሳድጉ የተደራጁ ሴቶች በ150 ብር እየሰጠ እነሱ በ190 ብር እንደሚሸጡ ተገልጿል፡፡ አፍሪካ ብሪኬት ፋብሪካ በ2.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 18 ሠራተኞች አሉት፡፡

 

 

Read 3111 times Last modified on Friday, 13 July 2012 16:33