Saturday, 14 July 2012 00:00

ጎበዝ! እኔ አድማ ላይ ነኝ፤ እናንተስ?

Written by  ምግባር ተካ
Rate this item
(0 votes)

እኔ እየተቃወምኩ ያለሁት ከልክ ያለፈውን ሸማቹን የሚጐዳውን፣ ሥጋውን በልቶ በአጥንት የሚያስቀረውን ቅጣ ያጣ ትርፍ ነው፡፡የመንግሥት ግልበጣ ፖለቲካ መስሏችሁ “ኧረ የምን አድማ! እዚያው በፀበልህ፤ ራስህ ቻለው እንጂ የምን ማስተባበር ነው?” እንዳትሉ፡፡ ፖለቲካ ሳይሆን ወዲህ ነው ነገሩ፤ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ይባል የለ! እንደዚያ ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ፤ የእናንተን አላውቅም እንጂ እኔ የለሁም፡፡ ሞቻለሁ ማለት ይቻላል፡፡ ዕድር ስለሌለኝ ነው እንጂ ይኼኔ ተቀብሬ ነበር፡፡ እናንተዬ፣ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? ኧረ ነፍሳችን ሳትወጣ እንዳይቀብሩን ትንሽ እንኳ እንንፈራገጥ እንጂ!

ምንድነው እሱ? ምን ተፈጠረ? ነው የምትሉት? ለማረጋገጥ ካልሆነ በስተቀር ዳር ዳርታዬ ሳይገባችሁ ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ አዬ ንገረና! ሆዳችንን በሰስፔንስ አትቁረጠው አላችሁ? አዲስ ነገር’ኮ አይደለም የማወራችሁ፤ ያው የምታውቁትና በየጊዜው ኧረ በየቀኑ ማለት ይቻላል፤ እየጨመረ፣ እየወጣ፣ እየተሰቀለ እንደ ኳስ ወደ ሰማይ እየጓነ፣ … የፈለጋችሁትን በሉት፣ የአገልግሎትና የሸቀጦች ዋጋ መናር ነው፡፡

ውይይ! ይህን ልትነግረን ነው’ዴ ኡኡታህን የምታቀልጠው? እኛ’ኮ አዲስ ነገር የምትነግረን መስሎን፣ ምን ተአምር ተፈጠረ? ብለን ነበር ሰፍ ያልነው፤ የምትነግረን ይህን ከሆነ፣ በቃህ፣ በቃህ፣ አንተ ቋጣሪ ነህ፡፡ አንተና መሰሎችህ ናችሁ በየሄድንበት እየተከተላችሁን፣ መጠጥ አላስጠጣ፣ ምግብ አላስበላ፣ ጮማ አላስቆርጥ፣ … ያላችሁን፡፡ እንዲያውም ከእናንተ ጋር እንዳንጋፋ ከዚህም በላይ በናረ፡፡ ደግሞ ይንራል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ልዩነታችን በምን ይታወቃል? ለምትሉት አይደለም መልዕክቱ፡፡

ገቢያችሁ የማይታወቀውን፣ በአየር ባየር (መኒ ላውንደሪ) ኪሳችሁ ላበጠ፣ ካዝናችሁ ለደለበ፣ መጠጥ ቤት ገብታችሁ በየቀኑ ውስኪ ለምታወርዱ፣ ሌሎች የሚያዳምጡትን ሙዚቃ መስማት የሚደብራችሁና እንዲለወጥ ለምታዙና ትዕዛዞች ወዲያውኑ ካልተፈፀመ ማይክራፎን በሽጉጥ ለምትበታትኑ፣ … አይደለም መልዕክቴ፡፡ እንደተባለውም እንደ’ኔ ላሉ ምስኪኖች ነው፡፡

የመልዕክቴን ባለቤቶች ከለየሁ፣ ወደ ጭብጡ ልግባ፡፡ አስገራሚና አሳዛኙ ነገር፣ አንዴ ዋጋው የተሰቀለ ነገር፣ ጥሬ ዕቃው ቢረክስ ወይም አቅርቦቱ ቢንበሸበሽ ዋጋው  አይወርድም፣ እንደ ተሰቀለ ይቆይና ትንሽ ቆይቶ ይጨምራል፡፡ የዚያ ጭማሪ ድንጋጤ ሳይለቀን በሳምንቱ ወይም በ15 ቀኑ ሌላ ጭማሪ ይቆለልብናል፡፡ እኔ አልቻልኩም፡፡ ለማን ላመልክት?

ከትናንት በስቲያ ወደቤቴ ስሄድ፣ መገናኛ አካባቢ ካለ ታዋቂ ካፌ ገብቼ ማኪያቶ አዘዝኩ፡፡ እዚያ ካፌ የማኪያቶ ዋጋ 5 ብር መሆኑን ነበር የማውቀው፡፡ ሁለት ወር ያህል ቆይቼ የዛሬ ሳምንት ወይም 10 ቀን ቢሆን ነው፣ ማኪያቶ ጠጥቼ 6.50 ከፈልኩ፡፡ ሌላ ጊዜ ጥንቁቅ ነበርኩ፡ ብዙ ጊዜ በትናንት ዋጋ ዛሬ ስለማይሸጡ፣ ዋጋ ሳልጠይቅ አላዝም፡፡ ከትናንት በስቲያ ግን ተሸወድኩ፡፡ እንደበቀደሙ ይሆናል በማለት ማኪያቶ ጠጥቼ 7፡00 ብር አስከፈሉኝ፡፡

ተገልጋይ፣ ዋጋ አትጨምሩብኝ ማለት አይችልም - እሺ ይጨምሩ፡፡ እኔ የምለው ቢያንስ ዋጋ ሲጨምሩ ለምን አያሳውቁንም? ነው፡፡ አዲሱን ዋጋ ሰው እስኪለምድ ድረስ የቡና፣ የማኪያቶ፣ የሻይ … ዋጋ ብለው ለምን በትንሽ ወረቀት ግድግዳ ላይ አይለጥፉልንም? እንደዚያ ካደረጉ፣ ዋጋውን አይቶ የተስማማው ይስተናገዳል ያልተስማማው ጥሎ ይሄዳል፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት ደግሞ እርር ያልኩበትን ላጫውታችሁ፡፡ ድሃ አይደለሁ… እንግዲህ ጥሎብኝ ጐመን እወዳለሁ፡፡ ሁለት ወር ተኩል ወይም ቢበዛ ሦስት ወር ይሆናል፡፡ እዚያው መገናኛ አካባቢ ጐመን በሥጋ 25 ብር በላሁ፡፡ ዋጋው እንደዚያው ይሆናል ብዬ ከሦስት ሳምንት በፊት ጐመን በስጋ አዝዤ በላሁ፡፡ ሂሳብ ልከፍል ደረሰኝ ስጠይቅ 34.50 መጣልኝ፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ፤ ያን ያህል ይጨምራል ብዬ ስላልገመትኩ በጣም ነው ክው ያልኩት፡፡ አስተናጋጁን

“ምንድነው ይኼ?” ብዬ ስጠይቀው፤ ጥርሱን ብልጭ አድርጐ “እንደዚያው ነው” አለኝ፡፡

“ከሁለት ወር በፊት 25 ብር ነበር የከፈልኩት፡ መቼ ነው የጨመረው?” አልኩት፡፡

“ኧረ ቆይቷል ወር ያልፋል፡፡ ያኔም ቢሆን 28 ብር እንጂ 25 አልነበረም” አለኝ፡፡

“እሺ ይሁን! ዋጋ ስትጨምሩ ለምን አታስታውቁንም?” ስለው

“የሚያውቁ መስሎኝ ነው” አለኝ፡፡

አሁንም ስህተቱ የእኔው ነው፤ ዋጋ ሳልጠይቅ መብላቴ፡፡ ከአሁን በኋላ በምንም ዓይነት ዋጋ ሳልጠይቅ አላዝም፡፡ እናንተም የእኔ ስህተት ትምህርት ይሁናችሁ እላለሁ፡፡

ካዛንቺስ አካባቢ አንድ ክትፎ ቤት አለ፡፡ ክትፎው ጥሩ ስለሆነ ብዙ ሰው ይራኮትበታል - በተለይ ፆም መያዣ ወይም መፍቻ ሲሆን፡፡ እኔ ያን ቤት የማውቀው የክትፎ ዋጋ 8 ብር በነበረ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ 10፣ 12፣ 15፣ 17፣ 20፣ 23፣ 27፣ 32፣ …እያለ 40 ቤት ገባ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ

“የጥራጥሬ ዋጋ ስለጨመረ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል” ብለው ለጠፉ፡፡ እዚያ ቤት ደስ የሚለኝ ነገር ዋጋ ሲጨምሩ ያሳውቃሉ፡ መጠነኛ ያሉት 8 ብር ጨምረው ነው፡፡ አስተናጋጁን በቀልድ፣ “እስካሁን ምን ዓይነት ጥሬ ነበር ስታበሉን የነበረው?” ብዬው ከፍዬ ወጣሁ፡፡ 53፣ 66፣ 75…እያለ 80 ቤት መድረሱን ከሰማሁ በኋላ በቅርቡ ደግሞ ስንት ደረሰ? ብዬ ሄጄ ነበር፡፡ “ቅቤ ስለተወደደ ዋጋ ጨምረናል” ይላል እንጂ ትክክለኛ ዋጋውን አይገልጽም፡፡ እኔ ከ48 ብር በኋላ አልበላሁም፤ አድማ አደረኩ፡፡

እዚያው ካዛንቺስ አካባቢ 8 ብር ይበላ የነበረ ዱለት፣ 10፣ 12፣ 14፣ 16፣ 19፣…እያለ ዛሬ 25 ብር ደርሷል፡፡ ቀይ ወጥና ቅቅል ደግሞ 12፣ 14፣ 16፣ 19፣ 22፣ እያለ ዛሬ 30 ሆኗል፡፡ ነገ ደግሞ ስንት ይሉን ይሆን? እኔ እዚያ ቤት አድማ የጀመርኩት 19 ብር ሲገባ ነበር፡፡

አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ፣ ካዛንቺስ ያሉ አራት ሉካንዳ ቤቶች ዋጋ የጨመሩት ስብሰባ ተቀምጠው ነው አሉ፡፡ መንግሥት ኪሎ 50 ብር ሽጡ ሲላቸው እነሱ “ከእኛ ነው ከመንግሥት” እያሉ የእኛ የሚሉትን 80 ብር ይሸጡ ነበር፡፡ ለፋሲካ፣ ያን ዋጋ 110 ብር አስገቡት፡፡ በቅርቡ ጨምረው እንደሆን አላውቅም እንጂ ስብሰባ ተቀምጠው 130 ብር እንዳስገቡት ወዳጄ ነግሮኛል፡፡

ስለዚሁ የሥጋ ዋጋ ስናወራ ቁርጥ የምትወደዋ የሥራ ባልደረባዬ “አንተ ይህን ትላለህ፣ የናዝሬቱ ባለሥጋ ቤት እዚህ ሥጋ ቤት ከፍቶ አንድ ኪሎ 170 ብር እየሸጠ ነው” አለችኝ፡፡ እኔስ ጥሬ ስጋ አልበላም፤ ይብላኝላችሁ አልኳት፡፡ ሌላዋ ባልደረባዬ ደግሞ “ጥሬ ሥጋ ካልበላህ ኢትዮጵያዊነትህ በምን ይገለጻል? በመታወቂያ ወረቀት?” አለችኝ፡፡ መታወቂያዬም ብሔሬን ነው እንጂ ኢትዮጵያዊነቴን አይገልጽም፡፡ የየት አገር ዜጋ እንደሆንኩ ለራሴም ግራ ገብቶኛል አልኳት፡፡ እሷም “ቀልዴን ነው፤ እኔም ጥሬ ስጋ አልበላም” አለች፡፡

እኔ የምለው፤ ይኼ የዜግነት ነገር ኢትዮጵያዊነት ቀርቶ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ …እንደተባለ ቀረ አይደል? ያልገባኝ ነገር የሌሎች አገር ዜጐች በአገራቸው ነው ወይስ በጐሳቸው ነው ዜግነታቸው? ለምሳሌ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሕንድ፣ ብዙ ጐሳ አላቸው፡፡ የእነዚህ አገር ዜጐች፤ ናይጄሪያዊ፣ ኬንያዊ፣ ሕንዳዊ፣ እንጂ በጐሳቸው አይጠሩም፡፡ የእኛ ታዲያ እንዴት በጐሳ ሆነ? የእኔ ነገር የጀመርኩትን ርዕሰ ጉዳይ ትቼ ወደ ሌላ ሄድኩ አይደል? ይቅርታ፡፡

እዚህ ላይ ነጋዴ በኪሳራ ወይም በዋናው ብቻ ይሽጥ እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ማንኛውም ቢዝነስ ለትርፍ እንጂ ለጽድቅ አይሠራም፡፡ ሰው ሠርቶ፣ ነግዶ ማትረፍ አለበት የሚል ጽኑ አቋም እንዳለኝ ይታወቅልኝ፡፡ እኔ እየተቃወምኩ ያለሁት ከልክ ያለፈውን ሸማቹን የሚጐዳውን፣ ሥጋውን በልቶ በአጥንት የሚያስቀረውን ቅጣ ያጣ ትርፍ ነው፡፡ በውጪው ዓለም የሚሠራበት የትርፍ ሕግ አለ፡፡ አንድ ሰው ማትረፍ ያለበት የወጪውን 10 በመቶ፣ ቢበዛ ደግሞ እንደ ዕቃውና እንደሁኔታው 50 በመቶ ቢደርስ ነው፡፡ በእኛም አገር ሕጉ ቢኖርም አይሠራበትም፡፡ አንድ ነጋዴ የወጪውን 100፣400፣ 500…ፐርሰንት ወይም ሺህና 4ሺህ በመቶ ካላተረፈ አይሸጥም፡፡

አንድ ተረት ላጫውታችሁ፡፡ ድሮ ነው፤ አንድ ሰው በየቀኑ የወርቅ ዕንቁላል የምትጥል ዶሮ ነበረችው አሉ፡፡ በየቀኑ የወርቅ ዕንቁላሉን መሰብሰብ ትቶ በአንድ ጊዜ ለመክበር “ለምን አርጄያት ሆዷ ውስጥ ያለውን ዕንቁላል አላፍስም?” ብሎ አረዳትና እስከነአካቴው አንዱንም አጣ ይባላል፡፡

እኔም የምለው ነጋዴዎቹ ምን አለ ቀስ ብለው ቢከብሩ? እኛ እኮ የትም አንሄድባቸውም፤ አብረን አይደል ያለነው፡፡ ቀስ እያሉ ቢያልቡን ይሻላል እንጂ በአንድ ጊዜ ለመክበር ብለው ካረዱን የሚጐዱት እነሱው ናቸው - እንደ ባለዶሮው ማለቴ ነው፡፡

ኳሷ በእነሱ እጅ ስላለች አይደል እንደፈለጉት የሚያደርጉን! ኳሷን ለምን አንቀማቸውም፡፡ እንዴት መሰላችሁ? እናድምባቸው! ለአንድ ቀን፣ ለአንድ ሳምንት፣ ለአንድ ወር ጨክነን ለሽያጭ ያቀረቡትን ነገር “አንገዛም” ብለን እናድም፡፡ ሥጋው፣ ክትፎው፣ ኬኩ፣ ቡናው፣ ማኪያቶው፣ አልሸጥ ብሎ ሲበላሽ ልክ ይገባሉ፡፡ እንዲከስሩ ፈልጌ አይደለም፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት እንተዳደር ለማለት ነው፡፡

ገንዘቤን እንደፈለኩ ባደርግ፣ ብቀደው፣ ባቃጥለው፣ በፈለኩት ዋጋ ብገዛ ምን አገባችሁ? የሚሉትን አይደለም እያነሳሳሁ ያለሁት፡፡ የእነሱ አኗኗሪ የሆኑትን ድሆችን ነው፡፡ ማን ይመራል? የሚለው አያሳስባችሁ፡፡ ሆድ የባሰን እኔም ሌሎችም አለን፡፡ እናንተ ብቻ ባለመግዛት፣ ባለመጠቀም፣ ተባበሩን፡፡

ያኔ ብቻ ነው በነፃ ገበያ ሥርዓት መተዳደር የምንጀምረው!

ጎበዝ እኔ አድማ ላይ ነኝ! እናንተስ?

 

 

Read 3602 times Last modified on Friday, 13 July 2012 16:38