Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 July 2012 11:31

“ታክስ፤ የህግ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የአካውንቲንግ እውቀትን ይጠይቃል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን መሰረት አድርጐ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር (የካቲት 5 ቀን 1995 ዓ.ም) በወጣ መመሪያ ዳቦ፣ እንጀራ ወይም ወተት የመሸጥ ሥራ ከታክሱ ነፃ ተደርጓል፡፡ “እነዚህን አቅርቦቶች ከታክሱ ነፃ የሆኑበት ምክንያት ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አቅርቦቶች በመሆናቸው ሲሆን አቅርቦቶቹን የሚያቀርብ ሰው እያከናወነ ያለው ተግባር ዕቃ የማቅረብ ተግባር ነው፡፡ “ነገር ግን ዳቦን ከሻይ ጋር አጣምሮ ወይም ወተትን አፍልቶ ወይም እንጀራን ከወጥ ጋር ቀላቅሎ መሸጥ እቃ የመሸጥ ተግባር ሳይሆን የካፊቴሪያ ወይም የምግብ ቤት አገልግሎት መስጠት ይሆናል፡፡ “በመሆኑም ዳቦን፣ እንጀራን ወይም ወተትን ብቻውን የሚሸጥ ሰው እቃ አቀረበ የሚባል ሲሆን እነዚሁን ዕቃዎች በካፍቴሪያ ወይም በምግብ ቤት የሚያቀርብ ሰው ግን የካፊቴሪያ ወይም የምግብ ቤት አገልግሎት ሰጠ ይባላል፡፡

“ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዕቃ አቅራቢው ገቢው ከ500 ሺ ብር በላይ ቢሆንም እንኳን ታክሱን የመክፈል ግዴታ የሌለበት ሲሆን የካፊቴሪያ ወይም የምግብ ቤት አገልግሎት የሚሰጠው ሰው ግን ገቢው ከ500 ሺ ብር በላይ ከሆነ ለታክሱ የመመዝገብ ግዴታ እና ታክሱን የመክፈል ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡”

ከላይ የቀረበው ድንጋጌ የተወሰደው “ተጨማሪ እሴት ታክስ በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በሳሙኤል ታደሰ ተዘጋጅቶ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ለአንባቢያን ከቀረበው መፅሐፍ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በወጣ አሥረኛ ዓመት ዋዜማ ታትሞ የቀረበው መፅሐፍ፤ ባለፉት ዓመታት ሕብረተሰቡ ግር ለተሰኘባቸው ብዥታዎች ማጥሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰፋ ያሉ መረጃዎችን ይዟል፡፡ ከቫት ነፃ የሆኑት ዳቦ፣ እንጀራና ወተት የቫት ሰለባ የሚሆኑበት ምክንያት ምን እንደሆነ የቀረበው አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በ288 ገፆች የቀረበው መፅሐፍ፤ ግብርና ታክስ በአለም ላይ ምን ታሪክ እንዳላቸው በማመልከት ነው ወደ ተነሳበት ርእሰ ጉዳይ የሚዘልቀው፡፡ ግብርና ታክስን “ክፈል፤ አልከፍልም” ሙግትና ትግል ከክርስቶስ ልደት በፊት በእስራኤላዊያን ዘንድ ይታይ እንደነበርና ንጉሥ ሰለሞን ግብርን ከሕዝቡ አስገድዶ ይቀበል እንደነበር ተገልጿል፡፡

ግብርና ታክስ አንዱ ሌላውን መወንጀያ፣ ማሳደጃ፣ መውቀሸያ… የመሆኑ ታሪክም እጅግ ጥንታዊ እንደነበር፤ ከሳሾቹ ከቄሳር ጋር ሊያጣሉት ሲሞክሩ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዜአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሎ በብልሃት ያሸነፈው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክም ተጠቅሷል፡፡በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሀብት ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት “ዘካ” በመባል የሚታወቀው ሃይማኖታዊ ግዴታ፣ በተለይም እስልምናን እንደ መንግሥት ሃይማኖት ተቀብለው የሚከተሉ አገራት ሕግ አውጥተው ዘካን እንደ ግብር በግዴታ እንደሚሰበስቡ ፓኪስታንን በምሳሌነት አቅርቧል - መፅሐፉ፡፡

በጥንታዊ ግብፅ፣ ግሪክ፣ ሮም ግብርና ታክስ የመሰብሰብ ሂደት ምን ይመስል እንደነበር የሚያስቃኘው የሳሙኤል ታደሰ መፅሐፍ፤ እንግሊዝና ፈረንሳይን ጦር ያማዘዘው የግብርና ታክስ ታሪካቸው ምን ይመስል እንደነበርም ያስቃኛል፡፡

በግብፅ፣ በግሪክ፣ በሮም እንደታየው ሁሉ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም በነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ቀረጥ ይሰበሰብ ነበር፡፡ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ የታክስና ግብር ሥርዓት እድገት እንዳሳየው ሁሉ በኢትዮጵያም ከ1412 እስከ 1429 ዓ.ም በአፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት ሰላሳ ዘጠኝ ግዛቶች ለማዕከላዊ መንግሥት ግብር ይከፈሉ እንደነበር ምንጭ ጠቅሶ ገልጿል፡፡

ግብርና ታክስን በተመለከተ ከጥንታዊያኑ ግብፅ፣ ግሪክና ከሮም ጋር ትመደብ የነበረችውና በመካከለኛውም ዘመን ከእንግሊዝና ፈረንሳይ እኩል ትታይ የነበረው አገራችን በብዙ ዘርፎች እንደሚታየው ተከታታይና ቀጣይነት ያለው እድገት ሳታስመዘግብ ቀረች፡፡ ሆኖም በ1995 ዓ.ም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን በማውጣት ጥለዋት የሄዱት አገራት ላይ ለመድረስ የሚያፈጥናትን አቋራጭ መንገድ የተከተለች ይመስላል፡፡

ስለ ተጨማሪ እሴት ታክስ የጥናት ፅሁፎች መቅረብ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ነው የሚለው የሳሙኤል ታደሰ መፅሐፍ፤ ታክሱን የግብር ሥርዓቷ አድርጋ በመንቀሳቀስ ጀማሪዋ ፈረንሳይ ነበረች - አ.ኤ.አ በ1948፡፡

በመቀጠል ኮትዲቭዋር፣ ሴኔጋል ተግባራዊ አደረጉት፡፡ እ.ኤ.አ በ1960 እና በ1970ዎቹ ብዙ የዓለም አገራት እንደ ተቀበሉት የሚጠቁመው መፅሐፍ፤ “በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ ዓመታት በዓለማችን የታክስ ሥርዓቶች ውስጥ ከታዩ እድገቶች መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ እድገት ዋነኛው ነው” ይላል፡፡

መንግሥታት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሥርዓትን እንዲከተሉ ያተጋቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና የደቡብ አሜሪካ አገሮች የተጨማሪ እሴት ታክስ ሥርዓትን የሚጠቁሙበት ምክንያትን የሚጠቁመው መፅሐፉ፤ ታዳጊ አገሮች የግብር ሥርዓቱን እንዲከተሉ ያስገደዳቸው ዋነኛው ምክንያት ከቀጥታ ታክስ የሚያገኙት ገቢ የሚያወላዳ ባለመሆኑ እንደሆነ ገልፃ፤ በአገራችንም በዚህ ዋነኛ ዓላማ አዋጁ እንደወጣ ተጠቅሷል፡፡

“ከአርባ አመት በፊት በዓለማችን በጥቂት አካባቢዎች ብቻ ይታወቅ የነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስ፤ በአሁኑ ወቅት 4 ቢሊዮን የሚያህል ሕዝብ ወይም ከዓለማችን ሕዝብ 70 በመቶ ያህሉ በሚገኝባቸው አገሮች ተግባራዊ ሆኖ ይገኛል” የሚሉት የመፅሐፉ ደራሲ፤ በ1996 ዓ.ም በፌደራል አገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን በነገረ ፈጅነት ተቀጥረው ሲገቡ ጀምሮ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች መኖራቸው እንደተረዱ ይገልፃሉ፡፡

“የታክስ ህግ በአንፃራዊነት ሲታይ ከሌሎች የህግ አይነቶች ሁሉ በውስብስብነቱ የታወቀ ነው፡፡ የዚህም ዋና ምክንያት ሆኖ የሚነሳው ደግሞ ህጉ የሌሎች በርካታ የማሕበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ማለትም የህግ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና የአካውንቲንግ ድምር ውጤት ሲሆን ህጉን በቀላሉ ለመረዳት በርካታ ባለሞያዎች ብዙ መሥራት ወይም መፃፍ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡”

በዚህ ምክንያትና ዓላማ ተጨማሪ እሴት ታክስን ርእሰ ጉዳይ ያደረገ መፅሐፍ ያዘጋጁት ደራሲው፤ ስለ ታክስ ምንነት፣ አተገባበሩ በተለያዩ አገራት ምን እንደሚመስልና በአገራችን በ1995 ዓ.ም የወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ ዋና ዋና ድንጋጌዎች ምን እንደሚመስሉ ምሳሌና ማሳያ እያቀረቡ ለማስረዳት ታትረዋል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አስር ዓመት ገደማ ቢሆነውም አሁንም ድረስ “በምንበላውና በምንጠጣው ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉ አግባብ አይደለም” የሚል ቅሬታ በስፋት ይደመጣል፡፡ ምግብ የቫት ሰለባ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሕጋዊ ትርጉሙን በሙያዊ ትንታኔ አቅርበዋል - ደራሲው፡፡

ለረጅም ዓመታት ልማዳዊ በሆነ መልኩ ሲሰራበት የቆየውን የግብርና ታክስ ሥርዓትን ለማሻሻል ከ1983 ዓ.ም በኋላ አገሪቱ የተከተለችውን የኢኮኖሚ ስርዓት መሰረት አድርጐ የወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በሥራ ላይ ሲውል የታዩት ክፍተቶች በዘርፉ ላይ ብዙ ሥራ መሰራት እንዳለበት ያመላከተ ነበር የሚሉት ፀሃፊው፤ ደራሲ በተለያዩ ጊዜያት በወጡ ሕጐች ውስጥ የተፈጠረ ልዩነት፣ የታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ድክመትና የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ተጠያቂነት አናሳ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ለአገራችን አዲስ እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ መደናገርና ብዥታ በአስፈፃሚውና በፈፃሚው ወገን ላይ ይታያል ያሉት ደራሲው፤ የታክስ ሥርዓቱ አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን የሚያመለክቱ ምሳሌና ትንታኔዎችን አቅርበዋል - በመፅሃፉ ማጠቃለያ፡፡

ህዳር 1 ቀን 1996 ዓ.ም በፌዴራል አገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን በሕግ ባለሙያነት ሲቀጠሩ መሥሪያ ቤቱ ስልሳኛ ዓመቱን ያከበረ ቢሆንም “በህግ ባለሙያነት ስራዬ ተግባራዊ ስለማደርጋቸው ህጐች የተፃፈ አንድ መፅሐፍ እንኳን አለመኖሩ ስልሳ አመት ስንት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል” የሚሉት የመፅሐፉ ደራሲ ሳሙኤል ታደሰ፤ በፌደራል አገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣንና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ለስምንት አመት ካገለገሉ በኋላ በተጨማሪ እሴት ታክስ ዙሪያ መፅሐፍ አዘጋጅተው ማሳተማቸው ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችንም ለተመሳሳይ ሥራ የሚያነሳሳ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ነው፡፡ መፅሐፉ ሐምሌ 12 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ ቪው ሆቴል በተመረቀበት ምሽት በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ተፈራ ዋልዋ “ጡረታ የወጣሁት እረፍት ፈልጌ የነበረ ቢሆንም ወጣቶች በየመድረኩ እየጋበዙኝ ንግግር ማድረጌን ቀጥያለሁ፡፡ በመፅሐፍ ምረቃ ላይ ስገኝ ሁለተኛ ጊዜዬ ነው፡፡ ዛሬ ወደዚህ መድረክ እንድመጣ ምክንያት ከሆነኝ አንዱ ሳሙኤል ታደሰ መፅሐፍ ባዘጋጀበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ሥራዎች እንዲሰሩ አልሞ መፅሐፉን ማሳተሙን በመስማቴ ነው” ብለዋል፡፡

ሌሎች ባለሙያዎችም ለደራሲውና ለመፅሐፉ ያላቸውን አድናቆት በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

Read 11116 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 11:43