በ120 አገሮች በጣም ተወዳጅ የሆኑ የተለያዩ ቢራዎችና ለስላሳ መጠጦች በማቅረብ ውጤታማ የሆነው ባቫሪያ ኤን ቪ በኔዘርላንድ፣ ከአርሶ አደሮች ኀብረት ሥራ ማኅበር ጋር በሽርክና ግዙፍ የብቅል ፋብሪካ አቋቁሞ ምርቱን በመላው ዓለም እያሰራጨ የሚገኝ ትልቅ ኩባንያ ነው፡፡ ባቫሪያ ኤን ቪ በኔዘርላንድና በሌሎች አገሮች ከ1000 በላይ ሠራተኞች እንዳሉትና በዓመት 6.5 ሄክቶ ሊትር ቢራ እያመረተ 70 በመቶ ምርቱን ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡
የባቫሪያ ኤን ቪ ሐበሻ ቢራ ፋብሪካን መቀላቀል፣ የኩባንያው አመራሮች በፋብሪካው የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽአ ያደርጋል ያለው የሐበሻ አክሲዮን ማኅበር ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ ባቫሪያ ኤን ቪ በቢራና በብቅል ምርት በዓለም ጉልህ ድርሻ ስላለው፣ ሐበሻ ቢራ ፋብሪካ፣ አስተማማኝ የገበያና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዕድል ይኖረዋል ብሏል፡፡