Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:41

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ ጠ/ሚ መለስ ምን ዘገቡ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አወንታዊና አሉታዊ ገፅታዎች

ይህ በመላ አሜሪካ ተወዳጅ የሆነ የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት በበኩሉ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1990ዎቹ አምባገነኖችን በመገርሰስ ዴሞክራሲን ያሰፍናሉ ተብለው ከተሞገሱት የአዲሱ ትውልድ መሪዎች ዋነኛው መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በልማት ላይ ባደረጉት አስተዋጽኦ እንደማመሰገነኑና ነገር ግን እ.ኤ.አ በ1995 ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ስልጣንን ለራሳቸው ጠቅልለው በመያዝ ተቃዋሚዎቻቸውንና ስለ እሳቸው መጥፎ የሚጽፉ ጋዜጠኞችን በማሰር በአገሪቱ የፍርሐት ሁኔታን የፈጠሩ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡

ከሶስት ወይም አራት ወራት በፊት ዓለማየሁ ገላጋይ እና በዕውቀቱ ስዩም አንድ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ይጽፉት የነበረው ክርክር የሚመስል ነገር የበርካታ አንባቢን ቀልብ ስቦ  እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ካልዘነጋሁት የክርክሩ ጭብጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ስለነበሩት ጃፓንና ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም የአንድ የጃፓን ንጉስና የአጼ ቴዎድሮስ መመሳሰልና አለመመሳሰል ነበር፡፡ እየቆየ ጉዳዩ አጼ ቴዎድሮስ ስብእና ላይ መሽከርከር ጀመረና ነገሩን ወደ ጡዘት ወሰደው፡፡ አለማየሁ ገላጋይ ንጉሰ ነገስቱን ታላቅ ራዕይና ብሩህ አእምሮ፣ ደግ፣ መሃሪና በዘመናቸው ከጥሩ ነገር ውጭ ምንም እንከን የማይገኝባቸው ወደ መለኮታዊነት የተጠጉ አድርጐ ሲያቀርብ፤ ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም ደግሞ እሳቸው ደም የጠማቸው ጨካኝ፣ ክራንቻና ቀንድ ያላቸው ሰው በላ አድርጐ ለማቅረብ ሞክሮ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ፀሐፊዎቹ እርስ በእርሳቸውም መወራረፍ ጀምረው ነበር፡፡ ሁለቱም ፀሐፍት ያነሱዋቸው ሃሳቦች ከታሪክ መጻሕፍት ጋር ቅርበት ላለው አንባቢ አዲስ አይመስሉኝም፡፡ ይልቅ በርካቶች የክርክሩ አካሄድ ትክክል ያለመሆኑን ይነጋገሩበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ እዛው ጋዜጣ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በገሳጭ ብዕራቸው ያስተላለፉት መልዕክት የበርካታ አንባብያንን ሃሳብ ያስተጋባም ይመስለኛል፡፡

ከላይ በጠቀስኩት ጉዳይ ላይ እኔ የታዘብኩትና ሁሌም የሚከነክነኝ አንድ ጉዳይ ግን፣ ይህ አይነቱ ጥግ የያዘ አስተሳሰብም ሆነ አጻጻፍ የእኛ የበርካቶች ኢትዮጵያዊያን ባህርይ እየሆነ የመጣ መምሰሉ ነው፡፡ አንዱን መደገፍ አሊያም መቃወም፡፡ (You are a friend or an enemy) አይነት አካሄድ፡፡ ሰሞኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈተ ሕይወት ተከትሎ ይህ ሁኔታ በጉልህ የተንፀባረቀ ይመስለኛል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ያለውን እንተወውና በመገናኛ ብዙኃን በኩል ሲለፈፍ የከረመውን ብንመለከት የኢሳት፣ የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮ የአማርኛ ፕሮግራሞች እንዲሁም በርካታ በውጭ አገራት የሚሰሩ የድረ ገጽ መገናኛ ብዙኃን/ብሎጐች በአብዛኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነንና ጨቋኝ፣ የገነቡት ስርዓትም ብዙ ፋይዳ የሌለው የሚያስመስሉ ዘገባዎችንና ቃለመጠይቆችን አስተያየት ሰጭዎች ለማቅረብ ሲሞክሩ፤ በአንጻሩ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዲሁም የህትመት ውጤቶችና ሌሎችም የግሉ ዘርፍ ጋዜጦችና ኤፍ ኤም ራዲዮኖች በአብዛኛው ያስተጋቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍጹማዊነትና ያለ እሳቸው ኢትዮጵያ ምን ይውጣታል የሚል ዝንባሌ ያለው ዘገባ ነበር፡፡

ይህ ማለት በሁለቱም ወገን የቀረቡት ሃተታዎች እውነት የላቸውም ማለት ሳይሆን ከሁለቱ የተውጣጣ የእሳቸውን ህይወትና የገነቡትን መንግስት በትክክል ለመግለጽ የሚያስችል ዘገባና ሃተታ ለመስራት አይቻልም ነበር ወይ ለማለት ነው? በእኔ አመለካከት በወዳጅነትና በጠላትነት ሁለት ጥጐች መሃል በእውነትና በምክንያት የተደገፈ ቦታ ያለ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለጋዜጠኞችና ለመገናኛ ብዙኃን!

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለቁጥር የሚያታክቱ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈተ ሕይወት፣ ውርሶችና (legacy) ከሳቸው በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል በሰፊው ዘግበዋል፡፡ እርግጥ ነው እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ጥቅሙ እንዲከበርለት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩለት አካል ፈጽሞ የለም፡፡ ለእውነትና ለእውነት ብቻ የቆሙ ናቸው እያልኩ ሳይሆን በአብዛኛው የሙያው የመርህ አጥሮችን በፈለጉት ሰዓት አይን ባወጣ ሸፍጥ እያፈራረሱ የሚፈልጉትን አይጽፉም፡፡ በርካታ ዘገባዎቻቸው ሚዛናዊና በእውነተኛ መረጃ የተደገፈ፣ ምክንያታዊነት ያላቸው ናቸው ለማለት ግን የሚያስችል ይመስለኛል፡፡

በዛሬው ጽሑፌም እነዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈተ ሕይወት አስመልክቶ የዘገቧቸውን ዘገባዎች በጨረፍታ እዳስሳለሁ፡፡

ዘ ኢኮኖሚስት

ስለ አቶ መለስና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በተደጋጋሚ በመዘገቡ የምናስታውሰው የእንግሊዛዊያን ተወዳጅ ጋዜጣ (ቅርጹ መጽሔት ቢሆንም ለምን ጋዜጣ እንደሚሉት አይገባኝም) አምባገነንነትን ቅቡል ለማድረግ የሞከረ ሰው (The man who tried to make dictatorship acceptable) በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለጋሽ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከተሉትን አሰራር እርሳቸው በፈለጉት መንገድ ማስኬድ ያስቻሉ፤ በዚህም አገራቸው በአፍሪካ ከፍተኛውን የለጋሾች እርዳታ ለማግኘት እንዳስቻሏት ይገልጻል፡፡ ዘገባው አያይዞም ይህን ከፍተኛ የውጭ እርዳታ በርካቶች አለአግባብ ሲያባክኑት፣ ኢትዮጵያ በተገቢው መንገድ በጥቅም ላይ እንድታውለው በማድረግ ባለፉት አስር ዓመታት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት በእጥፍ የሚልቅ የ10.6 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መቻሏን የዓለም ባንክን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጐች ቁጥር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገሪቷን ሲረከቡ ከነበረው 45% ወደ 30% በመቶ ዝቅ ለማድረግ መቻላቸውን፤ በኢንዱስትሪውና በግብርናው ዘርፍ ዕድገቶች መመዝገባቸውንና፤ የውጪ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን፤ በርካታ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በመገንባት ላይ መሆናቸውንና በቅርብ ዓመታት ሲጠናቀቁም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ተጨማሪ አጋዥ እንደሚሆኑ አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላኛው ሪከርዳቸው ጨቋኝ እንደሆኑ እንደሚያሳይም ጋዜጣው አልሸሸገም፡፡ ለዚህም አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችን ጠቅሶ ትርጉም ያለው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት እንዳይኖር በማድረጋቸው በፓርላማ ውስጥ ያለው የተቃዋሚ ወንበር ቁጥር አንድ ብቻ መሆኑን፤ ነጻ የሆኑ ማህበራት ከመምህራን ማህበር እስከ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን በማፈራረስና የሲቪል ማህበራት ከውጭ ሀገር በሚመጣ የገንዘብ ድጋፍ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በመግታት፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችን በማሰርና ከአገር እንዲሰደዱ በማድረግ እንዲሁም በነጻው ፕሬስ ላይ የፈጠሯቸውን አሉታዊ ተጽኖዎች በመጥቀስ ኮንኗቸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረኮች ደግሞ አቶ መለስ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ መሆናቸውን፣ የአሜሪካ አብራሪ - አልባ አውሮፕላኖች ማረፊያና መነሻ ቦታ መፍቀዳቸውን እንዲሁም የአካባቢው ፖሊስ በመሆን እንደሚያገለግሉም ጋዜጣው ዘርዝሯል፡፡ ከጐረቤት አገራት ጋር በተያያዘም ሠራዊታቸው የሶማሊያን ድንበር በተደጋጋሚ ጥሶ እንዲገባ ማድረጋቸውን፤ የኤርትራን መንግስት ደግሞ በተደጋጋሚ ከማስፈራራት አልፎ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ታማኝነት የሌለው መጥፎ መንግስት እንደሆነ በማሳመናቸው የብሔርተኝነት ስሜት ማሳደጉንና ይህም እርሳቸው በሌሉበት በሁለቱም ወገን ያሉ አክራሪ ኃይሎችን ድጋሚ ወደ ጦርነት ሊያሰልፍ እንደሚችል ያለውን ስጋት ጭምር ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በሁለቱ ሱዳኖች ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉትን አስተዋጽኦ አንስቷል፡፡

ጋዜጣው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግስታቸው የኃይል/ስልጣን ሁኔታና ሽግግር ብዙም ግልጽ ባለመሆኑ የስልጣን ሽግግሩን አስቸጋሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያሳዩ ዘገባዎችንም አክሏል፡፡

ዘ ታይምስ

በዓለም ላይ ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው የታይምስ መጽሔት The Strongman Who may Be Missed: Meles Zenawi, 1955-2012 በሚል ርዕስ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በስልጣን በቆዩባቸው ባለፉት 21 ዓመታት ለአገራቸው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገባቸው፤ በሚከሰሱባቸው በጭቆና ስርዓታቸው እና በእርሳቸው ህልፈተ ህይወት ምክንያት በአፍሪካ ፖለቲካ ከሚፈጠረው ቀዳዳ ጋር የተያያዘ የተደበላለቀ ውርስ (mixed legacy) ጥለው እንዳለፉ አስነብቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተደጋጋሚ ቃለ መጠይቅ እንዳደረገላቸው የሚያስታውሰው  መጽሔቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በተደጋጋሚ በስልጣን ላይ እያሉ መሞት እንደማይፈልጉ መናገራቸውን አስታውሶ፣ በተለይም በ2007 እ.ኤ.አ በዚህ ስራ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ ነገር ግን አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት ጊዜው አሁን መሆኑን መናገራቸውን አስታውሷል፡፡ ያም ሆኖ ምንም ሳያደርጉ በስልጣን መቆየታቸውንና እ.ኤ.አ በ2010 የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ታዛቢዎች ጥሩ ነው ባላሉት ምርጫ ከ547 የፓርላማ መቀመጫዎች የእርሳቸው ፓርቲና አጋሮቹ 545ቱን እንዲሁም በዘጠኙ ክልሎች ካሉት 1904 የህዝብ ተወካዮች ሸንጐ መቀመጫዎች 1903ቱን በማሸነፍ ስልጣናቸውን እንዳደላደሉ አስነብቧል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዞም እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ምርጫ የተፈጠረውን ውዝግብና የበርካታ ዜጐች ህይወት ማለፍን አስታውሷል፡፡

መጽሔቱ አክሎም በሰብዓዊ መብት ቡድኖች፣ በተቃዋሚ ድርጅቶችና በጋዜጠኞች የሚነቀፉ መሆናቸውን እንዲሁም እንደ ጠንካራ የአፍሪካ መሪ (Strong African leader) የሚታዩ እንዳልሆኑ ዘግቧል፡፡ ዘገባው በመቀጠል በ1980ዎቹ የችጋርና፣   የተስፋ መቁረጥ ምልክት ሆና የቆየችው አገራቸው በእሳቸው የስልጣን ዘመን ምንም እንኳ የድርቁና የረሃብ ሁኔታ አልፎ አልፎ መከሰቱ ባይቀርም በአገሪቱ 85 ሚሊዮን ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰውታል ብሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የህጻናት የምግብ እጥረት እ.ኤ.አ ከ2000 ወዲህ በአንድ ሶስተኛ የቀነሰ ሲሆን በታዳጊ አገራት ከተከናወኑና ውጤታማ ከሚባሉት በሚጠቀሰው የጤና አጠባበቅ ፕሮግራም ምክንያትም እ.ኤ.አ ከ2005-2011 ባሉት ዓመታት ብቻ በወባ በሽታ የሚጠቁትንና የሕጻናት ሞትን በግማሽ ለመቀነስ ያስቻለ ስራ መሰራቱን ገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ የችጋር መልሱ ልማት መሆኑንም ከ2004 ጀምሮ 11 በመቶ በማስመዝገብ ላይ ባሉት የኢኮኖሚ እድገት በተግባር ለማሳየት ችለዋል ብሏል፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የምርት ገበያ ድርጅት ያላት ሲሆን ከቡና፣ ከሰሊጥ፣ ከስንዴ፣ ከበቆሎ፣ ከአተርና አኩሪ አተር ምርቶች ሽያጭ በየስድስት ወሩ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደተቻለም ዘግቧል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት ከአቶ መለስ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ለአንባቢያን ለማስታወስ በዘገባው መሃል አስፍሯል፡፡

ዘ ጋርዲያን

የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ Ethiopian PM Meles Zenawi’s death sparks fears of turmoil በሚል ርዕስ፤ የአፍሪካ ጠንካራውና ከፋፋዩ (ችግር ፈጣሪው) መሪ  (most powerful and divisive) ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በውል ባልታወቀ ህመም ማረፋቸውን ጠቅሶ፤ የእርሳቸው ሞት በአካባቢው የኃይል ክፍተትን ሊያመጣ እንደሚችል ያለውን ስጋት አስተጋብቷል፡፡

ጋዜጣው የራሱ አስተያየትና ትንተና ላይ ከማተኮር ይልቅ ሌሎች ያሉትን በዝርዝር አስነብቧል፡፡ በዚህም አንዲት  ላለፉት 20 ዓመታት በባህር ማዶ ቆይታ የመጣች ሮዛ ቤተማሪያም የተባለች ኢትዮጵያዊት፣ በአገሪቱ የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክታ ደስታዋን ሳትጨርስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈተ ህይወት በከፍተኛ ሃዘን ላይ እንደጣላት ስትናገር፤ ጫት ቤት ተቀምጦ ጫት እየቃመ አስተያየቱን የሰጠ የኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው አብርሃም ጌታቸው በበኩሉ፤ እንደ ሰው ልጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሞታቸው ማዘኑን ነገር ግን እንደ መሪ በእርሳቸው ሞት ፈጽሞ ሃዘን እንዳልተሰማውና በእሳቸው አመራር ጥቅም አግኝተናል ብሎ እንደማያስብ፣ ይልቁንም ከ75 በመቶ በላይ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ዜጐች ስራ ለማግኘት እንደማይችሉ መግለጹን ጋዜጣው አስነብቧል፡፡ ወጣቱ ለአገራችን እድገት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ብንፈልግም ዕድሉን አላገኘንም ማለቱንም ጋዜጣው አክሎ ገልጿል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዞ ዴቪድ ካሜሮንን ጨምሮ በርካታ መሪዎች፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪና እንዲሁም አልሸባብ ጭምር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሰጡትን በጐና ተቃራኒ አስተያየቶች አስፍሯል፡፡

ዘ ኔውዮርክ ታይምስ

ይህ በመላ አሜሪካ ተወዳጅ የሆነ የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1990ዎቹ አምባገነኖችን በመገርሰስ ዴሞክራሲን ያሰፍናሉ ተብለው ከተሞገሱት የአዲሱ ትውልድ መሪዎች ዋነኛው መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በልማት ላይ ባደረጉት አስተዋጽኦ እንደሚመሰገኑ፤ ነገር ግን እ.ኤ.አ በ1995 ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ስልጣንን ለራሳቸው ጠቅልለው በመያዝ ተቃዋሚዎቻቸውንና ስለ እሳቸው መጥፎ የሚጽፉ ጋዜጠኞችን በማሰር በአገሪቱ የፍርሐት ድባብን የፈጠሩ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡

ተተኪያቸው ሊሆኑ የሚችሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የእሳቸውን ያህል ተደማጭነትና የማዘዝ ስልጣን ሊኖራቸው እንደማይችል በመግለጽ ይልቁንም እሳቸው እንደምልክት እንደሚሆኑና እውነተኛ ስልጣን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ተሳታፊ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች እጅ ሊሆን እንደሚችል ዘግቧል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ብዙም ለውጥ እንደማይኖርና ከአሜሪካ ጋር ያለው ጥብቅ ወዳጅነትም እንደሚቀጥል የተንታኞችን አስተያየት አስቀምጧል፡፡

ዘ ቴሌግራፍ

ዘ ቴሌግራፍ የተባለ በእንግሊዝ ተነባቢ የሆነ ጋዜጣም የመለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት የምዕራባዊያን ራስ ምታት (Ethiopia commentary: Meles Zenaw’s death a headache for the West/ መለስ ዜናዊ ጠንካራ ክንድ ያለው/ ጨቋኝ ለማለት ነው/ የህዳሴ መሪ  Meles Zenawi: A renaissance leader with an iron fist/ የመለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት አገሪቷን ወደ ማይታወቅ ሁኔታ ሊያመራት ይችላል  (Death of Ethiopia’s Meles Zenawi plunges country into uncertainty) እና የአፍሪካው ወዳጃችን (Our man in Africa) በሚሉ አርዕስቶች ስለ አቶ መለስ የ21 ዓመታት ጉዞ ሰፋ ያለና ዝርዝር ዘገባዎችን አስነብቧል፡፡ ዘገባዎቹ የአቶ መለስ አስተዳደር በኢኮኖሚው፣ በመሰረተ - ልማት ዝርጋታና በመሳሰሉት ሊመሰገን የሚገባው ስራ መስራቱን፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና የፖለቲካ መድረክ ደግሞ ሀገሪቱን ተደማጭ ማድረጋቸውን፤ አሜሪካ፣ እንግሊዝና የአውሮፓ ህብረትን ሸሪኮቻቸው ማድረግ መቻላቸውንና ነገር ግን በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ላይ በሚደርሱት በደሎች በአጠቃላይ በአገር ውስጥ የፖለቲካ መብቶች ረገድ ነቀፌታ እንዳለባቸው በዝርዝር ጽፏል፡፡

ዘ ዋሺንግተን ፖስት

ስለ መለስ ዜናዊ ልታውቋቸው የሚገቡ አምስት ነገሮች በማለት አቶ መለስ የቀድሞ ኮሙኒስት የህክምና ተማሪ የነበሩ መሆኑን፣ በአገራቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ መሪ መሆናቸውን፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዋነኛ የአሜሪካ ሸሪክ እንደነበሩ፣ አስቀያሚ የሚባል የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪከርድ ያላቸው መሆናቸውንና ህልፈታቸው የስልጣን ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል በሰፊው አብራርቶ ጽፏል፡፡

 

 

 

Read 5214 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:51