Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 07 November 2011 12:56

የተዓምር ዓለም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ተአምር የተፈጥሮ ህግ መዛባት ነው፡፡ ድንጋይ ወደ ላይ ተወርውሮ መሬት በመውደቅ ፋንታ በአየር ላይ ተንጠልጥሎ ቢቀር ሁኔታው ከታወቀው ውጭ ስለሆነ ተአምር ነው፡፡ 
አቶ ዘካሪያስ የግል ፋብሪካ ባለቤት ናቸው፡፡ ፋብሪካ የማንቀሳቀሻ ፈቃድ ከመንግስት አግኝተዋል፡፡ . . . ከወር በፊት ለፋብሪካው ሰራተኛ የሚሆኑ ሰዎችን በተለያየ የእጅ ሞያ ዘርፍ አወዳድረው ቀጥረዋል፡፡ . . . ሰራተኞቹ ግን ወሩን ሙሉ ለስራ ሲዘጋጁ ቆዩ እንጂ ምንም ተግባር አላከናወኑም፡፡
ማሽኖቹ በሸራ ተሸፍነው በፋብሪካው ውስጥ ቆመዋል፡፡ ሰራተኞቹም የተሸፈነውን ገልጠው አላዩም፤ ባለቤትየውም ገልጦ አላሳዩዋቸውም፡፡
ለወር ያህል በእየቀኑ ወደ ስራ ቦታቸው ይመጣሉ፡፡ በስራ መግቢያ ሰአታቸው ቱታቸውን ለብሰው ይቆማሉ፡፡

የፋብሪካው ባለቤትም በየቀኑ የድርጅት ታርጋ በተለጠፈበት መኪናቸው ወደ ሥራ ቦታው ይመጣሉ፡፡ . . . መኪናቸውን ወደ ቅጥር ግቢው እንዲያስገቡ ሰራተኛው በሁለት ወገን ተከፍሎ መንገድ ይሰጣቸዋል፡፡ ለወር ያልሰራበትን እጁን ከጀርባው በመሽቆጥቆጥ አጣምሮ፡፡ 
ባለቤትየው በየቀኑ ከራሳቸዉ በተጨማሪ አንድ ሰው ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከእሳቸው ጐን በጋቢና ወንበር አስቀምጠውት፡፡
ይዘው የመጡትን ሰው ወደ ፋብሪካው እና ሠራተኛው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደተሸፈኑት ማሽኖች እና ወደተተከለው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርምር እየጠቆሙ የሆነ ገለፃ ያደርጋሉ፡፡ . . . የተቀጠረው ሰራተኛ በሙሉ እጁን በንፁህ ቱታው ላይ አጥፎ ይመለከታል፡፡ . . . የፋብሪካው ባለቤት ይዘው የመጡት ሰው ለማሽኖቹ መቀስቀሻ ኤሌክትሪክ የሚዘረጋ ነው ብለው በማሰብ፡፡
የፋብሪካው ባለቤት ፊት ወንበር ላይ ጭነው ከመጡት ሰው ጋር እየተሽከረከሩ በብዙ እጅ ማወናጨፍ ገለፃ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ . . . በመጡበት ሁኔታ ያመጡትን ሰው ጭነው ከግቢው ይወጣሉ፡፡
ነገ ሌላ ሰው ይዘው በሰአታቸዉ ይደርሳሉ፡፡ ከገለፃ በኋላ ይዘውት ይመለሳሉ፡፡ ትላንት ይዘው ለመጡት ሰው ገለፃ ያደረጉት ጣራ ጣራውን እየጠቆሙ ከሆነ ዛሬው ለመጣው ሰው ደግሞ . . . መሬት መሬት እየጠቆሙ ሲገልፁ ይቆያሉ፡፡
ነገ ደግሞ ራሳቸው ወደ ቀጠሩት ሰራተኛ እና ሰማይ እያመለከቱ ሲያስረዱ ያረፍዳሉ፡፡
ለሳልስቱ ደግሞ፤ ወደ ያዙት የነጋሪት ጋዜጣ እና በዶሴ ወደታቀፉት የተለያየ ማህተም የተረገጠበት ወረቀት ያመለክታሉ . . . እያለ ይቀጥላል፤ ቀጥሏልም፡፡
ወደ ፋብሪካው በገቡ እና በወጡ ቁጥር ሳይሰለቹ የሚያከናውኑት አንድ ተግባር አለ፡፡ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ፤ ተከማችቶ የነበረው ሰራተኛ ገለል በማለት በለቀቀላቸው የማርያም መንገድ እያለፉ… እጃቸውን ከፍ በማድረግ አንድ የጅምላ ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ለሰራተኛው በሙሉ፡፡
አንድ ሰላምታ ሲገቡ፤ አንድ ሰላምታ ደግሞ ሲወጡ፡፡
ለሀያ ስምንት ቀናት ሀምሳ ስድስት ሰላምታ ሰጥተዋል፡፡
ከአርባው ቅጥር ሰራተኛ በቀን ሁለት ጊዜ ለሰጡት ሰላምታ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ አትርፈዋል፡፡
የተለመደው ህግ፤ መሆን የነበረበት፣ በተጠበቀበት ሊሆን ሳይችል ነው ተአምር የሚባለው ብያለሁ፡ . . . ሰራተኛው ምን እንደሚሠራ ሳያውቅ ወር መሉ ስራ እያለ ውሎ መግባቱ አስገራሚ ከተባለ፡፡ . . . ለምንድነው ስራ የማንጀምረው? ምን ቦታ ላይ ነው ምድቤ? . . . ማሽኑን ለምን አናየውም? . . . የሚመረተው ነገር ምንድነው? . . . እና የመሣሰሉትን ጥያቄዎች አለመጠየቁ ግን ተአምር ነው፡፡
ተአምር፤ ብዙውን ጊዜ ከብዙ ሺ ሙከራዎች ወይንም አጋጣሚዎች ውስጥ አንዴ ነው የሚከሰተው፡፡ ያውም ተከስቶ የሚቆየው በጣም ለአጭር ቅፅበት ብቻ ነው፡፡ . . . በዚህም ምክንያት፤ ክስተቱ አጋጣሚ ይመስላል፡፡ . . . ሲከሰትም ለሚጠራጠር ሁሉ ደግሞ ማሳየት ስለማይቻል፤ ተከስቶ የሚያዩት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ አይተናል የሚሉትንም ማንም አያምናቸውም፡፡ . . . ሰውም አያምናቸውም፤ እነሱም በጊዜ ቆይታ በኋላ ራሳቸውንም ማመን ተስኖአቸው፤ . . . ሲከሰት ያዩት ነገር… በገሀዱ አለም ላይ ሳይሆን፣ በራሳቸው ጭንቅላት ስርጭት ውስጥ መሆኑን ተቀብለው፤ ለስርጭቱ መዛባት ራሳቸውን በራሳቸው ይቅርታ ጠይቀው፤ አፋቸውን ቆንጥጠው ጭጭ ይላሉ፡፡
. . . ተአምር ለሀያ ስምንት ቀናት በአርባ ሰራተኞች ላይ፣ ያውም ፋብሪካን በሚያክል ሰፊ ቦታ ላይ ከተከሰተ፣ . . . ተአምር በትክክለኛው ተፈጥሮአዊ ህግ ፈንታ ሊሰራ በእውነታ መድረክ ላይ መጥቷል፡፡ ተአምር ነባራዊውን ሂደት ግራ ያጋባል፡፡
. . . ያኔ ድንጋዩም ወደ ሰማይ ተወርውሮ መሬት አለመውደቁ ሳይሆን መውደቁ ይሆናል ዋናው አነጋጋሪ ነገር፡፡ . . . የማይጠበቀው የሚጠበቅ፤ የሚጠበቀው የማይጠበቅ ሲሆን፤ ነገራት እና አለም ከዚህ በፊት እንደምናውቃቸው ከዚህ በኋላ አይሆኑም፡፡
. . . በሀያ ስምንተኛው ቀን ማንም በጥንቱ ህግ የሚሰራ ሰራተኛ… የፋብሪካም ሆነ የሌላ ደመወዝ መጠበቅ፣ ጠብቆ ካልሆነ መጠየቅ፤ መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ጭምር ነው፡፡
. . . ሰራተኞቹ ወደ ፋብሪካው በጠዋት ተነስተው መምጣታቸውን አላቆሙም፡፡ ቱታ አድርጐ መቆሙን፤ ቆሞ ውሎ… ፀሀይ ለመጥለቅ ስታኮበኩብ… ያጠለቁትን አውልቀው… ፀሀይ ከመጥለቋ ቀድመው ወደ ቤታቸው ለመጥለቅ መቸኮላቸውን፡፡ . . . የፋብሪካው ባለቤት አሁንም የሦስት ቁጥር ታርጋ በተለጠፈባት መኪናቸው ሆነው ከጐን ባለው ወንበር አዲስ ሰው ጭነው መምጣት ቀጥለዋል፡፡ . . . ለእያንዳንዱ እለታዊ ተረኛ ሰው አዲስ ነገር አጀንዳ አድርገው ሲገልፁለት ቆይተው፤ ሰላምታ ሰጥተው እንደገቡት፤ ጅምላ ሰላምታ ሰጥተው ይወጣሉ፡፡ ሰውየው በሚመጡበት ሰአት ከውጭ ሆኖ የጠበቃቸው ሰራተኛ እንደሌለ ሁሉ ወጥተው ሲሄዱ ወደ የትኛው አቅጣጫ አመሩ ብሎ የመጠየቅ ጉጉት ያደረበት፣ ከጀርባ ተመልክቷቸው የሚያውቅ አንድም ሠራተኛ እስካሁን የለም፡፡ . . . በተጠበቀው ሰአት ሁሌም ሲደርሱ ቆሞ ፀሀይ ለሚሞቀው ሰራተኛ እንደ ዱብ እዳ ነው የወደቁበት የሚመስለው፡፡ . . . ከገለፃቸው በኋላ ያንኑ መኪናቸውን ቀስቅሰው ሲወጡም እንደ ድንገተኛ ሞት ሰራተኛው ያልጠበቀው ነገር መከሰቱን በሚገልጽ በሚያስታውቅ ሁኔታ ይደነግጣል…አየኑን አፍጥጦ ይቀራል፡፡
. . . የሚያውቁትን ነገር መርሳት በቀድሞው አለም ተአምር ነው፡፡ የተለመደውን ነገር በእየእለቱ እንደ አዲስ መልመድ፡፡
. . . ባለቤትየው አቶ ዘካሪያስ አንዳንድ ጊዜ የአፈር ተመራማሪ ይመስል ወደ መሬቱ ተጠግተው ቁጢጥ ይላሉ፤ ከጐናቸው ቁጢጥ እንዲል ላደረጉት የእለቱ ተረኛ እንግዳቸው ከአፈሩ እየዘገኑ ሲያሳዩት፣ ሲያስሸትቱት፣ ሲያስደምጡት፣ ሲያስቀምሱት ቆይተው . . . ሰላምታ ሰጥተው በገቡበት ሁኔታ ሰላምታ ሰጥተው . . . ከፈገግታ ጋር ወደ መጡበት ወይ ወዳልመጡበት ይሰወራሉ፡፡
. . . ከእለታቶቹ በአንዱ ቀን፤ ይዘው ከመጡት ተረኛ አዲስ ባለሞያ ጋር ወደ ተሸፈኑት ማሽኖች አመሩ፡፡ የተሸፈኑበትን ሸራ መሳይ ጨርቅ . . . ከአንዱ ማሽን ወደ ሌላው እየሄዱ ቅርፊቱን ገፈው ጣሉ፡፡ . . . ሁለቱን እጆቻቸውን አንድ ላይ እያጨበጨቡ ትቢያውን አራገፉ፡፡…ብዙ ስራ እንደሰራ ሰው ላባቸውን ከግንባራቸው ላይ ጠረጉ፡፡
. . . ከተነሳው ጨርቅ ስር የተጠበቀው ማሽን አልነበረም፡፡ ለነገሩ የሚጠበቀው ማሽን ምን አይነት እንደሆነ የሚያውቅ አንድም ሠራተኛ የለም፡፡ …
ሠራተኛው ስለ ማሽኑ ያውቃሉ ብሎ ያሠበው ባለቤትየውን ነው፡፡ . . . ምናልባት ባለቤትየው ደግሞ ሠራተኞቹ ሳያውቁ አይቀሩም ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ . . . ተአምር ማለት ትርጉሙ ይሄ አይደል?
ነገር ግን ተአምር ሲከሰት የሚታየው አይነት ድንጋጤ በሠራተኞቹም በአሠሪውም በተጋባዥ እንግዳውም ፊት ላይ አልታየም፡፡
. . . ማሽኑን ሸፍኗል ተብሎ ይታሰብ የነበረውን ጨርቅ ገፈው ያሳዩት ባዶ ነገር ነው፡፡ የማይታይ ነገር ነው ያሳዩት፡፡ ባዶውን ገልጠው ካሳዩ በኋላ . . . ለተወሰኑ ደቂቃዎች እጃቸውን እያወናጨፉ ገለፃቸውን ገፉበት፡፡
ቀጥለው የራሳቸውን ገላ የሚሸፍነውን ክርፊት…ልብሳቸውን ተራ በተራ እየገፈፉ አወለቁ፡፡ . . . ልክ ከሽፋኑ ስር እንዳለው ማሽን ባዶ ስፍራ ከሰውየው ሽፋን ስር ብቅ አለ፡፡ . . . ባለቤትየው በሌሉበት ድምፃቸው ብቻ ሲያወራ ቆየ . . . ድምፃቸው እንደ ሁልጊዜውም ርቆ ስለሆነ አይሰማም፡፡ ሳይሰማ ድምፃቸው መኖሩም ተአምር ነው፡፡ በእጃቸው እንቅስቃሴ ነበር በፊት ሰራተኞቹ ቀጣሪያቸው እያወሩ እንደነበር የሚያውቁት፡፡ . . . የተገለፀውን ባዶነታቸውን ይዘው ወደ መኪናቸው በመጡበት ሁኔታ ገብተው ወደ ኋላ አፈገፈጉ፡፡ የመኪናዋ መሪ ብቻ በቀስታ ሲዞር ይታያል፡፡ . . . ከጐናቸው የተቀመጠው ሰው በሰውየው የሚገለፅለት ነገር እንደገባው በማስገንዘብ አይነት ጭንቅላቱን ይነቀንቃል፡፡ ሰውየውም እንደ ሰራተኞቹ የማይታይ የማይሰማ ነገርን የመረዳት ክህሎት አለው ማለት ነው፡፡
ሠራተኞቹ፤ የማይታዩት አለቃቸው እንደ ሁልጊዜው የሚሰጡአቸውን ሰላምታ ሲሰጧቸው ባያዩም፤ ያላዩትን ተቀብለው በአርባ እጥፍ አድርገው መለሱ፡፡
. . . በተለመደው የድሮ ህግ ቢሆን ይህ ሁሉ ሁኔታ ተአምር ተብሎ በተጠራ ነበር፡፡ የተለመደው ህግ መስራት ሲያቆም፣ ያልተለመደው ህግ መስራት ይጀምራል፡፡ ተአምሩ ቀጠለ፡፡
. . . ሠራተኞቹም ወደ ቤታቸው ከፀሀይዋ ጋር ሄደው ጠለቁ፡፡ . . . ተአምር የትርጉም ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞት ነው፡፡ . . . ከሞት መልሶ መነሳት አልቻለም፡፡ ቻልን ላሉት ደግሞ መቻላቸው ራሱ ተአምር ሆነ፡፡

 

Read 4343 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:09