Saturday, 14 July 2012 07:46

የሔደ እስኪመጣ …

Written by  ዋሲሁን በላይ (አ.ዋ.በ)
Rate this item
(0 votes)

ለስለስ ያለ ነፋስ …

እማያዝኑ፤ ሰው … ያፈራቸው የሰው ፍጡሮች …

ያኮረፈ … ድብርታም ነፋስ …

ሁሉም ይርመሰመሳሉ፡፡

***

ፀሐይዋ… የፈሪ ሰው ፈገግታ… (ግማሽ) ለመሳቅ የተከለከለች ትመስላለች፡፡ ስስታም ሰው ይመስል … ፈገግታዋን ቆጥባለች፡፡

ምልዕተ … መሀል አሸዋው ላይ ዝርፍጥ ብላ ተቀምጣለች፡፡ እግሮቿን ግራና ቀኝ ፈርከክ አድርጋ … በግራ እጇ በያዘችው የግራዋ ጭራሮ … ፍች የሌለው ስዕል ትሞነጫጭራለች …፡፡

ሰባራው የፊት መመልከቻ መስተዋት … ከነበተው ቀሚሷ ስር ተንጋሎ … ጭኖቿን ገርመም የሚያደርግ ይመስላል፡፡

የእግሮቿ አውራ ጣቶች ጥፍር … የሆነ አገር ካርታ ይመስላል … ሁለቱም ከእንክብካቤ እጦት ሽርፍርፍ ብለዋል … በዚያ ላይ ቆሽሸዋል፡፡ ሰው ሌላውን ለማስታወስ … ራሱን ሲረሳ እንዲህ ነው …?

***

አይኖቿ ማረፍያ ፍለጋ ርቀው ሔደዋል … የሆነ ነገር ፍለጋ … ብቻ የሆነ ነገር ፍለጋ … በዛውም ከተገኘ ከመጣ፡፡ ክርክም ብለው የተበጁት አይኖቿ ተነበው የማያልቁ ምስጢር አዝለዋል፡፡ የሱፍ አበባ ይመስል … እየተዟዟረች አስቀያሚዋን ፀሐይ ትሞቃለች … እቺ ላላቸውና ለደላቸው የምትወጣ አሽቃባጭ ፀሐይ የከፋው ሰው ይሞቃታል፡፡

***

አንድ ቀን ከቀንም የተመረጠ የሚመስል ቀን … ትኩስ የአይን ሽታ ሸተታት … ስፍስፍ የሚያደርግ፡፡ አንድ ቀን .. ከቀንም ውብ ሀምራዊ ቀለም የተቀባ ቀን … ልቧ ሸርተት ብሎ ልቧ … ውስጥ ወደቀ፡፡

አንድ ቀን ሰማዩ ላይ እግዜር በቀስተደመና ፍቅር የሳለበት ቀን… ክብሮምን አየችው … ትኩስ ሽታ … አይኗ ላይ … የብርሃን መጋረጃ ተጋርዶ እንፋሎቱ ያሳብቅ ነበር … አሁን ግን … ከልቧ ውስጥ የፈነዳው እንባ … አቧራ በለበሰው ፊቷ ላይ ወርዶ … ሐዲድ ሠርቶ ደርቋል፡፡ ከራሷ በቀር ማንም የማያነበው መልዕክት… እንባዋ ፊደል አበጅቶ ፊቷ ላይ ታትሟል፡፡

ምን አልባት … በዚህ መንገድ ሔዶ ይሆን ፍቅሯ ክብሮም የቀረባት…? ምን አልባት … ልቧ ውስጥ ተሸሽጐ ይሆን የጠፋባት ….? እና ጥበቃ የተቀመጠችው …? የሆነ ነገር ፍለጋ ተቀምጣ ሔዳለች … ሔዳ እዚህ ወድቃለች … ወድቃ እሚያነሳት አጥታለች…!

አይኗም … ልቧም … እጇም ሥራ ላይ ናቸው … ጭራሮውን መሠባበር ጀመረች … አብሮ ትዝታዋም እንዲህ እንክትክት ብሎ ቢደቅላት በወደደች … “አስቦ መውደድ ቢቻል ምናለበት…?” አለች ለራሷ … ለመጀመሪያ ጊዜ ለሠላምታ የዘረጋችለትን እጆቿን ተመለከተቻቸው … የአንዲት ጧሪ የሌላቸው ምስኪን አሮጊት ጣት መሠላት፡፡ ፊቷ ላይ ተደላድሎ የተቀመጠው ማድያት … የተበሳጨ ሰዐሊ የሣለው ቀሽም ስዕል ነው የሚመስለው፡፡ ያቺን የመሠለች ውብ … እንዲህ በጥበቃ መጠውለጓ ገረማት … ዛሬ ላይ ሆና ትላንት ታያት … “እርጅና እንዲህ ነፋስ የበረታበት የሳሙና አረፋ ነው እንዴ…? ስስታም ቀፋፊ” አለች … ድምጿ ቢያመልጣትም ራሷም አልሠማችው፡፡ ለሚጠብቅ .. አንድ ቀን አንድ ሺ  ቀን ነው፤ አንድ ቀን … አይገለፅም … አንድ ቀን እስትንፋስ ነው…፡፡

ከንፈሯ መረራት … ክብሮም ስሟት ሲሔድ ስንቅ እንዳቀበላት አልገባትም … እጦት ባጠወለገው መዳፉ ፊቷን በስስት ዳስሶ … ከእንባው ታግሎ ሲሔድ … ርሃብ ያጠወለገው ፊቱ… በልጃገረድ ደም የነተበ አሮጌ አንሶላ ነበር የሚመስለው … ትንሽ ከሔደ በኋላ ድጋሚ ተመልሶ ሳማት … ሳማት … ደጋግሞ ሳማት!

ልቧ ከደረቷ ተንሸራታ እግሯ ስር ወደቀች፡፡ የሆነ ቀን እንዲህ ብሏት ነበር… “ማጣት ያማል… የህሊና ቁስል ነው … ማጣት እንድትስቂ አይፈቅድም … እጅሽን በኩራት ዘርግተሽ እንጀራ አያስቆርስሽም … ሲስቁ እንኳን መሣቅ አትችይም … ከሌለሽ በሙሉ ልብሽ አትወጂም … የማይከፈልበትን አየር እንኳ በነፃነት አትምጊም … ብቻ ፍቅሬ፡፡ ምን አለፋሽ ማጣት እያየሽ አያሳይሽም … ይሔ ነው…” አላት የሌላ ሰው ስሜት አስመስሎ፡፡ ግን ዛሬም ድረስ ይሔ ነው ያሸሸው ብላ አልደመደመችም፡፡ ከልቧ ውስጥ ትዝታ እንጂ … ፍቅርን አልነበረም ትቶላት የሔደው፡፡ የቀዘቀዘ ፍቅር ልቧ ላይ ጥዶ .. ትዝታዋ ትኩስ ሆኖባት እስከ አሁን ይሸታታል፡፡ ያን ጊዜ ሳይኮረኩራት ስቃለች … ገና ሲያዋራት አይኖቿን ሲበረብር … ተስለምልማ ሳይስማት ራሷን ስታለች … ሳያቅፋት ሞቋታል፣ ሲያዋራት የሚዘፍንላት ነው የሚመስላት፡፡

እየተግባባችው … ይበልጥ እያፈቀረችው እያጣጣመችው ስትመጣ ልቧ ውስጥ የበቀለ መሠላት፡፡

አንዳንዴ ዝናብ እንዳረጠበው የተዳወረ ጥጥ ሙሙት ትላለች፡፡ አጠገቧ ሆኖ ሲናፍቃት ይርባታል፡፡

ከሳምንት በፊት ቀጠሮ ጠየቀችው፤

“ቅ..ቅ.ዳ.ሜ” አለች ምላሷ የጠፋት ይመስል … ፈገግ ብሎ ተመለከታት …

“ቅዳሜ ከሠዓት በኋላ እፈልግሃለሁ” ትንፋሽ አጠራት፡፡

“ለምን?” አላት ግርምቱ እያየለ፡፡

“ለምን አይባልም!” ተገርሞ አስገረማት … ለምን አይባልም ማለቷ እንግዳ ስሜት ፈጥሮበታል፡፡

“ለምን” አላት መልሶ …

“ውይ ክብሮምዬ … ለምን አይባልም እያልኩህ” ስልምልም አለች፡፡

“እሺ … ግን…” አላስጨረሰችውም … እየተሽኮረመመ ሳቀ፡፡

“ግን ተወው” የመጓጓቱ ነገር አይሎ ቁጣ አስመሠለባት …

“እሺ የኔ ቆንጆ…እ…እ..”

“እንደ እሱ ነው” ምንም ፋታ ሳትሠጠው … ዘላ አነቀችው …ጥምጥም፡፡

ያ ሁሉ መንገደኛ ወጪ ወራጅ ባለበት አጣጥማ ሳመችው … ማንም አላየም እንጂ … ከሠማይ የሆነ ነገር ወድቋል፣ /ነገን ጠቋሚ/ … ሁለቱም ለደቂቃ … የሎጥን ሚስት ይመስል … ደርቀው ቀሩ … ምርጥ ሀውልት መሠሉ … ከደረቷ ቀዝቃዛ ላብ ጡቶቿን ሠንጥቆ ወደታች ሲወርድ ተሠማት /ቅዳሜ …ማታን… አመላካች/

ይሔ ሁሉ ሲታወሳት … በኩርፊያ ውስጥ ፈገግ ለማለት ትሞክራለች … ያኔ … ሳይጠይቃት ልቧን፣ ሳይጠይቃት ሠጥታዋለች፡፡ እርሱም ኩራት ልቡ ሳያድር … ወንድነቱ አዳልጦ ሳይጥለው… በረከቱን ሁሉ ተቀበለ፡፡ ተቀብሎም አላሳፈራትም፡፡ እጥፍ አድርጐ መለሠላት፡፡ ያኔ ቅዳሜ ሌሊት ልቧ ውስጥ የሚቦርቀውን ፍቅር … በስጋ ሜዳ ላይ … ሥጋ በለበሰ በፍቅር ጦር ስታስወጋ … የተሠማት ስሜት ትርፍ ቢኖረው ድጋሚ እንደዛ አይነት ደስታ አይሠማትም፡፡

ቅዳሜ ሌሊት … ደስ የሚል ህመሟን በፍቅሯ እያከመች … ደረቱ ላይ ጐጆዋን ሰርታ … ተኛች … ተኝታ አለምን አሠሠች … ሲነጋ ወፎች ሳይሆኑ የገዛ ህልሟ ቀሠቀሣት … ባይነጋ … ከደረቱ … እንደተሰፋች … ከእቅፉ ባትወጣ በወደደች፡፡

***

ሙሉውን እሁድ እንደ እስረኛ ክፍላቸው እሚፈልጉትን እያስመጡ … እነሱ ሳይወጡ …ዋሉ…ፍቅር ምግብ ነበረ…ፍቅር መጠጥ ነበረ….

(ምንም አልጐደለባቸውም ነበር፡፡ ሙሉቀን መርፌው ገላ እየሰፋ…)

….ማታ…የአበባ ክምር…አስታቅፎ መኖሯን እስክትዘነጋ ስሞ… እግሯን እያስጐተተ ሸኛት፡፡

ሳትተኛ ሌሊቱ ነጋ….ከተኛች ያ ሁሉ ጣዝማ እውን…ህልም የሚሆንባት መሠላት…ከዛች ቅዱስ ቅዳሜ ሌሊት በኋላ…እርሱ አንድም ቀን አብራን እንደር ብሏት አያውቅም፣ እርሷ ግን ፍላጐቱን ቀድማ ስለምታውቅ…ቀድማ ማደሪያቸውን ተኮናትራ ትጠራዋለች…ምንም ሳያዋጣ…የፍቅር ቡፌ ይቋደሳል…ራሷን ትጋብዘዋለች፤…ተጠርቶ ቀርቶ አያውቅም…ለምናው…የለኝም ብሏት አያውቅም…(ምነው…ዛሬ…ታዲያ…?)

***

እንባዎቿ ከአይኖቿ ብልቃጥ ፈሰሱ …ቀጭን ገመድ የመሰለ የሚሳብ ፈሳሽ ከረጠበው አፍንጫዋ ወረደ… አንገቷን ደፋች…ቀጭን ጥንቅሽ የመሰለው አንገቷ ላይ የተንጠለጠለው የብር ሃብል…የህፃን ልጅ እጅ በሚመስል ልስላሴ…ጡቶቿን ዳሰሳት…/ በዶልፊን ምስል የተቀረፀ የብር ምስል/ በእነዛ በከፋቸው፣ በተጐሳቆሉ፣ በቆሸሹ ጣቶቿ የሀብሉን ማጫወቻ ያዘችው… የክብርሽ ስጦታ…ሀብሉ ከሚጠፋ አንገቷን ቢቀሏት ትመርጣለች፡፡ በእነዚህ የመከፋት ቀኖቿ መሀል…ትዝታዎቿ ሁሉ…ትኩስ ቁስል ሆኑባት፤ አተኩራ ተመለከተችው…ሀብሉም አንገቷም እኩል ተመሳስለው ቆሽሸዋል…ደጋግማ ሳመችው…ሳመችው…ከአፍንጫዋ ያመለጠው ቀጭን ፈሳሽ…ከንፈሯን ድጦ ወደ አፉ ሰጠመ… የመለየት የመለየት ጣዕም ጣማት…

“ምነው …ላላገኘው…ባላወቅሁት…” ሾልኮ ያመለጣት እውነት…

“ምነው…እንዲህ…ሊርበኝ ባልቀመስኩት…”

“ምነው…እንዲህ…ሊጠማኝ…ንፁህ ምንጭ የመሠለውን ፍቅሩን ባልተጐነጨሁ” ከገዛ ራሷ ጋር ተሟገተች…”ምነው…እንዲህ ትቶኝ (ሊሄድ)…መሄዱ ካልቀረ…ልቤንም ይዞት በሄደ…” ይሄንን የምሬት ቃል እንደመድፍ ጮኻ ነው የተናገረችው….ለማንም ግድ ስላልነበራት…ግድ አልሠጣትም፡፡

የሄደ እስኪመጣ…ማን ላለ ይጨነቃል...

ፀሐይዋ ትት ገባች፡፡

መንደርተኛው…ጥበቃዋን ጠቅጥቆ…ሊጋደም ትቷት ገባ፡፡

ፍቅሯ ላይ…ጢቅ…እያሉ…ዝማሬአቸውን ለውጠው…ወፎችም…የጐጇቸውን በር ዘጉ፡፡

ምሽቱ…ዋሽንት እየነፋ…በቅዝቃዜው ተውቦ አጠገቧ ቆሟል…ከዋክብቶች ለማጽናናት ጊዜም የላቸው…ወደሞቀበት…ለመሞቅ አዘቅዝቀዋል…፤ ጨለማ…ለካ…ለከፋው ሰው ከብርሃን ይበልጣል…?

ቀና ብላ ጨረቃን አየቻት…የድሮ የውቤ በርሃ “ሸርሙጣ” መሠለቻት፤ መልሳ..አተኩራ አየቻት…አሁን ደግሞ…አንድ ልጇን…ተረድታ ማቅ ያጠለቀች…ዘመን ያደቀቀት…ቆንጆ ግን በቁሟ የሞተች ሴት… ፊቷን ማድያት ያጠለሸው…መሠላት፡፡ ሠርስራ አየቻት…ክብሮምን የደበቀችባት መሠላት፡፡

“የሔደን መተው የሚችለው ማነው? ማንስ ነው መልስ የሚሠጠው….?”

“የከፋውን ሰው ማነው የሚመልሰው?...ማነው…? እንዴት ፍቅርን ያህል እርሾ ሴት ልጅ የልብ ማህፀን ውስጥ አስቀምጦ ያለምንም ምክንያት ይጠፏል…?” ምርር ብላ አለቀሰች…ም.ር.ር

“እንዴት በቅምሻ ርሃብን ያንጿል…” ብዙ እንዴቶች ተመላለሱባት…ትልቁ ጉዳይ (አለት) በጠብታ ጉዳይ (ውስጧ) ተሸርሽሮ ሲናድ እንዴት ፍቅር ውስጥ እንደሰጠመች ጠፋባት…የሄደባትን የምታስብ ምስኪን ሴት ያገኘችበት ተረሳት…

ቀዝቀዝ ያለው ነፋስ…የከፋውና የጐሰቆለ ፊቷን እየዳበሰ..ቀሚሷን ለመግለብ ይታገላል፡፡ ባለጌ ነፋስ የሚያሽኮረምም…

ለብዙ ሰአታት ከተቀመጠችበት ተነሳች…የተቀመጠችበት ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ ርሷል…የገዛ አፍንጫዋን የሆነ ነገር ሰነፈጣት…(ግድም አልሠጣት)…! ድንገት ቀሚሷን ከታች ወደላይ ተረተረችው…ወገቧን ያቀፈው…የቀሚሷ ወፍራም ላስቲክ ታግሎ ረታት፣ ሳበችው…ላለመረታት…ከመለጠጥ የዘለለ ወይ ፍንክች! መልሳ ወደ ጐን ተረተረችው…ሲቀደድ የነበረው ድምጽ ደስ ይላል፣ የሆነ ያልተፃፈ ሙዚቃ አይነት፤ እንደ እሷ ሆድ የባሰው ቀሚስ ከላይዋ ላይ በነፋሱ አጋፋሪነት…እየታጀበ መሬቱን በከንፈሩ ጠርዝ እየሳመ ተጐተተ…ልክ እንደ ቬሎ…ከውስጥ ምንም አልለበሰችም…

ጨለማው…በጥበቃ በተጐዳችው ሴት ገላ ቋመጠ…ሀጢያት ልቡ በቀለ፣ ሊተኛትም ከጀለ፤ ምልዕተ…ከላይ የለበሰችውን ስስ ሹራብ ከላይዋ ላይ ገፋ አሽከርክራ ወረወረችው…ጨለማውና ቅዝቃዜው ተርገብግበው…ገላዋን ዳበሷት…የብዙ አበባዎች ስብስብ የመሰሉት ጡቶቿ ያባትታሉ…እንዲህ ሆና ላያት… እንዲህም ቆሽሻ ታጓጓለች…እንዲህም ቆሽሻ…ጠረኗ በቅመም ያበደ የለጋ ቅቤ ጠረን ነው…ከሩቅ ይጣራል/እሚመጣው ግን…ዱርዬ ነው/

ቀስ እያለች በእግሮቿ አሸዋውን እየተመተመች…ቆይታም እየዘለለች…ተቀምጣበት ከነበረው ሥፍራ…ራቀች…ለመብረር እንደምትታትር የእርግብ ልጅ (ፂፂ) እጆቿን ዘርግታ እየተሽከረከረች እግዜሩ ላይ ጣቶቿን እየቀሰረች…”በዚህ ነው የሄደው…የእኔ ላይሆን ለምን ሰጠኸኝ…ላላገኘው ለምን አሳየኸኝ…?” ላልደርስበት… “እንባዎቿ ረገፉ…ቅስስ…ብላ…” በዚህ ነው የሚመጣው…የልቤ አባወራ…የአይኔ መጋረጃ… በዚህ ነው የሄደው…በዚህ …በ.እ.ዚ.ህ…” እያለች መጮህም ማልቀሱንም ቀጠለች…

የት እንደምትሄድ ባታውቅም…እየሄደች ነው….

***

ጨረቃ እንቅልፏ መጣ መሠለኝ…ትታት ወደ ሠገባዋ ገባች፤ አሽቃባጮቹ…ኮከቦችም…ለባለጊዜ… ለሞቀለት… ሲያሞቁ አምሽተው…በንጋት ተሸነፉ…አይናቸውን ከደኑ፡፡

***

ወፎች ወጡ…

ሰዎች ወጡ…

ያቺ …ለሞላላቸው የምትስቀው ፀሐይ…ከወትሮው ደምቃ ወጣች፣ ምልዕተ…ያን መሬት ላይ ይጐተት የነበረውን ቀሚሷን አውልቃ ጥላለች …እግሮቿ ከነ መቆሸሻቸው …የማታዋን ጨረቃ ውበት ያስንቃል፡፡

አሁን ሙሉ ሰውነቷ ያኔ ወደዚች ምድር የእናቷን ማህፀን ቀዳ ስትመጣ እንደነበረው ሆናለች…(አካላዊ ለውጣ ሲቀነስ)

ክብሮም …ወደሄደበት…መሮጥ…ይዛለች…ትላንት ትተዋት ያልፉ የነበሩ ዐይኖች…እንባ እያቆረዘዙ አዩዋት…ግድ ሳይኖራቸው ያልፉ የነበሩት ልቦች ማዘን ጀመሩ…ድጋሚ አይኖች አለቀሱላት …እንዲህ ነው የሄደ እስኪመጣ የነበረው ሲሄድ…

 

 

 

Read 3682 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 15:15