Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 31 July 2011 12:53

ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ የህንድ ፖሊሲ ሦስት አዲስ ተቀጣሪዎች ወንጀለኛ ለመከታተል ሥራ ለመመልመል ይፈልግና
አንድን ተጠርጣሪ እንዴት እንደሚለዩ የማወቂያ አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ላይ ነው፡፡
ለመጀመሪያው ተፈታኝ ለ5 ሰከንድ አንድ ፎቶ ያሳየውና ይደብቀዋል፡፡
..ተጠርጣሪው ሰው ይሄ ነው እንበል፡፡ ይሄን ሰው እንዴትና በምን ለማስታወስና ለመያዝ ትችላለህ..
ተፈታኙም፤ ..ይሄ በጣም ቀላል ነው፡፡ በቶሎ ተከታትለን ልንይዘው እንችላለን  ምክንያቱም ሰውዬው
አንድ ዐይን ብቻ ነው ያለው..

ፖሊሱ ተናደደ፤ ..ያሳየሁህ ፎቶኮ ሰውዬው በጎን የተነሳው ስለሆነ ነው አንድ ዐይኑ ብቻ የታየህ..  
ፖሊሱ ሁለተኛውን ተፈታኝ ጠርቶ ያንኑ ፎቶ ለአምስት ሰከንድ እያሳየው፤ ..ተጠርጣሪው አሁን ያየኸው
ነው፡፡ በምን ልትለየውና ልትይዘው ትችላለህ፤.. ሲል ጠየቀው፡፡
ሁለተኛው ተፈታኝም፤ ፈገግ ብሎ፤ ..ይሄን ሰው መያዝ በጣም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውዬው አንድ
ጆሮ ብቻ ነው ያለው!.. ፖሊሱ በጣም በመናደድ
..ምን ዓይነት ሰዎች ናችሁ፡፡ እንዴትስ ነው ነገሩ የማይገባችሁ፡፡   በእርግጥ በፎቶው ላይ የሚታየው
አንድ ዐይንና አንድ ጆሮ ነው፡፡ ያም የሆነው ሰውዬው ፎቶ የተነሳው በአንድ ጎን ስለሆነ ነው! ይሄ ብቻ
ነው መልሳችሁ በቃ?..   
በመጨረሻም ተስፋ በቆረጠ አኳኋን ሶስተኛውን ተፈታኝ ጠራና ፎቶውን አሳየው፤
..ተመልከት ይሄን ፎቶ፡፡ ተጠርጣሪው ይሄ ነው እንበል፡፡ ሌላ ጊዜ እንዴት ለይተህ ልትይዘው ትችላለህ?..
ተፈታኙ ፎቶውን ትኩር ብሎ ተመለከተና፤ ..ተጠርጣሪው የዐይን ብሌን ላይ የምትደረግ ሌንስ
(Contact Lens) ያደርጋል፡፡ በዚያ እለየዋለሁ..
ፖሊሱ በመልሱ ተገረመ፡፡ ምክንያቱም ተጠርጣሪው ሌንስ ያድርግ አያድርግ ራሱም አያውቅም፡፡
..እሺ ጥሩ ሙከራ ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ እዚሁ ጠብቀኝ፡፡ ሄጄ ፋይሉን አይቼ ሌንስ ያድርግ አያድርግ
ላጣራ.. ብሎ ይሄዳል፡፡ ሄዶ ከኮምፒዩተሩ ላይ የተጠርጣሪውን ፋይል አውጥቶ ፈገግ ብሎ መጣ፡፡
..አስደናቂ ነገር ነው! ለምን
አልቻልኩም፡፡ ዕውነትም ተጠርጣሪው ሌንስ ዐይኑ ላይ ያደርጋል! እንዲህ ልቅም አድርገህ አይተህ
እንዴት ልብ ልትለው ቻልክ፡፡ ማለቴ ለምሳሌ መደበኛውን መነር ያደርጋል ለምን አላልክም?..
ተፈታኙም፤ ..ይሄማ በጣም ቀላል ነው፡፡ መደበኛ መነር የማያደርገው አንድ ዐይንና አንድ ጆሮ ብቻ
ስላለው ነው!..
*   *   *
እይታን በአንድ በኩል ብቻ ማድረግ፣ የኋላ ትውስታንና ታሪክን አብሮ አለማገናዘብ ቅርብ-አዳሪ ያደርጋል፡፡ ነገርን አንሸዋሮ ለማየትም ይዳርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም ልብ ያልናቸውን ነገሮች ዛሬ ካጋጠሙን ነገሮች ጋር አሰናስለን ካላየን ፍርዳችን ሚዛን ያጣል፡፡ አመለካከታችን ጐዶሎ ይሆናል፡፡ ፍትሐዊ አሰራር ይቀጭጫል፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ማየት ግትር ያደርጋል፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ልክ ብለን ድርቅ እንድንል ያደርጋል፡፡ እያንዳንዱን ጉዳይ ከባህልም፣ ከኢኮኖሚም ከማህበራዊ አንድምታውም አኳያ አስተሳስሮ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ለአንዲት ትንሽ ጥቅም ወይም ለአንድ ዓላማ ብቻ ብለን ግራ-ቀኙን ሳናይ የምንወስነው ውሳኔ፣ የምንሰጠው ፍርድ፣ የምንወስደው አቋም፤ ኋላ አባዜው ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉን ነገር አንድ ዐይን ነው፤ ሁሉን ነገር አንድ ጆሮ ነው፤ ብለን አንዘልቀውም - ሙሉ ስዕሉን አናገኝምና! በተለይ በፖለቲካ አንፃር ሲታይ ፍፁም ጥመት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በጐን የተነሳ ፎቶ ሌላ ጐን እንዳለው አንርሳ፡፡
..ነገር ቢኖራችሁ ነው እንጂ የማለዳ መንገድ ጠፍቷችሁ ነወይ?.. ይላሉ አበው፡፡ በተለይ የአንድን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ መደላድል ማስተካከል በእርግጥም ከባድ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ አገር ኢኮኖሚ ለረዥም ዘመናት ተፈራራቂ ድርቅ፣ ረሀብና የፖለቲካ ምች ያጠቃው ኢኮኖሚ፤ እንደ ሸረሪት ድር የተተበተበና አንዱን ሲነኩት ሌላው የሚወድቅ (Domino-Effect እንዲሉ) በመሆኑ ውስብስብ ባህሪ ይኖረዋል፡፡ መፍትሄው ቅርብ አይደለም፤ ሆኖም ሩቁን መንገድ በትናንሽ ቅን እርምጃዎች መቀነስ ይቻላል፡፡ በኢኮኖሚው የንግድ አሰራር አንድን ዕቃ ከዐይን በማራቅ የገበያ እጥረት ማምጣት ይቻላል፡፡ በአገዛዝ፣ በአስተዳደርና በፖለቲካ ግን እጥረት መፍጠር ከባድ ነው ይላሉ፡፡ አንድ ፈላስፋ እንዳለው ባለመኖሩ በጣም የሚጐዳ ፀሀይ ነው፡፡ የዝናቡና የጭለማው ዘመን ይረዝማልና፡፡ ነፃነትም ሲያጥር እንደዚያው ነው፡፡ መገፋትን፣ መበደልን፣ ምሬትን ያበዛልና፤ ፀሀይን አትምጪ ብሎ መገደብ እንደማይቻል ነፃነትም አይገደብም - ለጊዜው ካልሆነ፡፡
በሁሉም መስክ ገደቦችን ማጤን ይገባል፡፡ ደንቦች የፍትህ እጥረት እንዳያመጡ መጠንቀቅና ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ እንደሚፈታ ማስተዋል ብልህነት ነው! የምንሰራውን ሥራ ብዛትና የጊዜ ገደብን አለማጣጣም ለአያሌ ስህተቶች ሊዳርግ እንደሚችል ማጤን ያባት ነው! የዘመቻ ሥራ የራሱ ድክመት አለው፡፡ ለደረቅ የመጣ እሳት እርጥብን ያነዳል ይሏልና፡፡ ከሁሉም በላይ ለእድገት መሰረቱ፤ የተገነዘበ፣ መረጃ ያገኘና የነቃ ህዝብ ነው - ለዚህ ደሞ ዋናው ግንዛቤን ማስጨበጥ ነው፡፡ ብዙ ጥረት ቢጠይቅም መንገዱን ማወቅ ማሳወቅ ነው፡፡ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ የሰለጠነ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ያደርጋል፡፡ የማወቅ መብቱን ያወቀ ህዝብ በየደረጃው ተሳትፎውን ለማሳየት ወደ ኋላ አይልም፡፡ መንግሥትን ለማረምም ሆነ ራሱን ለማረም የሰለጠነ ሥርዓት ይኖረዋል፡፡ እድገት ያመጣል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ..ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፤ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ.. የሚለውን ተረት ይተርታል፡፡

 

Read 4375 times Last modified on Sunday, 31 July 2011 12:59