Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 09:32

የተረገመችን እግር በቅሎ ነስቶ ጫማ ያሳጣታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ሁሉ ንጉሥ አያ አንበሶ ታሞ አልጋ ላይ ይውላል፡ የጫካው አውሬዎችና እንስሳት በሙሉ ሊጠይቁት ይመጣሉ፡፡ - ከቀበሮ በስተቀር፡፡
ተኩላ የቀበሮን አለመምጣት ተመልክቶ አጋጣሚውን ሊጠቀም ፈለገ፡፡ የረዥም ጊዜ ቂሙን ለመወጣት አስቦ ነው፡፡ ስለዚህም ወደ አያ አንበሶ ጠጋ ብሎ፤
«የዱር አራዊት ሁሉ የእርሶ ጤንነት አሳስቧቸው ሊጠይቁዎት ሲመጡ ቀበሮ ግን ምን ንቀት አድሮበት እንደሆን አይታወቅም በአካባቢውም የለች፡፡ በጣም የሚገርም ነገር ነው» አለ
አያ አንበሶም፤

«የሆነ ችግር ገጥሟት ይሆን?» ሲል ጠየቀ፡፡ ሁሉም አራዊት፤ «እረ ምንም ችግር የገጠማት አይመስለንም» አሉ
ተኩላ እንደገና ለማጠናከር፤
«ደን ውስጥ ከመዝናናት ወዲያ ወዲህ ስትል ታይታለች፡፡ የሷ ሽርሽር ከጌታዬ ከአያ አንበሶ ጤና ይብሳል እንዴ? ንቀት ነው እንጂ!» አለ
አያ አንበሶ ተናደደና ፈልጋችሁ ጥሯት ብሎ አዘዘ፡፡
ተኩላ ቀጥሎ «መች እሺ ብላ ትመጣለች፡፡ ልቧ አብጧልኮ፡፡ ጥግብ ብላለች» እያለ አሁንም ነገር በማባባስ ላይ ሳለ፤ ቀበሮ መጣች፡፡ የመጨረሻውን የተኩላን ንግግር ሰምታለች፡፡
አያ አንበሶ በቁጣ፤
«የት ቆይተሽ ነው እስካሁን?! የኔ ጤንነት ነገር ምንም አያሳስብሽም ማለት ነው?»
ቀበሮ ነገሩ ስለገባት በጣም በመለማመጥና በልመና አንደበት፤
«ጌታዬ አያ አንበሶ፤ የዘገየሁበትን ምክንያት ላሳውቅና የፈለጉትን እርምጃ ይውሰዱብኝ´
አያ  አንበሶም፤ «አጥጋቢ ምክንያት ካልሆነ ግን በክርን ደቁሼ አደቅሻለሁ» አለ፡፡
ቀበሮም፤
«ምክንያቴ በቂ መሆኑን አልጠራጠርም» አለች፡፡
«ቀጥይ በይ ተናገሪ» ተባለች፡፡
ቀበሮ እንዲህ ስትል ገለፀች:-
«ጌታዬ አያ አንበሶ፤ ከዱር አሪዊት ሁሉ ለእርሶ ጤንነትና ደህንነት የተጨነቅሁ እኔ ነኝ፡፡ እዚህ ከመምጣት ይልቅ በየቦታው እየተዘዋወርኩ ለርሶ መድሐኒት እነዲነግሩኝ ሐኪሞች ሳነጋግር ነው የቆየሁት»
«እና ምንድነው መድሐኒቱ አሉሽ? አገኘሽ መድሐኒቱን?» አለና አያ አንበሶ በጉጉት ጠየቀ፡፡
«አዎን ጌታዬ፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ አንድ አዋቂ ሀኪም አገኘሁ፡፡ እሱም ‹ለአያ አንበሶ መድሐኒት የሚሆናቸው አዲስ የተገፈፈ የተኩላ ቆዳ ለብሰው ሽፍንፍን ብሎ መተኛት ነው፡፡ በነጋታው ያላንዳች ሕመም ተነስተው መነቀሳቀስ ይችላሉ› አለኝ» ስትል አስረዳች ቀበሮ፡፡
አያ አንበሶ ይህን ሲሰማ ያላንዳች ማመንታት የተኩላውን አናት በክርን ብሎ ዘረረውና «በሉ ቆዳውን ግፈፉልኝ» አለ፡፡
ቀበሮም በሆዷ «በሌላው ላይ ክፉ ማሰብ እንዲህ የራስን ክፉ ያሳያል» አለች፡፡
*   *   *
ክፉ አስቦ የራሱን ክፉ ከሚያይ ይሰውረን፡፡ እርስ በርስ ከመጠላለፍ ያድነን፡፡ ሣር ፈልጐ አሣር ከሚገጥመው ይሰውረን፡፡ ከክፉ መድሐኒተኛ ያድነን፡፡ ትምህርታችንን ለበጐ እንጂ ለተንኮል እንዳናውል ልቡናውን ይስጠን፡፡ ተመክሮአችንን ሌላውን ለማጥቂያ እንዳንጠቀምበት ታሪክ ይምከረን፡፡ በሸረኞች ተመክረን እርጥብ የተኩላ ቆዳ ከመልበስ ያድነን፡፡ የፖለቲካም፤ የኢኮኖሚም የባህልም ተስፋችን በቅንና በጐ ልቦና የሚታሰብ መሆኑን ለማየት ዐይናችንን ይግለጥልን፡፡
ከቶውንም፤ ከፖለቲካ ጭካኔ፣ ከኢኮኖሚ ምዝበራ፣ ከባህላዊ ድንቁርና ይሰውረን ዘንድ የነጋ-ጠባ ጉዟችንን ያለወገናዊነት እንመርምር፡፡ ያወጅናቸውን አዋጆች፣ ያወጣናቸውን መመሪያዎች እኛው እኛው አፍራሽ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡ እንግሊዞች A LAW – MAKER IS A LAW - BREAKER የሚሉት እንዲህ አይነቱን ነው፡፡ ከዚያ ይሰውረን፡፡ አንድ ወደፊት ሁለት የኋሊት እንዳንሄድ ፍሬን ይኑረን፡፡ አንድ ችግር ለመፍታት ከመተኮሳችን በፊት ተጓዳኞቹን ችግሮች ለማየት ማስተዋል ይገባናል፡፡
«አጋዘን ሳድን መጀመሪያ ብቅ ያለው ላይ አልተኩስም፡፡ መንጋዎቹ እስኪሰበሰቡ እጠብቃለሁ፡፡» ይለናል ኦቶ ፎን ቢስማርክ፡፡
የከተማንና የገጠርን ዕድገት ማጣጣምና ማዋሃድ ከብዙ ውጣ ውረድ ያድነናል፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ-ልማት ወዘተ. . .፡፡ ተመጋጋቢ እድገት ካልፈጠርን እየናጠጠ ከሚሄደው የህዝብ ብዛትና እየተስፋፋ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር የነገ ተስፋችን እንዳይቀጭጭና ብርሃናችን እንዳይጭለመለም ዛሬ መጠንቀቅ ያባት ነው፡፡ በገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን የከርሞ ሰው ውስጥ፣ አብዬ ዘርፉ የተባሉ ገፀ-ባህሪ የገጠሬና ከተሜ ነገሮች ሲዛቡባቸውና የልባቸው ሳይደርስ ሲቀር:-
«…ተስፋዬ እንደጉም መንጥቃ
ምኞቴ እንደጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ፤ ለርስታቸው ሳላበቃ የእኔ ነገር በቃ በቃ!» ይሉናል፡፡
The “far future” is already upon us ይላሉ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ሊቃውንት፡፡ ሩቁ ነገ ዛሬውኑ ተጭኖብናል እንደማለት ነው፡፡
ተስፋችን ፍትሕ - ርትዕ የሰፈነባት የሰማች
አገር እንትኖረን ነው፡፡
ምኞታችን የፕሬስ ነፃነት
የሚከበርባት አገር
እንድትኖረን ነው፡፡ ተስፋችን |በቸሃ ዳፋ እነሞር ተደፋ´፣ |አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ´  የሚለው ተረት ዕውን እንዳይሆን ነው፡፡ ምኞታችን |በህግ ከተወሰደ በሬዬ፣ ያለህግ የተወሰደች ጥሬዬ´ የሚለው ተረት ዕውን እንዳይሆን ነው፡፡ ተስፋችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ ተስፋችን፤ ተስፋ የማንቆርጥባት አገር እድትኖረን ነው፡፡ ያለፉትን ዘመናት የፍትሕ ፈተና አስመልክቶ ገጣሚ የፃፈውን ልብ እንበል:-
|. . . ስንቱ ግፉዕ እልፍ - አዕላፍ´
እሥር፣ ግዞት፣ ስደት ዋጠው፤ አልፎ በኔም ባንተም ደጃፍ፡፡
እና እስኪያልቅለት ያ ግፍ ግፍ
ምን ያህል ህይወት ከፈለ፤ ከየት እስከ የትኛው ፅንፍ
የኔና ያንተን ነፃነት፤ ፍትሕን በደም ለመፃፍ!
ያረፈደ ፍርድኮ፣ ካልተፈረደው አንድ ነው
ችኩል ፍርድም ሚዛን የለው! . . .´
ቅድመ-ፍርድ ቅድመ-ጥላቻን መፍጠሩ አይቀሬ ነውና፤ ከቅድመ-ድምዳሜ ለመዳን ብርቱ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡
ከአንድ ፅንፍ ወደ ሌላ ፅንፍ ተስፈንጥሮ መሄድ አገራችንን የት እንዳደረሳት እስከ ዛሬ ያየነው ነገር ነው፡፡
|የሀገራችን ፖለቲካ ችግር በአንድ አቅጣጫ መክረሩ ነው፡፡´ አሉና |ሊብራላይዝ´ መደረግ አለበት፤ አሉ፡፡
አንድ በሳል ሰው፤
|ሊብራሊዝሙንም አታጥብቁት´ አላቸው አሉ፡፡
ከአንድ ፅንፍ አንድ ፅንፍ በመሄድ ማክረር አደገኛ ነው፡፡ እጅግ ማክረርም፣ እጅግ መላላትም የየራሳቸው አደጋ አላቸው፡፡ ሚዛናዊ አካሄድን መልመድ አለብን፡፡ የወረት ጉዞን መናቅ አለብን፡፡ የችኮላን ውሳኔና ድምዳሜን መራቅ አለብን፡፡ አንድን ጥፋት የፈፀምነው አዲሱ መሀንዲስ በቀደደው መንገድ ግራ ግራውን ብቻ በመሄዳችን ከሆነ፤ ሌላው መሀንዲስ የቀደደው መንገድ ደግሞ ቀኝ ቀኙን ብቻ ሂድ፤ የሚል ከሆነ፤ ሁለቱም የፅንፍፍ መንገድ ይሆንና ሁለተዜ ጥፋት ሊሆን ይችላል፡፡ |የተረገመችን እግር  በቅሎ ነስቶ ጫማ ይሰጣታል´ ማለት እንግዲህ ይሄ ነው፡፡ ቆም ብለን መካከለኛ መንገድ እናይ ዘንድ ዐይናችንን ይክፈትልን! የዐባይን ሁለት ሶስተኛ ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ፣ አንድ ሶስተኛ ውሃ የምትጠቀመው ሱዳንና፣ ምንም የማትጠቀመው ኢትዮጵያ፤ አንድም ሶስትም ናቸው፤ የሚለውን እንመረምር ዘንድም ልቦናውን ይስጠን!!  


 

Read 3512 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 09:41