Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 08:06

ድንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ” አይሆንም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ መሪ ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ ቆይተው ነበር ይባላል፡፡ የበታቾቻቸው ያንን የሥልጣን ወንበር ይቋምጣሉ፡፡ ብሶታቸውን ከሆዳቸው አውጥተው ለመናገር ግን አይደፍሩም፡፡ ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ የመሪውም ሥልጣን እየጠነከረና ዘመናቸውም በዚያው ልክ እየተራዘመ ሄደ፡፡ በአንፃሩ በሥልጣኑ ዙሪያ ያሉት ባለሟሎችም መከፋት እንደዚያው እየተባባሰ መጣ፡፡

አንድ ቀን አንደኛው ባለሟል፤ “እስከመቼ ፈርተን የሆዳችንን ሳንናገር እንቀመጣለን?” ብለው የሞት ሞቱን ጥያቄ ያቀርባል፡፡

“ጌታዬ፤ መቼም እስከዛሬ፤ ላልተቋረጡ ዓመታት በሥልጣን ላይ ተቀምጠዋል፡፡ እኛም ያለማቋረጥ በትህትና ስንገዛ ቆይተናል፡፡ አሁን ግን በዛብን፤ ለእኛም ተራ ይድረሰን፡፡ ነገሩም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ፍትሐዊ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል መኖር አለበት፡፡ ምን ይመስልዎታል?”

መሪውም፤

“መልካም፡፡ ጥያቄው ተገቢም አግባቢም ነው፡፡ ሆኖም እንደምታውቁት መሪነት ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ልምድ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው የመምራት አቅም፣ የመግዛት አቅም ይሰጡናል፡፡ አንተ ለምሳሌ ይሄ አቅም የለህም፡፡ ይሄንን ስል ምንም ሳልመዝንና ሳልመረምር አይደለም፡፡ እዚያ ድምዳሜ ላይ መድረሴ ግን ተጨባጭ መሆኑን ለማሳየት አንድ ጥያቄ እጠይቅሃለሁ”

ባለሟሉ፤

“መልካም፤ ልጠየቅ” አለ፡፡

መሪው፤

“እኔ ላደርግ የምችለውና አንተ ግን በምንም ዓይነት ልታደርገው የማትችለው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ መምራት እችላለሁ፤ ወንበርህን ስጠኝ፣ ባንተ ቦታ መተካት አለብኝ የምትል ከሆነ እኔ መሥራት የምችለውን ለመሥራት መቻል ይኖርብሃል”

“መልካም፤ እርሶ መሥራት የሚችሉትን ለመሥራት አለመቻሌን ልፈተንና ይረጋገጥ” አለ ባለሟሉ፡፡

“ጥሩ፡፡ ይሄን ከረጢት ተመልከት” አሉ መሪው፡፡ “በዚህ ከረጢት ውስጥ ያለውን ነገር መሬት ላይ ትዘረግፈዋለህ፡፡ ከዛ አንድ በአንድ ለቅመህ መልሰህ ከረጢቱ ውስጥ ትከተዋለህ፡፡”

“ይሄንን ከባድ አድርገው ነው ጌታዬ? ያለምንም ችግር እሠራዋለሁ” አለና ፎከረ ባለሟሉ፡፡

ከረጢቱ ተሰጠው፡፡ አፉን ፈትቶ ውስጡ ያለውን ሲዘረግፈው ለካ ያገር አይጦች ናቸው፡፡ ፉር ፉር እያሉ በየአቅጣጫው ሮጡ፡፡ አንዷን ሲይዝ ሌላዋ ስታመልጥ እንዲሁ እንደተበታተነ ሁለት ሶስትም ሳያስገባ ቀረ፡፡

መሪው ከት ብለው ሳቁበት፡፡

ባለሟሉ ተናዶ፤ “እሺ እኔ አልቻልኩም፡፡ እርሶ ይስሩና ያሳዩኛ አላቸው”

መሪው ሌላ ከረጢት ተሰጣቸው፡፡ እሳቸው ብልጥ ናቸው፡፡ ከረጢቱን አፉን ያዙና ከራሳቸው ጭንቅላት በላይ አሽከረከሩት፡፡ ብዙ ካዞሩት በኋላ አፉን ፈቱት፡፡ አይጦቹ ስለዞረባቸው እየወጡ መሬት ላይ ፈዘው ቁጭ ቁጭ አሉ፡፡ አንዷም አይጥ መሮጥ አልቻለችም፡፡ ምድር ሰማዩ ዞሮባቸው ሁሉም ባሉበት ቆሙ፡፡ ያይጦች ባህሪ ነው፡፡ መልሰው እያንዳንዳቸውን እየለቀሙ ከረጢቱ ውስጥ ከተቷቸው፡፡

መሪው ባሸናፊነት ስሜት፤

“እንዲህ አንጐላችሁን እያዞርኩ ነው የምገዛችሁ” አሉ፡፡

***

አንጐል እያዞረ ከሚገዛ መሪ ይሰውረን፡፡ ያለ ችሎታ ወንበር ከመቋመጥ ይሰውረን፡፡  ምድር ሰማዩ የዞረበት አይጥ ከመሆን ያድነን፡፡ ከላይ ከሚጫን መሪና ከስር ከሚሸከም ሎሌ ባለሟልነት ያወጣን ዘንድ ልቡናውን ይስጠን፡፡ በብልህነት እንጂ በብልጥነት አንኩራራ! ጠንካራና ደካማ ጐናችንን ካለመገንዘብ የምናጣው ነፃነት የዕጦት ሁሉ ዕጦት ነው፡፡ ከላይ የሚስቅብን አለቃ፣ የፖለቲካ መሪ፣ ኃላፊ ወይም ጠርናፊ መኖር የመርገምት ሁሉ መርገምት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታም የምትገኝ ዲሞክራሲ የበለስ ፍሬ ናት የተከለከለች፡፡ መንግስተ ሰማይን ቀርቶ መንግሥተ ምድርን አናገኝባትም፡፡ “በመንግሥትህ አስበኝ” እንል ዘንድም አይቻለንም፡፡ ፍትሕን መመኘት በቀር አናገኛትም፡፡

መልካም አስተዳደርን ከማውራት በቀር አንኖርባትም፡፡ ከሙስና የፀዳን እጅ አናገኘውም ይልቁንም አዳፋውን እጅ በጓንት ሸፍነን ኦፕራሲዮን የሚያደርግ ሐኪም እንመስልበታለን፡፡ እኛም ሀኪም አንሆን፣ በሽተኛውም አይድን! ለሁሉም ቁልፉ የአለቃና የምንዝር ግንኙነት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ የሆነ አየር የምንተነፍስበት ሁኔታ ከሌለ ይህ ግንኙነት የጌታና የሎሌ ብቻ ይሆናል፡፡

ቀና ብሎ አለቃን መተቸት፣ አስተያየት መስጠት ወይም መገምገም ከቶ አይቻልም፡፡ ቁልፉ የዲሞክራሲው ሃሳዊ አለመሆን ነው፡፡ ሃቀኛ ዲሞክራሲ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን ማረጋገጫ ነው፡፡ የአሸናፊን ብቻ ሳይሆን የተሸናፊን መብት ማረጋገጫ ነው፡፡ የሀቀኛ ዲሞክራሲ አለመኖር ብሶት እንዲጠራቀም እንደሚያደርግ አንዘንጋ! ብሶት ከመጠን ያለፈ ሲጠራቀም ምሬትን ይወልዳል፡፡ ያኔ ደግሞ፤

“ኧረ ምረር ምረር፣ ምረር እንደቅል

አልመርም ብሎ ነው፤ ዱባ እሚቀቀል” የሚለው አገርኛ ግጥም ይዘከራል፡፡ ያ ደግ አደለም! “ነካ ነካ ሳያረግህ ዕብደት አይጀምርህም” ይላሉ አበው፡፡ በኢኮኖሚም፣ በማህበራዊም፣ በፖለቲካም ነካ ነካ ካረገን ዕብደት ቅርብ ይሆናል፡፡ ከዚያ ይሰውረን የበላይና የበታች ችግርን በሚገባ ካልተወያዩ፣ ካልተተቻቹ መፍትሔ አይገኝም፡፡ እየተፈራሩ ዲሞክራሲ የለም፡፡ አንድ ቀን “ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ” አይሆንም፤ የሚለው ተረት መቀየር አለበት - ዲሞክራሲ ይኖር ዘንድ!

 

 

 

Read 4419 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:11