Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:18

“መንግሥት ዝሆን ነው ዞሮ አያይም፣ ያየነውን እንንገረው” የድሬዳዋ ገበሬ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሰውዬው ከሚስቱ ተፋቶ ሲያበቃ ሚስቲቱ ሌላ ባል ታገባለች፡፡ አዲሱ ባል አሮጌውን ባል እጅግ አድርጐ ይፈራዋል፡፡ ስለዚህ በዋለበት አይውልም፡፡ በሄደበት አይሄድም፡፡

አንድ ቀን ሳያስበው አንድ መሸታ ቤት ይገናኛሉ፡፡

ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ አዲሱ ባል ልዩ ትህትና አለው፡፡ ሰውነቱ ግዙፍ ነው፡፡ ሆኖም እንደትልቅነቱና እንደግዝፈቱ አይታበይም፡፡ ደርሶ ሰውን አይዘልፍም፡፡ በአንፃሩ የዱሮ ባል ከመሬት ተነስቶ ቁጣ ቁጣ ይለዋል፡፡ አልፎ አልፎም ካልተደባደብኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፡፡ አዲሱን ባል ሲያየው አሮጌው እንዲህ አለ:-

“ልብ ነው እንጂ ጡንቻ ቢወጣጠር ምን ያደርግ መሰለህ?” ይለዋል፡፡

“ይሆናል” ይላል አዲሱ ባል፡፡

“ባይሆንስ ምን እንዳትሆን ነው?” ይላል የዱሮ ባል፡፡

“ካልሆነማ በቃ አልሆነም” ይላል ትሁቱ ባል፡፡

“ቢሆንስ ባይሆንስ ምን አገባህ?”

“ምንም”

“ምንምማ ሊሆን አይችልም”

“አንድ ጨዋታ ላጫውትህ ወዳጄ”

“ተጫወት”

“በዱር የሚኖር አንድ የሚፈራ አንበሳ ነበር ይባላል”

“በጄ”

“ዝንጀሮ ስለዚያ አንበሳ በርካታ ነገሮችን ይሰማል…አንዴ ሲያገሳ ሣር ቅጠሉ ይንቀጠቀጣል…አንዴ ከያዘ በክርኑ ብቻ መኖርህን እንድትረሳ ያደርግሃል … ሲሮጥ የሰማይ አዕዋፋትም አይቀድሙትም … ሲቆጣ የጫካው አውሬዎች ሁሉ መሬት ቆፍረው ቢቀበሩ ይመርጣሉ ወዘተ … ወዘተ … ይባልለታል፡፡

“እሺ ከዛስ?”

“ለካ ይሄ ሁሉ ዝናና ታሪክ ይነገርለታል እንጂ አንበሳ ካረጀ ቆይቷል፡፡

አንድ ቀን ዝንጀሮ አንበሳው ምን እንደሚመስል ለማየት ፈልጐ በጫካው እየተዘዋወረ ሲፈልገው አንድ በማቃሰትና በመጮህ መሀከል ያለ ድምጽ ይሰማል፡፡ ጩኸቱን ወደሰማበት አቅጣጫ ሲሄድ አንበሳ በጐሽ ተወግቶ ተኝቶ ሲያቃስት አገኘው፡፡ ከዚያም፤

“አዬ!! አንበሳ ጮኸ - ቀለለ፡፡ የሱን ቅሌቱን ለእኔ ቦታውን እንዳውቅ ረዳኝ” አለ ይባላል፤ አለው፡፡

***

አንዳንድ ፖለቲከኞች ምንም ሳይናገሩ ተከብረው፣ ተፈርተው ሲኖሩ ሳለ፤ በተደጋጋሚ በመናገርና በመለፈፍ ምክንያት ዝናቸው ቀሎ፣ ይከበሩ በነበረበት አገር ተዋርደው፣ ይረክሳሉ፡፡ በተቆጡ ቁጥር ቅሌታቸው በጮኹ ቁጥር ደረጃቸው እየለየ ይመጣል፡፡

ከዚህ ይሰውረን፡፡ በዝናና በስም ብቻ ከመኖር ያድነን፡፡ የውስጥ ነገር አውቆ ቅሌትንና ደረጃን ከሚያይ አስተዋይ ዐይን እንደማናመልጥ ልብ እንበል፡፡ ከመቻቻል እንጂ ከክልከላ ፖለቲካ ያውጣን፡፡ ከግለ ሳንሱር (Self – censorship) ወደዋና ሣንሱር አሳንሰር እንዳንሸጋገር ፀሎተ - ትራንስፎርሜሽንን ደግመን ደጋግመን እንፀልይ፡፡ እንደጀርመን ግንብ ከጭንቅላታችን ካልፈረሰው የክልከላ አስተሳሰብ ያድነን፡፡ ታዋቂው በርናርድ ሾው “ትንሽ ሴንሰርሺፕ እኮ ያስፈልጋል” ቢሉት፤ ትንሽ እርግዝና መኖሩን ካረጋገጣችሁልኝ የናንተን ትንሽ ሴንሰርሺፕ እቀበላለሁ” አለ አሉ፡፡

መቼም የዘንድሮ ነገር፤ አዝማሪዋ እንደገጠመችው

“የደሀ ልጅ ወደድኩ አንጀቱን አጥፌ

የሀብታም ልጅ ወደድኩ ብሮቹን አጥፌ

ከአንጀትና ከብር ምረጪ ቢሉኝ

አንጀቱን ዘርግቼ ብር ብር አልኩኝ” ሆኗል፡፡ ችግሩ የብር - ሥርዓት (ካፒታሊዝም) እንኳ በወጉ ልንተገብረው አለመቻላችን ነው፡፡ የፈረሰ ቤተ - ክርስቲያን የምናድስ እንጂ አዲስ ቤተ - ክርስቲያን እየገነባን አይመስልም፡፡ ትራንስፎርሜሽን ደሞ በባህሪው ሥር - ነቀል ለውጥ እንጂ ሲሞቅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ ዓይነት ለውጥ አይደለም፡፡ እርምጃችን ዝሆንን በጉንዳን እንደመመተር መሆን የለበትም፡፡ “በቀን ሦስት ጊዜ ለመመገብ የቻለ ማንም ሰው፤ ከወሲብ መፃሕፍት ይልቅ የምግብ አሠራር መፃሕፍት ለምን ሦስት እጥፍ እንደሚሸጡ መረዳት ይኖርበታል” ይላል የፈረንጅ ፀሐፊ፡፡

በመንግሥትና ህዝብ ዙሪያ ያሉ አያሌ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከራስጌ ያሉትን መንግሥት ያውቃቸዋል፣ ሊፈታቸውም ይገባል፡፡ ከግርጌ ያሉት እጅግ ብዙ ናቸው፤ ወይ ካልወረዱ ወይ ህዝብን ካልወደዱ፤ እንዲህ በዋዛ አይገኙም፡፡ በዋዛም አይመለሱም፡፡ እነዚህንና ሌሎችን እንደመሳለጫ መንገድ ሆነው የሚያሳልጡ የፕሬስ ሰዎች ናቸው፡፡ የማናየውን እንድናይ፣ ቃል የገባነውን መፈፀም አለመፈፀማችንን እንድንገነዘብ የሚያደርጉ እነዚሁ የፕሬስ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱን መገደብ ወይም መከልከል፤ የህዝብን የኢንፎርሜሽን ነፃነት መገደብ ወይም መከልከል ነው፡፡ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ፣ ከራስጌም ሆነ ከግርጌ የምናካሂደው ክልከላ ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም! መንግሥት ዝሆን ነው - ዞሮ አያይም፡፡ ያየነውን እንንገረው” ያለው የድሬዳዋ ገበሬ ዕቅጩን ተናግሯል!

 

 

 

Read 4808 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:25