Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 16 June 2012 11:47

““ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(Let’s frustrate together!) አፍሪካዊ ገጣሚ

አንድ ንጉሥ ወደፊት ለልጆቹ ምን ማውረስ እንዳለበት ሲጨነቅ ሲጠበብ ቆይቶ፤ አንድ ቀን አንድ የፍተሻ ፈተና ለልጆቹ ሊሰጥ ይወስንና ልጆቹን ያስጠራቸዋል፡፡

ከዚያም የሚከተለውን ጥያቄ ይጠይቃቸዋል:-

“ልጆቼ! መቼም ‘ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት’ የሚቀር የለም፡፡ እኔም እድሜዬ እየገፋ፣ መቃብሬ እየተማሰ፣ መገነዣ ክሬ እየተራሰ ያለ መሆኑን ትገነዘባላችሁ፡፡ ስለሆነም፤ የትኛው ልጄ መንግሥቴን መውረስ እንዳለበት ለመለየት ቀላል ፈተና እሰጣችኋለሁ፡፡ በዚህ ትስማማላችሁ?”

አንደኛው - በደስታ!

ሁለተኛው - በጣም ፈቃደኛ ነኝ!

ሦስተኛው - ስመኘው የነበረ ነው! አሉ፡፡

ንጉሡ ደስ ብሎት፤

“እንግዲያው፣ በየግላችሁ ወደ ጫካ ትሄዱና በጣም ጠንካራና የማይሰበሩ ናቸው የምትሏቸውን ሁለት ሁለት እንጨቶች ይዛችሁ ትመጣላችሁ፡፡ የማይሰበረውንና የተሻለውን እጅግ ጠንካራ እንጨት ያመጣው ልጄ የዙፋኔ ተረካቢ ይሆናል!” ሲል ይገልፅላቸዋል፡፡

ሦስቱም በሃሳቡ ተስማምተው ወደ ጫካው በረሩ፡፡ በነጋታው ሁሉም ጠንካራ ናቸው ያሏቸውን ሁለት ሁለት እንጨቶች ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡ ትእዛዙን በመፈፀማቸው ሁሉንም አመሰገኑ፡፡

“መልካም! ልጆቼ ሆይ! እንዳልኩት ያመናችሁባቸውን ጠንካራ እንጨቶች ይዛችሁ መጥታችሁዋል፡፡ ከሁለቱ አንዱን እንጨት ለብቻው አስቀምጡ፡፡ የቀረውን እንጨት አንዳችሁ ላንዳችሁ ስጡና መሰበር አለመሰበሩን እራሳችሁ አጣሩ፡፡”

እርስ በርስ እየተሻሙ አንደኛው የአንደኛውን እንጨት ባለ በሌለ ጉልበት ሰባበሩ፡፡ የማናቸውም እንጨት ጠንካራ አለመሆኑን ንጉሡ አስተዋሉና፤

“በሉ አሁን ደግሞ መሬት ያኖራችኋቸውን ሦስት እንጨቶች አምጡ” አሉ፡፡

ሦስቱን እንጨቶች አመጡላቸው፡፡

“በሉ አንድ ላይ እሰሯቸው” አሉ፡፡

አሰሯቸው፡፡

“እያንዳንዳችሁ አንድ ላይ የታሰሩትን ሦስት እንጨቶች ስበሩና አሳዩኝ” አሉ፡፡

ሦስቱም ለመስበር ሞከሩ፡፡ በጭራሽ ለመስበር አቃታቸው!

ንጉሡም፤ “ይሄውላችሁ ልጆቼ፡፡ በተናጠል ሲታዩ የመረጣችኋቸው እንጨቶች ሁሉ በቀላሉ ተሰባሪ ናቸው! አንድ ላይ ሲሆኑ ግን የማይታበል ኃይል አላቸው፡፡ ዙፋኔ የሦስታችሁም ነው፡፡ የሁላችሁም እንጨት ነው፡፡ ልቦቻችሁን አስተሳስራችሁ አስቡ! ለየብቻ ሄዳችሁ የትም አትደርሱም!” ብለው አሰናበቷቸው!!

***

ዙፋኑን ለልጆቹ ለማውረስ ዝግጁ የሆነ መሪ አይንሳን!

በተናጠል ከመጓዝ ይሰውረን! የራሳችን እንጨት ዕጣ-ፈንታ መሆኑን ሳናስተውል የሌላውን እንጨት ለመስበር ከመጣደፍ ይሰውረን! የጊዜው ጥያቄ፤ Pern-men of the world unite! (የዓለም ፀሀፍት ተባበሩ!) የሚል ይመስላል፡፡ የፕሬስ ሰዎች ብዕሮቻችሁን አስተባብሩ እንደማለትም ነው፡፡

“አወይ ልቤ ደጉ፣ ይላል ትር-ትር

ሆዴ ባዶ እንዳይቀር፣ ሁሉን ስናገር” የሚል መንፈስ ሊኖረው ይገባል፡፡

ግፍ ባለበት ቦታ ሁሉ፤ ተገፊው ድምፁን ማሰማቱ አሌ የማይባል እውነት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሆዳችን በጮኸ ቁጥር የፖለቲካ ልሳናችን መከፈቱ፤ ማህበራዊ ተቋማችን መርበትበቱ፤ “ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ!” እንደሚባለው መሆኑም እውነት ነው፡፡

በዘመነ ካፒታሊዝም የሀብት ባለቤት አድራጊ-ፈጣሪነቱና አንድ ለእናትነቱ ሌላ ባለሀብት እንዳይፈጠር እንዳልሆነም ሊታበል አይችልም፡፡ በዘመነ-ካፒታሊዝም ሰው እንደ ሸቀጥ መታሰቡ ያረጀ ሀቅ የመሆኑን ያህል፤ የድንገቴ/የገጠመኝ (novis) ሀብታሞች ሸቀጥ ልውውጡን ራሱን የሙስና መናኸሪያ ማድረጋቸው፤ በእቅድ ይመራል የሚባለውን ካፒታሊዝም ራሱን፣ እቅደ-ቢስ ያደርገዋል፡፡ ይሄ በመንግሥት ደረጃ ከተከሰተ ደግሞ ለያዥ-ለገራዥ የሚያስቸግር የአገር አባዜ ይሆናል፡፡ በዚህ መንፈስ ሲታሰብ በጥንት ጊዜ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፤ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው!” ይባል የነበረው መፈክር፤ ዛሬ “ማፍረስ ቀላል ነው! መገንባት ፈፅሞ አይቻልም!” ወደሚል እንዳይሸጋገር ልንሰጋ ይገባል!

ሰው እየረሳን ሸቀጥና ብር ብቻ እያሰብን ባገር ሰበብ በግል ወይ በቡድን ስንሄድ፤ ለዚች ማዕከላዊ መደብ (Middle Class) ላልተፈጠረባት አገር ምን አይነት የጥፋት ውሃ እየተመኘንላት መሆኑን ማስተዋል ተስኖናል፡፡ አንድ አበሻ ገጣሚ ስለዘመነ-ካፒታሊዝም እንዲህ ይለናል:-

“ውበትሽ የነበር፣ ኩል ሳይኖር ነበረ

ሙሉ-ልብሽ ጠፋ፣ ጌጥ ሆነ እያደረ!

ያ ንፁህ ገፅታሽ፣ ሰዓሊ እሚያነበው

ዛሬ አርተፊሺያል ፊት፣ የሽያጭ ዕቃ ነው!!”

(ላልታደለች አገር)

መረጃ-ያለው/ያገኘ ማህበረሰብ ሳይኖር ሥልጣኔን ማሰብ ዘበት ነው፡፡ የመረጃ ፍሰት የሚኖረው በጤናማ መንገድ የመረጃ ፍሰቱን የሚሰሩ ሚዲያዎች ሲኖሩ ነው፡፡ እኒህ ሚዲያዎች ተጣምረው ካልተጓዙ ደግሞ እንደ ግለሰቦች ትግል “አንድ አይነድ፣ አንድ አይፈርድ” ናቸው፡፡

መደራጀት ግድ ነው፡፡ አፍሪካዊው ገጣሚ “ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!” ይላል (Let’s frustrate together!) አለበለዚያ ሌላው አፍሪካዊ ገጣሚ እንዳለው They only love the Dead (የሞቱትን ብቻ ይወዳሉ እንደማለት ነው!) ለሚለው አባባል መዘባበቻ ሰለባ እንሆናለን!”

ስለሞቱልን እናወራለን፡፡ ስለተሰዉልን እናወጋለን! ስለትላንት ፍቅራችን እንገልፃለን! ስለዛሬስ? ነው የሚለው ገጣሚው! “ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!”

United we stand separated we fall! ከተባበርን እንቆማለን፤ ከተነጣጠልን እንወድቃለን፤ ማለት ነው! የዱሮ መፈክር - ግን የዛሬም እውነት ነው!

 

 

Read 3764 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:00