Friday, 06 January 2012 11:46

በሰለጠነ ሰው የሚወልዱ ሴቶች የመሞት እድላቸው ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

“ከሰለጠነ ሰው እና ከህክምና ተቋም ውጭ በቤት ውስጥ ልጅን መውለድ ሆስፒታል ውስጥ ከሚወልዱት ይልቅ በሶስት እጥፍ ለችግር ያልጣል፡፡ በቤት ውስጥ የሚወለዱ ልጆች የትንፋሽ ችግር እንዲሁም የልብና የመመረዝ የመሳሰሉት የጤና እውክታዎች ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳረጉት ልጆች በአብዛኛው በቤት ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ ማንኛዋም ሴት ከህክምና ተቋም እርቃ እንኩዋን ብትገኝ በእርግዝናዋ ወቅት የመውለጃዋ ጊዜ ሲቃረብ ወደ ተቋሙ ቀረብ ብላ መቆየት ብልህነት ነው፡፡”

(WWW/Home birth.com)

ልጅን በሰለጠነ ሰው ወይንም በህክምና ተቋም የመውለድን አስፈላጊነት በሚመለከት ለዚህ እትም ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና  የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኢሶግ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ልጅ መውለድ ጥሬ ቃሉ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ልጅ መውለድ ማለት ምን ማለት አንደሆነ ማንም ትርጉሙን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድን ልጅ ለመውለድ ምን ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ? ሂደቱስ ምን ይመስላል ? የሚለውን ለይቶ ማወቁ ላይ ማተኮር ተገቢ ይሆናል፡፡ አንድ ወሊድ ትክክለኛና (Normal ) ትክክል ያልሆነ ወይንም ችግር ያለበት ተብሎ ይለያል፡፡ አንድ ወሊድ ትክክለኛ ነው የሚባለው ምጡ በጊዜው የጀመረ ሲሆን ነው፡፡ ይሄውም የመጨረሻው የወር አበባ በታየ ከ37 - 42 ሳምንት ውስጥ መሆን አለበት፡፡ ከ37 ሳምንት በፊት ምጥ ቢመጣ ያለጊዜው የመጣ እንዲሁም ደግሞ ከ42 ሳምንት በሁዋላ ከሆነ የዘገየ ተብሎ ይለያል፡፡ ስለዚህ...

ምጥ በትክክለኛው ጊዜ መምጣት አለበት፡፡

የምጥ ጊዜው ወይንም የሚፈጀው ሰአት የተወሰነ መሆን አለበት ፡፡

የሽንት ውሀው የፈሰሰው በምጥ ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት፡፡

እናትየው ያለምንም መሳሪያ ድጋፍ በእራራስዋ አምጣ መውለድ አለባት፡፡

የተወለደው ልጅ ጤነኛ መሆን አለበት፡፡

ከወሊድ በሁዋላ በአራራስ ቤት ምንም አይት ችግር መፈጠር የለበትም፡፡

እነዚህ መስፈርቶች የተሟሉ ሲሆኑ ወሊዱ ጤናኛ ወይንም ትክክለኛ ነው ይባላል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ወሊዱ ትክክለኛ አይደለም ተብሎ ሊለይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወሊድ በሰለጠነ ሰው እና በህክምና ተቋም መወለድ አለበት የሚባለው ምጡ በማንኛውም ጊዜ ችግር ቢገጥመው ማከም እንዲቻል ሲባል ነው፡፡

አንዲትን እናት ከሚፈጠሩት ችግሮች መታደግ እንዲቻል በእርግዝና ወቅት ሙሉ የሆነ የህክምና ክትትልና እንክብካቤ ቢያንስ ለአራት ጊዜ ልታደርግ ይገባታል፡፡

1/ ከእርግዝና በፊት የሚደረግ ክትትል ፣

አንዲት ሴት ከማርገዝዋ በፊት የጤንነትዋ ሁኔታ የተስተካከለ ነው ወይ ? የሚለው መረጋገጥ አለበት፡፡ የደም ግፊት ፣የኩላሊት ችግር ፣ስኩዋር በሽታ፣ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት፣ ኤችአይቪን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች፣ የልብ ሕመም ሊኖር ስለሚችል አስቀድሞውኑ ክትትል ማድረጉ ይጠቅማል፡፡ እነዚህ ቀድሞውኑ የነበሩት ሕመሞች ክትትል ሳይደረግላቸው እርግዝና በሚፈ ጠርበት ጊዜ ወደተባባሰ ሁኔታ ሊለወጡና ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

2/ ቅድመ ወሊድ ክትትል፣

ይህ ክትትል እርግዝናው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከወሊድ ድረስ የሚደረገው የእርግዝና ክትትል ነው፡፡ ይህ ክትትል በእርግዝናው ላይ የሚፈጠሩት ለውጦች ትክክለኛ ናቸው ወይንስ አይደሉም የሚለውን ለይቶ በማወቅ ከበሽታ ጋር የተያያዘ ለውጥ የሚያሳዩ ከሆነ ምክንያታቸውን አውቆ እንክብካቤ ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ በእርግዝናው ወቅት የደም መፍሰስ ፣እራስ ምታት፣ የፊትና የእጅ እብጠት፣ መጥፎ ፈሳሽ ከማህጸን ትኩሳት፣ ማንቀጥቀጥ የመሳሰሉት እና እንዲሁም የሽንት ውሀ ከምጥ በፊት ቢፈስ ፣የእርግዝናው ወይንም የሽሉ እንቅስቃሴ ቢጠፋ አሳሳቢ እና አደገኛ ነገር ሊከሰት እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች ስለሆኑ ጥብቅ የህክምና ክትትል ያስፈልገዋል፡፡

3/ የወሊድ ጊዜ እንክብካቤ ፣

የእርግዝና ክትትል ትርጉም የሚኖረው ከወሊድ እንክብካቤ ጋር አብሮ ሲቆራኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ችግሮች ከእርግዝናው ውጭ በወሊድ ጊዜ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነው፡፡

የምጡ ጊዜ እረጅም መሆን፣

በምጥ ሰአት ደም መፍሰስ፣

በምጥ ጊዜ ሽሉ ሊታፈን የሚችልበት አጋጣሚ፣

በምጥ ጊዜ የደም ግፊት በአደገኛ ሁኔታ ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትና የመሳሰሉት ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመገመት በተቻለ መጠን በሰለጠነ ሰውና በህክምና ተቋም መውለድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አምጣ መውለድ የምትችለውንና ብታምጥ በእራስዋም ሆነ በህጻኑ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መገመት የሚቻለው እርጉዝዋ ሴት በህክምና ተቋም ለመውለድ በቀረበች ጊዜ ነው፡፡

4/ ከወሊድ በሁዋላ የሚደረግ ክትትል፣

አንዲት ሴት ከወለደች ጊዜ ጀምሮ እስከሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት ድረስ የህክምና ክትትል ልታደርግ ይገባታል ፡፡ እናትየው እንደወለደች የመጀመሪያው አሳሳቢ ነገር የደም መፍሰስ ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ለብዙ እናቶች በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ለሞት የሚዳርግ ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሚሞቱት እናቶች ከአራቱ የአንዱዋ ምክንያት የደም መፍሰስ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 90 የሚሆኑት ሴቶች የሚሞቱት ከወሊድ በሁዋላ መቆጣጠር በማይቻል የደም መፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የደም መፍሰስ ለመቆጣጠር በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በሁዋላ የሚሰጡ መድሀኒቶች ያሉ ሲሆን ይህንን መጠቀም የሚቻለው በህክማና ተቋም ሲወልዱ ነው፡፡ ከወሊድ በሁዋላ በማህጸን አካባቢ እንደማመርቀዝ እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የደም መርጋት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በእግር እና በማህጸን አካባቢ ባሉ ትላልቅ የደም ስሮች ውስጥ የረጋው ደም ተጎርዶ ካለበት የደም ስር ወደ ልብና ሳንባ ከሄደ በአደገኛና በድንገተኛ ሁኔታ ለሞት የሚዳርግ ነው፡፡ እንዲሁም አልፎ አልፎ ወሊድ የሰውነት እና ማህበራዊ ለውጦችን ስለሚያመጣ ልጅን መንከባከብ ፣ሌሎችም ተመሳሳይ የኑሮ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተጨማሪ ስራ ስለሚሆን ጥቂት የማይባሉ ሴቶች የአእምሮ መረበሽ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ እናቶች ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ጊዜ ፣በወሊድ እና ከወሊድ በሁዋላ ከሕክምና ክትትል መራቅ የለባቸውም ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት እንደገለጹት፡፡

ዶ/ር ይርጉ በህክምና ሙያ በሰለጠነ ሰው የማይወልዱ እናቶች እንዲወልዱ የሚገደዱት ባልሰለጠነ ሰው ነው ብለዋል፡፡ያልሰለጠነ ሰው ሲባል ዘመድ ጉዋደኛ የልምድ አዋላጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ተፈጥሮአዊ የሆነ ምጥ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ ሲከሰት በተቻለ መጠን እርዳታ ማድረግ ተገቢ ስለሆነ  እንደድንገት ማናቸውም በቅርብ ያሉ ሰዎች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያለው ሁኔታ አደጋን ሊያስትል እንደሚችል በመገመት ምንጊዜም በአቅራቢያ ባለው የጤና ተቋም ለመገልገል መዘጋጀት ጠቀሜታው ከዚህ በመለስ የማይባል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን አደረጃጀት ብንመለከት አሉ ዶ/ር ይርጉ በህብረተሰቡ አቅራቢያ ያሉ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች የህብረተሰቡን ጤና ለመንከባከብ ከሚሰሩዋቸው ወደ አስራ ስድስት ከሚደርሱ የጤና አገልግሎቶች መካከል ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር የሚሰሩዋቸው ስራዎች አሉ፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ የሆነን የመከላከል ሕክምናን ፣ጤና የማበልጸግ ምክሮችን ወይንም እንቅስቃሴዎችን በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖር ሰው ከጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ማግኘት ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጤና ጣቢያዎች ፣የጤና ኬላዎች፣ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎችን እንደቅርበታቸውና እንደችግሩ ከባድነት መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡ እነዚህ ጤና ጣብያዎችና ሆስፒታሎች ሁሉንም አይነት ማለትም ከእናቶች ጤናና ሕይወት ጋር የተያያዘውን መሰረታዊና ከፍተኛ የሆነ የህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

በስተመጨረሻም በአለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቀው በሰለጠነ ሰው የሚወልዱ ሴቶች የመሞት እድላቸው  በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ሕጻናቱም በሚደረግላቸው እንክብካቤ የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ በእርግጥ የእናቶችንና የህጻናቱን ሞት ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አዳጋች ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ግን መቀነስ ይቻላል ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ አስቀድሞውኑ በመዘጋጀት ወደ ህክምና ተቋማቱ በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ የህክምና ተቋማት ከእርግዝና በሁዋላ ጥሩ ውጤት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ እንደዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኢሶግ ፕሬዝዳንት፡፡

 

 

Read 4055 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:53