Print this page
Saturday, 28 April 2012 12:33

..የነበረው የእናቶች ሞት እንዳይመለስብን...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

..አንዲትን እናት ከሞት ማዳን ቀላል ነገር አይደለም፡፡  አገልግሎት የምንሰጥባቸው ቦታዎች በጣም እሩቅና የመገናኛ ዘዴ የሌለባቸው መንገድ ለምሳሌ...ተርጫ ሆስፒታል ዳውሮ ዞን ፓዌ ፣ጊዳ አያና ወለጋ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ስናይ እንኩዋንስ አንዲት እናት በምጥ ተይዛ ቀርቶ ለሌላውም ሰው ተጉዋጉዞ ወደሚቀጥለው ከተማ ወይንም ወደ ሆስፒታል የመድረስ እድሉ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኙ እናቶችን ለማዳን የሚያስችል የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና በመሰጠቱ ብዙ እናቶችን ከሞት የማትረፍ እድል ይኖራራል ተብሎ ይታመናል...ደግሞም እየታየ ነው፡፡..

ዶ/ር መሀዲ በክሪ

ዶ/ር መሐዲ በክሪ በኢሶግ የ Emergency obstetric & neonatal care ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ በኢሶግ የ  Emergency obstetric & neonatal care ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መሃዲ በክሪ እንደሚገልጹት ይህ ፕሮጀክት በዋናነት እናቶችን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ በተለይም ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶች የሚገጥማቸውን እስከአሁን የነበረውን የጤና ችግር ለማቃለል ወይንም እገዛ ለማድረግ የተጀመረ ነው፡፡ በመጀመሪ ያው ዙር በስምንት ክልል መስተዳድሮች ውስጥ በተመረጡ አስራ ሶስት ሆስፒታሎች እድሉ ተሰጥቶ ከእያንዳንዱ ሆስፒታል ቢያንስ እስከ ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ስል ጠና እንዲያገኙ ተደርጎአል፡፡ አፋጣኝና አስቸጋሪ በሆነ ምጥ ለተያዙ ሴቶች የቀዶ ሕክ ምና አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ ሌሎች የጽንስና የማህጸን ሕክምናዎችአገልግሎትም ለስድስት ወር ያህል አሰልጣኞቹ ከሰልጣኞች ጋር አብረው ሲሰጡ ቆይተዋል ፡፡ በሁለተ ኛው ዙር ደግሞ በአማራ ፣በኦሮሚያ ፣በደቡብ እና በትግራይ በሚገኙ ዘጠኝ ሆስፒታ ሎች ስልጠናው እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በእያንዳንዱ ሆስፒ ታል በትንሹ ሁለት ጠቅላላ ሐኪሞች አሰልጥነው ኦፕራሲዮን እስከማድረግ ያለውን አሰራር አለማምደው ለአገልግሎት ያበቃሉ፡፡እነዚህ በአሰልጣኝነት የተመደቡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲሄዱ የሰለጠኑት የህክምና ባለሙያዎች አሰል ጣኙን በመተካት አገልግሎቱን ለእናቶች በተገቢው ይሰጣሉ ብለዋል ዶ/ር መሐዲ፡፡

በዚህ እትም ወደፍኖተ ሰላም በመጉዋዝ በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የሚታከሙ እናቶችን ሁኔታ እና አሰልጣኝና ሰልጣኝ የህክምና ባለሙያዎችን ሀሳብ በመቀጠል እናስነብባችሁዋለን፡፡

..... ስሜ ባንተይገኝ ብዙነህ ይባላል፡፡ ምእራብ ጎጃም ውስጥ ወረዳው ጃቤ ጠና ይባላል፡፡ ከተማው ፍኖተ ሰላም ሆስፒታሉም ፍኖተ ሰላም ይባላል፡፡ እኔ እዚህ ሆስፒታል ከ1984ዓ/ም መጨረሻ ጀምሮ ወደ ሀያ አመት ገደማ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ በዚህ ዘመን ያየሁት ነገር ብዙ ጊዜ ወደዚህ ሆስፒታል የሚመጡ እናቶች ወደው ወይንም ሕክምና አለ ብለው ሳይሆን ከሁለት ሶስት ቀን በላይ በምጥ ከተሰቃዩ በሁዋላ ከአቅማቸው በላይ በሚሆንበት ጊዜ ነበር የሚመጡት፡፡ አብዛኛዎቹ እናቶች የማህጸን ሐኪም ስላልነበረ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስ ጠት ስለማይቻል ወደሌላ ሆስፒታል እንዲወስዱአቸው ሲነገራቸው የገንዘብ ችግር ስለሚገጥማቸው ወደቤታቸው ይመልሱአቸው ነበር፡፡ ውጤቱም ያው ሞት ነው፡፡ ወደቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታም መጀመሪያውኑ ምጥ የያዛትን ሴት ወደ ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የሚያመጡት ከብትም ሆነ እህል ሸጠው ሲሆን እንደገና ወደባህር ዳር ወይንም ወደ ደ/ማርቆስ ሆስፒታል ውሰዱ ሲባሉ ከአንድ ሺህ እስከ ሺህ አምስት መቶ ብር ስለሚጠየቁ አቅም ስለሌላቸው ሴትየዋ እንደምትሞት እያወቁ በዚያው በቃሬዛው ተሸክመው ወደቤታቸው ይመልሱአ ቸዋል፡፡ በእርግጥ አሁን የተሸለ ሁኔታ አለ፡፡ መንገድም ተሰርቶአል፡፡ አሁን ደግሞ ሐኪሞች እየሰለጠኑ ስለሚገኙ የወደፊቱ ይበልጥ ይሻሻላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡..

ከተወለደች ሶስት ቀኑዋ ነው፡፡ የመኝታ ክፍሉን በለቅሶ አድምቃዋለች፡፡ እናትየውን ወይንም አንረዋት ያሉትን ሰዎች ለማነጋገር የሕጻኑዋን ለቅሶ እስኪያበቃ መጠበቅ ነበረብን፡፡ ወላድዋ በቤተሰቡዋ ተከባለች፡፡ አስተያየታቸውን እንዲህ ነበር የሰጡን፡፡

.....ስሜ ሽመላሽ ይባላል፡፡...እኔ የወላድዋ ቤተሰብ ነኝ፡፡ እኔ በዚሁ አገር ነዋሪ ነኝ፡፡ በዚህ ሆስፒታል ኦፕራሲዮን የሚባል ነገር ሰምተን አናውቅም፡፡ ኦፕራሲዮን ወደ ባህርዳር ወደ ደብረማርቆስ እንጂ በዚህ ሆስፒታል እኔ አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ አሁን ይህች እህታችን እዚህ እድሉ ስለገጠማት ኦፕራሲዮን ሆና ይኼው ልጁዋን አቅፋ በሰላም ...አረፍ ብላ ተኝታለች፡፡ ሌሎችም ከሌላ እራቅ ካለ ቦታ እየመጡ ኦፕራሲዮን እየተደረጉ ይገኛሉ ፡፡ ..

#...መላኩ እሱባለው እባላለሁ፡፡ ወላድዋ እህ ነች፡፡ በፍኖተሰላም ሆስፒታል የገጠመን ይህ ጥሩ ነገር ሌሎችም እንደ እኛ ይቸገሩ የነበሩ እንዲገጥማቸው እመኛለሁ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ...ወላዶች በምጥ ሲሰቃዩና ከሕክምና ባለሙያ እጥረት የተነሳ ወደባህርዳር ወይንም ደብረማርቆስ ሂዱ ሲባሉ መንገድ ላይ ሲሞቱ ስለሚመለከቱ ቢቀርብንስ በማለት ልጅ መውለድን ገሸሽ እንደማ ድረግ ብለው ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ባለሙያ ሳይሄድ በወለድን እያሉ ለመውለድ እየተዘጋጁ ያሉ አሉ፡፡ እግዚአብሔርን የምንለምነው ያ ቀደም ባለ ጊዜ የነበረው የእናቶች ሞት እንዳይመለስብን እና ይህ አገልግሎት እንዲቀጥልልን ነው ፡፡ ..በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል እርዳታ ሳያገኙ እየቀሩ ለሞት ይዳረጉ የነበሩትን እናቶች ሕይወት በመታደግ በኩል በፈቃደኝነት ሁለት ጠቅላላ ሐኪሞች ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡

.....ዶ/ር ሲሳይ አድማሱ እባላለሁ፡፡ በሙያዬ ጠቅላላ ሐኪም ነኝ፡፡ በዚህ በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ስሰራ ወደ ሶስት አመት ሆኖኛል፡፡ ከአሁን ቀደም ባለው የስራ ልምዴ በሆስፒታሉ የጽንስና ማህጸን ሐኪም ሰለሌለ ወላዶች ሲመጡ ወደሌላ አቅራቢያ ሆስፒታል ነበር የምንልከው፡፡ በእርግጥ ወላዶቹ ኦፕራሲዮን ሊያስፈልጋቸውም ላያስፈልጋቸውም ይችላል፡፡ ቀለል ባለና በምጥ ማምጫ በመሳሰሉት መንገዶች ሊወልዱ ይችሉ እንደነበር እንገምታለን፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን አስቀድሞ መገመት አስቸጋሪ ስለሚሆን ደፍረን እጃችን ላይ  አናቆያቸውም፡፡  ምናልባት ከፍ ያለ ሕክምና ማለትም እንደኦፕራሲዮን ያለ ቢገጥመን በሁዋላ ችግር ስለሚያስከትል አንሞክረውም ነበር፡፡ በእርግጥ ሂዱ የተባሉት ሁሉ ወደሚቀጥለው ሆስፒታል አይሄዱም፡፡ ምክንያቱም ወደተላኩበት ሆስፒታል ለመሄድ ከበድ ያለ የትራንስፖርት ክፍያ ስለሚጠየቁ ወደቤታቸው ነበር የሚመልሱአቸው፡፡ ያው ወይ መንገድ ላይ አለበለዚያም እቤታቸው ከደረሱ በሁዋላ  ይሞታሉ ፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ገጠመኛችን ነበር ፡፡ ስልጠናው ከሁለት ወር በፊት ነው የተጀመረው፡፡ አሁን ከአሰልጣኝ ሐኪማችን ጋር እየሰራን ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ወደሆስፒታሉ የሚመጡ ወላዶች በርካታ እየሆኑ ነው፡፡ ምክንያ ቱም ባለሙያ አለ ስለተባለ ነው፡፡ እንግዲህ አሰልጣኙ በሚሄድበት ጊዜ ህብረተ ሰቡ ስጋት እንዳይገባው ጠንክረን አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ ከአሁን ቀደም ያየናቸውን የእናቶች ስቃይ ለመቀነስና የህጻናቱንም ሕይወት ለመታደግ ከሙሉ ፍላጎት ጋር በመሰልጠን ላ እንገኛለን፡፡ ..

በመቀጠል ያነጋገርነው አንዲት ወላድን ነው፡፡ የወለደችው ልጅ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ነገር ግን የተገላገለችው በኦፕራሲዮን ነው ፡፡ በእርግጥ ...አሉ ...በሆስፒ ታሉ ስልጠና በመስጠት ላይ ያሉት ሐኪም ...

.. ዶ/ር ባዘዘወ ፈቃደ እባላለሁ፡፡ በሙያዬ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊ ስትነኝ፡፡  በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ያለኝ የስራ ድርሻ ሁለት ጠቅላላ ሐኪሞችን የ Emergency obstetric care” በሚመለከት በኢሶግ የሚሰጠውን ስልጠና በመስጠ ትና በተጉዋዳኝም የጽንስና የማህጸን ችግሮችንም ለታካሚዎች ሕክምና በመስ ጠት ላይ እገኛለሁ፡፡ ቀደም ሲል ያነጋገራችሁዋት ወላድ በእርግዝና ክትትልዋ ጊዜ ምንም ችግርያልታየባት ስትሆን በመውለድ ጊዜ ግን ሕጻኑ እየታፈነ በመምጣቱ ኦፕራሲዮን ማድረግ ግድ ነበር፡፡ ይህ ሕክምና አሁን እኔ ስላለሁና በሆስፒታሉ ያሉ የጠቅላላ ሐኪሞችም በመሰልጠን ላ ስላሉ ስናትየውን ረድተናታል፡፡ ባይሆን ኖሮ አስቸጋሪ ነበር... አሉ፡፡..

ወደ ወላድዋ ስንመለስ  .. እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ይህ ሐኪም ባለበት ጊዜ ባይሆን ኖሮ እንግዲህ ወደሌላ ሂጂ ስባል ...ገንዘቡስ ከየት ይመጣል...ቢሆንም ደግሞ ...ገንዘቡም ቢገኝ ማለ ነው...ገና ከዚያ እስክደርስ ድረስ ምን እንደሚሆን አላውቅም፡፡ መቼም ሞት እግዚሀር ካለ አይቀርም፡፡ ግን በጤንነቱም በኩል ያለው ነገር እጅግ ያሳስበኛል፡፡ ሌሎች እህቶቼም ደግ እንዲገጥማቸው እመኛለሁ፡፡..

ይቀጥላል

 

 

 

Read 3215 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:39