Print this page
Saturday, 19 May 2012 11:52

....በአግባቡ ወልዶ ልጅን አቅፎ መሄድ ቀላል አይደለም፡፡..

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

አጣጥ ሆስፒታል የዛሬው የአምዳችን ትኩረት ነው፡፡ አጣጥ ሆስፒታል የተቀናጀ የጤና አገልግሎትን ማለትም መከላከልን ፣ማዳንንና ልማትን ለተጠቃሚዎች የሚያበ ረክት ሆስፒታል ነው፡፡ አጣጥ ሆስፒል በደቡብ ምእራብ አዲስ አበባ ከወልቂጤ ከተማ 17/ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሆሳእና መንገድ የሚገኝ ነው፡፡ አጣጥ ሆስፒታል ይበል ጡን አገልግሎት የሚሰጠው በደቡብ ብሄር ብሔረሰቦች ጉራጌ ዞን ጨጫ ወረዳ ሲሆን ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ የሚገመተው ህብ ወደ 800.000 የሚሆኑ ናቸው፡፡በሽታን በመከላከል ደረጃ ሆስፒታሉ ለ12/ ገበሬ ማህበር አባላት በተለይም 36500/ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በዚያም 16/ የጤና ማእከላትና ሰባት ክሊኒኮች ሆስፒታሉን እንደ ሪፈራልሕመምተኛን በመላክ ይጠቀማሉ፡፡

ለአጣጥ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ የሚባሉ ሆስፒታሎች ወሊሶ የሚገኘው ሉቃስ ሆስፒታል በ60 ኪ/ሜትር ርቀት እና ሆሳእና ሆስፒታል በ120/ኪ/ሜትር ርቀት ናቸው፡፡ ሆስፒታሉን የጎበኘነው ይበልጡኑ እናቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ካላቸው የአኑዋዋር ባህርይ የተነሳ ሊደርስ ባቸው የሚችለውን ችግር ለመከላከል ማረፊያ ተዘጋጅቶ እስከሚወልዱበት ቀን ድረስ እንዲሁም ከወለዱም በሁዋላ ደህንነታቸው እስከሚረጋገጥ እንዲቆዩ መደረጋቸው የተለየ የሚያሰኘው አገልግሎት በመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አገልግሎት በሌላም አካባቢ የሚሰጥ ሲሆን በአገር ደረጃ ግን በቁጥር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

 

አጣጥ ሆስፒታልን በሜዲካል ዳይሬክተርነት የሚመሩት ዶ./ር ሪታ ሺፋ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ በእምነት የካቶሊክ ሲስተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ሪታ እንደሚገልጹት ሆስፒታሉ ከተቋቋመ ወደ 43 አመቱን የያዘ ሲሆን እሳቸው በሆስፒታሉ ወደ 15 አመት አገልግለዋል ፡፡ ዶ/ር ሪታ እንደሚገልጹት ...

..አጣጥ ሆስፒታል የሚተዳደረው በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ አጣጥ ሆስፒታል የሚገኝበት ቦታ ቀድሞ ሲመሰረት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት ሲሆን ነገር ግን በጊዜው በዚህ ደረጃ የሚማር በቂ ተማሪ ስላልነበረ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጤና አገልግሎት ቢሰጥበት ይሻላል በሚል ስለወሰነ ወደሆስፒታልነት ተቀይሮአል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ማሻስ ቂስሳሽሰሮቁ ቂሽቋቋሽቄቃ ቋሽቋስቈቋ   ስራውን የጀመሩ ሲሆን እንደአሁኑ በተስፋፋ መልኩ ሳይሆን በክሊኒክ ደረጃ ፍራሽ እየዘረጉ ሕመምተኞችን መርዳት ነበር፡፡ አሁን ግን ትልቅ ተብሎ ባይጋነንም ሆስፒታሉ በጣም ብዙ ተጠቃሚ ያለው ቀኑን ሙሉ ያለእረፍት የሚሰራ ነው፡፡ በወደፊቱ የማስፋፋት ስራው በግቢው ውስጥ ተጨማሪ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ትልቅ ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ የሆስፒታሉ አልጋ ቁጥር 65/ነው፡፡ አጣጥ ሆስፒል በቀን ከ200 እስከ 250 በተለያዩ ምክንያቶች የታመሙ ሰዎችን የሚያክም ሲሆን የታካሚው ቁጥር በአመት ወደ 70/ ሺህ ይደርሳል፡፡ አጣጥ ሆስፒታል አነስተኛና ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን የሚሰጥ ሲሆን ቁጥሩም ወደ 1500/አንድ ሺ አምስት መቶ ይደርሳል፡፡ አጣጥ ሆስፒታል ወደ 2000/ የሚሆኑ የማዋለድ አገልግሎ ቶችን በየአመቱ ይሰጣል፡፡ ከምንም በላይ ክትትል የምናደርግበት ስራችን ደግሞ የእናቶችን ደህንነት መጠበቅ ሲሆን ከዚህም መካከል የእናቶች ማቆያ ቤት ከ30/አመት ላላነሰ ጊዜ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡..

በአጣጥ ሆስፒታል የእናቶች መቆያ ክፍል ያገኘናቸው የተለያዩ እናቶች ከየት አካባቢ እንደመጡና የገጠማቸውን ችግር እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡

.. እኔ የመጣሁት ከዳርኪ ነው፡፡ ዳርኪ በግምት ኪሎ ሜትሩ ባላውቀውም እሩቅ ነው፡፡ እርግዝናዬ የመጀመሪያ ነው፡፡ ነገር ግን መንገዱ የማይመች ከመሆኑ የተነሳ ምናልባትም በቤ ሆኜ ምጥ ቢይዘኝ ልጎዳ እችላለሁ፡፡ ይህንን ግን ያወቅሁት እዚህ ለህክምና ስመጣ ስለነገሩኝ ነው፡፡ ስለዚህ እስከምትወልጂ ድረስ እዚህ ቆዬ ብለውኝ ተቀምጫለሁ፡፡ ስንቄን ቤተሰቦቼ ያመላልሳሉ፡፡ እኔም እዚህ ኩችና ስላለ ትንሽ ትንሽ እሰራለሁ፡፡ አስታ ማሚ አንድ ሰው ስለሚፈቀድልኝ ባለቤ ከእኔ ጋር አብሮ አለ፡፡ አሁን ያለስጋት የምወልድበትን ቀን እየተጠባበቅሁ እገኛለሁ፡፡ ..

ሲስተር ብዙነሽ ተረዳ በአጣጥ ሆስፒታል በተለያዩ የህክምና ክፍሎች ለአስራ አምስት አመት ያህል ሰርተዋል፡፡ ሲስተር ብዙነሽ እንደሚሉት ...

..ከአሁን ቀደም በነበረው ልምዳችን እናቶች ለምርመራም ሆነ ለመውለድ ቀደም ብለው አይመጡም ነበር፡፡ ብዙዎቹ ወደሆስፒታሉ የሚመጡት ምጥ ከያዛቸው ከቀናት ስቃይ በሁዋላ ስለነበር እነዛን ሴቶች ለማዳን ከፍተኛ ችግር ይገጥመን ነበር፡፡ ምናልባትም ከዚህ ስቃይ በሁዋላም ወደሆስፒታሉ የሚመጡት እድለኞቹ ማለትም ለመጉዋጉዋዣ የሚከፍሉት ገንዘብ ያላቸው እና መጉዋጉዋዣ ያገኙት ስለሆኑ የቀሩት ግን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚወድቁ ለማወቅ አይቻልም፡፡ በአሁን ወቅት ግን እናቶች ወደሆስፒታሉ የሚመጡት በምጥ ሲያዙ ለመውለድ ብቻ ሳይሆን ከመውለድ አስቀድሞም የእርግዝና ክትትል ለማድረግ በብዛት በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ አጣጥ ሆስፒታል በአካባቢው ላሉ የጤና ጣቢያዎች ክሊኒኮች ሁሉ እንደሪፈራል የሚያገለግል ስለሆነ ከየትኛውም አካባቢ የሚመጡ እናቶች በሰላም ልጃቸውን ይወልዳሉ፡፡ .. አጣጥ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሪታ ሺፋ እንዲህ ይላሉ...

....የእናቶች ማቆያ ክፍላችን ከሰላሳ አመት ጀምሮ ስራውን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ይህ የእናቶች ማቆያ ክፍል የተቋቋመበት ዋናው ምክንያት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እንዲረዳ ነው፡፡ በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ በምጥ በሚያዙበት ወይንም በጠና በሚታመሙበት ጊዜ ከትራንስፖርት እና ከገንዘብ እጦት የተነሳ ወደሆስፒታል ስለማይመጡ ባሉበት ለህልፈት ይዳረጉ ነበር፡፡ ይህ ዜና በየጊዜው ወደ ሆስፒታሉ በተለያየ መንገድ ይመጣ ስለነበር ሆስ ፒታሉ ከተቋቋመ ወደ አስር አመት ገደማ እንደሆነው ሶስት ባህላዊ ጎጆ ቤቶች እንዲሰሩና እናቶች እስኪወልዱ ድረስ እዚያ ውስጥ እየመጡ እንዲቆዩ ማድረግ ተጀመረ፡፡ይህ ስራ የተጀመረው እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1970/ መጨረሻ ሲሆን በጊዜው የነበረው 20/አልጋ ብቻ ነበር፡፡ የእናቶች ማቆያ በጅምሩ ወቅት በአመት እስከሁለት መቶ የሚደርሱ እናቶችን ያሳርፍ ነበረ፡፡  አሁን ግን ወደ 44 አልጋዎች ሲኖር በአመት ከሰባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚሆኑ እናቶች በአመት ይስተናገዳሉ .. ብለዋል፡፡

ሌላዋ እናት የመጣችው ከጉመር ወረዳ ነው፡፡ ጉመር አጣጥ ሆስፒታል ካለበት ወደ 50/ ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡መንገዱ በኪሎ ሜትር ከመለካቱ በላይም በጣም አስቸጋሪ ነው እንደእንግዳችን  ምስክርነት፡፡

..... እዚህ እናቶች ማቆያ የገባሁት የዛሬ አስራ አምስት ቀን ነው፡፡ እርግዝናው ዘጠኝ ወር ሆኖታል፡፡ እንደሐኪሞቹ አባባል ከዚህ በሁዋላ ምናልባት ሁለት ሳምንት ይቀረዋል፡፡ እኔ ግን አስቀድሜ መጥቼ የተኛሁበት ምክንያት የአገሬ መንገድ እንኩዋንስ እንደእኔ ለደከመ ለሌላውም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ የእግር መንገድም አለው፡፡ ስለዚህ ምጥ ቢመጣ ወደ ሆስፒታሉ መምጣት አይቻልም፡፡ እኔ ከአሁን ቀደም ሁለት ልጆችን እዚሁ ሆስፒታል ወልጃለሁ፡፡ ስለዚህ የሚሰጡ ትን አገልግሎት ስለማውቅ መጣሁ እንጂ እንደእኔ ያሉ የደከሙ ይህንን የማያ ውቁ ግን ብዙ አሉ፡፡ ስለዚህ በምጥ ሰአት ይቸገራሉ፡፡ በመከራ ቢወልዱም እንኩ ዋን ወይ ልጁ ይሞታል ወይንም ደግሞ እናትየው ትጎዳለች፡፡ እዚህ ግን በቂ እረፍት አለ፡፡ እሩቅ ቦታ ...ገበያ የመሳሰለው አንሄድም እንጂ እራሳችን አብስለን እንበላለን፡፡ ህብረት አለ፡፡ ከዛ በተረፈ ምጥ ቢመጣ ወደ ሕክምናው ቶሎ እንደር ሳለን፡፡

ዶ/ር ሪታ ሽፋ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር እንደሚሉት ...

..እነዚህ እናቶች ስለታመሙ አይደለም እናቶች ማቆያ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ የሚደረገው፡፡ እዚህ በቂ እረፍት አግኝተው የምጥ ጊዜያቸውን እንዲጠባበቁ ለማድረግ ነው፡፡ በስራ...በኑሮ መጎዳትን ሊቀንስላቸው ይችላል፡፡ ምናልባት በቀላሉ መውለድ የማይችሉ ቢሆን...ኦፕራሲዮን ቢያስፈልጋቸው ወይንም ልጁን ለማዋለድ የተለያዩ የህክምና አገልግሎትን የሚያስፈልጋቸው ቢሆን ሐኪም በቅርባቸው ስለሚገኝ ቀን ሆነ ሌሊት በማንኛውም ጊዜ በፍጥነት እርዳታ ይደረግላቸዋል፡፡በተለይም በመውለድ ጊዜ ልጅ የሞተባቸው ወገኖች ለእራሳ ቸውም ሆነ በአቅራቢያቸው እርጉዝ ሆነው ለሚያዩዋቸው ሁሉ ወደአጣጥ ሆስፒታል ሂዱ እያሉ ይመክራሉ፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት ብዙ እናቶችን እያዳንን ነው፡፡ ..ብለዋል፡፡

.. ...የመጣሁትበ አካባቢ ወደ 72 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ወረዳው ሙህራቢል ይባላል፡፡ በእርግዝናዬ ወቅት አንድ ወር ያህል ቆይቼ ወልጄ ሄጄ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕመም ሲያመኝ ተመልሼ መጥቼ እረፍት እንዳደርግ ከዚህ ተኝቻለሁ፡፡ ...እኔ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ያለብንን ችግር ተረድተው ኑሮአችንን አውቀው እንደዚህ እንደ እናት ቤት አሳርፈው ተንከባክበው በማዋለዳቸው በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በዛሬ ቀን በአግባቡ ወልዶ ...ልጅን አቅፎ መሄድ ቀላል አይደለም፡፡..

ሲ/ር ብዙነሽ እንደሚገልጹት ...

..በተለይም የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ባሉበት ቦታ ሁሉ አስቀድሞውንም የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ እናቶችን ስለሚመክሩና ስለሚከታተሉ በአሁኑ ወቅት የተጠቃሚዎች እናቶች ቁጥር ጨምሮአል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእርግዝና ክትትል ሳያደርጉ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ቀንሶአል፡፡ እንዲያውም አልፎ አልፎ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእናቶች ማቆያ የሚገለገሉት እናቶች በአመት ከሁለት ሺህ በላይ ናቸው፡፡ ..

ይቀጥላል

 

 

 

Read 3826 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:55