Print this page
Saturday, 15 September 2012 14:10

እንኩዋን ከዘመን ዘመን በሰላም አሸጋገራችሁ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

2005ዓ/ም የሰላም ... የጤና ... የእድገትና የብልጽግና ይሁንላችሁ፡፡

ዘመን ሲለወጥ ባለፈው ዘመን የነበረውን ማስታወስ እና ቀጣዩ ደግሞ ካለፈው የሚሻልበትን ማሰብ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በተለይም የዘመን መለወጫ በአልን በቤቱ ከቤተሰቡ ጋር ማሳለፍ እንደሚፈልግም እሙን ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም በስራእና ቤተሰባዊ ወይንም ግላዊ በሆኑ ምክንያቶች ከቤት ውጭ በአልን ማሳለፍ ያጋጥማል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ እትም የአንባቢዎችን እይታ ወደጋንዲ ሆስፒታል መለስ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ ማክሰኞ መስከረም 1/2005 ዓ/ም የጋንዲ ሆስፒታል ከዘወትር በተለየ ገጽታ ነበር የዋለው፡፡

ጋንዲ ሆስፒታል በመደበኛው የስራ ቀን በብዙ ሰው የተጨናነቀ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ...ለወሊድ የሚመጡ...ከታካሚዎች ወይንም ከወላዶች ጋር የሚመጡ ሰዎች... ለስራና ወላዶችን ለማድረስ እንዲሁም ከወለዱ በሁዋላ ለማውጣት በሚመጡ መኪኖች የተጨናነቀ ነው፡፡ መስከረም አንድ ቀን ግን ተረኛ ሐኪሞችና ለመውለድ የሚገቡ እንዲሁም በሆስፒታሉ ቀደም ብለው አልጋ የያዙ እናቶና ቤተሰቦቻቸው በስተቀር መደበኛው አገልግሎት ስለማይሰጥ ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በአል በኢትዮጵያ በየቤቱ አቅም በፈቀደ እየተከበረ ባለበት እለት ጋንዲ ወላዶችን መቀበል እና ማዋለድ እንዲሁም ወልደው ለተኙት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ከሆስፒታሉ ይጠበቅ ስለነበር ይኼው ነበር በመከናወን ላይ ያለው፡፡ የዘመን መለወጫን በአል ለማክበር ከቤተሰብ እርቀው በስራ ጉዳይ መስክ የነበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰባቸው ጋር የማይኖሩ ወይንም ቤት እንደመመስረት ብለው ከቤተሰባቸው የወጡ ...ነገር ግን በእንደዚህ ያለው የበአል ቀን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገው ከቤተሰባቸው ጋር በአልን ለመዋል የሚቀላቀሉ ሁሉ ቤት ያፈራውን ሰብሰብ ብለው በመቋደስ ላይ ቢሆኑም ለእኔማ ልጄን መገላገል ከበአል በላይ ይቆጠራል ... ዋናው ነገር ሁለት መሆን ነው ያሉ ወላዶችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ በጋንዲ ሆስፒታል ታድመዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በወላጆች ምርጫ የሚወሰን ሳይሆን በተፈጥሮ ሂደት ግዴታ ውስጥ የሚገቡበት መሆኑ አይካድም፡፡ ከወላዶች መካከል ያነጋገርናቸውን አስተያየት እናስነብባችሁዋለን፡፡

“እኔ የምኖረው በአዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢነው፡፡ ልጄን የወለድኩት በአመት በአል ዋዜማ ነበር፡፡ ከአሁን በፊት ልጅ አልነበረኝም ፡፡ የምኖረው ብቻዬን ነበር፡፡ አሁን ግን ሁለት ሆኛለሁ፡፡ ከባለቤ ጋር እንግዲህ ሶስት መሆናችን ነው...የተጋባን ጊዜ የነበረው የሽማግሌዎች ምርቃት ምንም አይረሳኝም፡፡ አሁን ሁለት ናችሁ፡፡ ለከርሞው ሶስት ያድርጋችሁ፡፡ ይሉ ነበር፡፡ ዘፈኑም ደግሞ እንዲህ ይል ነበር፡፡

እኔ ለሙሽሪት የምመኛላት ...ጠበብ ያለች ጎጆ ፍቅር የሞላት...

እኔ ለሙሽራው የምመኝለት ...ጠበብ ያለች ጎጆ ፍቅር የሞላት...

የዛሬ አመት... የማሙሽ እናት...

የዛሬ አመት... የሚሚዬ አባት...

ልክ ቤተሰባችን...ወዳጅ ዘመዶቻችን በተመኙልን መሰረት ፍቅርም ሳናጣ ይኼው ዘመኑ ሲጀመር የወንድ ልጅ እናትና አባት ለመሆን በቅተናል፡፡ ለእኛ እንቁጣጣሻችን ልጃችን ነው፡፡ በአሉ ይደርሳል፡፡ እኔ ከሆስፒታል ወጥቼ እቤ ስገባ ዘመን መለወጫ እንደ አዲስ ይከበራል፡፡”

--------------///------------------

በመቀጠል ያነጋገርናት እናት ልጁዋን አሻግራ በአልጋዋ ውስጥ እየተመለከተች እሱዋ ጋደም ብላለች፡፡

“ ...እኔ በዘመን መለወጫ እለት አዲስ ልጅ በመታቀፌ በጣም

ደስታ ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ የምወልድበት ቀን ደርሶ አይደለም

የወለድኩት፡፡ ነገር ግን ያለቀኑ ምጥ ስለመጣ ወደሆስፒታሉ መጥቼ

በኦፕራሲዮን ተገላግያለሁ፡፡ እኔ አሁን በአሉን የማስበው ልጄን በሰላም

መገላገሌን እንጂ እቤት መሆን ያለመሆኔ ...ዶሮ ወጥ መስራት አለመስራ

ስላልሆነ ምንም አይሰማኝም፡፡ በቃ ... እቤ እና ስለአለች እሱዋ ትሰራለች...

እዚህ ዘው ይመጣሉ ...አብረን እንበላለን...እንጠጣለን...በቃ ...ቤተሰቡ የሚደሰተው በዘመን መለወጥ ብቻ ሳይሆን በእኔም ልጅ መውለድ ጭምር ስለሆነ ሁለት ደስታ ነው በቤተሰባችን የተገኘው፡፡”

-----------///-------------

በሆስፒታሉ አልጋ ከያዙት ሴቶች መካከል አንዲት ሴት ተመለከትን፡፡ እርጉዝ ናት፡፡ ባልተቤቷም አብሮአት በሆስፒተሉ ከአጠገቡዋ ስለነበር ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡

“ ...እኔ ሆስፒታል የገባሁት እርግዝናው ትንሽ ችግር አለው ተብዬ ነው፡፡ በእርግጥ ዘጠኝ ወሬ ደርሶአል፡፡ ጊዜው የመውለጃ ጊዜዬ ነው፡፡ አሁን በዘመን መለወጫ በዚህ ሆስፒታል ብገኝም ገና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ትሄጃለሽ ስለተባልኩ እየተጠባበቅሁ ነው፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ሰአት እኔ ስለበአሉ ምንም እሳቤ የለኝም ፡፡ የማስበው በምን ሁኔታ ልጄን ልገላገል እንደምችል ብቻ ነው፡፡ አመት በአል ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ነው፡፡ አለበለዚያ ምንም ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ዘመኑ በመለወጡ እንደማንኛውም ሰው ደስ ይለኛል፡፡ ለአሁኑ ግን ...ሌላም የምጠብቀው ነገር ስላለ ሀሳብ ላይ ነኝ፡፡”

“እኔ አሁን ያነጋገርሻት ሴት ባለቤት ነኝ፡፡ በአርግጥ በአሁኑ ሰአት

እንደማንኛውም በአሉን እንደሚያከብር አባወራ ከቤ ሁኜ በግ ወይንም

ዶሮ ማረድ ሳይሆን የሚስን መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል በመጠባበቅ

ላይ ነኝ፡፡ ዘመኑ በመለወጡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን ይበልጡኑ ደስተኛ

የምሆነው ባለቤ በሰላም ብትገላገልና ልጄን ባቅፍ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ስለማምን

ይህ እድል እንደሚገጥመኝም አልጠራጠርም፡፡ ለዛሬው ግን ቤተሰባችን የሚሰጠንን

እዚሁ ከእሱዋ ጋር እቃመሳለሁ፡፡ እሱዋን ሆስፒታሉም ያስተናግዳታል፡፡ ከዚህ ውጭ

እኔም የትም ሳልሄድ አብሬአት በአሉን አሳልፋለሁ፡፡ ..

በመቀጠል ያመራነው በጋንዲ ሆስፒታል ወደምግብ ማብሰያው ነበር፡፡ የምግብ ማብሰያው ሰፋ ያለ እና በእለቱ ተረኛ የነበሩ አብሳዮች ከነኃላፊዎቻቸው ወዲያ ወዲህ የሚሉበት ነበር፡፡ መክተፊያዎቹ ሰፋ ሰፋ ያሉ ጠረጴዛዎች ሲሆኑ በስተዳር በኩል የቡና ስኒዎች ከነረከቦታቸው እንዲሁም የቡና ጀበናዋም ከቦታዋ ተቀምጣለች፡፡ ሰራተኞቹ ስራቸውን ሳያቋ ርጡ በስራ መካከል ቡናውን ፉት ይላሉ፡፡ ምግቡ ለታካሚዎቹ ተዘጋጅቶአል፡፡

.. እኔ የሻረግ ያለው እባላለሁ፡፡ በምግብ ቤቱ ኃላፊ ሆኜ እሰራለሁ፡፡ እንቁጣጣሽን በተመለከተ የምናዘጋጀው ሁለት አይነት የስጋ ወጥ በተሟላ መልኩ በሚጣፍጥ ሁኔታ ሲሆን እንደ እንቁላል፣ ወተት፣ ዳቦ የመሳሰሉትን እንጨምርላቸዋለን፡፡ ወጡም ቢሆን አልጫና ቀይ ወጥ ሆኖ በደንብ ተስማምቶቸው እንዲበሉ እና እዚህ በመሆናቸው ቤታቸው እንዳይናፍቃቸው ለማድረግ የሚሰራ ነው፡፡ ምግቡ ካልጣፈጠና ቅር የሚለው ነገር ካለም አስተያየት እንቀበላለን፡፡

------------////-----------------

“...እኔ አቦነሽ አለማየሁ እባላለሁ፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል የምግብ ቤቱ ዝግጅት ክፍል ሰራተኛና አንዳንዴም ኃላፊዋን ወክዬ የምሰራ ነኝ፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል ወልደውም ሆነ በተለያየ ሁኔታ ለተኙ እናቶች በምንም መንገድ ቅሬታ እንዳይሰማቸው...ቤታቸውንም እንዳያስቡ እንዲሁም በሆስፒታሉ የተገኙት ለበጎ ማለትም ልጅ ለመውለድ፣ ታክሞ ለመዳን፣ መሆኑን እያስረዳን ...በእኛ በኩል ግን የጣፈጠ ምግብ ሰርተን...እንኩዋን አደረሳችሁ እያልን ምግቡን እናቀርብላቸዋለን...እነርሱም በደስታ ይመገባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በበአል ቀን ከዚህ ተረኛ ሆነን ስራ ላይ የምንውል ሰዎች ቤታችንንም እንደአመሉ በማስተናገድ እና ለስራ ቅድሚያ በመስጠት ከቤተሰባችን ጋር ተግባብተን ኃላፊነታችንን በተገቢው እንወጣለን፡፡ “

-------------////-------------

ከላይ ያነበባችሁዋቸው ገጠመኞች ከብዙ በጥቂቱ በጋንዲ ሆስፒታል መስከረም 1/2005 የሰበሰብናቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ስራ መሳንት ትብብር ላደረጉልን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

ልጅ በመውለድ ወይንም በህክምና ምክንያት በሆስፒታል ሆነው የዘመን መለወጫ በአልን ላሳለፉም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ 2005/ የሰላም ፣የጤና ፣የእድገትና የብልጽግና እንዲሆን የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ምኞቱን ይገልጻል፡፡

 

 

Read 3219 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 14:42