Saturday, 29 September 2012 09:45

...ልክ... የደመራራ... እለት...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ይህንን ታሪክ ከባለጉዳይዋ ጋር ተወያይታ ገጠመኙን ለንባብ ያዘጋጀችውን አዲስ አለም ብርሀኔን በቅድሚያ በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ፡፡ ደመራራ ባለፈ በአራራተኛ ቀኑ ታሪኩን እነሆ...

አዲስ፡  ማን ልበል?

ከበቡሽ፡ ስሜ ከበቡሽ ይልማ ይባላል፡፡ተወልጄ ያደግሁት ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን አካባቢ

ሲሆን በተለይም ያደግሁት ጭድ ተራ እየተባለ ይጠራ ከነበረው አካባቢ ነው፡፡

አዲስ፡  እድሜሽ ምን ያህል ነው?

ከበቡሽ፡ እድሜዬ ወደ 49/አርባ ዘጠኝ አመት ገደማ ይሆናል።

አዲስ፡ እድሜሽን የጠየቅሁሽ የዚያን ጊዜውን የጭድ ተራ እንቅስቃሴ ልጠይቅሽ ፈልጌ ነው፡፡

ከበቡሽ፡ እኔ ልጅ ሆኜ ጭድ ተራ ጋሪ እንደልብ የሚነዳበት...አህዮች ጭድ ጭነው

የሚቆሙበትና የሚሸጡበት...ሴቶች ብቅል በብዛት እየነከሩ አስፋልት ላይ እያደረቁ የሚያከፋፍሉበት...በርበሬም እንደዛሬው ሳይሆን በቃጫ ታሽጎና በከባድ ሚና ተጭኖ የሚሽጥበት ...ብቻ ሞቅ ያለ አካባቢ ነበር፡፡

አዲስ፡  ጭድ ተራ ዛሬም በጣም ሞቅ ያለና የሰው ነብስ ሲቀር ሁሉም ነገር የሚገኝበት ወይንም

የሚሸጥበት  ነው ይባላል፡፡ ይህ እውነት ነው?

ከበቡሽ፡ ትክክል ነው፡፡ እኔ አሁንም እናን ለመጠየቅ ስሄድ የምመለከተው ነገር ነው፡፡

አዲስ፡  እሺ ከበበቡሽ.. ልክ የደመራ እለት ምን ገጠመሽ? ደመራውስ የመቼው ነው?

ከበቡሽ፡ገጠመኙ የተፈጸመው የዛሬ ስድስት አመት በ1999ዓ/ም ሲሆን ቀኑን ግን በውል

አላስታውሰውም፡፡ በዚያን ጊዜው ደመራ ቀን በሚያስገርም ሁኔታ ከአስራ አምስት አመት በላይ አብሮኝ የኖረ...የሶስት ልጆቼ አባት ሻንጣውን እንኩዋን ሳይይዝ ባዶ ቤት ጥሎኝ ወደእናቱ ቤት የኮበለለበት እለት ነው፡፡

አዲስ፡ ምነው? ምን ተፈጠረ?

ከበቡሽ፡ ነገሩ ...በእርግጥ ቀደም ብሎ ከተከሰተ ነገር ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡

.. ባለቤ በአንድ የእርዳታ ሰጪ ድርጅት ውስጥ በከባድ መኪና ሾፌርነት የሚሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ በሄደበት አካባቢ ከሶስት ወር ላላነሰ ጊዜ የሚቆይ እና ወደ እቤትም ከመጣ ከአንድ ሳምንት በላይ የማናገኘው ሰው ነው፡፡ ስራው በጣም ያንገላታዋል ከሚል በጣም ነበር የማዝንለት፡፡ በተለይም አዲስ አበባ መጥቶ ምንም ሳንጠግበው ተመልሶ ስለሚሄድ በጣም ነው እበሳጭ የነበረው፡፡ ልጆቹ እንዲያውም ...ለምን ይህንን ስራ አይተወውም...የምንበላው የምንጠጣው ተቀንሶ እሱ አብሮን ቢኖር ይሻለናል የሚል ሀሳብ ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር፡፡

አዲስ፡ ችግሩ የተከሰተው ከስራው ባህርይ ጋር በተያየዘ ነውን?

ከበቡሽ፡በእርግጥ በቀጥታ ችግር የፈጠረው ስራው ነው ባልልም በስራው ምክንያት ግን

የእራሱን ባህርይ መግታት አቅቶት የተከሰተ ችግር ነው እላለሁ፡፡

አዲስ፡  ከስራው ጋር በተያያዘ ...ማለትም በስራው ምክንያት ከመስክ ብዙ መቆየቱ...በቤቱ ብዙ

አለመገኘቱ ...ምንን አስከተለ?

ከበቡሽ፡ ...አንድ ቀን ምን ተፈጠረ መሰለሽ?

አዲስ፡ እሺ

ከበቡሽ፡ ከመንገድ መጥቶ ሻንጣውን ከፍቼ ልብሱን ለማጽዳት በወሰድኩት እርምጃ ...አንድ

የማላውቀው ጋቢ አገኘሁ፡፡

አዲስ፡ የተለበሰ ነው? ወይንስ?

ከበቡሽ፡ የተለበሰ ነው፡፡ ሽቶ ሽቶ ይሸታል፡፡ የጸጉር ቅባትም ይሸታል፡፡ ደግሞ ዝም ብሎ

ከገበያ የተሸመተ ረጋ ሰራሽ የሚሉት አይነት አይደለም፡፡ ደምበኛ ሸማኔ የሰራው ...ጥሩ አርብ እና ቁመት ያለው...ቆንጆ ጋቢ ነው፡፡ እናም የማን ጋቢ እንደሆነ ማወቅ ስለፈለግሁ ልጠይቀው አሰብኩ፡፡ ነገር ግን መንገዱን በሰላም ይሂድ ብዬ ተውኩት፡፡ ጋቢውን ግን ከሻንጣው አውጥቼ በፌስታል ቋጥሬ አርቄ አስቀመጥኩት፡፡

አዲስ፡ እሱ ግን ጋቢውን አምጪ አላለም?

ከበቡሽ፡ ጋቢው ከእሱ ልብስ ጋር መጫኑን እሱም አላወቀውም፡፡ ከሚሄድበት ሲደርስ ግን

በስህተት መጫኑ ይነገረዋል፡፡ ስልክ ደውሎ ጠየቀኝ፡፡ የእኔ ሳይሆን የሌላ ሹፌር ጋቢ ነው አለኝ፡፡ እኔም ጥሩ ነው ስትመጣ ትወስደዋለህ ብዬ...ነገር ግን ቅይም አልኩኝ፡፡

አዲስ፡  ለምን?

ከበቡሽ፡በቃ መቼም በሚወዱት ሰው መቅናት የተገባ ነውና ቀናሁ፡፡ በሁለተኛው ዙር ሲመጣ

እሱም እረስቶት ሄደ ፡፡ እኔም አላስታወስኩትም፡፡

አዲስ፡  ቀጣዩ ነገር ምን ነበር?

ከበቡሽ፡ ቀጣዩ ነገር በጣም ያሳዝናል፡፡ በዘጠንኛ ወሩ ማለት ነው...ከመስሪያ ቤቱ ስልክ

ተደውሎ ቦሌ ሄጄ እንድቀበለው ተነገረኝ፡፡ ለምንድነው ስል...ታምሞአል የሚል ሆነ መልሱ..እኔም በጣም ደንግጬ ከመስሪያ ቤ አስፈቅጄ ልቀበለው ስሄድ ...ያ ሸበላ ባለቤ የመጣልኝ እጥፍጥፍ ብሎ በሚገፋ ወንበር ተደጋግፎ ነበር፡፡

አዲስ፡ ምንድነበር ሕመሙ?

ከበቡሽ፡ ለጊዜው ምንም አልታወቀም፡፡ ባለበት ሁኔታ ከቤቱ አድርሰውልኝ ከሁለት ወር ላላነሰ

ጊዜ አስታመምኩ፡፡ የትኛውም ሐኪም ቤት ብንሄድ በሽታው ይሄ ነው ሊሉን አልቻሉም፡፡ እኔም ግራ ገባኝ፡፡ በየመሐሉ ስልክ ይደወላል፡፡ እሱም ግራ ያጋባኛል፡፡ ጉዋደኞቹ መልእክት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከማን ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ብቻ ኑሮአችን በጣም እየተበጠበጠ መጣ፡፡ በሁዋላማ...እኔ የማውቀው ሐኪም የሚሰራበት ክሊኒክ ሄጄ ሁኔታውን አማከርኩ፡፡ ሐኪሙም እራሳችሁን ተመርምራችሁ አውቃችሁዋልን? የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔም እስከአሁን ምርመራ እንዳላደረግንና አሁን ባለው ሁኔታ ግን አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ ብዬው ለባለቤ ልነግረው ወደቤ ሄድኩ፡፡

አዲስ፡  ስትነግሪው ተስማማ?

ከበቡሽ፡አልተስማማም፡፡ አንቺ ለእራስሽ ከፈለግሽ ወይንም እራስሽን የምትጠረጥሪ ከሆነ

መመርመር ትችያለሽ ...በእኔ በኩል ግን ምንም ችግር የለም አለኝ፡፡ እኔም ይህንኑ መልሱን ተመልሼ ለሐኪሙ ነገርኩኝ፡፡ ሐኪሙም አንቺ የራስሽንም ብቻ ቢሆን አሰሪና ከዛ በሁዋላ እንነጋገራለን አለኝ፡፡ ተስማማሁ፡፡ ውጤ ከቫይረሱ ነጻ የሚል ሆነ፡፡ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ውጤን ይዤ ወደሐኪሜ ጋ ስሄድ ...ለማንኛውም እሱን በማስታመሙ ረገድ ልወስደው የሚገባኝን እርምጃ ነገረኝ፡፡

አዲስ፡  ባለቤትሽ አልመረመርም እንዳለ ቀረ?

ከበቡሽ፡እኔማ... ምን ይሻላል ብዬ ለጉዋደኞቹ ሳማክር..እኛም እንፈልግሽ ነበር...እሱ እኮ

ተመርምሮአል፡፡ ውጤቱንም አውቆአል፡፡ከቫይረሱ ጋር በመኖር ላይ ነው፡፡ አሉኝ፡፡ እጅግ በጣም አዘንኩ፡፡ በሕይወ ከደረሰብኝ ሁሉ የከፋ ሐዘን ነበር የገጠመኝ፡፡ ከምንም በላይ ያዘንኩት...ውጤቱን ካወቀ በሁዋላ ለቤተሰቡ ጥንቃቄ ለማድረግ ጥረት አለማድረጉ ነበር፡፡ እንደነስር...የአካል ቁስለት...የመሳሰሉትን ነገሮች ስንጠርግለት...በጨርቅ ስናስር በመሳሰለው እኔም ሆንኩ ልጆቹ ምንም ጥንቃቄ አናደርግም ነበር፡፡ ሁኔታውን ሳስበው በጣም አዘንኩ፡፡

አዲስ፡  የጋቢውስ ነገር ምን ሆነ ?

ከበቡሽ፡ ጋቢው የማን እንደሆነ ጠይቄማ...........ዝምታ... የጋቢው ባለቤት ሞታለች......እሱም

እንደዚህ የታመመው በእሱዋ መሞት ደንግጦ ነው...አሉኝ ከዚያማ ሁኔታውን በሙሉ ቤተሰቡን ቁጭ አድርጌ ነገርኩት፡፡ ሁኔታውን ባስረዳሁት በሳምንቱ ልክ የደመራ እለት ጠዋት እንደወጣ በዚያው ቀረ፡፡ ልጆቹ ስልክ ደውለው ሲጠይቁት...እኔማ ከዚህ በሁዋላ ወደእናንተ አልመጣም፡፡ በቃ፡፡ አላቸው፡፡

አዲስ፡  አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛላችሁ?

ከበቡሽ፡ እሱ ለጤንነቱ እጅግ በጣም ደህና ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን ተቀብለን እየተረዳዳን

መኖር እንችላለን የሚለውን የእኔን ሀሳብ አልቀበል ብሎ ነው ተለያይተን የምንኖረው፡፡ ልጆቹ ጠዋት ማታ ስለማያገኙት በጣም ያዝናሉ፡፡ እኛም ለየብቻ ኑሮአችንን መግፋት አልቻልንም፡፡ ባጠቃላይም ሕይወታቸው በእንደዚህ ያለ ሁኔታ የሚረበሽ ሰዎች ነገሮችን ከመወሰናቸው በፊት የሚሻለውን በእርጋታ ማሰብና መወሰን ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ፡፡

አዲስ፡  አመሰግናለሁ፡፡

 

 

Read 2366 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:53