Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 October 2011 09:35

ከታሪክ መማር ብልህነት ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ930 ዓ.ዓ (ቅድመ ልደት ክርስቶስ) የአንዲት የቀጣናዋ ልዕለ - ሃያል የነበረች ሀገር ሕዝቦች፤ ለአርባ አመታት (ከ970 ዓ.ዓ - 930 ዓ.ዓ) የምድሪቱ ንጉስ የነበረውንና በሞት የተለየውን አባቱን ተክቶ የንግስና ዘውዱን ሊደፋ ተገቢ ሆኖ የተገኘው ልጁ የአባቱ አልጋ ወራሽ ሆኖ ወደ ዙፋኑ ለመምጣት በተዘጋጀበት ወቅት፣ ለበዓለ ሲመቱ በመረጧት ሴኬም በተባለች ከተማ በነቂስ ወጥተው ተሰበሰቡ፡፡

እነኚህ የዚህን ስርወ መንግስት ሶስተኛ ንጉስ ለማንገስ በዓለ ሲመቱ በሚከወንባት ከተማ የተሰበሰቡት ሕዝቦች በዓሉን ከመታደምም ባሻገር አባቱን ሊተካ ለተዘጋጀው ንጉስ ያዘጋጁትን ጥያቄ ይዘውም ነበር በታላቁ በዓል ስፍራ የተሰበሰቡት፡፡ እነኚህ ሕዝቦች እስራኤላውያን ሲሆኑ ንግስናውን ሊረከብና በአደባባይ ዘውድ በመድፋት የስርወ መንግስቱ ሶስተኛ ንጉስ ሊሆን የተዘጋጀውም አባቱን ጠቢቡን ሰሎሞንን እንዲተካ የተመረጠው ወጣቱ ሮብዓም ነበር፡፡
በዚህ በዓለ ሲመት ላይ ከሀገሬው ነዋሪ በተጨማሪም ሮብዓም የተካው አባቱ ሰሎሞን ንጉስ በነበረበት ዘመን በተፈጠረ ፖለቲካዊ አለመግባባት የተነሳ ህይወቱን ለማትረፍ ሀገሩን ለቅቆ በስደት ወደ ግብጽ ኮብልሎ የነበረ ኢዮርብዓም የተባለ ሰው ተገኝቶም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር የነገስታቱን ታሪክ ያጠናቀረው ዘጋቢ እንዲህ ሲል ዘግቦታል፡፡
“እስራኤል ሁሉ ያነግሱት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፡፡ እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ እርሱም ከንጉሱ ከሰሎሞን ፊት ኮብልሎ በግብጽ ተቀምጦ ነበርና በግብጽም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና...”
በዓለ ሲመቱ ተከውኖ ሲያበቃም ከጊዜው ንጉስ ከሬብዓም አባት ጋር በነበረው የፖለቲካ አለመግባባት በስደት በግብጽ በከረመው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም የሚመራው የእስራኤል ጉባኤ ወደ አዲሱ ንጉስ በመቅረብ “የእኛ ነው” ላሉት ንጉሳቸው እንዲህ ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
“ኢዮርብዓብምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት”
(1ኛ ነገ 12፤3-4)፡፡      
የአዲሱ ንጉስም ምላሽ ህዝቡን ያሳመነና ተገቢ ነበር፡፡ ንጉስ ሮብዓም ሊያነግሰው በነቂስ ወጥቶ በአመጽ ሳይሆን በተገቢው ሰላማዊ ሁኔታ ጥያቄውን ላቀረበው ህዝብ
“ሂዱ በሶስተኛውም ቀን ተመለሱ” የሚል የጨዋ ምላሽ ሲሰጥ ከንጉሱ ምላሽ በኋላ የህዝቡ እርምጃ ምን እንደነበር ዘጋቢው ሲዘግብ፤  
“ህዝቡም ሔዱ” ነበር ያለው፡፡ (1ኛ ነገ.12፣5)
አዲሱ ንጉስ የሶስት ቀን የጊዜ ገደብ ያደረገው፣ ተገቢ የሆነውን ምክር መጠየቅ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ሁለት የተለያዩ የአስተሳሰብ ጽንፎች ካሏቸው ቡድኖች ጋር ተገናኝቷል፡፡ ለንጉሱ ምክር የመስጠት የመጀመሪያ ዕድል የተሰጣቸው፣ በንጉሱ አባት በሰሎሞን ዘመን አባቱን በአማካሪነት ያገለግሉ የነበሩ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ንጉሱ ሮብዓም እነኚህን ሽማግሌዎች እንዲህ ሲል ጠየቀ፡፡
“. . . ለዚህ ህዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድነው”
(1ኛ ነገ 12፣ 6)፡፡   
ሽማግሌዎቹም (በስብሰባው ላይ ባልገኝም) እንዲህ ሲሉ የመለሱ ይመስለኛል፡፡
“ንጉስ ሆይ እነኚህ ሕዝቦች ለልማታዊው መንግስታችን ራዕይና የአራት አስርት አመታት ስትራቴጂ የጀርባ አጥንት የነበሩ፣ ልማታዊው መንግስታችን ይህቺ ምድራችን በእስካሁን ዘመኗ ያላየቻቸውን ልማታዊ ስራዎችን ሲያቅድና ለትግበራውም ሲቀሳቀስ ሁለ ነገራቸውን ሳይሰስቱ ያገለገሉ፤ አባትህ ለልማቱ ራዕይና ስትራቴጂ ግብ መምታት ያጠበቀውን የግብር እና ቀረጥ ህግ ያለአንዳች ተቃውሞ የተቀበሉ፣ የልማታዊ መንግስታችን ልማታዊ ትልም ከግብ ደርሶ ምድራችንም በታሪኳ ታላቅ ስራዎችን  እንድትከውን ያለአንዳች ማወላወል ከጐኑ የቆሙ ህዝቦች ናቸውና ትልቅ መስዋዕትነት ከከፈሉባቸው የልማት አርበኝነት ዘመናት በኋላ የተጣለባቸው ግብርና ቀረጥ ሊለዝብላቸውና እነርሱም በተራቸው ሊካሱ ይገባቸዋል፡፡ እነርሱ ለመንግስታችን ያሳዩትን ወገናዊነት ከግንዛቤ በማስገባት መንግስታቸውም አሁን ጥያቄያቸውን በይሁንታ በመመለስ ወገናዊነቱን ሊያሳያቸው ይገባል፡፡ ይኼንን ብታደርግና ጥያቄያቸውን ይሁን ብትላቸው በሌላም ጊዜ መንግስታቸው ለሚያቀርብላቸው ልማታዊ ጥያቄ ያለአንዳች ማንገራገር በሆታ በመነሳት ከጐኑ ይቆማሉ”
የሚል ትርጉም የሚሰጥ ምክር ለአዲሱ የልማታዊው መንግስት ተረኛ አውራ ለገሱ፡፡  
“ለዚህ ሕዝብ ባርያ ብትሆን ብትገዛላቸውም (ጥያቄያቸውን በይሁንታ ብትቀበላቸውና የኑሮ ጫናውን ተረድተህ አባትህ ለልማቱ ስራ የጫነውን ግብር ብታለዝብላቸው) መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ይሰሙሃል፤ ሃሳብህን ለመተግበር ሙሉ ፈቃደኛ ይሆኑልሃል፤ ያከብሩሃል) ብለው ተናገሩት” (1ኛ ነገ 12፤ 7)፡፡  
ቀጣዩ የንጉሱ “ምክር” የመስጠት ዕድል የተሰጣቸው “ከንጉሱ ጋር ያደጉና በፊቱ ይቆሙ የነበሩ ብላቴኖች” ሲል ዘጋቢው የገለፃቸው ፍፁማዊ ቆራጥነትና ቁጡነት የተላበሱ ወጣቶች እንዲህ አሉ፤  
“ንጉስ ሆይ እነኚህ ሰዎች የሚጠይቁህን እሺ ካልክና ለሃሳባቸው ይሁንታን ከሰጠህ ተልፈሰፈስክ ማለት ነው፡፡ መንግስት ደግሞ መልፈስፈስ የለበትም፤ አያምርበትምም፡፡ መልፈስፈስ የጀመረ ወይም የመልፈስፈስ ምልክት የታየበትና የሕዝቡን ጥያቄ ሁሉ “እህ” ብሎ ማድመጥ የጀመረ መንግስት የሕዝቡ ማላገጫና በሕዝቡ ጥያቄ የሚመራ ለንቋሳ ነው የሚሆነው፡፡ ንጉስ ሆይ፤ እስኪ ዙሪያህን ተመልከት፤ የትኛው የአካባቢያችን (በዘመናችን አጠራር አህጉራችን) ንጉስ ነው ለህዝቡ ጥያቄ አዎንታን የሚሰጥ? ኧረ እንዲያውስ ለሕዝቡ የጥያቄ ዕድል የሚሰጥ ንጉስ በአካባቢያችን (በአህጉራችን) አለን? የለም! ንጉስ ሆይ፡፡ የአካባቢያችን (የአህጉራችን) ነገስታት ይሄንን የሕዝብህን ጥያቄ “ይሁን” ብለህ የማስተናግድህን ወሬ ሲያደምጡ መንግስትህን መሳለቂያ ከማድረጋቸውም ባሻገር ንቀታቸውን በአካባቢው ላይ ያለህን የበላይነትና ተሰሚነት በመገዳደር ሊያሳዩህ መንቀሳቀሳቸውም አይቀሬ ነው፡፡ ይልቅስ እነኚህ ለመንግስት ተገቢውን ክብር በመንፈግ የድፍረት ጥያቄያቸውን ያቀረቡትን ወሮበሎች በቆራጥነት ተጋፍጠህ፣ ከአባትህ የላቀ የአስገባሪነት ቆራጥነት ያለህ ቆፍጣና መሪ መሆንህን ልታሳውቃቸው ነው የሚገባህ፡፡ በዛ ላይ የሚሉህን “እሺ” ካልክ የንጉስ ገቢ እንደሚዛባና የአለቆች የድሎት ህይወት እንደሚስተጓጐል ልትገነዘብ ይገባሃል፡፡ ንጉስና መንግስት የሚያምርባቸው ቆራጥና ቆፍጣና ሲሆኑ ብቻ ነው” ካሉት በኋላ፣ በወጣትነት ትኩስ ስሜት እንዲህ ሲሉ ጨመሩበት፡፡  
“አባትህ ቀንበር አክብዶብናል አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፡፡ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው” ብለው ተናገሩት (1ኛ ነገ 12፣ 10-11)፡፡  
እስኪ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲፈጠርልን ይሄን “ግብርና ቀረጥ በዛብን፣ ህይወትም አስቸጋሪና አዳጋች ሆነብን፤ ስለዚህም ግብርና ቀረጡን ለዘብ አድርግልን” የሚል ጥያቄ ከተመሪው ሕዝብ የቀረበለትን መንግስትን አመጣጥ መለስ ብለን በመጠኑ እንቃኝ፡፡
በ1050 ዓ.ዓ (ቅ.ል.ክ) ላይ እስራኤል የምትባለውን ፌደራላዊ አመሠራረት የተከተለች የምትመስልን ሀገር የመሰረቱትን አስራ ሁለት ነገዶች የሚወክሉ ሽማግሌዎች በጊዜው ይመሩበት የነበረው “እግዚአብሔራዊ ንግስና” ስርዓት አብቅቶ እንደ ጐረቤቶቻቸው “ሰዋዊ የንግስና” ስርዓት ይተካላቸው ዘንድ በጊዜው በእግዚአብሔራዊው የንግስና ስርዓት ምርጫ ባለተራ ሆኖ በዚህ ሕዝብ ላይ ይፈርድ የነበረው ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል ወደሚገኝበት አርማቴም ወደተባለ ስፍራ ተሰበሰቡ፡፡ እንደ ወትሮውም ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡም እንዲህ አሉ፤  
“የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና እነሆ አንተ ሸምግለሃል ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም አሁን እንደ አህዛብ ሁሉ የሚፈርድልንን ንጉስ አድርግልን አሉት”
(1ኛ ሳሙ 8፣ 4-5)፡፡
ይሄ በሳሙኤል ዘንድ ያልተጠበቀ የህዘቡ የአስተዳደር ስርዓት ለውጥ ጥያቄ ታላቁን ነቢይ በጣም ያስከፋው እንደነበር መጽሐፉ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፤  
“የሚፈርድልንም ንጉስ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው”
(1ኛ ሳሙ 8፣6)፡፡
በሕዝቡ ሽማግሌዎች ያልተጠበቀ ጥያቄ የተከፋው ነቢዩ ሳሙኤል፤ ያዘነ ስሜቱን እንደያዘ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዲፈርድና እንዲሰለጥን ወደ መረጠውና ወደ ወከለው በጊዜው ሕዝቡ የሚተዳደርበት የእግዚአብሔራዊ ንግስና ስርዓት ዋና ንጉስ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ፀለየ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናገረው፡፡
“እግዚአብሔርም ሳሙኤል አለው በእነርሱ ላይ እንዳልነግስ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ”
(1ኛ ሳሙ 8፣ 7)፡፡  
ከዚህ በኋላ ሳሙኤል የአስተዳደር ስርዓት ለውጡን የጠየቁትን ሽማግሌዎች ሃሳብ ለመተግበር ተንቀሳቅሶ ከአስራ ሁለቱ ነገዶች አንዱ ከሆነው ከብንያም ነገድ የተገኘውንና “ሃያል ሰው” ተብሎ ከተገለፀው ቂስ ከተባለ ሰው ቤት ልጁን ሳኦልን በመውሰድ እንደ ሕዝቡ ሽማግሌዎች ምኞት በ1050 ዓ.ዓ (ቅ.ል.ክ) ላይ በእስራኤል ታሪክ የመጀመሪያው የሰዋዊ ንግስና ስርዓት ንጉስ አድርጐ ቀባው፡፡  
በንግስና ላለመቀባት እስከ መሸሸግ የደረሰውና የሰዋዊው ንግስና ስርዓት የመጀመሪያው ንጉስ ሆኖ ከተቀባ በኋላ ግን አምላኩንም ሆነ የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ከመዳፈር አልተቆጠበም፤ ሳኦል፤ በንግስና በቆየባቸው አርባ አመታት ውስጥ ይዝራኤላዊው ኤታን የተባለ አንድ ሰው፤  
“ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት...ከምድር ነገስታት ከፍ ይላል...ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ” (መዝ 88 (89) 20፣ 27፣ 29)  
ሲል በትምህርታዊ ዝማሬው የተቀኘለት፤ ዳዊት ወደ እስራኤላውያኑ ልብና አንደበት ቀረበ፡፡ እስራኤላውያኑም ብላቴናውን በውዳሴ ቃል
“ዳዊት እልፍ ገዳይ” (1ኛ ሳሙ 18፣7) በማለትና ለብላቴናው ታላቅነትን በማላበስ የንጉስን ልብ በጥርጣሬ እሳት አቃጠሏት፡፡ “መፈንቅልን” የፈራው ንጉስም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተለይቶ ያልተጠቀሰ “ሽብር” ስለከፈተበት ብላቴናው በተራሮች ከተከታዮቹ ጋር መሸገ፡፡ በግምት ከ25-30 ለሚጠጉ አመታትም “ቤቴ” ባለው ዱር እየተዘዋወረ በስተመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ፤   
“በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ብዙ ዘመን ጦርነት ሆነ፤ የዳዊት ቤት እየበረታ የሳኦል (ቀለሙ ያልተገለፀ ሽብር ከፋቹ) ቤት እየደከመ የሚሄድ ሆነ” (2ኛ ሳሙ 3፣1)  
በማለት እንደገለፀው ከ1050 ዓ.ዓ እስከ 1010 ዓ.ዓ ለአርባ አመታት የዘለቀውና ሕዝብን ለማገልገል በንግስና ዙፋን ላይ ተቀምጦ ዘውድ ቢደፋም ሕዝቡ በገዛ አንደበታቸው
“የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን (ዳዊት ተቆጣጥሯት ወደነበረች ሃገር) ወጥተው እነሆ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የስጋህም ቁራጭ ነን፡፡ አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉስ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ”  
2ኛ ሳሙ 5፣ 1-2
ሲሉ ለአርባ አመታት የገዛቸውና የነገሰባቸው ነገደ ብንያማዊው ሳኦል የንግስና ዘውዱን ጭኖ ሳለ እንኳን ከራሱ ቤት መሙላትና ከግብር አለመጓደል በስተቀር ለሕዝቡ ሰላምም ሆነ ለሀገሪቱ ድንበር ሉዓላዊነት ግድ የለሽ የነበረ ሲሆን ለሕዝቡ የመቆርቆር ስሜት ይታይበት የነበረው ቀለሙ ያልተገለፀውን ሽብር ሸሽቶ ዱር ቤቴ ያለውና አሁን ላይ በሳኦል ቤት ላይ ድልን እየተቀዳጀ ኬብሮን የተባለችን ከተማ ለመቆጣጠር የበቃው ዳዊት መሆኑን ገልፀው ነበር፡፡  
ይህ ቀለም የለሹን ሽብር ሸሽቶ ዱር ቤት ብሎ የነበረ ከይሁዳ ነገድ የተገኘው ሰውም አምባገነኑንና ራሱን ለማስደሰትና ለማገልገል ብቻ የሚተጋውን ነገደ ብንያማዊ የአርባ አመት ዕድሜ ጨቅላ ስርወ መንግስት በመገርሰስ፣ በአዲስ ነገድ (በይሁዳ) ላይ የቆመ አዲስ ስርወ መንግስት መስርቶ የንግስና ዘውዱን ደፋ፡፡ ራሱ መስራቹም ከ1010 ዓ.ም እስከ 970 ዓ.ዓ ድረስ ለአርባ አመታት በንግስና ያቺን ምድር ሲመራ ቆየ፡፡ በንግስናው አመታትም ይሄ ንጉስ የተለያዩ ታላላቅ ሀገራዊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
ከዚህ በኋላ ይሔ ጦረኛና ነፃ አውጪ ከሳኦል ቀለም የለሽ ሽብር ሸሽቶ በዱር በገደሉ ሲንከራተት የቆየና በኋላም ድል ነስቶ የንግስናውን ዘውድ በመድፋት፣ የብንያምን ነገድ የበላይነት በማንኮታኮት የአዲስ ነገድ (የይሁዳ) ስርወ መንግስትን የዘረጋ ሀገሩን በዙሪያዋ ባሉ ነገስታት ዘንድ የምትከበርና የምትፈራ ያደረገ ሃያል ንጉስ፤ ፊቱን ወደ ልማታዊ አስተሳሰቦች በመመለስ ስለ ግንባታዎች ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ይህ ሀሳቡ ግን ከአምላኩ አዎንታዊ ምላሽን ሳያገኝለት ቀረና አምላኩ እግዚአብሔር ልማታዊ ግንባታዎች (መሠረተ ልማቶች) በልጁ ዘመን እንደሚከናወኑ ገለፀለት፡፡ ይኼ ጦረኛ ንጉስም ወዲያውኑ ሙሉ ትኩረቱን ልማቱን ለማፋጠን የሚረዱ ግብዓቶችን ለልጁ በማዘጋጀት ላይ በማድረግ፣ ለመሰረት ልማት ግንባታዎቹ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ማሰናዳቱን ጀመረ፡፡ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ምዕራፍ 28 ሙሉ ምንባብ የሚያስረዳን ይኼንን እውነታ ነው፡፡
ከዚህ የልማታዊው ስርወ መንግስት መስራችና አባት ህልፈተ ህይወት በኋላ ስፍራውን የወረሰው ልጁም አለምን ጉድ ያሰኙ ግንባታዎችን በመገንባት የስርወ መንግስቱን ልማታዊነት በግልጽ አሳየ፡፡ ስራዎቹም በግልጽ የሚታዩ ነበሩና የይሁዳ ነገድ መራሹን ስርወ መንግስት ልማታዊነት ለመካድ የሚሞክር ሰውም አልነበረም፡፡ አባቱን ተክቶ ልማታዊውን ስርወ መንግስት በመምራት አስገራሚ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን የሰራው ልጅ ሰሎሞንም በስራው ጊዜያት የሕዝቡን ድጋፍና “ሆ” ብሎ በአንድ ልብ የመቆም ቆራጥነት በሚገባ አግኝቶ ነበር፡፡ ሕዝቡ የዚህን መንግስት ልማታዊ አስተሳሰቦች ለመደገፍ ያለውን ሁሉ ከመስጠትም ባሻገር ኑሮውን አስጨናቂ ያደረጉበትን ከባባድ የግብርና ቀረጥ ድንጋጌዎችን ሁሉ “ልማቱ ለራሴ” በሚል አስተሳሰብ ተቋቁሞ “ይሁኑ” ብሎም ነበር፡፡ ሕዝቡን ለአንድ የልማት ራዕይ አስተባብሮ ያስነሳውና ያለውን ሁሉ ሳይሰስት እንዲሰጥ ያደረገው ንጉስ ከልማታዊ ግንባታዎቹ መጠናቀቅ በኋላ ለልማታዊ ግንባታዎቹ መገንባት አላማ ተጥለው የነበሩትን አስጨናቂ የግብርና ቀረጥ ድንጋጌዎች ማለዘብና ለልማቱ ሲባል እንዲጨነቅ የተደረገው ሕዝብ ትንሽ ተንፈስ እንዲል ማድረግ ሲገባው በቸልተኝነት፤ ስግብግብነት፤ መዘናጋት ወይም ሌላ ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቶ ከልማታዊ ግንባታዎቹ መጠናቀቅ ጥቂት አመታት በኋላ እርሱም አለፈ፡፡ በስፍራው ተተክቶ ዘውድ የሚደፋው ሮብዓም የተባለ ልጁ በዓለ ሲመቱን ሲከውን ግን የተቸገረው የተመሳቀለ ኑሮውን የሚያይለት ያጣው ምናልባትም “አገርህ በአንድ፤ በሁለት ከዘለለም በሶስት ዲጂት የሚለካ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች” እየተባለ የሚነገረው፤ ሕዝብ፤ “አልቻልኩምና ለልማታዊ ግንባታዎቹ ሲባል የተጣለብኝ ግብርና ቀረጥ ይለዝብልኝ” የሚል ጥያቄውን ይዞ ብቅ አለ፡፡
ይህ “ግብርና ቀረጥ ይለዝብልኝ” የሚል ጥያቄውን ይዞ ወደ ልማታዊው ከቀለም አልባ ሽብር የተረፈው ነገደ ይሁዳዊ እረኛ፣ ወደመሰረተው ስርወ መንግስት ተረኛ ንጉስ የመጣ ሕዝብ እንደ የኔዋ ሀገር በገዛ ምድሩ ወደ ኬክ ቤቶች ጐራ ብሎ ጣፋጭ ኬኮችን በመመገቡ ብቻ ተመግቦ እንደጨረሰ በሚቀርብለት የሂሳብ መጠየቂያ ቢል ላይ “ቫት” በሚለው የገቢ ርዕስ ትይዩ የተመገበውን ኬክ ዋጋ ያህል ገንዘብ እንዲገብር (እንዲቀረጥ) ተጠይቆ እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም ለመንግስቱ ያቀረበው “የእንተሳሰብ” ጥያቄ ግን ልመናው ከምሬቱ ማህፀን መውጣቱን እርግጠኛ ነኝ፡፡
እነኚህ ሰላማዊውን “የግብርና ቀረጥ ይለዝብልን” ጥያቄ “የእኛው ነው” ላሉት መንግስታቸው ያቀረቡ ሕዝቦች፤ ይህንን ጥያቄ ከማንሳታቸው አራት አስርት አመታት አስቀድሞ መንግስታቸው ያቀረበውን ልማታዊ ጥሪ ተከትሎ ልክ አሁን እኛ ሙሉ ትኩረትና ሁሉም አቅም ወደ ሕዳሴው ግድባችን በማለት በብሔራዊ ደረጃ እንደተነሳነው፣ ሁሉ ነገራቸውን ለብሔራዊው ልማት ለመቅደሱና ተዛማጅ ግንባታዎች የሰጡ የነበሩ ሲሆን ከአራቱ አስርት አመታት ማለቅና ከልማቱ መሪ ህልፈት በኋላ ተተኪው በጥቂቱ እንኳን ሳይደላደል ጥያቄውን ለማንሳት የተራወጡት ለምን ይሆን?  ምን አገኛቸውና “በቃን” አሉ?
ሲመስለኝ የተቀመጠው ግብ በስኬት በመጠናቀቁ የግብሩና የቀረጡ ቀጣይነት እንዲሁም የራሳችን ነው የሚሉት መንግስታቸው ሁሉ ነገራቸውን ሰጥተውት ሳለ በመጠኑም ቢሆን ኑሮአቸውን አይቶ፣ ችግራቸውን ተመልክቶ እፎይታን የሚፈጥርላቸውን ማለዘቢያ ያለማድረጉ፣ ምን ያህል ስግብግብ እንደሆነ በግልጽ አሳያቸው፡፡ እንደ እነኚህ ሕዝቦች አስተሳሰብ መንግስታቸው ያንን ማድረግ የነበረበት ያለ እነሱ ጥያቄ ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ባለመሆኑም ከመንግስታቸው ልማታዊ ራዕይ ጐን በሙሉ ልብ ቆመው በነበሩት ሕዝቦች ውስጥ ምሬትን ፈጠረ፡፡ የእነኛ ሕዝቦች የህይወት ጉዞም ከልማት ወደ ሌላ የላቀ ልማት ሳይሆን ከልማት ወደ ምሬት መበታተንና መጠላላት ሆነ፡፡ በመንግስታቸውም ላይ የነበራቸው ፍፁማዊ አመኔታ ጠፋና “እኛም በሰላማዊ አንድነታችን አንተም በእውነተኛ ልማታዊ መንግስትነትህ እንድትቀጥል ሃሳባችንን ስማን” ሲሉ ለአብሮነታቸው መቀጠል እንዲህ የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ፡፡
“አባትህ (ለልማቱ ሲባል) ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን (ይህ ሲሆን) እኛም እንገዛልሃለን”
1ኛ ነገ 12፣ 4
እናስ ምን ሆነ? ልማታዊው መንግስት ሁለቱን የአማካሪ ቡድኖች ሃሳብ እያደመጠ ከባለ ጥያቄው ሕዝብ ጋር የሚገናኝበት ሶስተኛ ቀን እስኪመጣ ጠበቀ፡፡ በመጠበቂያ ቀናቱ ከሁለቱ የአማካሪ ቡድኖች ማለትም “ከሽማግሌዎቹ” እና “ከብላቴኖቹ” ያገኛቸውን እጅግ የተራራቁ ምክሮች ማመንዠኩን ቀጥሎ ነበር፡፡ ለአዲሱ ብላቴና ንጉስ ትኩስ ልብ ጣፋጭ ዜማ የማዳመጥ ያህል የጣመው የእኩዮቹና ብዙ “ላይፍ” አብረው የቀጩት ብላቴኖች ምክር ነበርና ሶስተኛው ቀን ደርሶ ሕዝቡ ከንጉሳቸው “የቀደመ ፍቅራቸውንና መተሳሰባቸውን ጠብቆ በአብሮነት የሚያስጉዛቸውን ”መልካም ቃል” የናፈቁና የጠበቁ ጆሮዎቻቸውን እየኮረኮሩ ወደ ቀጠሮው ስፍራ አቀኑ፡፡ የጠበቃቸው ምን ነበር? ልማታዊው ስርወ መንግስት ተቀይሮ ነበር የጠበቃቸው፡፡ የልማታዊው ስርወ መንግስት ተረኛ አለቃ፤ በወኔ ተሞልቶ ፊቱንም አጨማድዶ ምናልባትም የሚናገርበትን አትሮኖስ በጨበጠው ቡጢው እየወቀጠ፤  
“ግብሩና ቀረጡ ከበደን” ላሉት ሕዝቦቹ እንዲህ ሲል “ቁርጥ ነው” ያለውን አቋሙን አሳወቀ፡፡
“አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን (አዎ እኔ ግን) በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ”
1ኛ ነገ 12፣14
ከልማታዊው መንግስታቸው ጐን በመቆም ሁሉ ነገራቸውን ለልማት የሰጡትና ለልማታዊ መንግስታቸው የአመታት ስትራቴጂ ስኬት የለፉት ሕዝቦች፤ ልማታዊው መንግስት ወደ ስግብግባዊ መንግስትነት በመቀየሩ ጀርባቸውን ሰጡት፡፡ በልማታዊ አስተሳሰብ ዘመኑ የሠራቸውና ዝናቸው ወደ አለም ሁሉ ወጥቶ ታላላቅ መንግስታትን ሳይቀር በቱሪስትነት የሳቡት ሞዴል ግንባታዎችና የአስተዳደር ስራዎች ሁሉ የእነኚህን “የራሴ” በሚሉት መንግስታቸው ክህደት እንደተፈፀመባቸው የተረዱትን ሕዝቦች ልብ ልማታዊ ከነበረውና በጊዜ ሂደት ስግብግባዊ ከሆነው መንግስታቸው ጋር እንዲቆዩና አብረው እንዲቀጥሉ ማሳመን አልቻሉም፡፡ ልማታዊ የነበረው መንግስት በልማታዊ አስተሳሰብ ዘመኑ የገነባቸው የቱሪስት መስህብና የሀገር ሐብት የሆኑ ታላላቅ ስነ ህንፃዊ ጥበባት የተንፀባረቁባቸው ስራዎች ሁሉ “ምሬት” በተሰማው ልባቸው ውስጥ ስፍራ አጡ፡፡ ሁሉም ነገር ቀርቶባቸው “ልማታዊ” ከነበረውና ጊዜ “ለህዝብ የማያዝን፤ የሕዝቡ ጩኸትና ስቃይ የማይሰማው” አድርጐ ከቀየረው መንግስት መለየት ምርጫቸው ሆነ፡፡ የአንድነት ታሪካቸው ሁሉ እዚህ ግባ የማይባል ሆነባቸው፡፡
እናም ንጉሳቸው “ቁርጥ ያለ” አቋሙን ባሳወቀበት መድረክ ፊት እነርሱም “ቁርጥ ያለ” አቋማቸውን እንዲህ ሲሉ አሳወቁ፡፡
“በዳዊት ዘንድ (ልማታዊ በነበረውና አሁን ግን ለሕዝቡ የማያስብ ስግብግብ መንግስት በሆነው) ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም”
1ኛ ነገ 12፣16
ከታሪክ መማር ብልህነት!

 

Read 6089 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:42