Saturday, 10 September 2011 11:16

የ2003 ዓ.ም.ትውስታዎች

Written by  ጽዮን ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የአራተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤትን በመያዝ የተጀመረው የ2003 ዓ.ም. ፓርላማ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል በቀር የተለየ ሐሳብ የሚያንፀባርቅ አባል አልነበረውም፡፡ በግል ተወዳድረው ፓርላማውን የተቀላቀሉት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስም፤ ከጅምሩ ..ዓላማዬ የኢሕአዴግን ዓላማ ማስፈም ነው.. በሚል የምርጫ ቅስቀሳ ነው የተወዳደሩት፡፡ እናም ለኢሕአዴግ ያላቸውን ድጋፍ ያሳዩበት ዓመት ሆኖላቸው አልፏል፡፡ ፓርላማው በአንድ የሚያስቡ፣ አንድ ዓይነት አቋም እና ዓላማ ያላቸውን ሰዎች አጭቆ ሥራ መጀመሩን ይፋ ያደረገበት ዕለት፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው በኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ላይ ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የፓርቲ መሪዋ ከእስር መፈታት

በምርጫ 97 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የተቀላቀሉት ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በፖለቲካ ሥራቸው ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ ለ10 ወራት የታሰሩበትን የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ጥለው የወጡት መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም. ነበር፡፡ የወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከእስር መውጣት እና ከእስር የወጡበት መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ የፓርቲ መሪዋ ቀጣይ የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ሊሆን እንደሚችል ባለመታወቁ ጉዳዩ ለስድስት ወራት ያህል አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ወ/ት ብርቱካን ከእስር በፊት ይመሩት የነበረው አንድነት ፓርቲ፤ ለሁለት ተከፍሎ ነው ያገኙት፡፡ ለሁለቱም አካላት ለትምህርት ወደ አሜሪካን ስለሚሄዱ ለጊዜው ከፓርቲው ሥልጣን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሰጥተው በመጋቢት ወር ልጃቸውን ሃሌ ሚዴቅሳን ይዘው ወደ አሜሪካን ሄደዋል - ወ/ሪት ብርቱካን፡፡ አሜሪካ ከደረሱ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት በሳንፍራንሲስኮ ከቤተሰብ ጋር ቆይተው ያገኙትን የትምህርት ዕድል ለመከታተል ወደ ሜሪላንድ አቅንተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ክስተት የአንድነት ፓርቲ የሥራ አመራር አባል የሆኑት አቶ ስየ አብርሃ፤ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ያቀኑበት ዓመት መሆኑ ነው - የፖለቲካ ስደት ያየንበት ዓመት እንበለው?
የዋጋ ተመን
ታኅሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ማምሻውን የወጣው ዜና፤ በሻጩ እና በሸማቹ መካከል ትርምስን የፈጠረ ነበር፡፡ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት መፍትሔ ነው በማለት ለሸቀጦች የዋጋ ጣሪያ በማስቀመጥ ነጋዴዎች ከተተመነው ዋጋ በላይ እንዳይሸጡ የሚያዝ መመሪያ ያስተላለፈበት ምሽት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ሳሙና እና የመሳሰሉት ለዕለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከገበያ ላይ በመሰወራቸው፤ ኅብረተሰቡን ይብስ ለምሬት የዳረጉ ወራቶች ነበሩ፡፡ ገበያውን ለማረጋጋት በሚል የተላለፈውን መመሪያ በማይተገብሩ ነጋዴዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሲወሰድ የቆየ ሲሆን፤ የየቀበሌው ሠራተኞች ወደ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች በመግባት ያደርጉት የነበረውን ማስፈራራት፤ ለነጋዴዎች የዓመቱ ትውስታ ሆኗል፡፡
..በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስም ጥቂት ነጋዴዎች ተመሳጥረው ገበያውን እያናሩት ነው.. የሚል መግለጫ በመስጠት መንግሥት የዋጋ ተመን ጣሪያ ሲያውጅ፤ ብዙዎች ተስፋ አድሮባቸው ነበር፡፡ ትልቅ አሻጥር በመንግሥት ክትትል እንደተደረሰበት በመገመት፤ ከእንግዲህ በኋላ ኑሮ ሊረክስ ነው የሚል ተስፋ የነበራቸውና እርምጃው በሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ላይ እንደሚቀጥል ተስፋ ያደረጉም በርካቶች ነበሩ፡፡ መንግሥት ..እርምጃውን የወሰድኩት በቂ ጥናት ካካሄድኩ በኋላ ነው.. በማለት በእርግጠኝነት መግለጫ ቢሰጥም፤ እርምጃው ጥናት እንዳልተደረገበት የሚጠቁሙ ክስተቶች የተበራከቱት ሳምንት ባልመላ ጊዜ ነው፡፡ በሻጭ እና በገዢ መካከል ከተፈጠረው አለመግባባት ገበያው ተረበሸ፡፡ እናም የዋጋ ቁጥጥር መግለጫው አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው፣ በሳሙና ዋጋ እና ግራም ላይ ሌላ የማስተካከያ መግለጫ እንደወጣ ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን ኅብረተሰቡ በተወሰደው እርምጃ፤ ሞራ የተቀላቀለበት ስጋ ለጥቂት ጊዜያት ሲያገኝ የነበረ ቢሆንም፤ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ያከፋፈለው ዘይት ወደ ጥቁር ገበያ ለመግባት እና ከዐይን ለመሰወር ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አብዛኞቹ ነጋዴዎች፤ እርምጃው በጥናት ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን በመግለጽ ሲወተውቱ ከርመዋል፡፡ መጀመሪያውኑም በጥናት ላይ ያልተመሠረተ የሚመሰለው የዋጋ ተመን ለአምስት ወራት ያህል ኅብረተሰቡን ከወዲያ ወዲህ ሲያናጋ ከቆየ በኋላ፤ በሚያዚያ ወር በለስላሳ መጠጦች እና በቢራ ላይ የተጣለው የዋጋ ተመን ተነሳ፡፡ ሳምንት ቆይቶም የዋጋ ተመኑ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ ሸማቹ እና ነጋዴው ወደ ቀድሞው ግንኙነታቸው ተመለሱ፡፡
መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ወሰድኩት ያለው እርምጃ፤ ዋጋውን አንሮ ኅብረተሰቡን ጭርሱኑ ወደባሰ አለመረጋጋት የከተተበት ዓመት ነበር - 2003 ዓ.ም.፡፡ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ቱሳ፤ የዋጋ ንረቱን አስመልክተው ..የኑሮ ውድነት ከተጀመረበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ችግሩን ሲያጠና፣ ሲፈትሸና በዝርዝር እያየ መፍትሔ ሲሰጥባቸው ቆይቷል፡፡ ይህም እርምጃ ከእነዚህ መፍትሔዎች አንዱ ነው፡፡.. በማለት የዋጋ ተመኑ በበቂ ጥናት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ..መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች መተግበር እና አለመተግበር የአገሪቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የመተግበር እና ያለመተግበር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግሥታችን ወደኋላ የሚመለስበት ሁኔታ የለም.. ያሉበት ዓመት ነበር፡፡ በአምስት ወራት ውስጥ ተመኑ ሲነሳ ምን ብለው ይሆን? ምላሻቸውን በ2004 እንሰማው ይሆናል፡፡  
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ማኅበረሰብ፤ ጫንቃው ችግርን መሸከም ቢችልለትም ባይችልለትም፣ የባሰን በመፍራት ..ተመስገን.. እያለ መኖር አንዱ መገለጫው ነው፡፡
..መኖር.. እጅግ እየተወደደ የመጣው ከ1999 ዓ.ም. ወዲህ ቢሆንም፤ 2003 ዓ.ምም. የነዳጅ ዋጋ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ ለምግብነት የሚያገለግሉ ሸቀጦች አጠቃላይ ለመኖር ዋስትና የሚሰጡ ሸቀጦች ዋጋ እጅግ የናረበት ዓመት ነበር፡፡ የኑሮ ውድነቱን ሊቀንስ ይችላል በሚል መንግሥት በድንገት የወሰደው የዋጋ ትመና መፍትሔ አላመጣም፡፡ በደመወዝ ጭማሪ የተደረገው ሙከራም፤ ጭማሪውን መልሰው የሚወስዱ እቅዶች በመውጣታቸው ለንረቱ መፍትሔ አልሰጠም፡፡ የዋጋ ተመኑ ተነሳ ከተባለበት ዕለት ጀምሮም የዋጋ ተመን ተጥሎባቸው የነበሩ ምርቶች ዋጋ በእጅጉ ንሯል፡፡ ነጋዴዎች በዋጋ ተመኑ ጊዜ ያጡትን ለማካካስ ያሰቡ ይመስል፣ በተራ መዝናኛ ቤቶች ሳይቀር የለስላሳ መጠጦች እና የቢራ ዋጋ ጨምሯል፡፡ አንድ ኪሎ ስጋ ከ70 እስከ 100 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ለዚያውም አንዳንድ ሥጋ ቤቶች በዋጋ ተመኑ ጊዜ ያስቀሯቸውን አገልግሎቶች ሳይመልሱ፡፡
የዋጋ ንረቱ እጅግ እየተባባሰ በመምጣቱ የዘንድሮው አዲስ ዓመት፤ በ1300 ብር ጤፍ፣ በ60 ብር አንድ ኪሎ በርበሬ፣ በ125 ብር አንድ ኪሎ ቂቤ፣ በ80 ብር ዶሮ ሊከበር ነው፡፡   
የህዳሴው ግድብ እና ቦንዱ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አቶ አለማየሁ ተገኑ እና የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበ ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር፤ ኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ላይ ..የሚሌኒየም ግድብ.. ልትሠራ መሆኗን የሚገልጽ ዜና ይዘው ብቅ ማለታቸው የዓመቱ ድንገተኛ እና ታላቅ ዜና ነበር፡፡
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ከሱዳን ድንበር በ40 ኪ.ሜ. ያህል ርቀት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ላይ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ፤ ..የሚሌኒየም ግድብ.. 5250 ሜጋ ዋት ኀኀይል ለማመንጨት እንደሚያስችልና፤ 63 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ግድቡን ለመሥራት የሚያስፈልገውን 80 ቢሊዮን ብር ወጪ አገሪቱ ከገዛ ኪሷ ወጪ ለማድረግ መወሰኗን ጠ/ሚ በወቅቱ ሲናገሩ፤ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እና የዓለም መነጋገሪያ ርእሰ ወሬ ሆኖ ነበር፡፡ ከቀናት በኋላም የግድቡ ስም ተቀይሮ ..የህዳሴ ግድብ.. በሚልም ተተክቷል፡፡ ዜናውና የመንግሥት መግለጫ የብዙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍና ስሜት ያስገኘ ሲሆን፤ ከዚያም ጋር አብሮ የተለያዩ አስተያየቶች፣ መላምቶችና ጥርጣሬዎችንም አስተናግዷል፡፡ የህዳሴው ግድብ ..በአረብ አገራት ውስጥ፤ ለአብዮት መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ውስጥም በተጨባጭ በመኖራቸው፤ ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ልትሆን ትችላለች.. ከሚል ስጋት ኢሕአዴግ የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ መቀየር ይፈልጋል የሚል አስተያየት ያቀረቡ ሰዎች፤ የአባይ ግድብ ለዚህ ዓላማ አገልግሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ..መንግሥት አገሪቱን ለማስተዳደር የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው..፤ ..አቶ መለስ ሥልጣን ከመልቀቃቸው በፊት አንድ ታሪክ ለመሥራት ፈልገው ነው.. የሚሉ እና የመሳሰሉ መላምቶችና አስተያየቶች ሲሰጡ ከርመዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በቀናነት የተመለከቱት እና ለአገር የሚሰጠውን ጥቅም በመተንተን ያደነቁትም በርካቶች ነበሩ፡፡ መንግሥት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን 80 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንዲያስችለው ይፋ ያደረገው ..የቦንድ ሽያጭ.. እስከ ዛሬ ድረስ የቀጠለ የዓመቱ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ምናልባትም ..ቦንድ.. የሚለው ቃል ለምን ያህል ጊዜ እንደተጠራ ቢቆጠር እስከዛሬ በኢትዮጵያ ስማቸው ተደጋግሞ ከተነሱት ነገሮች ሁሉ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ አይመስላችሁም?
ረኀኀብ         
በ2003 ዓ.ም. በአሳዛኝነታቸው ከሚታወሱት ክስተቶች አንዱ፤ በምሥራቅ አገራት በተለይ በሶማሊያና በኢትዮጵያ የተከሰተው ረኀኀብ ነው፡፡ የዓለም የምግብ ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ ከዛሬ 65 ዓመታት ወዲህ፤ በተለየ ሁኔታ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች በድርቅ ተጠቅተው ረኀኀብ እየፈጃቸው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አገራት ረኀኀብተኞች ውስጥ የዓለምን ትኩረት የሳቡ እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ጥሪ የቀረበላቸው የሶማሊያ ረኀኀብተኞች እና ስደተኞች ናቸው፡፡ የኢሬቴድ ጣቢያዎችም፤ አንድም ኢትዮጵያዊ ያልተራበ እስኪመስል ስለሶማሊያ ረኀኀብተኞች ሲያራግቡና ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪውን ሲያስተጋቡ የቆዩበት ዓመት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ስደተኞች በሯን ክፍት አድርጋ እየተቀበለች መሆኗ ምስጋና ሊያሰጣት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በመግለጽም ሲወተውቱ ከርሞል፡፡ በመጨረሻ ከረጅም ማቅማማት በኋላ፤ መንግሥት በግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል፤ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ አድርጓል፡፡
በቅርቡም ቱሪስት መስለው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በአንድ መንደር ውስጥ ጥናት እንዳደረጉ የተናገሩ የቢቢሲ ጋዜጠኞች፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በረኀኀብ ከመጠቃታቸው የተነሳ ቅጠል ሲበሉ ማየታቸውን እና በረኀኀብ ሰው ሲሞት መመልከታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ መንግሥት በየዓመቱ ከለጋሽ አገራት የሚቀበለውን የእርዳታ እህልና ገንዘብ፤ በድብቅ እና በግልጽ ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈሚያነት፣ ተቃዋሚዎቹንና የተቃዋሚዎቹን ደጋፊዎች ለማጥቃት እንደመሳሪያ እንደሚጠቀምበት በመግለጽ ትንተናቸውን አቅርበዋል - ጋዜጠኞቹ፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የብዙሃን መገናኛዎች የሚያቀርቡበትን ትችትና ዘገባ በማስተባበል ተደጋጋማ መግለጫዎችን ያወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ እንዳለፉት ዓመታት ዘንድሮም ከቢቢሲ እና በኢትዮጵያ ላይ ሪፖርት ካቀረቡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲወዛገብም ከርሟል፡፡ አወዛጋቢው ዳግም ምዝገባ
በንግድ ምዝገባ ዐዋጅ ቁጥር 686/2002 መሠረት፤ ለአዲስ የንግድ ሥራ ፈቃድ እና ለዳግም ምዝገባ አገልግሎት የወጡት መስፈርቶች፤ በ2003 ዓ.ም. ተግባራዊ እንዲደረጉ አስገዳጅ መመሪያ መተላለፉ፤ ለነጋዴው የዓመቱ ፈተና ሆነውበት ነበር፡፡
ነጋዴዎች መስፈርቶቹን አሟልተው እስከ ሰኔ 30 ተመዝግበው እንዲያጠናቅቁ ጥብቅ መመሪያ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜው አልተጠናቀቀም፡፡ ጠ/ሚሩ ከአዲሱ የንግድ ፍቃድና ምዝገባ ዐዋጅ ጋር ተያይዞ፣ ነጋዴዎች ካፒታላቸውን ቀንሰው ለመመዝገብ ይሞክራሉ በሚል ችግር እንደተፈጠረና ይህን ለመቅረፍ ጥናት እንዲካሄድ የፍትሕ ሚኒስቴርን፣ የንግድ ሚኒስቴርንና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡ የዚህ ትዕዛዝ መሰማቱን ተከትሎም በአዲሱ የንግድ ምዝገባ ፈቃድ መሠረት በየዕለቱ የዳግም ተመዝጋቢዎች ቁጥር በማደጉ የምዝገባው ጊዜ መራዘሙ ተገልል፡፡ ምዝገባው የተራዘመው እስከ ነሐሴ 15 ቀን ድረስ ሲሆን በርካታ ነጋዴዎች የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልተው ለመመዝገብ አሁን ድረስ እየተሯሯጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡
xw²UbþW GBR
የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን በ2003 ዓ.ም. በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደውን 54.18 ቢሊዮን ብር ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱን በሚያሳይ መልኩ የነጋዴዎቹን መንደር ሲያስስ የከረመበት ዓመት ነበር፡፡ መንግሥት ቫትን ለመቆጣጠር እንዲያስችለው እያንዳንዱ ነጋዴ የ8ሺህ ብር ካሽ ሬጅስተር እንዲገጥም የተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ የካሽ ሬጅስተሩ ዋጋ፤ ከንግድ ካፒታላቸው በላይ የሆነባቸው ነጋዴዎች አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡ በምግብ እና በመጠጥ ዋጋ ላይ የተጣለው ቫት በአስገዳጅ ሁኔታ በማምጣቱ በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን አስጨንቋል፡፡ በካሽ ሬጅስተር ግዢ ዓመቱን ሙሉ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ላይ ሮሮ ሲያሰሙ የነበሩት ነጋዴዎች በመጨረሻም ምላሽ ያገኙት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማ ተገኝተው፤ ..አነስተኛ ሱቆች የካሽ ሬጅስተር ማሽን ለመግዛት አይገደዱም.. የሚል መልእክት ሲናገሩ፤ ለነጋዴዎቹ እፎይታ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ በእነዚህ ነጋዴዎች ላይ በዓመቱ መጨረሻ የተጣለባቸው ቁርጥ ግብር ግን፤ እፎይታቸውን የሚቀማ እና ወደ እሮሮ የሚመልስ ሆኖባቸዋል፡፡
ቀሪ ትውስታዎች
በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥቂት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሌሎቹ ዓመቶች ሁሉ በዘንድሮው ዓመትም እርስ በእርስ የተነካከሱበት፤ ለፓርቲያቸው ሥልጣን የተሻሙበት ዓመት ነበር፡፡
በ2003 ዓ.ም. የሥነ ጥበብ ባለሞያዎች ከጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ውይይት ያደርጋሉ መባሉ፤ ውይይቱ እና ከውይይቱ በኋላ የተፈጠረው የእርስ በእርስ ፍጥጫ የዓመቱ አወዛጋቢ ትውስታ ነበር፡፡

 

Read 2609 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:20