Saturday, 14 April 2012 11:29

ጤንነቱ ያልተረጋገጠሥጋ መመገብ ለሞት ይዳርጋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ በየእለቱ ከ5ሺ በላይ ህገወጥ እርድ ይፈፀማል

ለወራት ከሥጋና ቅቤ ታቅቦ የቆየው ህዝበ ክርስቲያን  ፆሙን ፈቶ ከራቃቸው ምግቦች ጋር ሊገናኝ ነው፡፡ እለተ ፋሲካ በክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በእጅጉ የሚወደድና በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና አብዛኛው የበዓሉ አክባሪ የቤቱ የበግና የፍየል እርድ የሚያከናውንበት፣ በየሰፈሩ የተቧደኑ ሰዎችም በጋራ የገዙትን በሬ አርደው የቅርጫ ሥጋ ይከፋፈሉ የነበሩበት ዘመን ቅርብ ነው፡፡ እጣ ተጥሎ የደረሰውን የቅርጫ ሥጋ ፣ በትሪና በዘንቢል አሸክሞ ከቤቱ የሚደርስ አባወራን ማየት ዛሬ የሚናፈቅ ሆኗል፡፡ የዘንድሮው የበግና በሬ ዋጋ ይህን የቆየ የበዓል አከባበር ሥርዓት ሊያስቀጥል የሚችል አይመስልም፡፡ የዶሮ ዋጋ የቀድሞውን የበግ ዋጋ አክሎ፣ በጉ የበሬ ዋጋ ላይ ደርሶ የማይቀመስ ሆኗል፡፡

የዛሬው ጉዳያችን ግን ከበግና በሬ ዋጋ መወደድ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ይልቁንም በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ የሚቀርቡና ጤንነታቸው ያልተረጋገጠ የከብትና የበግ ሥጋዎች ሞት ሊያስከትል ለሚችል የጤና ችግር እንደሚዳርጉ ከባለሙያዎች ያገኘነውን ልናካፍላችሁ አስበን ነው፡፡

ጤንነቱ ያልተረጋገጠ ሥጋ የሚገኘው በአብዛኛው በየመንደሩና በየሰፈሩ በሚደረጉ እርዶች እንደሆነ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ ይናገራሉ፡፡ በህገወጥ መንገድ ለእርድ የሚቀርቡ እንስሳት በቅድሚያ የጤና ምርመራ የሚደረግላቸው ባለመሆኑ፣ በቀላሉ ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉና ሞትን የሚያስከትሉ በሽታዎችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ እርዱ በሚከናወንበት ጊዜም ንፅህናው ባልተጠበቀ ስፍራና መሣሪያዎች የሚፈፀም በመሆኑ፣ ሥጋው በቀላሉ እንዲበከልና በሽታ አምጪ የሆኑ ነገሮች እንዲራቡበት ይሆናል የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ ይህ ደግሞ ለምግብነት በሚውልበት ወቅት እንደ አባሠንጋና የመሰሉ ገዳይ በሽታዎችንና ኮሌራና አሜባ የመሳሰሉ በባክቴሪያ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ያመጣል ይላሉ፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ሆኖ ጤናማነቱ የተረጋገጠ የእርድ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ ድርጅቱ ለእርድ የማቀርበው እንስሳ ከመታረዱ በፊት በሚደረግለት የቁም ምርመራና ከታረደ በኋላም በማደርግለት የበድን ምርመራ ጤናማነቱ የተረጋገጠ ሥጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ለሚሰጠው የእርድ አገልግሎትም ለበሬ 180 ብር እንዲሁም ለበግ 30 ብር እንደሚያስከፍል፤ ይህም በመንደሩ ለእርድ ከሚከፈለው ዋጋ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

ለእርድ የሚቀርቡ እንስሳት የቁም ምርመራ ሲደረግላቸው የበሽታ ምልክቶች ከታዩባቸው ለብቻቸው እንዲሆኑ ተደርገው የህከምና ክትትል እንደሚደረግላቸውና ለውጥ ካመጡ በኋላ ታርደው የበድን ምርመራ እንደሚካሄድ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ በዚህ ምርመራ በሥጋው ላይ በቀላሉ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ መኖሩ ከተረጋገጠ ሥጋው እንዲቃጠል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በከብት አቅራቢው ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ የሉካንዳ ነጋዴዎች ማህበር ካሳ በመክፈል ይታደጋል፡፡ ማህበሩ በዚህ ጉዳይ ላይ እየሰራ ያለው ነገር የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ህገወጥ እርድ የሚከናወነው በድብቅ በመሆኑ በአብዛኛው እርዱ የሚፈፀመው በቆሻሻ መውረጃ ወንዞችና ቱቦዎች ሥር፣ በየመፀዳጃ ቤቱ በመሆኑ ሥጋው በቀላሉ ለብልሽት እንደሚዳርግ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ ቄራዎች ድርጅት ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ከጤና ጥበቃ፣ ከፍትህና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ክትትል እንደሚያደርግና በህገወጥ እርድ የተገኙ የእንስሳት ሥጋን ተቀብሎ የማስወገድ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀን ከ5ሺ ያላነሱ በግና ፍየሎች በህገወጥ መንገድ እንደሚታረዱ የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም፤ የፒያሳው ጀጐል ሰፈርና የመርካቶው አሜሪካን ግቢ ህገወጥ እርድ ከሚከናወንባቸው ስፍራዎች ግንባር ቀደሞቹ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፈትሒ መሀመድ በበኩላቸው፤ ጤንንቱ ያልተረጋገጠ ሥጋን መመገብ ከኮሶ ትል አንስቶ ገዳይ እስከሆኑ አባሰንጋና መሰል በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ጠቁመው፤ በህገወጥ መንገድ የሚከናወን እርድ በሁለት መንገድ በሥጋው ጤንነት ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡ እንስሳው ከመታረዱ በፊት በቂ ምርመራና ክትባት ሳይደረግለት መቅረቱ አንዱ ችግር ሲሆን ሥጋው ከታረደ በኋላ በአቀማመጥና በማጓጓዝ ሂደቶች የተለያዩ ገዳይ ባክቴሪያዎችን ሊያፈራ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡ ሥጋ በባህርይው ባክቴሪያዎችን ቶሎ ማፍራት ይችላል ያሉት ዶክተሩ፤ ይህም ከቁርጠት ጀምሮ ለሞት ሊዳርጉ እስከሚችሉ በሽታዎች ድረስ ሊያስከትል እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ እንስሳው ከሞተ በኋላ ታርዶ ለምግብነት መዋሉ ያለውን ችግር አስመልክተው ሲናገሩም፤ ከብቱ እንደሞተ በፈርሱ ውስጥና በተለያዩ ቦታዎች ያሉት ባክቴሪያዎች በቀላሉ ወደ ሥጋው በመግባት የመራባት እድል ስለሚኖራቸው፣ ሥጋው በቀላሉ ሊበከልና ለጤና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ዶ/ር ፈትሒ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መንገድ የተበከለ ሥጋ በማብሰል ሊጠፉ (ሊሞቱ) የማይችሉ ባክቴሪያዎች ሊኖሩበት ስለሚችሉ፣ በሰአታት በሚቆጠር ጊዜ ለሞት ሊዳርግ የማችል ችግር ያስከትላልም ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ጤንነቱ ያልተረጋገጠ ሥጋን በመመገብ ከሚመጡ ችግሮች ራሱን መከላከልና በተቻለው መጠን ሥጋን አብስሎ መመገብ እንዳለበትም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል ከ2ሺ እስከ 2ሺ አምስት መቶ የሚደርሱ የበግና የፍየል እርድ ትእዛዝ ተቀብሎ እንደሚያከናውን የገለፁት የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ ድርጅቱ በራሱ ከ2ሺ ያላነሱ በጐችን በማረድ በሁለት የኮንደሚኒየም ሱቆቹና በዋናው የድርጅቱ የመሸጫ ሱቆች ኪሎውን በ72 ብር ከ60 ሣንቲም ሂሣብ ለማከፋፈል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡ ላለፉት ሁለር ወራት የእድሳት ሥራውን ሲያከናውን የቆየው ድርጅቱ፤ ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም የእርድ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የተናገረት አቶ ኤፍሬም፤ በዚህ በዓል የተቀበሉት የእርድ እንስሳ ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የፆም መያዣን በመሳሰሉ ጊዜያት እስከ 5ሺ ሊደርስ የሚችል የእርድ ትእዛዛት እንደሚኖሩ ዳይሬክተሩም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ለማከናወን ባቀደው የግማሽና ሙሉ በግ ሥጋ ሽያጭ እስከአሁን ከ500 በላይ ደንበኞች መመዝገባቸውንም አክለው ገልፀዋል፡፡

 

 

Read 3455 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:39