Saturday, 29 September 2012 09:22

ከኢትዮጵያ ህዝብ ግማሽ ያህሉ ሜዳ ላይ ይፀዳዳል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

“ህዝቤ ሆይ በእዳሪ የሚተላለፉ በሽታዎች እየተበራከቱ ነውና እዳሪህን በመኖሪያ ቤትህ አጠገብ ጉድጓድ እየቆፈርክ ተቀመጥ፡፡ ሳትቆፍር እዳሪ ተቀምጠህ ክፉ በሽታ የተገኘብህ እንደሆነ መቀመጫህን ለደመወዝተኛ አደርገዋለሁ፡፡”ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ይህንን አዋጅ ያስነገሩት ጥቅምት 25 ቀን 1998 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ ንጉሱ አዋጁን ያስነገሩበት ምክንያትም በሰገራ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች መበራከታቸውን በጊዜው የህክምና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት ሩሲያውያኖች ስለነገሯቸው ነበር፡፡ ህዝቡ በመፀዳጃ ቤት ስለመጠቀም ምንም በማያውቅበት በዚያ ዘመን ንጉሡ ይህንን አዋጅ ማውጣታቸው ህዝቡን ግራ ቢያጋባውም አዋጁን ተግባራዊ ከማድረግ ግን አልተቆጠበም፡፡

ይህንን ሁኔታ የሚቆጣጠሩ የጤና ተቆጣጣሪዎች በመቅጠርም አዋጁ እንዲከበርና ህዝቡ በመፀዳጃ ቤት የመጠቀም ልምዱን እንዲያዳብር ቁጥጥር ይደረግ ነበር፡፡ በመቀጫ መልክ የሚገኘው ገንዘብ ለጤና ተቆጣጣሪዎቹ ደመወዝ እንዲሆኑ በማድረግ፣ በሠገራ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከልና ህዝቡም በመፀዳጃ ቤት የመጠቀም ልማዱን ለማሣደግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

ቀድሞ ባለመደውና በማያውቀው መንገድ እንዲፀዳዳ የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪም ቀስ በቀስ ከመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ጋር እየተላመደና ተጠቃሚ እየሆነ ሄደ፡፡

እዳሪውን ዓይኑ ሣያይበት መፀዳዳት መቻሉም ደስታን ፈጠረለት፡፡ ቀስ በቀስ የነዋሪው ቁጥር ሲጨምር፣ ከተማው እያደገ ሲሄድ፣ መኖሪያ ቤቶች ሲበራከቱ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ማግኘቱ ችግር እየሆነ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያትም አብዛኛው የከተማው ነዋሪ ሠገራውን በየመንገዱ ዳርና በየቤቶቹ አጥር ሥር መፀዳዳት ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታም የከተማው ፅዳት እንዲበላሽና ህዝቡም ለበርካታ ተላላፊ በሽታዎች እንዲጋለጥ ምክንያት ሆነ፡፡

የአለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጋራ እ.ኤ.አ በ2010 ጥናት አድርገው በቅርቡ ይፋ ያደረጉት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ38 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ በሜዳ ላይ ይፀዳዳል፤ ይህም ከጠቅላላው ህዝብ ወደ ግማሽ ያህሉ የሚጠጋ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ጥናቱ ይፋ እንዳደረገው፣ ወደ 49 ሚሊዮን የሚጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ በሜዳ ላይ ይፀዳዳ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት መሻሻል አሣይቶ፣ ወደ 38 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል፡፡ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምን አስመልክቶ በተደረገው ጥናት መሠረትም ከገጠር ይልቅ በከተማ የመፀዳጃ ቤት የመጠቀም ልምዱ የተሻለ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ከሚያገኘው ህዝብ መካከል በአግባቡ የሚጠቀመው ከ30 በመቶ በታች እንደሆነ ይኸው ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

የመፀዳጃ ቤትን በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የተቅማጥ በሽታ፣ ውሃ ወለድ በሽታዎችና ከምግብ መበከል ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ዋንኞቹ ሲሆኑ ከዚሁ ችግር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ካላቸው በሽታዎች መካከል የተቅማጥ በሽታ በገዳይነቱ የሚታወቅ በሽታ ነው፡፡

ይህ በሽታ ህፃናትና በገዳይነት ከሚታወቁት በሽታዎች ውስጥ ከሣንባ ምች ቀጥሎ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ከ250ሺ በላይ የሚበልጡ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በየዓመቱ በተቅማጥ በሽታ ይሞታሉ ይህ ማለት ከሚወለዱ 5 ህፃናት መካከል 5ኛ የልደት በዓላቸውን ከማክበራቸው በፊት አንዱ በተቅማጥ በሽታ ይሞታል፡፡

መፀዳጃ ቤትን በአግባቡ በመጠቀም፣ ንፅህናውን የጠበቀ ውሃን በመጠጣትና፣ እጅን በወሣኝ ጊዜያት በመታጠብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ከሞት መታደግ ይቻላል፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልል ባህርዳር ከተማ ውስጥ ሰሞኑን በተካሄደው አራተኛው የኢትዮጵያ ሃይጂንና ሣኒቴሽን ፌስቲቫል ላይ የቀረቡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ የመፀዳጃ ቤት ሽፋኑ 66 በመቶ የደረሰ ቢሆንም አጠቃቀሙ ግን ከ30% በታች መሆኑን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የባለፈው ዓመት ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ለ3 ቀናት በተካሄደው በዚህ ፌስቲቫል ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚ/ር የውሃ ሳኒቴሽንና ሃይጂን አማካሪው አቶ ጌታቸው በላይነህ እንደገለፁት፤ የመፀዳጃ ቤት በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ህብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር ከፍተኛ የቅስቀሣ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡

በየሜዳው ላይ መፀዳዳት የሚያስከትለው የጤና ችግርና አስነዋሪነቱን ለህብረተሰቡ ለማስተማር እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ለውጥ እያስገኙ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ህብረተሰቡ በተለይም በየክልል ከተሞችና በየገጠሩ የሚኖረው ህዝብ ከዚህ ፀያፍ ድርጊት ጋር ስሙ እንዳይነሣ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባው ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት እጥረት ጐልቶ በሚታይባቸውና ብዙ ህዝብ ተፋፍጐ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የህብረተሰቡ የመፀዳዳት ልማድ ሌላው እጅግ አሣሣቢና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ እንደ ማሣያ ይሆን ዘንድ የመርካቶውን ሰባተኛ አካባቢ ልንቃኝ ወደድን፡፡

እርስ በርሣቸው የተዛዘሉ በሚመስሉት የመርካቶው ሰባተኛ አካባቢ ቤቶች ውስጥ የማይካሄድ የንግድ ዓይነት የለም፡፡ የአካባቢውን ነዋሪ አቅም ያገናዘቡ ምግቦችና መጠጦች፣ ልብስ ጫማ፣ ጠላና አረቄ፣ ጫትና ሺሻ ወዘተ… በሥፍራው ለገበያ የማይቀርብ ነገር የለም፡፡ ይህቺን አካባቢ ሙጥኝ ብለው ለዓመታት ገላቸውን ለሽያጭ እያቀረቡ ኑሮዋቸውን የሚገፉ ሴተኛ አዳሪዎችም መናኸሪያ ናት፤ የመርካቶዋ ሰባተኛ፡፡

በጣሊያን ወረራ ዘመን እንደነገሩ እየተውተፈተፉ እንደተሰሩ የሚነገርላቸው ቤቶቿ ጊቢና የመፀዳጃ ቤት የናፈቃቸው ናቸው፡፡ ከንግድ ሥፍራነት ተርፈው አሊያም ቀን ቀን የንግድ፣ ምሽት ላይ ደግሞ የመኖሪያ ወይም በተቃራኒው ቀን ቀን የመኖሪያ፣ ምሽት ላይ የንግድ ቤት በመሆን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡት የሰባተኛ ቤቶች ውስጥ መፀዳጃ ቤት ፈልጐ ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ማለዳ ላይ እግር ጥልዎት ቢገኙ እርምጃዎ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን ይገደዳሉ፡፡ ሰባተኛ ምሽቱን ሲፀዳዳ  ያደረውን ሠገራ በስስ ፌስታል እየቋጠረ ማለዳ ላይ አደባባይ ያውለዋል፡፡

እርስዎ አገር ሠላም ብለው በለመዱት ሁኔታ ስልክዎን እያወሩ ወይም ከጓደኛዎ ጋር እየተጫወቱ ዘና ብለው ሲሄዱ ምናልባትም እግርዎ ከእነዚህ የአደባባይ ሲሣዮች አንዱን ሊጨፈልቅ ይችላል፡፡ ይህ ክስተት እንደመርካቶ ባሉና ብዙ ህዝብ ተፋፍጐ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ሂደትም የጤና ባለሙያዎቹ (fly toilet) እያሉ ይጠሩታል፡፡ ሂደቱ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማና በሌሎችም የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች በስፋት የሚታይ መሆኑንም የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የውሃ ሣኒቴሽንና ሃይጂን አማካሪው አቶ ጌታቸው በላይነህ ይናገራሉ፡፡

የዚህ አገልግሎት (ሠገራን በፌስታል ቋጥሮ የመጣል አገልግሎት) ተጠቃሚዎች በአብዛኛው በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩና የኑሮ ደረጃቸውም ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎችና ጐዳና ተዳዳሪዎች እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ እነዚህ ዜጐች የመፀዳጃ ቤት በአካባቢያቸው ባለመኖሩና አገልግሎቱን የሚያገኙበት መንገድ ስለሌላቸው በዚህ እጅግ አደገኛ በሆነ መንገድ እንዲፀዳዱ መገደዳቸውን ተናግረዋል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ችግሩን ለመቅረፍ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚ/ር፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚ/ር፣ ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንና፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር የከተማ ሣኒቴሽን አገልግሎት ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ለማግኘት እንዲችሉ የማድረጉ እንቅስቃሴም ቸል እንዳልተባለ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ በት/ቤቶች፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማትና በሆስፒታሎች አካባቢ ያሉ የመፀዳጃ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ከዩኒሴፍና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በት/ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ የመፀዳጃ ቤቶች እንዲገነቡ ዲዛይን እያዘጋጁ መሆናቸውንና በቅርቡ ታትሞ ለሁሉም ክልሎች እንደሚሰራጭ ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም የአገልግሎት መስጫ ተቋም ግንባታ በሚካሄድበት ወቅት አካል ጉዳተኛውንም ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱንና የአፈፃፀም መመሪያውም እንደሚወጣ አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ዋሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አጋር ድርጅቶች በትብብር ባዘጋጁት በዚህ ፌስቲቫል ላይ፣ አካባቢያቸውን በንፅህና በመጠበቅና ህብረተሰቡ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ልምዱን እንዲያሣድግ በማስተማሩ ረገድ፣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል የተባሉ የክልል መረጃዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተሸልመዋል፡፡

 

 

Read 3745 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:29