Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 November 2012 13:03

የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ፕሮጀክት ተቆጣጠሩ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የኢትዮጵያ መንግስት ሊያካሂድ ያሰበውን የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮሙኒኬሽን ዝርጋታ ፕሮጀክት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ሊቆጣጠሩት እንደሆነ ተገለፀ፡፡ “ዜድቲኢ እና “ሁዋዌይ” የተባሉት ሁለቱ የቻይና የቴሌኮም ኩባንያዎች ለፕሮጀክቱ የተጫረቱ ሲሆን “ሁዋዌይ” 50 በመቶ ድርሻ ማሸነፉን የተለያዩ ድረገፆች ዘግበዋል፡፡ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ለብሉምበርግ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር የሁለት ዓመት ኮንትራት በቀጣዮቹ ሳምንታት ይፈራረማል፡፡

ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በምን ያህል ድርሻ ለሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች እንደሚሰጥ ባይገልፁም “ዜድቲኢ” እና “ሁዋዌይ” ተገቢውን ድርሻ በመያዝ አብረውን ይሰራሉ ማለታቸውን ብሉምበርግ ጠቁሟል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት የአዲስ አበባን የኔትዎርክ ጥራት ከፍ ለማድረግ እና የኢትዮጵያ ቴሌኮም ገበያን ያሳድጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ በበኩላቸው፤ የጨረታው ሂደት ገና እንዳልተጠናቀቀ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ብዛት በእጥፍ በማሳደግ 40 ሚሊዮን እንደሚያደርስ ሚኒስትሩ ለብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለሁለቱ ኩባንያዎች ለማከፋፈል እና በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በመመካከር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት አጠቃላይ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ታውቋል፡፡
በከፊል በቻይና መንግስት ባለቤትነት የተያዘውና በስልክ ቀፎዎች አምራችነት የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ኩባንያ የሆነው “ዜድቲኢ”ላለፉት ስድስት ዓመታት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የአገሪቱን የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማራው ሌላው የቻይና የቴሌኮም ኩባንያ “ሁዋዌይ” በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዝርጋታ ፕሮጀክት 50 በመቶ ድርሻ እንዳሸነፈ “ሲ114” የተባለ የቻይና ግዙፍ የቴሌኮም ድረገፅ እና “ቲያኒያ” ለተባለ የቴክኖሎጂ ድረገፅ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
የ“ሁዋዌይ” ኩባንያ ፕሬዚዳንት በተለያዩ አገራት የሚሠሩ የኩባንያው ሠራተኞች ሽልማት በሰጡበት ነው በኢትዮጵያ ያለውን ፕሮጀክት 50 በመቶ ድርሻ ማሸነፋቸውን የገለፁት በኢትዮጵያ የኩባንያው የፕሮጀክት ሃላፊዎችም ሽልማት እንዲሰጥ ፕሬዚዳንቱ መመሪያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

Read 3521 times