ኳሬዳ ለተሰኘው ትል በምቹ መራቢያነት የተጠቀሰውን የሣር ጎጆ በቆርቆሮ ክዳን በመለወጥ ለመከላከል እንደሚቻል በተሞክሮ የተረጋገጠ ሲሆን ቤቶቹ የተደገፉባቸውን የዕንጨት ምሰሶዎች በግንብ /ኮንክሪት/ በመተካት ደግሞ የምስጡን ጥቃት መቋቋም የሚቻል በመኾኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሀገረ ስብከቱ ጥያቄና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈቃድ ከተቋቋመው የገዳሙ እርዳታ አሰባሳቢና ልማት ኮሚቴ ጋራ የተጠየቁትን የግንባታ ቁሳቁሶች በዐይነትና በገንዘብ በመስጠት የተቻላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ የኮሚቴው ሓላፊዎች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በቁጥር ከሦስት መቶ ኀምሳ ያላነሱ ሴት መነኰሳዪያት ብቻ በማኅበር ለሚኖሩበት ገዳም የእህል ወፍጮ፣ የውኃ መሳቢያ ሞተርና የውኃ ማጠራቀሚያ ታንኮችን ለመትከል፣ ዘመናዊ የንብ ማነብ/የማር ምርት/ እና ሌሎችም የራስ አገዝ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር እንደሚንቀሳቀስ የጠቆመው ኮሚቴው አክሎ እንደገለጸው÷ እንደ ጾሙና ጸሎቱ ሁሉ ሥራን የጽድቅ መሠረት አድርገው በማኅበር የሚኖሩት ከሦስት መቶ ኀምሳ በላይ ማኅበረ ደናግሉ፤ በከፍተኛ ሙቀትና በሌሎችም የአካባቢ ለውጦች ሳቢያ ራሳቸውን የሚረዱባቸው የዳጉሳና የማሽላ ሰብሎቻቸው ፍሬ ሊሰጧቸው ስላልቻሉ አስቸኳይ የምግብ (ባቄላ፣ ዘንጋዳ፣ ዳጒሳ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ጨው፣ በርበሬ) እና የአልባሳት (ስድሳ ጣቃ አቡጀዲ ጨርቅ) እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም አስታውቋል፡፡