Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 10:58

የሰንደቅ ዓላማ አዋጁ ወዴት አለ? Featured

Written by 
Rate this item
(9 votes)

በተለያዩ በዓላት፣ በህዝባዊ ሰልፎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በመምህርት ተቋማት፣ በንግድ ማዕከሎች … ወዘተ ተንጠልጥለው ወይም ተሰቅለው የማያቸውን ብዙዎቹን የሰንደቅ ዓላማዎች ከሰንደቅ ዓላማ አዋጁ ድንጋጌዎች አንፃር ስመለከታቸው አዋጁ ስለመኖሩ እንድጠራጠር ያደርገኛል። ላለፈው አንድ ዓመት ሰንደቅ ዓላማችንን በተመለከተ የታዘብኩትን ጥቂት ነገር ላካፍላችሁና ፅሑፌን ልጀምር።
ነሐሴ 2003 ዓ.ም፡- መገናኛ አካባቢ ባለ መንግስታዊ መ/ቤት አጠገብ ሳልፍ ከቅፅር ግቢው ውስጥ በተሰቀለው ሰንደቅ ዓላማ ላይ ዓይኖቼ ተተክለው ቀሩ። ሰንደቁ ላይ የሚውለበለበው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተዘቅዝቆ ነበር።

ከባልደረባዬ ጋር ወደ መ/ቤቱ ዘልቀን ጉዳዩን ለጥበቃ ኃላፊው ስናስረዳው፣ በነገሩ እጅግ በጣም በመደናገጥ በቅፅበት ስህተቱን ማረም ጀመረ። የሰንደቅ ዓላማው መዘቅዘቅ ቢያናድደኝም ጥበቃው ላይ ባየሁት መደናገጥ ቢያንስ የፈፀመው ስህተት ሊያስከትል የሚችለውን ሕጋዊ ውጤት የተረዳው ስለመሰለኝ በጥቂቱም ቢሆን ተፅናናሁ።
ጳጉሜ 01/2003 ዓ.ም፡- በፋና ኤፍኤም የ90 ደቂቃ ፕሮግራም ላይ የሚከተለውን አስገራሚ ዘገባ ሰማሁኝ። ደሴ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ውስጥ ላለፉት ስልሳ ሶስት ዓመታት ጠዋትና ምሽት 12፡00 ሲሆን የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል። በዚህ ጊዜም በሥፍራው በተሽከርካሪ የሚያልፉ ሰዎች ከተሽከርካሪያቸው በመውረድ፤ በእግራቸው የሚጓዙትም ባሉበት በመቆም ለሰንደቅ ዓላማችን ያላቸውን ክብር ሲገልፁ ኖረዋል። ይህ ሥነ-ሥርዓት ለዘመናት ሲካሄድበት የነበረው ቦታ በመልሶ ማልማት ሳቢያ በመፍረሱ ምክንያት ሥነ-ሥርዓቱ ለስምንት ወራት ከተቋረጠ በኋላ፣ በከተማዋ በሚገኝ አዲስ ቦታ ላይ ሥነ-ሥርዓቱን ለማስቀጠል ልዩ ፕሮግራም ተዘጋጀ። (በነገራችን ላይ ከአራት ዓመት በፊት ወደነቀምቴ ከተማ የተጓዘ ወዳጄ ተመሳሳይ ሁነት ማስተዋሉን አጫውቶኛል፡፡)
ነሐሴ 2004 ዓ.ም፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ የጋዜጠኛ ሳምሶም ማሞን የክስ ሂደት ለመከታተል በሄድኩበት አጋጣሚ በስህተት የታደምኩበት ችሎት ነበር። ችሎቱ በሚሰየምበት ግራና ቀኝ ሁለት ባንዲራዎች ተሰቅለዋል። የሰንደቁ ልሳን (የመስቀያ ጫፍ) ግማሽ ክብ ቅርፅ ሊኖረው ሲገባ፣ የጦር ቅርፅ የያዘ ሲሆን የሰንደቅ ዓላማው ዙሪያም ልሙጥ መሆን ሲገባው ወርቃማ ከለር ያለው ዘርፍ ተሰፍቶበታል። ይህ ችሎት በወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የሚታይበት ችሎት መሆኑን ልብ ይበሉ። ተመሳሳይ ባንዲራዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውስጥም መኖሩ፤ አዋጁ በተደነገገበት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዋና በር ቅፅር ግቢ የሚገኘው የሰንደቅ ልሳንም የጦር ቅርፅ የያዘ መሆኑን ሳስበው ትዝብቴን አጉልቶታል።
ጳጉሜ 04/2004 ዓ.ም፡- የቀድሞ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊን ዜና እረፍትን ተከትሎ የታወጀው ብሄራዊ የሐዘን ቀን ከተጠናቀቀ 7 ቀናት አልፈዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ት/ት ቤት ቅፅር ግቢ የተሰቀለውን ሰንደቅ ዓላማ ግን የሐዘን ቀኑ መጠናቀቁን አያመላክትም - አሁንም ዝቅ ብሎ ይውለበለባል። ሁኔታውን እሰስከመጨረሻው ለማየት ዝምታን መረጥኩ። ለጥቂት ቀናት በዚሁ ሁኔታ ቆይቶ ከፍ ብሎ መውለብለብ ጀመረ። በነገራችን ላይ የጠ/ሚ/ሩ አስከሬን አቀባበል ከተደረገለት ጊዜ ጀምሮ እስከግብአተ መሬታቸው ድረስ አስከሬናቸው ከለበሰው ሰንደቅ ዓላማ ጀምሮ የተፈፀሙ ግድፈቶች አያሌ ነበሩ። ያንን የሐዘን ድባብ ላለማስታወስ ብቻ ጉዳዩን ሳላነሳ ማለፍን መርጫለሁና አትታዘቡኝ።
መስከረም 01/2005 ዓ.ም፡- በመስኮብ የተደረገውን የኢትዮጵያ አበባ የንግድ ትርዒት መነሻ በማድረግ ከስፍራው በተጓዘ ጋዜጠኛ አማካኝነት በኢ.ቴ.ቪ. በቀረበ ዜና ላይ በጉዳዩ ላይ ገለፃ ለመስጠት በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ አምባሳደር በቲቪ መስኮት ብቅ ሲሉ ማብራሪያውን ከሚሰጡበት ቢሮ ከበስተኋላቸው ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ተመለከትኩኝ። አሁንም ግርምትና ድንጋጤ ተፈጠረብኝ። በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ያረፈበት ቀለም ከአዋጁ አንፃር ሲታይ ደማቅ ሰማያዊ መደብ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አይወክልም።
ጥቅምት 26/2005 ዓ.ም፡- ጥቅምት 19 የተከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ በዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ የተሰቀሉት ባንዲራዎች በአዋጁ መሰረት ጥቅምት 20 ምሽት 12፡00 መውረድ ሲገባቸው፣ ሜክሲኮና ብሔራዊ ቲያትር አደባባዮች፣ ከለገሃር ወደ ቸርችል ጎዳና እና ከለጋሃር በመስቀል አደባባይ ወደብሔራዊ ቤተ-መንግስት በመንገድ ግራና ቀኝ የተሰቀሉት ባንዲራዎች አስታዋሽ አጥተው፣ አብዛኛዎቹም ከታሰሩበት ዘንግ ላይ በከፊል ተፈትተው እስከ ጥቅምት 26 ድረስ ተሰቅለው ተመለከትኳቸው።
የደሴ ከተማ ተሞክሮ ለሰንደቅ ዓላማ የተሰጠን ዘመን ተሸጋሪ ፍቅርና ክብር ሲያሳየኝ በተለይ የፍ/ቤቶቹ እና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትዝብቴ ደግሞ አዋጁን ለማክበርና ለማስከበር ዋነኛ ተዋናዮችም ጭምር የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁ.654/2001 ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ሰንደቅ ዓላማችን ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ከተደረጉ ጥረቶች አንዱ፣ በአዋጁ አንቀፅ 4 የተገለፀውና በየዓመቱ መስከረም 2ኛ ሳምንት ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ነው። የዘንድሮው ክብረ በዓል በልዩ ምክንያት ወደጥቅምት ወር ተዛውሮ ተከብሯል። ይህንን በዓል በየዓመቱ ማክበሩ ‘የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነት እና የህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት መገለጫ’ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችንን እንዴት ማክበር እንዳለብን ግንዛቤ ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ለተነፈገው ሰንደቅ ዓላማችን ተገቢውን ቦታ ለመስጠት ጠቃሚ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
የመንግስት አስፈፃሚ፣ ሕግ አውጪና ሕግ ተርጓሚ አካላት፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ድርጅቶች፣ ዜጎች … ወዘተ ሰንደቅ ዓላማውን በዓመት አንድ ቀን ከመዘከር ባሻገር በአዋጁ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማስፋት፣ በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት የሚፈፀሙትን በአዋጁ የተከለከሉ (የወንጀል ቅጣት የሚያስከትሉና የማያስከትሉ) ድርጊቶችና ግድፈቶችን በማረም ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅዖ እንድናደርግ ይረዳ ዘንድ በተደጋጋሚ ካስተዋልኳቸው መካከል የሚከተሉትን እነሆ፡-
ቀለምና መጠን፡- የአዋጁ አንቀፅ 6(2) ቀለማቱ ብሩህ እና መሰረታዊ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል። በአንቀፅ 6(3)፣10 እና 11 ስር ደግሞ የሰንደቅ ዓላማው ወርድ የቁመቱ እጥፍ መሆን እንዳለበት በመግለፅ ስድስት የሰንደቅ ዓላማ መጠኖችን አስቀምጧል። ለምሳሌ በመ/ቤቶች፣ በከፍተኛ ት/ት ተቋማትና ድርጅቶች የሚሰቀል ሰንደቅ ዓላማ 135 ሣ.ሜ. በ270 ሣ.ሜ. እና በትላልቅ ህንፃዎች ምድር ቤት ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶችንና የንግድ ቤቶች ደግሞ 105 ሣ.ሜ. በ210 ሣ.ሜ. መሆን አለበት። ሆኖም በዝናብ፣ በፀሐይ፣ በንፋስ፣ በአቧራና በእርጅና ምክንያት ቀለማቸው የፈዘዘና የተቀደዱ እንዲሁም መጠናቸው ከአዋጁ የሚቃረን ሰንደቅ ዓላማዎችን በተለያዩ ቦታዎች ማየቱ የተለመደ ነው። ትክክለኛውን ቀለምና መጠን አለመጠቀም በአንቀፅ 23(3) መሰረት የተከለከለና ለግለሰቦች እስከ 3000 ብር ለድርጅቶች እስከ 6000 ብር የገንዘብ መቀጮ ወይም አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ እንደሆነ በአንቀጽ 24(2) እና (3) ስር ተደንግጓል።
ዓርማ፡- አንቀፅ 6(1) እና 6(4) የዓርማው ቀለም ሰማያዊ መደብ እንደሆነ መጠኑ ደግሞ “በሰንደቅ ዓላማው መካከል ላይ የሚያርፈው የክቡ ዙሪያ የአረንጓዴውንና የቀዩን ቀለማት ቁመት አጋማሽ አክሎ ይሆናል” በማለት ደንግጓል። የኮከቡም ሆነ የጨረሮቹ አሰፋፈርም ሥርዓት ተበጅቶለታል። ሆኖም አንዳንድ ባንዲራዎች ላይ የምናየው ዓርማ በዘፈቀደ የሚለጠፍ በአብዛኛውም በአረንጓዴው ቀለም ስር እና በቀዩ ቀለም አናት ላይ (በቢጫው ሜዳ ላይ ብቻ) የሚውል ነው። መስመሮቹም ቢሆን በእጅ ከተሳሉ ጀምሮ በወረቀት ላይ ታትመው እስከተለጠፉ ድረስ ናቸው። የሰንደቅ ዓላማው ስዕላዊ መግለጫን በሚሳየው አንቀፅ 9 ላይ ደግሞ ሰማያዊው ቀለም ብሩህ እንጂ ደማቅ ሰማያዊ አለመሆኑን ያሳያል። በአንቀፅ 23(6) ስር ደማቅ ሰማያዊ የያዙ ዓርማዎችንም ሆነ ትክክለኛውን የአርማ መጠን የሌላቸውን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም የተከለከለ ነው።
ልሳን (ጫፍ)፡- የተሻረው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 48/1989 - እንደተሻሻለው) በአንቀፅ 10 ስር የሰንደቁ ልሳን (መስቀያ ዘንግ/ምሰሶ ጫፍ) የጦር ቅርፅ ይኖረዋል ይል ነበር። አዲሱ አዋጅ ግን ይህንን በማሻሻል በአንቀፅ 13 ስር የሰንደቁ ልሳን የክብ አምሳል (ቅርፅ) እንደሚኖረው ደንግጓል። በአብዛኞቹ መንግስታዊ ተቋማት ግቢ ውስጥ የምናያቸው የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ ምሰሶዎች በደርግ ዘመን የነበሩ ሲሆን ልሳናቸው የጦር ቅርፅ እንደያዘ አሁንም ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀልባቸዋል። አዳዲስ በሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ መ/ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ድርጅቶች የሚሰቀሉ ሰንደቅ ዓላማ ልሳኖች የጦር ቅርፅ የያዘ እንደሆነ በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል።
አንድነት፡- የአሁኑ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት በነበረው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰንደቅ ዓላማው ሶስት ዓይነት እንዲሆን ታስቦ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ቀለማቱና ዓርማው እንዳለ ሆኖ ዙሪያውን ዘርፍ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ነበር። ሆኖም አዋጁ ሲፀድቅ በአንቀፅ 16 ስር ሰንደቅ ዓላማው አንድ ዓይነት ብቻ እንደሆነ በመደንገግ ረቂቅ ሐሳቡን ውድቅ አድርጎታል። እስከአሁን ድረስ በተለይ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ፅ/ቤቶች ጠረጴዛ ላይና በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያ ልዑካኖች በሚቀመጡበት ቦታ ላይ ዘርፍ ያላቸው ሰንደቅ ዓላማዎችን በተደጋጋሚ እናስተውላለን።
መስቀያና መውረጃ ጊዜ፡- በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በሌሎች አስፈፃሚ አካላት ፅ/ቤቶች፣ በፍ/ቤቶች፣ በት/ት ቤቶች (ጠዋት ላይ የተማሪዎች ሰልፍ የሚካሄድባቸውን ት/ት ቤቶችን ሳይጨምር) እና በፖሊስ ተቋማት ሰንደቅ ዓላማው ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ተሰቅሎ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት መውረድ እንዳለበት በአንቀፅ 15(1) ስር ተደንግጓል። በተለምዶ የምናየው ግን ባንዲራዎቹ እዛው ያድራሉ (ምሳሌ አራት ኪሎ ፖስታ ቤት ህንፃ አናት ላይና ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰዓቱ አናት ላይ ያሉት ባንዲራዎች) አልያም ከማውረጃና መስቀያ ሰዓት አርፍዶ ሲሰቀልና ሲወርድ ይስተዋላል። በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 3 ላይም በበዓላት ወቅት ሰንደቅ ዓላማው ከዋዜማው ጀምሮ እስከበዓሉ ማግስት ተሰቅሎ፣ በበዓሉ ማግስት ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ መውረድ እንዳለበት ቢደነገግም፣ ለተለያዩ ክብረ በዓላት የተሰቀሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ሰንብተው ይወርዳሉ። አምና የተከበረው የብሔር ብሄረሰቦች ቀን ላይም በማግስቱ ምሽት 12፡00 ሰዓት መውረድ የሚገባው ሰንደቅ ዓላማ ሶስት ቀን ቆይቶ መውረዱን አስታውሳለሁ።
ከክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሲሰቀል፡- በአንቀፅ 18 መሰረት የሪፐብሊኩ (የኢትዮጵያ) ሰንደቅ ዓላማ ከክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሲያዝ/ሲሰቀል እንደሚከተለው መሆን አለበት። 1ኛ ከአንድ ክልል ሰንደቅ ጋር ሲሰቀል የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ በስተቀኝ ይሆናል። (በአዋጁ አንቀፅ 2(4) መሰረት ቀኝ ማለት አንድ ሰው ፊቱን ወደ ተመልካች አቅጣጫ በማድረግ ባንዲራው ከሚሰቀልበት ቦታ መሀል ሲቆም የሚኖረው የቀኝ እጅ አቅጣጫ ነው።) 2ኛ ከሁለት ክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሲያዝ ወይም ሲሰቀል የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ከመሀል ሆኖ በቁመቱ ልክ ከሁለቱ ሰንደቅ ዓላማዎች በላይ ይውላል። ቅደም ተከተሉንም በተመለከተ የክልሎቹ ሥያሜ የአማርኛ ፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሰረት ቀዳሚው በስተቀኝ ይሆናል። ለምሳሌ የሱማሌና የቤኒሻንጉል ክልል ሰንደቅ ዓላማዎች ከሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ቢሰቀሉ ከ‘ሱ’ እና ከ‘ቤ’ የሚቀድመው ‘ሱ’ በመሆኑ የሱማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በስተቀኝ ይውላል። 3ኛ ከሁለት ክልልሎች በላይ ሰንደቅ ዓላማ ሲኖር ደግሞ የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም በስተቀኝ ይውልና የተቀሩት ሰንደቅ ዓላማዎች የክልሎቹ ሥያሜ የአማርኛ ፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሰረት ይደረደራሉ። ለምሳሌ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የሱማሌ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ሰንደቅ ዓላማዎች ቢኖሩ የሪፐብሊኩ ሰንደቅ በቀኝ ይሆንና ‘አ’ን፣ ‘ሐ’ን፣ ‘ሱ’ን፣ ‘ኦ’ን እና ‘ት’ን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ሐረሪ፣ ሱማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ትግራይ በማድረግ በስተግራ ይደረደራሉ።
አዋጁ ይህንን ቢልም አዘወትረን የምናየው ግን የክልሎችን ቅደም ተከተል በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 47(1) ላይ በተቀመጠው መሰረት ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ … ወዘተ በማድረግ ሲሰቅሉ ይስተዋላል። (ይህ አንቀፅ የክልሎችን ዝርዝር ከመግለፅ ባሻገር ክልሎችን አስገዳጅ በሆነ ቅደም ተከተል የማስቀመጥ ዓላማ የለውም።) ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የቀይሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ጋር የተሰቀሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ናቸው። አንዳንዴም የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ ከመሀል አድርጎ ሌሎቹን በክብ ቅርፅ መደርደር (ለምሳሌ ጃን ሜዳ አካባቢ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ካምፕ ውስጥ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤ/ት የዘንድሮ የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ በም/ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ከቀድሞው ጠ/ሚ/ር ፎቶግራፍ ጋር የተደረደሩ ባንዲራዎች)ና የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ መሀል አድርጎ የክልሎቹን ሰንደቅ ዓላማ በግራና ቀኝ በቀጥታ መስመር መደርደር ይስተዋላል። በነገራችን ላይ አዋጁ ከሁለት በላይ ክልሎች ሲኖሩ የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ ከሌሎቹ ከፍ ብሎ ስለመውለብለቡ ምንም አይገልፅም።
የሰንደቅ ዓላማ አዋጁን ለመደንገግ አስፈላጊ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰንደቅ ዓላማን የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመወሰን እንደሆነ በአዋጁ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል። ይህ ዓላማ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ አዋጁን ትኩረት ሰጥቶ በማክበርና በማስከበር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ሕጎች ከሚሻሩባቸው መንገዶች አንዱና ያልተለመደው መንገድ ሕጎችን በተግባር እንዳይውሉ በማድረግ ወይም በዝምታ መሻር ነው። ለምሳሌ የበ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ህግ ስለ ስሞች የወጣው ሕግ የምንጠቀምባቸው ስሞች እንደምዕራባውያን የቤተሰብ ስም መያዝ አለበት ቢልም ይህ ግን እስከአሁን ተፈፅሞ አያውቅም። ስለዚህ የሰንደቅ ዓላማው አዋጅም ይህ እድል እንዳይደርሰው ከወዲሁ ተገቢው ቦታ ሊሰጠው ይገባል።
ሰንደቅ ዓላማውን ለማክበርና ለማስከበር ከዜጎች የሚጠበቀውን ቁርጠኝነት ማሳያ የሚሆን አንድ የፍ/ቤት ውሳኔን ልጥቀስ። ከጥቂት ወራት በፊት በኮ/ቀ/ክ/ከተማ በሚገኝ አንድ ት/ቤት ውስጥ የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት ሲካሄድ በቦታው የነበሩ ሁለት የክ/ከተማው የወንጀል መከላከል የፖሊስ አባላት ከተቀመጡበት ቦታ አለመነሳታቸውን የተመለከቱ የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ከተቀመጡበት በመነሳት ለሰንደቅ ዓላማው ክብር እንዲሰጡ በትህትና ቢጠይቋቸውም “ደክሞናልና አንነሳም አሻፈረን” በማለት መልስ ሰጧቸው። በፖሊሶቹ ምግባር ያዘኑት ሰራተኞች ጉዳዩን ወደሕግ ቦታ በማድረሳቸው፣ ፖሊሶቹ በወንጀል ተከሰው የስድስት ወር እስራትና የ1000 ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል። ይህንን ውሳኔ ከሰማሁኝ በኋላ በተለያዩ ክልል ውስጥ የሚገኙ ፖሊስና ዓቃቢያነ ሕግ የሰንደቅ ዓላማ አዋጁ ተጥሷል የሚል ክስ ወይም ጥቆማ ደርሷቸው እንደሆን ለማጣራት ስሞክር፣ አንድ እንኳን አጋጣሚ ለማስታወስ ሲቸገሩ አስተውያለሁ፡፡ ለመሆኑስ የወንጀል ምርመራ ይጣራ ቢባል ከከፍተኛ የመንግስት መ/ቤቶች እስከ በመንገድ ዳር የምትገኝ ኪዮስክ፣ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን እስከ ለፍቶ አዳሪ ግለሰብ በወንጀል ከመጠየቅ ማን ይተርፍ ነበር?
የሰንደቅ ዓላማን በዓመት አንድ ቀን ብቻ በማክበር አዋጁን ማስከበር የማይታሰብ ነው። የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሰፉ ስራዎች መስራት በ365ቱም ቀናት ሊቀጥል ይገባል። “መፅሐፉን እንጂ ቄሱን አትይ” የሚል ብሂል ለህግ ጉዳይ ስለማይሰራ “ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት እንሰራለን” የምንል ከከፍተኛ እስከዝቅተኛ አመራር ያለን የመንግስት ሰራተኞችና ኃላፊዎች ግንዛቤያችንንና ቢሯችንን እንፈትሽ። ባንዲራችን ተገቢውን ክብር ተነፍጓል ብለን የተቆጨን ሰዎችም ቢሆን ለባንዲራችን ያለንን ፍቅር ከትችት ባለፈ በተግባራዊ እንቅስቃሴም እንግለፀው። ከሁላችንም የሚጠበቀው እንደደሴ ነዋሪዎች ወይም እንደት/ት ቤቱ ሰራተኞች መሆን ነው የሚል እምነት አለኝ - ሕግን አክብሮ ማስከበር። ስለዚህም በኔ እምነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ለመስራትም ሆነ በዚህ በማይመለሱት ላይ የወንጀል ምርመራ ለመጀመር ሰዓቱ አሁን ይመስለኛል፡፡ ለዘመናት በነፃነት ለመኖራችን አንዱ ምክንያት ለአገራችን ያለን ፍቅር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። የአገራችንን ፍቅር ከሚገለፅበት መንገድ ግንባር-ቀደሙ ለባንዲራችን ተገቢውን ክብር መስጠት ነው። ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይሉ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ባስቃኘበት ‘ቀያይ ተራሮች’ የሚል መፅሐፉ ላይ፣ የፆረና ግንባር ውጊያ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድል አድራጊነት መጠናቀቁን አስመልክቶ በገፅ 322 የሚከተለውን ፅፏል፡- “ከፆረና ማዶ … በጣም ርቆ የድል ሰንደቅ ተተከለ።” ይላል ለአገር ክብርና ሉዓላዊነት የተከፈለው መስዋዕትነት መገለጫ ከድል በኋላ የተሰቀለው ሰንደቅ ዓላማችን መሆኑን ሲገልፅልን።
የነፃነታችን ምልክት፣ የአንድነታችን ዓርማና የፅናታችን መለያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችንን በማክበርና በማስከበር ለአገራችንን ያለንን ፍቅርና ክብር የምንገልፅ የተግባር ሰዎች ያድርገን።
አድራሻ፡- ፀሐፊውን በFacebook አድራሻ Asiyo Dan@News Paper ወይም በEmail አድራሻ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይችላሉ።።

Read 5087 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 12:49