Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 10:54

የተዛባው የመድሃኒት አጠቃቀማችን!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአለም ጤና ድርጅት መድሃኒቶችን ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ በተለያየ አይነትና መጠን ተዘጋጅተው በሽታን ለማከም የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ናቸው ሲል ይተረጉማቸዋል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በተለያየ መንገድ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ከገቡ በኋላ ለበሽታ ፈውስ ቢያስገኙም የሚያስከትሉት ተያያዥ የጐንዮሽ ጉዳት አላቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ የሚያደርጋቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፣ ሁሉም መድሃኒቶች የጐንዮሽ ጐጂ ባህርያት አሏቸው፡፡ መድሃኒቶች በጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅትም ይኸው የጐንዮሽ ጐጂ ባህሪያቸው ይጠናል፡፡

 

ጠንከር ያለ የጐንዮሽ ጉዳት የማያስከትል ከሆነም በጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም ሆኑ በየፋርማሲው በመድሃኒት ሽያጭ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎች፣ መድሃኒቶችን ለህሙማን በሚሸጡበት ወቅት ስለሚያስከትሉት የጐንዮሽ ጉዳትና ስለመድሃኒቶቹ አጠቃላይ ባህርይ ለህመምተኛው መንገር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሽያጭ ያቀረቧቸው መድሀኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈባቸውና በአቀማመጥ ችግር ለብልሽት ያልተጋለጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ህብረተሰቡ በአብዛኛው ትክክለኛ የሆነ የመድሃኒት አጠቃቀምን የመከተል ባህርይ የለውም፡፡ 
ጤናማ ያልሆነውና ህይወትን ለአደጋ የሚያጋልጠው የመድሃኒት አጠቃቀማችን፣ ብዙዎችን ለከፍተኛ ችግር ሲዳርግ ተስተውሏል፡፡ ከእነዚህ ህገወጥ የመድሃኒት አጠቃቀማችን መካከል መድሃኒቶችን ያለሐኪም ትዕዛዝና ከማዘዣ ወረቀት ውጪ ገዝቶ መጠቀም፣ የታዘዙልንን መድሃኒቶች በአግባቡ አለመጠቀም፣ መድሃኒቱን ያለጊዜው ማቋረጥ ወይም ከትዕዛዝ በላይ መውሰድ፣ የመድሃኒቶችን የመጠቀሚያ ጊዜ ሳይመለከቱ መድሃኒቶችን ገዝቶ መውሰድና ከመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲዎች ወይም መደብሮች ውጪ መድሃኒቶችን ከየሸቀጣሸቀጥ ሱቆች እየገዙ መጠቀም ይገኙባቸዋል፡፡
መድሃኒቶች በዓለም አቀፍ የመድሃኒት ማምረቻ ስንታንዳርድ መሠረት ተመርተው ለገበያ እስከሚቀርቡበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃሉ፡፡ መድሃኒቶቹ የሚቀመጡበት የሙቀት እና የብርሃን መጠንም እንደዚሁ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡
አንድ መድሃኒት መድሃኒት ለመባል የሚያስችለውን ንጥረ ነገሮች በተገቢው መጠን መያዝ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች እንደመድሃኒቱ አይነት በፀሐይ ብርሃን ወይንም በሙቀት ሊበላሹና መድሃኒቱን ከጥቅም ውጪ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ መድሃኒቱ በሽታውን በመፈወስ የሚፈለገውን ውጤት ካላመጣና የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈ መድሃኒቱ ፈዋሽነቱን አጥቷል ይባላል፡፡ የማንኛውም መድሃኒት የመጠቀሚያ ጊዜ ወርና ዓመተ ምህረቱ በግልጽና በቀላሉ ሊነበብ በሚችልበት ሁኔታ ሊፃፍ ይገባዋል፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች በምንም ሁኔታ በጥቅም ላይ ሊውሉ አይገባቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛው ምክንያት መድሃኒቶቹ ውስጥ ያለው ኬሚካል በጊዜ ብዛት ስለሚለወጥና ይህም ለሰውነታችን እጅግ አደገኛ የሆነ ንጥረ ነገር ለመፍጠር ስለሚያስችለው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መድሃኒቱ ከተሰጠው ጊዜ በላይ በመቆየቱ ምክንያት የመፈወስ አቅሙን ስለሚያጣ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ስለዚህም በመድሃኒት ቁጥጥር ተግባር ላይ የተሰማሩ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች በገበያ ላይ እንዳይውሉና መድሃኒቶቹ በአግባቡ መወገዳቸውን መከታተልና መቆጣጠር ይኖርባቸዋል፡፡
ሌላው ከመድሃኒት አጠቃቀማችን ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደውና እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ መድሃኒቶችን ያለ ሐኪም ማዘዣ መግዛትና ከየሸቀጣቀጥ ሱቆች እየገዙ መጠቀም ናቸው፡፡
በመሠረቱ አብዛኛዎቹ መድሃኒቶች ያለ ሐኪም ማዘዣ ፈጽሞ ሊሸጡ የማይገባ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ መድሃኒቶች ደግሞ ከዚህም በዘለለ የተለየ የመድሃኒት ማዘዣ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ማንኛውም ሐኪም ሊጽፋቸው አይችልም፡፡ በበሽታው የተለየ ስልጠናና ትምህርት የወሰዱና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሐኪሞች ብቻ እነዚህን መድሃኒቶች እንዲጽፉ ይፈቀድላቸዋል፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች ሱሰኝነትን ወይንም የመድሃኒት ጥገኛ መሆንን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ያለሃኪም ትዕዛዝ መሸጥ በህግ ያስቀጣል፡፡ በእርግጥ ያለ ሐኪም ማዘዣ የሚሸጡ የመድሃኒት ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ የበሽተኛውን ህመም ከማስታገስ የዘለለ ውጤት የማያመጡ ናቸው፡፡
ለራስ ምታት፣ ለጉንፋን ለአለርጂና ለመሳሰሉት ቀላል ህመሞች የፋርማሲ ባለሙያው ለህመምተኛው ሊሰጣቸው የሚችል መድሃኒቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የህመም አይነቶች ግን ለሌላ ውስብስብ እና ትልቅ የጤና ችግር መከሰት ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ህመምተኛው ማስታገሻውን ወስዶ ትንሽ ከተሻለው በኋላ ህመሙ ተመልሶ የሚከሰትበት ከሆነ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንዳለበት የፋርማሲ ባለሙያው ሊነገርው ይገባል፡፡ ሌላው በመድሃኒት አጠቃቀማችን ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ ተግባር፣ በራሳችን ፈቃድና ፍላጐት ከየፋርማሲውና ከየሸቀጣሸቀጥ መደብሩ እየገዛን የምንወስደው የመድሃኒት አጠቃቀም ነው፡፡ ይህ ተግባር በአብዛኛው ከከተማ ይልቅ በክልል ከተሞችና በገጠር አካባቢዎች ይስተዋላል፡፡ ከሐኪም ትዕዛዝ ውጪና ያለ ምርመራ መድሃኒቶችን እየገዙ መጠቀም መድሃኒቶቹ ከበሽታው ጋር በመላመድ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መድሃኒቶቹ ፈውስ ከሚሰጡበት በሽታ ይልቅ ሌላ በሽታዎችን እንዲከሰት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ከየሸቀጣሸቀጥ ሱቆች እየተገዙ የሚወስዱት መድሃኒቶችም በአቀማመጥ ምክንያት በቀላሉ ለብልሽት የተጋለጡ ስለሚሆኑ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡
አብዛኛዎቻችን መድሃኒቶችን በተሰሩበት አገርና በሚሸጡበት ዋጋ ልክ የፈውስ መጠናቸውን እንገምታለን፡፡ ይህ ትክክለኛ ያልሆነ ግምትና አስተሳሰብ ነው፡፡ መድሃኒቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ እና አለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟሉ እንዲሆኑ የሚያስችለውን “ፋርማ ኮፒያ” የተባለ መጽሐፍ መሠረት አድርገው እስከተሰሩ ድረስ ሁሉም መድሃኒቶች አንድ ዓይነት የመፈወስ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ መድሃኒቶች በሚመረቱበት ወቅት ለተፈበረኩበት አገር የባለቤትነት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው እስከ 15 ዓመት ሊደርስ የሚችል የህግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ የጥበቃ ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ ወይም አምራች ኩባንያው ከሌሎች አገራት ኩባንያዎች ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሠረት፣ ሌሎች አገራትም የመድሃኒቱን ስታንዳርድ ጠብቀው ሊያመርቱ ይችላሉ፡፡ መድሃኒቱ ከመጀመሪያው መድሃኒት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለውና የመፈወስ አቅሙም እኩል ነው፡፡ አምራች ድርጅቶቹ መድሃኒቶቹን ካመረቱ በኋላ የፈለጉትን ስምና መጠሪያ ይሰጡታል፡፡
በዚህ ምክንያትም ለአንድ አይነት በሽታ የሚታዘዝና አንድ አይነት የመፈወስ አቅም ያለው መድሃኒት በተለያዩ የብራንድ ስያሜዎች ገበያ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ ጊዜም በመድሃኒቱ የመሸጫ ዋጋ ላይ መለያየት ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በበለፀጉት አገራት የሚገኙ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች መድሃኒቱን በሚያመርቱበት ወቅት ለሠራተኛ፣ ለታክስና ለግብአት ቁሳቁሶች መግዣ የሚያወጡት ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ዋንኛ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ወጪ በታዳጊ አገራት ላይ ስለሚቀንስ የአገራቱ የመድሃኒት መሸጫ ዋጋቸው ሊለያይና ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ይህ ግን ከመድሃኒቱ የመፈወስ አቅም ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ከመድሃኒቱ ፈዋሽነት ጋር የሚያያይዘው አንዳችም እውነት እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እናም መድሃኒቶችን በአግባቡና ከሐኪም በሚሰጠን ትዕዛዝ መሠረት መውሰዳችንን ከማረጋገጣችን ውጪ መድሃኒቶቹ ስለተሰሩባቸው አገራት ልንጨነቅ አይገባም፡፡

Read 4912 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:35