Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 17 November 2012 11:59

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ተወኝ
ላታስታምም አትመመኝ
ላትወስደኝ አታንጠልጥለኝ
ይቅር፣ አንጀቴን ቁረጠኝ
ጋሽዬ፣ አልወድሽም በለኝ፡፡
እጅ እጅ አልበል አታባከነኝ
ባክህ፣ ወንድ ነው ቆራጡ፣ እንትፍ - እርግፍ አርገህ ተወኝ፡፡
አየህ፣ እንዳንተ አባት አለኝ
ሴት በወለድኩ ተዋረድኩሀ፣ ረከስኩ ቀለልኩ እሚለኝ፣
እኔም እንዳንተ እህት አለኝ
ሥጋሽን ሳይሆን ልብሽን ፣ ከፍተሽ ጥለሽ ነው እምትለኝ
እና ተወኝ፣ ባክህ ተወኝ፤
እንዳንተ እኔም አለኝ እናት

የሴት ቁንጮ እምመስላት 
ጐረቤት ፊት እምታፍር፣ እንዲህ ሆነችልሽ ሲሏት!...
እና፣ አልሆንሽም በለኝ
ባክህ አንጀቴን ቁረጠኝ…
ፍቅር እንደሁ የኔ ይበቃል፣ ላንተም ለኔም እኔው ልውደድ
ከዘመድ ግንባር ደብቄ፣ እኔ የብቻዬን ልንደድ፣
ብቻ፣ ከወጥመድህ ለየኝ
አልችልህም፣ ንቀህ ማረኝ
ካንተም ከስሜም ከቤቴም፣ ያጣሁ ብኩን አታድርገኝ፣
ባክህ፣ አንጀቴን ቁረጠኝ
ተወኝ፣ ተወኝ፣ ተወኝ፡፡
(ፀጋዬ ገ/መድህን “እሳት ወይ አበባ”)


Read 6023 times

Latest from