Saturday, 17 November 2012 12:32

የዲሞክራቲክና የሪፐብሊካን ፓርቲዎች የሀገራችን ፓርቲዎች ቢሆኑ ኖሮ …

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሰሞን የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአርባ አራተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በባራ ኦባማ አሸናፊነት ተጠኗቋል፡፡ በ2008 ዓ.ም በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲውን ወክለው በመቅረብ ተቀናቃኛቸውን የሪፐብሊካኑን ተወካይ ጆን ማኬይን በሠፊ ልዩነት በማሸነፍ አርባ አራተኛው የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ባራክ ኦባማ፤ ዘንድሮም የሪፐብሊካኑን እጩ ሚት ሮምኒን በማሸነፍ በድጋሚ በፕሬዚዳንትንት ተመርጠዋል፡፡ ይህኛው ምርጫ ልብ አንጠልጣይና ከባድ የምረጡኝ ፉክክር የተደረገበት፣ በአሜሪካ ታሪክም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት እጅግ ውዱ የምርጫ ዘመቻ ነበር፡፡

ከምርጫው በፊት በነበሩት የምርጫ ቅስቀሳዎች ተፎካካሪዎቹ ያደረጉትን እንቅስቃሴዎች መሠረት በማድረግ የተደረጉ የህዝብ አስተያየት መለኪያዎች ሁለቱም እጩዎች አንገት ላንገት መያያዛቸውን ያመለክቱ ስለነበር ማን ያሸንፍ ይሆን የሚለው ነገር በእርግጥም ልብ አንጠልጣይ ነበር፡፡ እንዲያውም በርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ሚት ሮምኒ ሳያሸንፍ አይቀርም ብለው በከፍተኛ ደረጃ ተማምነው ነበር፡፡ ምርጫው እየተካሄደ በነበረበት የመጀመሪያዎቹ ሰአታት የሚወጡት ውጤቶች ሚት ሮምኒ እየመሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ስለነበር ብዙዎች የደጋፊዎቻቸው ግምት የሚሰምር መስሎዋቸው ነበር፡፡ 
የአብዛኞቹ ግዛቶች የምርጫ ውጤት መታወቅ ሲጀምር ግን ነገሮች ሁሉ በብርሀን ፍጥነት ተለዋወጡ፡፡ አሸናፊውን ለመለየት ወሳኝ የሆነ ቁልፍ ሚና አላቸው እየተባለ ይነገርላቸው የነበሩት እንደ ኦሀዮ የመሳሠሉት ግዛቶች የምርጫ ውጤት ከመገለፁ አስቀድሞ አርባ አራተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ተቀናቃኛቸውን በሰፊ “የኢሌክቶራል ቮት” ልዩነት በማሸነፍ በድጋሚ መመረጣቸው መረጋገጥ ቻለ፡፡
ምርጫው ከተጠናቀቀ ከአራት ቀናት በኋላ ዘግይታ የኦባማን አሸናፊነት ይፋ ያደረገችው ፍሎሪዳ ብትሆንም መዘግየቷ በምርጫው ውጤትና በኦባማ አሸናፊነት ላይ ያመጣው አንዳች አይነት ለውጥ አልነበረም፡፡
የምርጫው ውጤት አሸናፊውን ወገን በይፋ እንዳሳወቀ አሸናፊው ወገን ያሸናፊነት ደስታውን፣ ተሸናፊው ወገንም የተሸናፊነት ሀዘንና ሰቀቀኑን የገለፀበት ሁኔታ የምርጫ ፉክክሩን እንዳካሄዱበት አይነት እጅግ የሰለጠነና በጨዋነት የተሞላ ነበር፡፡
ይህ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በእርግጥም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከተካሄዱት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ሁሉ በጨዋነት የተሞላ፣ ድንቅና እልህ አስጨራሽ የምርጫ ፉክክር የተካሄደበት ነበር፡፡ ሚት ሮምኒም ሆኑ ባራክ ኦባማ አንዳቸው አንዳቸውን ከመዝለፍና ከማጥላላት በመቆጠብ በዋና ዋና ሀገራዊና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር፣ በስርአት የታነፀ የስነምግባር ባለቤት መሆናቸውን ያስመሠከሩበት ምርጫ ነው፡፡
የሁለቱም ወገን የምርጫ አስፈፃሚ ቡድኖችም አንዳቸው ለአንዳቸው ያሳዩት ስሜት ልክ እንደ አለቆቻቸው ሁሉ መልካም ስነምግባርን የተከተለ ነበር፡፡
አሸናፊው ቡድን አሸናፊነቱ በፈጠረለት ከፍተኛ የድል አድራጊነት ስሜት ሳያብጥና ሳይኩራራ፣ ለተሸናፊው ቡድን መልካም ምኞቱን ሲገልጽ፣ ተሸናፊው ቡድንም መሸነፍ በፈጠረበት የመረታት ስሜት ልቡንና ስሜቱን በምሬት ሳያጐሽ አሸናፊውን ወገን “እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት በመልካም ምኞት ተሠናብተዋቸዋል፡፡
በዋናዎቹ እጩ ተፎካካሪዎች ዘንድ የታየውም ልክ እንዲሁ ነው፡፡ ባራክ ኦባማን ለማሸነፍ ላለፉት አራት አመታት ዋና ነገሬ ብለው ሲዘጋጁ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ሚት ሮምኒ፤ ጠቅላላው የምርጫ ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት መሸነፋቸውን እንዳወቁ ወዲያውኑ ስልክ በመደወል ፕሬዚዳንት ኦባማን “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት ቀጣዩ የስራ ዘመናቸው የተቃና እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀውላቸዋል፡፡ በምርጫው መሸነፋቸውን በይፋ በገለፁበት ንግግርም፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ በቀጣዩ የአራት አመት የስልጣን ዘመናቸው ስራቸው እንዲቃናላቸውና ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንደሚመኙላቸውና ለዚህም እንደሚፀልዩላቸው ተናግረዋል፡፡
ደጋፊዎቻቸው አርባ አራተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ለመጠቆም “ሚስተር ፎርቲ ፎር” እያሉ የሚያቆላምጧቸውና ድል አድራጊው ፕሬዚዳንት ኦባማም ባደረጉት ንግግር፤ ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ሚት ሮምኒን በተመረጡ አረፍተ ነገሮችና ልብ በሚነካ የአነጋገር ስልት ከፍ አድርገው በማሞገስ፣ በቀጣዩ የፖለቲካም ሆነ ሌላ ህይወታቸው መልካም ነገሮች ሁሉ እንዲገጥሟቸው ከልባቸው ተመኝተውላቸዋል፡፡
ይህ የአሜሪካውያን የፖለቲካ ባህል በእርግጥም ድፍን አለሙን ሁሉ ማስቀናት የሚችልና የእኔም ሀገር የፖለቲካ ባህል በሆነ የሚያሰኝ ነው፡፡ የዚህ ቅናትና ምኞት ከሌሎች ሀገራት ይልቅ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ በእጅጉ የበረታ እንደሚሆን አፍን ሞልቶ ለመናገር ፈላስፋነት አሊያም ነብይ መሆንን ጨርሶ አይጠይቅም፡፡
ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የእኛ የፖለቲካ ባህል ከአሜሪካኖቹ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የትየለሌ ስለሆነ ነው፡፡ ምናልባትም ልዩነት አለው ካልን እንዲያው በአንዱ ጥግም ቢሆን ትንሽዬ የሚመሳሰል ነገር አለው እንዳልን ሊያስቆጥርብን ስለሚችል፣ ትክክለኛው አገላለጽ የእኛ የፖለቲካ ባህል ከአሜሪካኖቹ የፖለቲካ ባህል ጋር ተቃራኒ ነው የሚለው ነው፡፡
አሁን አንድ ጥያቄ እናቅርብ፡፡ የአሜሪካ የሪፐብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች እንዲሁም ባራክ ኦባማና ሚት ሮምኒ ኢትዮጵያውያን ቢሆኑ ኖሮ ምርጫውን በእንዴት ያለ ሁኔታ ያካሂዱትና ውጤቱንም ይቀበሉት ነበር? ጥያቄው በጣም ቀላል ነው፡፡ እያንዳንዳችን የምንሠጠው መልስ ጨርሶ ልናጣ አንችልም፡፡ የአቀራረብና የቋንቋ አጠቃቀም ልዩነት ካልሆነ በቀር የሁላችንም መልስ ከዚህ በታች ከቀረበው ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡
ከምርጫው መጀመሪያ እንነሳ፡፡ የምርጫው የዝግጅት ጊዜ ሲቃረብ ኢትዮጵያውያኑ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሚት ሩምኒና የገዥው ፓርቲ መሪ ባራክ ኦባማ የሚሠጡት መግለጫ እንዲህ የሚል ይሆናል፡፡
ሚት ሮምኒ፤ “የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ በጠበበት፣ ገዥው ፓርቲ የህዝብ የመገናኛ ብዙሀንን በብቸኝነት በመቆጣጠር በሚጠቀምባትና የምርጫ ቦርዱ ገለልተኛ ባልሆነበት ሁኔታ ምንም አይነት ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለን ስለማናምን፣ የገዥውን የዲሞክራቲክ ፓርቲ የይስሙላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መልክ ለመስጠት ብለን በዚህ ምርጫ የመወዳደር ፍላጐት የለንም፡፡” ባራክ ኦባማ፤ “ዲሞክራሲያዊ ስርአት በዚች ሀገር ላይ የመገንባት ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ እናም ገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲና እሱ የሚመራው መንግስት ይህንን ምርጫ እንከን አልባ ምርጫ ለማድረግ በመወሠን ለመላ አባላቱ የስነ ምግባር ደንብ አውጥቷል፡፡”
ከትንሽ ቀናት ቆይታ በኋላ ሚት ሮምኒ፤ “ቀደም ብለን ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አካል አይደለም በማለት አሳውቀናል፡፡ የምርጫውን ሂደትና አፈፃፀም በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን ለመንግስት አቅርበናል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎቻችን ባስቸኳይ ምላሽ ካልተሠጠን በምርጫው ገዥውን ፓርቲ ለማጀብ ፈቃደኞች አይደለንም፡፡ በዚህ ምርጫም አንሳተፍም፡፡”
ባራክ ኦባማ፤ “ተቃዋሚው ፓርቲ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታው ለመሳተፍ ቁርጠኛ አቋም ካለው ህዝባዊ ምርጫን ሊፈራና ከህዝብ ብይን ሊያፈገፍግ አይገባውም፡፡
ችግሩ ግን ተቃዋሚው ፓርቲ ቁርጠኛ አቋም ብሎ ነገር ከነአካቴው አልፈጠረበትም፡፡ ዋነኛው ችግሩ የአላማና የመስመር ጥራት ስለሌለው ነው፡፡ እኛ እንደ አንድ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር የታነፀ ፓርቲና እንደ አንድ ልማታዊ መንግስት ይህንን ምርጫ እንከን አልባ እንዲሆን ወስነናል፡፡ በዚህ ውሳኔአችንም ፀንተን እስከምርጫው ፍፃሜ ድረስ እንገፋበታለን፡፡ ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት ሰበብ የመደርደር አባዜውን ማቆም አለበት”
የምርጫው ዝግጅት መሟሟቅ ሲጀምር ደግሞ ሚት ሮምኒ፤ “ከተለያዩ አባሎቻችን ባገኘነው መረጃ መሠረት፤ ገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ይህን ምርጫ ለማጭበርበር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ደርሰንበታል፡፡ ምርጫው ገና ከመጀመሩ በፊት ተጭበርብሯል” ባራክ ኦባማ፡- የተዋቃሚው ፓርቲ መሪ የሠጡት መግለጫ በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡
የመግለጫቸው ዋነኛ መነሻው ገና ሲፈጠሩ ጀምሮ የተጠናወቷቸው የህዝብን ብያኔ መሸሽና ባቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የመቋመጥ አባዜ ነው፡፡ ገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋነኛ መሠረቱ ህዝቡ ነው፡፡ እኛ ዘጭ ያልነው ህዝቡ ላይ ነው፡፡”
የምርጫ አስፈ ፃሚዎችን በተመለከተ ደግሞ ሚት ሮምኒ፡- “ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ገዥው ፓርቲ ይህን ምርጫ በማጭበርበር ለማሸነፍ ካዘጋጃቸው ተቋማት አንዱ የምርጫ ቦርድ ነው፡፡
የምርጫ ቦርድና ሌሎች የምርጫ አስፈፃሚዎች የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም፡፡ እኛ በምንም ተአምር በምርጫ ቦርድና በምርጫ አስፈፃሚዎች ላይ ቅንጣት ታክል እምነት የለንም፡፡”
ባራክ ኦባማ፡- “በህገ መንግስቱ መሠረት በህግ የተቋቋሙ የዲሞክራሲ ተቋማትን ክብር መንካትና ማንቋሸሽ ህገወጥ ተግባር ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ከዚህ ህገወጥ ተግባሩ ባስቸኳይ እንዲቆጠብ ለማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ለሁከትና ለብጥብጥ መቋመጥ ነው፡፡ የዚህ መዘዝ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡”
የምርጫ ታዛቢዎችን በተመለከተ ሚት ሮምኒ፡- “ገዥው ፓርቲ የምርጫ ታዛቢዎች የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ብቻ ይሁኑ የሚለው ምን ሊያደርግ አስቦ እንደሆነ እኛ ቀደም ብለን ነቅተንበታል፡፡ በምርጫው ምዝገባ ወቅት የእኛን ደጋፊዎች ያለ አንዳች ታዛቢ እንይመዘገቡ እንዳደረገው ሁሉ በድምጽ አሠጣጡና ቆጠራው ወቅት እንደለመደው በጠራራ ፀሀይ የምርጫ ኮረጆ ለመገልበጥ እንዲመቸው ነው፡፡ የውጭ ታዛቢዎች በተለይ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ካልገቡ ሪፐብሊካን ፓርቲያችን ከምርጫው ራሱን ሊያገል ይችላል፡፡”
ባራክ ኦባማ፡- “ተቃዋሚው ፓርቲ የጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ የፈሪ ዱላ ነው፡፡ በህዝብ ድምጽ የሚተማመን የሰው ስም አያጠፋም፡፡ የሆኖ ሆኖ እኛ ዲሞክራቶች የውጭ ታዛቢዎች የሀገሪቱን ህግና የምርጫ ታዛቢነት አለም አቀፍ ህግን አክብረው የሚንቀሳቀሱ እስከሆነ ድረስ ምንም ችግር የለብንም፡፡”
የምርጫ ክርክር ሂደት ወቅት
የክርክሩ መሪ
የተከበራችሁ የሪፐብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲው የምርጫ ተከራካሪዎች በተሠጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የየፓርቲያችሁን አቋምና መከራከሪያ የምታቀርቡት በተሠጣችሁ የሠባት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከሠባት ደቂቃ በላይ ከተጠቀማችሁ አስቆማችኋለሁ፡፡ የተከበሩ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ሚት ሮምኒ ክርክርዎን መጀመር ይችላሉ፡፡
ሚት ሮምኒ፡- “በእውነቱ የዚህ የሰአት ነገር በጣም አስገራሚ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ የመገናኛ ብዙሀንን በሞኖፖል በመቆጣጠር እንዳሻው የምርጫ ቅስቀሳውን እያጧጧፈ ባለበት በአሁኑ ሰአት ለእኛ ምንም አይነት አማራጭ ለሌለን ሠባት ደቂቃ ብቻ መሠጠቱ ሂደቱ ምን ያህል ኢፍትሃዊ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህንን ህገወጥና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ድርጊት መላው የአለም አቀፍ ማህበረሠብና ህዝቡ በሚገባ እንዲገነዘቡልንና በዚህ ምርጫ የምንፎካከረው በእንዴት ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንደሆነ ልብ እንዲሉልን እናስገነዝባለን፡፡
የሆኖ ሆኖ በዚህ ፍትሀዊ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥም ሆነን ለዲሞክራሲና ለህዝቦች መብት መከበር የምናደርገውን ትግል በምንም አይነት ሁኔታ አናቆምም፡፡ መታገላችንን እንገፋበታለን ለማለትና ይህንንም በይፋ ለማስታወቅ ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል ወደ ክርክሩ እገባለሁ፡፡ የተሠጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓርቲያችን የሪፐብሊካን ፓርቲው መከሪከሪያ በነገራችን ላይ ይህን የመከራከሪያ ርዕስ የመረጠው ገዥው ፓርቲ እኛ አይደለንም፡፡ አከራካሪ ወገኖችም ቢሆኑ ስለ ርዕሱ ቀደም ብለው የነገሩን ነገር የለም፡፡
ያው የገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲው አባሎችና ወገንተኞች መሆናቸውን ስለምናውቅ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ የፓርቲያችንን የሪፐብሊካን ፓርቲን አቋምና መከራከሪያ አቀርባለሁ፡፡
የክርክሩ መሪ፡- “የተከበሩ ሚት ሮምኒ ሶስት ደቂቃ ይቀርዎታል”
ሚት ሮምኒ፡- አያችሁት! ያው ቅድም በመግቢያዬ ላይ እንደተናገርኩት እኮ ነው! ደህና ግዴለም፡፡ በቀረችኝ ሶስት ደቂቃም ብትሆን ድምፃችንን ከማሠማት ወደሁዋላ ጨርሶ አንልም፡፡ ስለዚህ እቀጥላለሁ፡፡
“የተከበራችሁ የፓርቲያችን የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ የተከበራችሁ የፓርቲያችን ደፊጋዎች፣ የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፡፡
የተከበራችሁ የፓርቲያችን የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ለመሆን እያሰባችሁና እየፈለጋችሁ ነገር ግን በገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲው ኢፍትሃዊና ኢዲሞክራሲያዊ ተጽዕኖ ምክንያት አባል መሆን ያልቻላችሁ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማራችሁ፣ እንዲሁም የሀገራችንን ዳር ድንበር ከተለያዩ የውጭ ወራሪ ሀይሎች ደማችሁን በማፍሰስና አጥንታችሁን በመከስከስ አስከብራችሁ የኖራችሁት ጀግኖች አርበኞች፣ ፓርቲያችን እጅግ የላቀና የሞቀ ሰላምታውን በዚህ ሀገራዊ የምርጫ ክርክር ወቅት ያቀርብላችኋል፡፡ ይህን የሞቀ ሠላምታውን ሲያቀርብላችሁም ከፍ ያለ ደስታና ኩራት ይሠማዋል፡፡
በመግቢያ ላይ ቀደም ብዬ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት፣ በዛሬው እለት እንድንከራከርበት የተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ የተመረጠው በገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲውና በአጋሮቹ ማለትም እዚህ በመካከላችን በመገኘት በሚያከራክሩን ወይም ደግሞ እናከራክራችኋለን በሚሉን አካላት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእኛ እጅ ጭርሱኑ የለበትም፡፡ እንግዲህ ለመግለጽ የሞከርኩላችሁ በጉዳዩ ላይ የገዥው ፓርቲ እንጂ የእኛ እጅ የሌለበት መሆኑን ነው፡፡
“እንግዲህ የተከበራችሁ…”
የክርክሩ መሪ
“የተከበሩ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ የተመደበልዎት ጊዜ ተጠናቋል፡፡ ስለዚህ አሁን ተራው የዲሞክራቲክ ፓርቲው ስለሆነ ተወካዩ የተከበሩ ባራክ ኦባማ በተመደበልዎ የሰባት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ የፓርቲውን አቋምና መከራከሪያ ማቅረብ ይችላሉ፡፡
ባራክ ኦባማ፡- “በዚህ የውይይትና የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ላይ ገዥው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ላለፉት ተከታታይ አመታት ያስመዘገበው ድልና ውጤት በተጨባጭ የሚታይ ስለሆነ ብዙ ማብራራት የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፡፡ እኛ ባስመዘገብነው ድል እንኳንስ ህዝቡ ተቃዋሚው ፓርቲም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ዛሬ እዚህ እኛ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው የፖለቲካ ክርክር ለማካሄድና መቸም ቢሆን አያገኟትም እንጂ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ መወዳደር የቻሉት፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ታጋዩን ህዝብ ከጐኑ አሰልፎ ለአስራ ሠባት አመታት ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ አምባገነኑን ስርአት በማስወገድ ባስገኘው ድል ነው፡፡ ከእኛ ከዲሞክራቲኮች ጋር ለመፎካከር የበቁት እኛ ባስገኘነው ዲሞክራሲ አማካኝነት ነው፡፡
እንግዲህ መቸም ሁላችሁም እንደምታውቁት ከዚህ የበለጠ ተጠቃሚነት፣ ከዚህ የበለጠ እድለኛነት ከየትም ሀገር ሊገኝ አይችልም፡፡
“የዲሞክራቲክ ፓርቲው ደምና አጥንት ገብሮ ያስገኘውን ይህን ነፃነትና ዲሞክራሲ በምንም አይነት ጊዜም ሆነ አጋጣሚ አሳልፎ ሊሠጥ አይችልም፡፡ ተቃዋሚው ፓርቲና አጨብጫቢዎቹ ይህን በሚገባ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
እደግመዋለሁ! ይህን በሚገባ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን ዲሞክራሲና ይህቺን ሀገር እንዲመሯት ለተቃዋሚ ፓርቲው መተው ጨርሶ የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡ አመሰግናለሁ”
የምርጫ ድምጽ መስጠት ሲጀመር ሚት ሮምኒ፡- “ገዥው ፓርቲ ቀደም ብሎ እንደተዘጋጀው የህዝብን ድምጽ ካልዘረፈና ምርጫውን ካላጭበረበረ በዚህ ምርጫ ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ ማሸነፉ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተለይ የውጭ የምርጫ ታዛቢዎች በጥብቅ እንዲከታተሉልን አበክረን እንጠይቃለን፡፡”
ባራክ ኦባማ፡- “የተቃዋሚው ፓርቲ በምርጫው የማሸንፈው እኔ ነኝ እያለ የሚነዛውን ማደናገሪያ ባስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን፡፡ የምርጫ ቦርድም ይህንን ህገወጥ ተግባር ተከታትሎ በተቃዋሚው ፓርቲ ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ እንዲህ ያለው የዘፈን ዳርዳርታ ለምን እንደሆነ እኛ በደንብ እናውቀዋለን፡፡”
የአንዳንድ ግዛቶች የምርጫ ውጤት ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ እየቀናው መሆኑን ማሳየት ሲጀምር ደግሞ የሚሆነው እንዲህ ነው፡፡
ሚት ሮምኒ፡- “ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለን ላሰማራናቸው የምርጫ ታዛቢዎች፣ በተለይም ለውጪ ታዛቢዎች ምስጋና ይሁንና አስቀድመን እንደተናገርነው ገዥው ፓርቲ ድምፃችንን መዝረፍ ስላልቻለ፣ በምርጫው ገዥውን ፓርቲ በዝረራ ማሸነፋችን በይፋ እየተረጋገጠ ነው፡፡ የፓርቲያችን ላዕላይ ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ትኩረቱን አድርጐ እየተወያየ የሚገኘው ስለምንመሠርተው መንግስትና ተሸናፊውን የዲሞክራቲክ ፓርቲ ይጨምር ወይስ አይጨምር በሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡”
ባራክ ኦባማ፡- “የድምጽ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ የተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫው አሸንፌ አለሁ ማለቱ ከፍተኛ ብጥብጥ ለማስነሳት ስለፈለገ ነው፡፡ የዲሞክራቲክ ፓርቲውና መንግስት ይህን የሁከትና የብጥብጥ ሙከራ እጁን አጣጥፎ ሊመለከት አይችልም፡፡”
ምርጫ ቦርድ ገዥው ፓርቲ ማሸነፉን ሲያስታውቅ፡-
ሚት ሮምኒ፡- እኛ ቀደም ብለን ተናግረናል፡፡ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን አጭበርብሯል ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ዘርፏል፡፡ የህዝቡ ድምጽ ተዘርፏል፡፡ የድምጽ ቆጠራው ጨርሶ ሳይጠናቀቅ ገዥው ፓርቲ አሸንፌአለሁ ማለቱ የሚያሳየው ምን ያህል ለህዝብ ድምጽ እንደማይገዛና ምን ያህል አምባገነን መሆኑን ነው፡፡ በሶስት ግዛቶች የምርጫ ቆጠራ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን ያጭበረበረውን ድምጽ ስለሚያውቅ ገና ለገና አሸናፊነቱን በማን አለብኝነት አውጇል፡፡ በተለያዩ ግዛቶች የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የእኛን የምርጫ ታዛቢዎች ለማስወጣት ከፍተኛ ዛቻ፣ እስርና ወከባ ቢያደርሱባቸውም ይህን ሁሉ እንግልትና መከራ ተቋቁመው የህዝብን ድምጽ ላለማዘረፍ ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረጉ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ የአለምአቀፉ ማህበረሠብና የውጭ ታዛቢዎች በሚገባ ተገንዝበው፣ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱልንና የተዘረፈውን የህዝብ ድምጽ እንዲያስመልሱልን እንጠይቃለን፡፡
የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ይፋ ሲሆን፡-
“ገዥው ፓርቲ በዚህ ምርጫ ያሸነፈው በትክክለኛው ዲሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድሮ ሳይሆን በየምርጫ ጣቢያዎች ባስቀመጣቸው የምርጫ አስፈፃሚ ካድሬዎቹና በደህንነት ሀይሎቹ አማካኝነት በጠራራ ፀሀይ የምርጫ ኮሮጆዎችን በመገልበጥና የህዝብ ድምጽን በመዝረፍ ነው፡፡ ስለዚህ የሪፐብሊካን ፓርቲያችን የዚህን የምርጫ ውጤት ጨርሶ አይቀበልም፡፡
ህዝቡም የተዘፈረና የተቀማውን ድምፁን በማንኛውም አይነት መንገድ ማለትም በሰላማዊ መንገድ እንዲያስመልስ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡” ባራክ ኦቦማ፡- “በዚህ ዲሞክራሲያዊ ሀገራዊ ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲያችን የተቀዳጀው ከፍተኛ ድል የሚከተለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት ርዕዮተ አለም መስመር ጥራት ውጤት ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲው በምርጫው ያገኘውን ውጤት በመቀበል የህዝብን ውሳኔ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡
እንደለመደው ህዝብን ለአመጽና ለሁከት እየቀሰቀሰ፣ ህጋዊውንና ህገወጡን መንገድ እያጣቀሰ እቀጥላለሁ ካለ ግን ሁከትና ጥፋት የሚጠነቁሉ ሁለት ጣቶቹን እንቆርጥለታለን፡፡”
ምርጫው ከተጠናቀቀ ከወርና ሁለት ወር በኋላ የወጡ ጋዜጦች የፊት ለፊት ገጽ የዜና ርዕሶች እንዲህ የሚሉ ናቸው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲው ህዝቡ የተዘረፈውን ድምፁን እንዲያስመልስ ጥሪ አቀረበ
ህዝቡ በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞውን እንዲያሠማ ጥሪ ቀረበለት፡፡
መንግስት ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ ከሁከትና አመጽ ተግባሩ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ፡፡
መንግስት ተቃዋሚው ፓርቲ ለህግና ስርአት ተገዥ እንዲሆን ጥሪውን አቀረበ፡፡
ገዥው ፓርቲ አክራሪ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ህዝቡ አንጥሮ እንዲለያቸውና እንዲታገላቸው አሳሠበ፡፡
ተቃዋሚው ፓርቲ ህዝቡ በሠላማዊ ተቃውሞው እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲገፋበት አሳሠበ፡፡
ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ መንግስት ያሠራቸውን በርካታ ደጋፊዎቹንና አባላቶቹ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈታ ጠየቀ፡፡
ተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ ፓርላማ እንደማይገባ አስታወቀ፡፡
መግስት ከፍተኛ አክራሪ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡
ከፍተኛው የፌደራል ፍርድ ቤት ሁከትና አመጽ በመቀስቀስና በመምራት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን ከፍተኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቀጣ፡፡

 

Read 3114 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 12:55