Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 12:57

ሜሲ 4ኛውን የወርቅ ኳስ ይወስዳል!?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሊዮኔል ሜሲ በዓለም ኮከብ ተጨዋችነት ለአራተኛ ጊዜ የወርቅ ኳሱን ሊሸለም እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አገኘ፡፡እነፔሌ፤ ዲያጎ ማራዶና፤ ዮሃን ክሩፍ፤ ቤከንባወር ፤ ፕላቲኒ እና አልፍሬዶ ዴስትፋኖ በተጨዋችነት ዘመናቸው በኮከብ ተጨዋነት ያገኙአቸውን ክብሮች በመሰብሰብ እና የግብ ሪከርዶች በማሻሻል እና በመጋራት ታሪክ መስራቱን የቀጠለው የ25 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ የምንግዜም ምርጥ ተጨዋች እየተባለም ነው፡፡ሊዮኔል ሜሲ በፊፋ እና ፍራንስ ፉትቦል መፅሄት የሚዘጋጀውን የወርቅ ኳስ ዘንድሮም ማሸነፍ ከተሳካለት በሽልማቱ ታሪክ 4 የወርቅ ኳሶችን በመውሰድ የመጀመርያው ተጨዋች ይሆናል፡፡ በ2013 የፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ኮከቦች ምርጫ ላይ ለመፎካከር የቀረቡት 23 እጩዎች ከ2 ሳምንት በፊት ታውቀዋል፡፡

ይሄው የፊፋ የወርቅ ኳስ ሽልማት 23 እጩዎች ይፋ ከመሆናቸው 1 ሳምንት በፊት ሊዮኔል ሜሲ በ2011/12 የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የወርቅ ጫማ ተሸልሟል ፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በ34 ጎሎች ተመሳሳይ ሽልማት የወሰደው ሜሲ ዘንድሮ ደግሞ የቅርብ ተፎካካሪውን ክርስትያኖ ሮናልዶ በአራት ጎሎች በመብለጥ ባገባቸው 50 ጎሎች የአውሮፓ ሊጎች ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የወርቅ ጫማውን ለ2ኛ ጊዜ ሊወስድ ችሏል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ሰሞኑን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የስፔን ላሊጋ የ2011/ 12 የዓመቱ ኮከብ ተጨዋችነት ክብሩን በማስጠበቅ በድጋሚ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ያለፈው የውድድር ዘመን የስፔን ላሊጋ ምርጥ አጥቂ ተብሎም ተጨማሪ ሽልማትንም አግኝቷል፡፡ በ2012 በሁሉም ውድድሮች ለባርሴሎና እና ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን 76 ጎሎች ያገባው በዚህ የጎል ብዛት ፔሌ በ1958 እኤአ ለሳንቶስ እየተጫወተ ያገባውን የ75 ጎሎች ክብረወሰን ሲያሻሽል ገርድ ሙለር ለባየርሙኒክ እና ለምእራብ ጀርመን በመጫወት በ1972 እኤአ በ85 ጎሎች ላስመዘገበው የከፍተኛ ጎል ክብረወሰን ለመጋራት 9 ጎሎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ 
የ2013 የእግር ኳስ ኮከቦችን በመምረጥ የፊፋ አባል አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኞች፤ አምበሎች እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን የወከሉ ይሳተፋሉ፡፡ የመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ከ15 ቀናት በኋላ ታውቀው አሸናፊዎቹ 2013 በገባ በሰባተኛው ቀን በዙሪክ በሚከናወን ስነስርዓት ይሸለማሉ፡፡
ዘንድሮ በወርቅ ኳሱ ፉክክር ለሊዮኔል ሜሲ የቅርብ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው በ2008 እኤአ የወርቅ ኳሱን የተሸለመው ፖርቱጋላዊው የሪያል ማድሪድ አጥቂ ክርስትያኖ ሮናልዶ ነው፡፡ ስፓንያርዶቹ ዣቪ እና ኢንዬስታ፤ የብራዚሎቹ ኔይማር እና ፋልካኦ እንዲሁም የአይቬሪኮስቱ ዲዲዬር ድሮግባ ከእጩዎቹ መካከል ለደረጃ የተጠበቁ ሆነዋል፡፡በእጩዎቹ ዝርዝር ለመካተት የበቃው ብቸኛው እንግሊዛዊ ደግሞ የማን ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ ነው፡፡
የሜሲ ምርቃት
የ2012/ 13 የውድድር ዘመን ከተጀመረ በኋላ በሁሉም ውድድሮች 20 ጎሎች ያገባ ሲሆን በላሊጋው በ15 ጎሎቹ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን በስፔን ላሊጋ 50 ጎሎች በማስመዝገብ የመጀመርያው ተጨዋች ለመሆን የበቃ ሲሆን ሴዛር ሮድሪጌዝ የተባለው የባርሴሎና ተጨዋች በ232 ጎሎች የክለቡ የምንገዜም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለ57 ዓመታት የቆየውን ክብረወሰንም ተረክቦታል፡፡
በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ታሪኩ ያገባቸው ጎሎች ብዛት ከ300 አልፈዋል፡፡ ለባርሴሎና 347 ጨዋታዎች አድርጎ 273 እንዲሁም ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን 75 ጨዋታዎችን አድረጎ 31 ጎሎችን ከመረብ አዋህዷል፡፡እነዚህ ጎሎቹን 247 በግራ እግሩ፤ 40 በቀኝ እገሩ፤ 12 በጭንቅላት እንዲሁም አንድ በአካል ንከኪ እንዲሁም አንዷን በእጁ ከመረብ አዋህዷል፡፡
በሻምፒዮንስ ሊግ ለ4 የውድድር ዘመናት ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በመጨረስ ብቸኛ የሆነው እና ለባርሴሎና እየተሰለፈ በውድድሩ 53 ጎሎች አሉት፡፡ በባርሴሎና ታሪክ ከፍተኛው ግብ አግቢ ሆኖ በሪቫልዶ ተይዞ የነበረን ክብረወሰን ነጥቋል፡፡ በውድድሩ ታሪክ በምንግዜም ኮከብ ግብ አግቢ ደረጃ 3ኛ ሆኖ በአንደኛነት የሚገኘውን በ71 ጎሎች የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ተጨዋች ራውል ጎንዛሌዝ እያሳደደ ነው፡፡
ለባርሴሎና ሲጫወት በሁሉም ውድድሮች 21 ሃትሪክ ሰርቷል፡፡ በላሊጋው ለባርሴሎና 15 ሃትሪኮችን በማስመዝገብ ብቸኛው ሆኗል፡፡

Read 5574 times