በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ይነሳሉ የተባሉት 3 ዋና ዋና ነጥቦች…የአገሪቱ ህዝብ ሁኔታ፣ የፓርቲዎች ሁኔታ (የገዥውም የተቃዋሚዎችም) እና የምህዳሩ ሁኔታ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የአገሪቱ ህዝብ ያለበት ሁኔታን አስመልክቶ በሚያነሱት ነጥብ ላይ ህዝቡ በቂ መረጃ የሌለው፣ ያልተደራጀና ብሶቱን በማጉረምረም ከመግለጽ የተሻለ ነገር ማድረግ ያልቻለ መሆኑን የሚጠቁሙ ሃሳቦች እንደሚነሱ ዶ/ር ነጋሶ ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ እየደረሰበት ያለውን በደልና የኑሮ ውድነቱን ተሸክሞ እያጉረመረመ ከመኖር በዘለለ አንዳችም ትርጉም ያለው ንቅናቄ ሲያደርግ አለመታየቱን የተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፤ በዚህ በኩል የእስልምና እምነት ተከታዮች እያካሄዱት ያለው ንቅናቄ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የገዥውም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በዶ/ር ነጋሶ የሚነሳው የውይይት መነሻ ሃሳብ መድብለ ፓርቲ አለመኖሩን፣ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነና አፋኝ ገዥ ፓርቲ መኖሩን፣ ገዥው ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማይከተልና አፋኝ ሥርዓት መሆኑን፤ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እራሳቸው ጥንካሬና ጽናት የሚጐድላቸውና የተበጣጠሱ እንደሆኑ የሚያመለክቱ ናቸው ተብሏል፡፡
በገዥው ፓርቲ በኩል ከምርጫው በፊትም ሆነ በምርጫው ወቅት ፍትሃዊና የተስተካከለ የምርጫ ሂደት አለመኖሩን የሚያመለክቱ ነጥቦችም እንደሚነሱ ተገልጿል፡፡ ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በውይይቱ ላይ እንደሚያነሱ ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የፓርቲው ልሣን የሆነው “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ በአገሪቱ በየትኛውም ማተሚያ ቤት እንዳትታም እገዳ እንደተጣለበት ከፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡