Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 11:53

በወንጀል ጉዳይ በስህተት የተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

አቶ አሰፋ ከሲቶ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል የሥነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር እንዲሁም የፍትህ ቢሮ ሃላፊ እና የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ በስህተት የተላለፈ የወንጀል ቅጣት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የሰጡትን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የወንጀል ፍርድ በስህተት የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ?
በቅድሚያ የወንጀል ፍትህ ሥርዓት ገጽታዎችን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ዓላማ የመንግሥትን፣ የሕዝቡንና የነዋሪውን ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብት እና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ግብ ደግሞ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ወንጀል አድራጊዎችን ለሕግ በማቅረብና በማስቀጣት ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑና እንዲታረሙ ማድረግ ነው፡፡

የወንጀል ሕግ ዓላማና ግብ ተግባራዊ የሚሆነው በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ (በተለምዶ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ተብሎ የሚጠራው) በሚመሰረተው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት እና አካላት ነው፡፡ 
የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ በራሱ ግብ ሳይሆን የወንጀል ሕግ ዓላማና ግብ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ እና የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ያለ ፈጻሚ አካል ዋጋ የላቸውም፡፡
በመሆኑም በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ እና ሌሎች ሕግ አውጭው በሚያወጣቸው ሕጎች የሕግ አስከባሪ አካላት እና የዳኝነት አካላት ይመሰረታሉ፡፡
በዚህ ረገድ የተለመዱት የሕግ አስከባሪ አካላት ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ እና የማረሚያ ተቋም ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቶች ደግሞ የዳኝነት አካላት ናቸው፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላት ተግባርና ሃላፊነት እንደ የሥነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽኖች፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ወዘተ… በሕግ የተሰጠ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ዓላማ ወንጀል አድራጊዎችን ብቻ በመለየት ለሕግ በማቅረብ፣ በሕግ የተወሰነውን ቅጣት ወይም ሌላ የጥንቃቄ እርምጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ እና ንጹሃን በስህተት እንዳይቀጡ ሥርዓት ማበጀት ነው፡፡
ስለሆነም ከዚህ አንጻር በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተዋናይ የሆኑ መርማሪዎች፣ ከሳሾች፣ ምስክሮች፣ ጠበቆችና ዳኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህም ሆኖ በወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ውስጥ ተዋናይ ከሆኑ አካላት አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም ተንኮል ወይም ቸልተኝነት በንጹሃን ሰዎች ላይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ የሚተላለፍበት እንዲሁም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከቅጣት የሚያመልጡበት አጋጣሚ አይኖርም አይባልም፡፡
እዚህ ላይ አንድ ሰው በስህተት የወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ከሚቀጣ አስር የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ነጻ ቢወጡ ይሻላል የሚለውን ብልህ አነጋገር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ንጹህ ሰዎች በስህተት ጥፋተኛ ተደርገው የተቀጡበት እና ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከሕግ ያመለጡበት ሁኔታ ካለ ቢጠቅሱልን?
የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አካላት በተለይም መርማሪ ፖሊስ እና ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ዳኛ ንጹሃን በስህተት እንዳይቀጡ እንዲሁም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከሕግ እንዳያመልጡ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች፣ መከላከያ ምስክሮች፣ የወንጀል ተጎጂዎች እና ጠበቆች እውነቱን በማቅረብ የፍትህ ሥርዓቱን መደገፍ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም ቢሆን እንኳንስ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ባደጉ አገሮች ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከቅጣት የሚያመልጡበት ሁኔታ አለ፡፡
በኢትዮጵያ ንጹሃን ሰዎች በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የተቀጡበት፣ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ያመለጡበት እና ወንጀል ያልፈጸሙ ሰዎች በተሳሳተ ማስረጃ የተቀጡበትን አጋጣሚዎች ለማየት ችያለሁ፡፡
በቀድሞ አጠራር በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ መስቃንና ማረቆ ወረዳ ዶቢ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በመተላለፍ ጥቅምት 22 ቀን 1980 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አንድ ሰው በጦር ወግቶ ገድሏል በሚል ተከሰሰ፡፡ ጉዳዩን ያየው ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 976/80 ጥር 29 ቀን 1980 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ በተከሰሰበት ጉዳይ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ያስተላለፈ ሲሆን ጉዳዩን በይግባኝ ባየው ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸናበት፡፡
ግለሰቡ በሐሰት በተሰጠ ምስክርነት የተፈረደበት መሆኑን ቢከራከርም ጉዳዩን የሚያቀርብበትና ፍትህ የሚያገኝበት አማራጭ ሳይኖረው በመቅረቱ፣ የተላለፈበትን የእስራት ጊዜ በማጠናቀቅ ላይ እያለ በ1999 ዓ.ም ይቅርታ እንዲደረግለት ለፍትህ ሚኒስቴር አመለከተ፡፡ ሆኖም ጥፋተኛ አለመሆኑን ገልጾ በይቅርታ ለመፈታት የይቅርታ ጥያቄ ላቀረበ ሰው ይቅርታ ማድረግ አግባብ ባለመሆኑ ጉዳዩ በፖሊስ እንዲጣራ ተደረገ፡፡ በፌዴራል ፖሊስ በኩል ጉዳዩ የደረሰው የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ፖሊስ የሐሰት ምስክሮችንና የወንጀሉን አድራጊዎች ይዞ ምርመራ ማጠናቀቁን በመግለጹ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርዱን እንደገና እንዲያይ ቢጠየቅም በሕግ ያልተፈቀደ መሆኑን በመግለጹ ሳይታይ ቀረ፡፡ እኔም የነበርኩበት የይቅርታ ቦርድ አባላት በሚገኝበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት በመገኘት ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ካሰባሰብን በኋላ፣ ታራሚው እንደጥፋተኛ የይቅርታ ጥያቄ እንዲያቀርብ ተደርጎ ለርዕሰ ብሔሩ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት፣ ይቅርታ ተደርጎለት ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም ከማረሚያ ቤት ወጥቷል፡፡
እንደዚሁም አንድ ግለሰብ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የ5 ዓመት እስራት ቢወሰንበትም ወንጀሉን አለመፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘቱን ጠቅሶ ዳኝነት እንደገና ይታይልኝ በማለት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልክቶ ጉዳዩን ጥር 7 ቀን 2000 ዓ.ም ያየው 3ኛ ወንጀል ችሎት “… በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ሥርዓት ይህ ዓይነቱ ጥያቄ የሚስተናገድበት አግባብ በሕግ ላይ የተቀረጸ ባለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ትዕዛዝ በማጽናት ይግባኝ ባይን አሰናብተናል፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡” የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም ግለሰቡ ሐምሌ 11/2000 ዓ.ም ለፍትህ ሚኒስቴር በጻፈው አቤቱታ፣ ዳኝነት እንደገና የማይታይ ከሆነ ይቅርታ እንዲደረግለት ቢያመለክትም ጥፋተኛ ላልሆነ ሰው ይቅርታ የሚደረግበት ሥርዓት ባለመኖሩ የተወሰነበትን ቅጣት ለመፈጸም ተገዷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ግለሰብ ጥቅምት 30 ቀን 2000 ዓ.ም ሰው ገድሏል በሚል ተከሶ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሲተላለፍበት፣ ጉዳዩን በይግባኝ ባየው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ 10 ዓመት ጽኑ እስራት ተለወጠ፡፡ ግለሰቡ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ቢከራከርም ተቀባይነት በማጣቱ የተወሰነበትን ቅጣት ማረሚያ ቤት ገብቶ መፈጸም ግድ ሆነበት፡፡ ሆኖም በፍትህ ሚኒስቴር የመመርመርና ውሳኔ የማሰጠት የሥራ ሂደት አካል የሆነው፣ የአዲስ አበባ ዐቃቤ ሕግ ለይቅርታ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ፣ ለሕግ ታራሚ ሹሜ ረጋሳ ሄይ ይቅርታ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ፡፡ የዐቃቤ ሕግ የይቅርታ ጥያቄ መነሻ “ገዳዩ ሌላ ግለሰብ መሆኑ በሰውና በሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠ ስለሆነ፣ ይህን ግለሰብ በፍርድ ጥፋተኛ አሰኝቶ ለማስቀጣት በቅድሚያ በስህተት የተፈረደበት ሰው ነጻ መሆኑ መረጋገጥ ስለሚገባውና በአንድና ተመሳሳይ ጉዳይ ሁለት ጊዜ ፍርድ ማሰጠት በሕግ የተከለከለ በመሆኑ፣ ይህን ክፍተት ለመሙላት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ይቅርታ እንዲደረግለት” የሚል ነው፡፡
የይቅርታ ቦርድም በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ መርምሮ፣ ጥፋት ያልፈጸመ ሰው ይቅርታ ሊደረግለት የማይገባ ቢሆንም አንድ ግለሰብ ያለጥፋቱ ቅጣት ተወስኖበት ከሆነና ጥፋተኛ አለመሆኑ ሲታወቅ ማስተካከል የሚቻልበት የሕግ ማዕቀፍ ከሌለ፣ አጥፊዎች በጥፋታቸው እንዲቀጡና ንጹህ ዜጎች በስህተት ከተላለፈባቸው ቅጣት ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ ፍትሐዊ በመሆኑ … በዚህ መንገድ ብቻ ካልሆነ በስተቀር (በይቅርታ) ከእስር ስለማይወጣና ሌሎች አጥፊዎችም በጥፋታቸው ስለማይቀጡ፣ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ሲባል፣ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ በሙሉ ድምጽ ደግፎ ይቅርታ እንዲደረግ በማለት ያዘጋጀውን የይቅርታ የውሳኔ ሀሳብ ለርዕሰ ብሔሩ ላከ፡፡
ጉዳዩ የቀረበለት የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ጥፋተኛ ላልሆነ ሰው ይቅርታ ማድረግ ስለማይቻል ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ቀርቦ መፍትሔ እንዲሰጥ ለይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤትም ግለሰቡ የፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበለትን የይቅርታ ጥያቄ መቀበሉንና በይቅርታ መጠየቂያ ቅጽ ላይ መፈረሙን አረጋግጦ፣ ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ በመሆኑም ይህ በስህተት የ10 ዓመት እስራት የተፈረደበት ግለሰብ፣ ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም ይቅርታ ተደርጎለት ከማረሚያ ቤት ሊወጣ ችሏል፡፡
እኔ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር አባል በነበርኩበት ወቅት ከቤንች ማጂ ዞን የተወከሉት አንድ የምክር ቤት አባል ያቀረቡት ቅሬታም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ በሰው መግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በቀረበበት ክስ፣ ጥፋተኛ ተብሎ የ12 ዓመት እስራት ቅጣት ተወስኖበት ማረሚያ ቤት ከገባ በኋላ፣ በዚሁ ጉዳይ ወንጀሉን የፈጸመው ሌላ የ16 ዓመት እስራት ሲፈረድበት፣ የሐሰት ምስክሮች ደግሞ እያንዳንዳቸው የ12 ዓመት እስራት ተወሰነባቸው፡፡ ዐቃቤ ሕግ የመጀመሪያው ፍርደኛ በስህተት የተፈረደበት ስለሆነ፣ ጉዳዩ እንደገና ታይቶ ፍርዱ እንዲሻርለት ያቀረበው ጥያቄ፣ በፍርድ ቤቶች በኩል ተቀባይነት ማጣቱ ነበር ለምክር ቤቱ አባል ቅሬታ መነሻ ሆኖ የነበረው፡፡
ይህ በስህተት የ12 ዓመት እስራት የተፈረደበት ግለሰብ፣ 6 ዓመት ያህል በማረሚያ ቤት ካሳለፈ በኋላ፣ የክልሉ ጠቅላላ ፍርድ ተዘዋዋሪ ችሎት፣ ጉዳዩን እንደገና አይቶ፣ ፍርደኛውን ነጻ የሚያደርግ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ቤንች ማጂ ዞን አንድ ግለሰብ በሰው መግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በ1997 ዓ.ም የ15 ዓመት እስራት ተወስኖበት ነበር፡፡ ጉዳዩ እንደገና የሚታይበት መደበኛ ሂደት ካበቃ በኋላ እና ፍርደኛው ቅጣቱን በመፈጸም ላይ እያለ ወንጀሉን የፈጸመው ሌላ ሰው መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ ክስ ቀርቦበት የእስራት ቅጣት ከተወሰነበት በኋላ በስህተት የተፈረደበት ሰው ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ጉዳዩን እንደገና አይቶ በሰጠው ውሳኔ ነጻ ለመሆን ችሏል፡፡
በመጨረሻ የማነሳው ጉዳይ በደ/ብ/ብሕ/ክልል ሐዋሳ ከተማ የተከሰተው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፋይል አገላብጨ ዝርዝር ሁኔታውን ባላይም ከሚዲያ ለማየት ችያለሁ፤ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎችም አረጋግጠውልኛል፡፡ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ ወጣት ላይ በተፈጸመ የግድያ ወንጀል ጉዳይ ክስ የቀረበባቸውን ሶስት ሰዎች በወንጀል ሕግ ቁጥር 540 ሥር ጥፋተኛ በማለት እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ተከሳሾቹ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸንቷል፡፡ ሰዎቹ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበውም የሕግ ስህተት ባለመገኘቱ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ፍርደኞች በፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን ቅጣት በመፈጸም ላይ እያሉ ቀደም ሲል ጉዳዩን መርምሮ ክስ የመሰረተው ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉን የፈጸሙት ሌሎች መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ደረሰው፡፡ በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉን ፈጽመዋል በተባሉት ሌሎች ሶስት ሰዎች ላይ ቀደም ሲል ይህኑን ጉዳይ አይቶ ፍርድ በሰጠው ፍርድ ቤት አዲስ ክስ በመመስረቱ፣ መስከረም 14 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ በእያንዳንዳቸው ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወስኗል፡፡ ቀደም ሲል በስህተት የ10 ዓመት እስራት የተወሰነባቸው ሰዎች ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባላውቅም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደገና አይቶ የቀድሞውን ፍርድ ያርማል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እንዲህ ዓይነት ስህተት መፈጸሙ ከታወቀ በኋላ የፍትህ አካላት የሚወስዱት መፍትሄ ምን ይመስላል?
በስህተት በንጹሃን ላይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ስህተት መሆኑ ሲታወቅ የተወሰዱ እርምጃዎች ወጥነት የላቸውም፡፡ በዋናነት መሰጠት የነበረበት መፍትሔ ለፍርድ ቤት በማቅረብ በስህተት የተሰጠው ፍርድ እንዲታረም ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት በስህተት የተሰጠ ፍርድ የሚታረምበት ሥርዓት የለም በማለት ተቀብለው አያስተናግዱም፡፡ በአንጻሩ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስህተት የተላለፈውን ፍርድ በድጋሚ በማየት ፍርደኞችን ነጻ አድርጓል፡፡
በስህተት ከሕግ ያመለጡትን በመክሰስ ከማስቀጣትና በስህተት ጥፋተኛ ተብለው የእስራት ቅጣት የተወሰነባቸውን ከማረሚያ ቤት ከማስወጣት አንጻር እስካሁን የፍትሕ ሚኒስቴር የወሰደው አቋም በስህተት የተፈረደባቸው ሰዎች እንደጥፋተኛ ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ በይቅርታ እንዲፈቱ ማድረግ ነው፡፡ ወንጀል ያልፈጸመ ሰው ወንጀለኛ ነኝ ብሎ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ ፍትሐዊ ባይሆንም ለግለሰቦች ነጻነት ከመስጠት አንጻር ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡
በስህተት ከሕግ ያለመለጡትን ከመክሰስ አንጻር በክልል ፍትህ ቢሮና በፍትህ ሚኒስቴር መካከል መሰረታዊ ልዩነት መኖሩን ከላይ ከቀረቡት ጉዳዮች ማየት ይቻላል፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር በስህተት ከሕግ ያመለጡትን ለመክሰስ፣ በስህተት የተፈረደበት ሰው በቅድሚያ መፈታት እንዳለበት አቋም ሲይዝ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ዐቃቤ ሕግ ግን በስህተት የተፈረደባቸው ሰዎች በመታረም ላይ እያሉ በዚያው ጉዳይ በአዲስ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት ጥፋተኛ በማሰኘት ቅጣት አስወስኗል፡፡ ከዚያም በስህተት የተፈረደባቸው ሰዎች ነጻ እንዲወጡ በመንቀሳቀስ ተሳክቶለታል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩን የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓታችን ያልዳበረ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ ተረባርበው መፍትሔ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ በተለይም የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ወጥ መሆን እንዳለበት በሕገመንግሥቱ የተደነገገ መሆኑ ከግምት መግባት አለበት፡፡
በወንጀል ሕጋችን ውስጥ በስህተት የተሰጠ የወንጀል ጉዳይ ፍርድ እንደገና ታይቶ የሚታረምበት ሥርዓት የለም?
በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ስህተት መፈጸሙ ሲታወቅ መፍትሔው ፍርዱን እንደገና ማየት (Review of Judgement) ወይም መከለስ (revison of Judgement) ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የሚታይበት ሥርዓት የለም በሚል በስህተት የተፈረደባቸው ሰዎች ጉዳይ እንደገና በፍርድ ቤቶች ታይቶ እየታረመ አይደለም፡፡ በአንጻሩ የደ/ብ/ብሕ/ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስካሁን የቀረቡለትን ሁለት ጉዳዮች በማስተናገድ በስህተት በተከሳሾቹ ላይ የተላለፈውን ፍርድ አርሟል፡፡ በስህተት የተሰጠ የጥፋተኝነት እና የቅጣት ፍርድ የሚታረምበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕግ ባይደነገግም፣ ስህተት አይታረምም የሚል ድንጋጌም የለም፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሚያነሱት ክርክር፣ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠውን የመጨረሻ ፍርድ እንደገና ማየት፣ በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 23 እና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 2(5) መሰረት ድጋሚ ክስ (double jeopardy) ነው የሚል ነው፡፡ በአንጻሩ የተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎች የሚናገሩት አንድ ሰው ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋኝነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነጻ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም የሚል እንጂ በፍትህ አካላት ወይም በምስክሮች የተፈጸመ ስህተት ታርሞ ዜጎች ፍትህ ማግኘት አይገባቸውም የሚል አይደለም፡፡ በስህተት የተፈረደበት ሰው ፍርዱን እንዲፈጽም ማድረግ ወይም በስህተት ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ የሆነ ሰው ተጠያቂ እንዳይሆን ማድረግ የወንጀል ሕግና የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ዓላማ እንዳይሳካ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የሕጉ ዓላማ ወንጀል የፈጸሙትን ለይቶ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲሁም ንጹሃን በስህተት ተጠያቂ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የደ/ብ/ብሕ/ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቋም የተለየ አቋም በመያዝ በስህተት የተሰጡ የወንጀል ጉዳይ ፍርዶችን በድጋሚ እያየ ማረም የጀመረው፡፡
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና ማየት ባይደነገግም የተከለከለ አይደለም፡፡ ሁለት አካዳሚክ የሆኑ መከራከሪያዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ አንደኛው “ያልተከለከለ የተፈቀደ” ስለሆነ በስህተት የተሰጠ የወንጀል ፍርድ እንደገና አይቶ ማረም አልተከለከለምና ማየት ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው “ያልተፈቀደ የተከለከለ” ስለሆነ በስህተት የተሰጠ የወንጀል ፍርድ ጉዳይ እንደገና ማየት አልተፈቀደምና ማየት አይቻልም የሚል ነው፡፡ ከፍትህ አንጻር እኔ የምደግፈው “ያልተከለከለ የተፈቀደ ነው” የሚለውን ነው፡፡
በብዙ የኮመን ሎው እና የሲቪል ሎው ተከታይ አገሮች በስህተት የተሰጠውን የወንጀል ፍርድ እንደገና አይቶ ማረም የተለመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ሲረቀቅ፣ አስቀድሞ በሲቪል ሎው ሥርዓት ተከታይ አገሮች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ነጻነትን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የእንግሊዝ ዜጎች ባሳደሩት ተጽዕኖ ወደ ኮመን ሎው ሥርኣት ያደላ ሆኖ የሲቪል ሎው ሥርዓትም ተካቶበታል፡፡ በሲቪል ሎው ሥርዓት ተከታይ አገሮች እና በኮመን ሎው ሥርዓት ተከታይ አገሮች ተግባራዊ የሆነው በስህተት የተሰጠውን የመጨረሻ ፍርድ እንደገና ማየት፣ በኢትዮጵያ ሕግ ያልተካተተበት ምክንያት ባይታወቅም በስህተት የታለፈ ነው ከማለት ውጭ ሕግ አውጭው ሆን ብሎ አድርጎታል ለማለት አይቻልም፡፡ ችግሩ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕጉ ከወጣበት ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ግማሽ ምዕተ-ዓመት ያለበትን ክፍተት ለይቶ ወቅታዊ ማድረግ አለመቻል ነው፡፡
የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይመስላል?
ከ1998-2001 ዓ.ም የፍትህ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜ በወንጀል ፍትህ አስተዳደራችን ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና በፖሊሲ በማስደገፍ ክፍተቶቹን ለመሙላት በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የተወሰነ እንቅስቃሴ ለማድረግ ችያለሁ፡፡
በአሜሪካ ኒውዮርክ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ መሰረት፣ የመጨረሻ የወንጀል ፍርድ በተከሳሹ አቅራቢነት ፍርዱን በሰጠው ፍርድ ቤት እንደገና ታይቶ ይታረማል፡፡
ጉዳዩን እንደገና ለማየት ከሚያበቁ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ፡- ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ወይም በተከሳሹ ላይ ሥልጣን የሌለው መሆን፤ ፍርዱ የተሰጠው በማታለል ወይም በማጭበርበር መሆን፤ በተከሳሹ ላይ የቀረበው ማስረጃ ሐሰተኛ መሆን፤ ለፍርዱ ምክንያት የሆነው ማስረጃ የተከሳሹን ሕገመንግሥታዊ መብቶች በመጣስ የተገኘ መሆን፤ ፍርዱ በተሰጠበት ወቅት ተከሳሹ በአእምሮ ችግር ምክንያት የክሱን ሂደት የመከታተል ችሎታ የሌለው መሆን እና የተከሳሹን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ሊያስቀይር የሚችል አዲስ ማስረጃ መገኘት ናቸው፡፡
በፈረንሳይ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ መሰረት፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ እንደገና የሚታይበት ሁኔታ ‘’revision’’ ይባላል፡፡ በወንጀል ተከሶ የተቀጣ ሰው ፍርዱ እንዲከለስለት የሚያመለክተው፡- በሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ እንደሆነ ሞተ የተባለው ሰው በሕይወት መኖሩን የሚያመለክት ጥርጣሬ ሲኖር፤ ቅጣቱ ከተወሰነ በኋላ በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በይግባኝ ሥልጣኑ ሌላኛው ፍርድ ቤት ተመሳሳይ ክስ በተመሰረተባቸው ሰዎች ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ቀድሞ ከተወሰነው ጋር የማይጣጣም ሲሆንና የተፈረደበትን ሰው ንፁህ መሆን የሚያመለክት ሲሆን፤ የጥፋኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ከምስክሮች ቢያንስ አንዱ በሐሰተኛ ምስክርነት ሲከሰስና ጥፋተኛ ሲሆን ወይም ሊገኝ የማይችል ሲሆን፤ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ፍርዱ በተሰጠ ጊዜ ለፍርድ ቤቱ ያልታወቀ አዲስ ነገር ሲከሰትና የተከሳሹን ጥፋተኛ መባል ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሲሆን ነው፡፡
የፍርድ ክለሳ (revision) ጥያቄ የሚቀርበው በፍትህ ሚኒስቴር፣ ጥፋተኛ በተባለው ሰው (ችሎታ የሌለው ከሆነ በወኪሉ) ወይም ተከሳሹ የሌለ ወይም የሞተ እንደሆነ በትዳር ጓደኛው፣ በልጆቹ፣ በወላጆቹ፣ በወራሾቹ ወይም እሱ ሃላፊነት በሰጣቸው ሰዎች ነው፡፡ የፍርድ ይከለስ አቤቱታ የሚቀርበው አምስት አባላት ላሉት የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ነው፡፡
ዐቃቤሕግ የሚወከለው በሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ዐቃቤሕግ ነው፡፡ ጉዳዩን የሚያየው ፍርድ ቤት በማንኛውም ጊዜ የቀድሞውን የፍርድ አፈጻጸም ማስቆም ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተከሳሹ ንጹህ መሆኑን ካረጋገጠ ፍርዱንና የተያያዙ ውሳኔዎችን ከመዝገብ ይሰርዛል፡፡
የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔው የተሻረለት ሰው ለደረሰበት ጉዳት ሙሉ የማቴሪያልና የሞራል ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ነገር ግን ጥፋተኛ የተባለው እውነተኛ ወንጀል ፈጻሚ ከሕግ እንዲያመልጥ በተሳሳተ ክስ ሆን ብሎ ጥፋተኝነቱን አምኖ የተቀበለ መሆኑ ከተረጋገጠ ካሳ አያገኝም፡፡ በጥፋተኝነትና በቅጣት ውሳኔ ጉዳት ደረሰብኝ የሚል ማንም ሰው ካሳ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ የካሳው መጠን የሚሰላው በባለሙያ ሲሆን ውሳኔ የሚሰጠው በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ነው፡፡ ጥፋተኛ አለመሆኑን ያረጋገጠው ሰው ንፁህ መሆኑን ውሳኔ የሰጠው ፍርድ ቤት የካሳውንም ጉዳይ እንዲወስንለት መጠየቅ ይችላል፡፡ ካሳው የሚከፈለው በመንግሥት ሆኖ፣ መንግሥት በበኩሉ በማንኛውም ሐሰት ጠቋሚ፣ ሐሰተኛ ምስክር ወይም በማንኛውም ጉዳዩ በሚመለከተው ሰው ላይ ክስ የመመስረትና ገንዘቡን የማግኘት መብት አለው፡፡ ተከሳሹ ነጻ መደረጉ በፍርድ ቤቱ በተመረጡ አምስት ጋዜጦች ታትሞ መውጣት አለበት፡፡
የፍትህ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ የሚታዩትን ክፍተቶች ለመለየትና በፖሊሲ ለማስደገፍ እንቅስቃሴ ማድረግዎን ገልጸዋል፡፡ ምን ውጤት ተገኘበት?
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት በፖሊሲ በማስደገፍ ለመዝጋት ከተለዩት ችግሮች አንዱ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና ስለሚታይበት ሁኔታ ነበር፡፡ በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የሚታየው በስህተት የተፈረደበትን ሰው ነጻ ለማድረግ ወይም በስህተት ነጻ የሆነው ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን ከላይ ከተመለከቱት የሌሎች አገሮች እና ዓለም አቀፍ ልምዶች ለማየት ይቻላል፡፡ በ1999 ዓ.ም ተዘጋጅቶ በ2001 ዓ.ም ለፌዴራልና ለክልል የፍትህ አካላት ውይይት ቀርቦ በነበረው ረቂቅ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ ላይ፤ በስህተት ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣም ሆነ በስህተት ነጻ የሆነ ሰው ጉዳይ እንደገና ታይቶ ፍትሐዊ ውሳኔ የሚሰጥበት መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫ በአንቀጽ 2.4.11. ተመላክቶ ነበር፡፡ ይኸውም፡- “ፍርድ ቤት በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ጥፋተኛ የተባለ ሰው ከውሳኔው በኋላ ጥፋተኛ አለመሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ከተገኙ በዐቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሹ አቤቱታ አቅራቢነት የመጨረሻውን ውሳኔ በሰጠው ፍርድ ቤት እንደገና ታይቶ ተከሳሹ ነጻ ሊሆን ይችላል፡፡ በፍርድ ቤት በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ በነጻ የተለቀቀ ተከሳሽ በሐሰተኛ ማስረጃ የወጣ መሆኑ ከተረጋገጠ በዚሁ ምክንያት የወንጀል ክስ የሚቀርብበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነጻ በተባለበትም ድርጊት ዐቃቤሕግ በድጋሚ ክስ ሊመሰረትበት ይችላል፡፡” የሚል ነው፡፡
በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም ረቂቅ ፖሊሲውን ለተሰብሳቢዎቹ ያቀረብኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ሰብሳቢው ደግሞ በወቅቱ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ነበሩ፡፡ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ተሳታፊዎቹ የፌዴራልና የክልል ፍትህ አካላት የበላይ አመራሮች፤ በስህተት የተፈረደበት ሰው ጉዳይ እንደገና ይታይ የሚለውን የፖሊሲ አቅጣጫ ደግፈው ነበር፡፡ ነገር ግን በሐሰት ማስረጃ ነጻ የወጣ ሰው ጉዳይ እንደገና ይታያል የሚለው በአብዛኛው ተሳታፊ ውድቅ ሲደረግ የድጋፍ ድምጽ የሰጠነው እኔና አቶ ተፈራ ዋልዋ ብቻ ነበርን፡፡
የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው በዚህ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ አንቀጽ 4.8.1.3፤ በሐሰተኛ ማስረጃ ነጻ የሆነ ሰው እንደገና የሚከሰስበትን ሁኔታ ሳያካትት በስህተት የተፈረደበት ሰው ነጻ የሚደረግበት ሥርዓት ብቻ ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት በመጨረሻ ውሣኔ ጥፋተኛ የተባለ ሰው ከውሣኔው በኋላ ጥፋተኛ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ከተገኘ በዐቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሹ አቤቱታ አቅራቢነት ጉዳዩ የመጨረሻ ውሣኔ በሰጠው ፍርድ ቤት እንደገና ታይቶ ተከሳሹ ከወንጀሉ ነፃ ሊደረግ የሚችልበት ሥርዓት በተዛማጅ ሕጎች ውስጥ በግልጽ እንዲሰፍር እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡
ከላይ እንዳነሳሁት ጥቅምት 2001 ዓ.ም በረቂቅ ፖሊሰው ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት፣ በሐሰት ከሕግ ያመለጠ ሰው ጉዳይ እንደገና መታየት እንደሌለበት በመንግሥት ከፍተኛ አካላት አቋም የተያዘ ሲሆን ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲጸደቅም ይሄው ሃሳብ ሳይካተት መቅረቱ ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡
የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ ከወጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፖሊሲው ከወጣም በኋላ ችግሩ ለምን ቀጠለ?
ፖሊሲው የመጨረሻው የወንጀል ፍርድ ውሣኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት እንደገና ታይቶ ተከሳሹ ከወንጀሉ ነፃ ሊደረግ የሚችልበት ሥርዓት በተዛማጅ ሕጎች ውስጥ በግልጽ እንዲሰፍር እንደሚደረግ ደንግጓል፡፡ ሆኖም ወደፊት በሚወጣው የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ውስጥ እስከሚደነገግ ድረስ ፖሊሲውን በመጥቀስ ጉዳዩን ፍርድ ቤት በማቅረብ መከራከር የማይቻል መሆኑ በፍትህ አካላት ስለታመነ ነው ፖሊሲው እያለም ችግሩ የቀጠለው፡፡
በእኔ እምነት ግን እንኳንስ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተካቶ ቀርቶ ቀድሞውንም በስህተት የወንጀል ቅጣት የተወሰነባቸው ሰዎች ጉዳይ እንደገና ታይቶ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዳይሰጥ የሚከለክል ሕግ አልነበረም፡፡ ስለሆነም የመጨረሻ የወንጀል ፍርድ በድጋሚ የሚታይበት ሥርዓት የለም ብሎ መከራከር ተቀባይነት የለውም፡፡
በወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ውስጥ የሚታየው የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የማየት ችግር መፍትሔው ምንድ ነው?
ይህ ለዜጎች መብትና ነጻነት እንዲሁም ለአገሪቱ የፍትህ ሥርዓት ፈታኝ የሆነው ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡
ዋነኛው መፍትሔ አዲስ በመረቀቅ ላይ ባለው የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ውስጥ ፖሊሲው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የሚታይበትን ሁኔታ በማካተትና በፍጥነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡
በእርግጥ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕጉን በአዲስ መልክ ለማውጣት ጥረት ማድረግ የተጀመረው ከአስር ዓመት በፊት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም፡፡ የአቅም ውስንነትና የማርቀቁ ሂደት የተበታተነ መሆን፣ ክልሎች የየራሳቸውን የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ እንዲያወጡ መመሪያ መተላለፉ፤ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲው የተካተቱ አንዳንድ መርሆዎች ውስብስብ በመሆናቸው ዘርዝሮ በሥነሥርዓት ሕጉ ለማካተት ዕውቀትና ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ፣ ወዘተ… ለመዘግየቱ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡ አሁን ግን በሕገመንግሥቱ መሰረት የወንጀል ሕግ የማውጣት ሥልጣን የፌዴራል መንግሥት ነው የሚል ስምምነት ስለተደረሰ፣ በፌዴራል ደረጃ እየተረቀቀ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ሆኖም የወንጀል ሥነሥርዓት ሕጉ አሁን ላጋጠመው ችግር ቶሎ ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ሌላው መፍትሔ የወንጀል ሥነሥርዓት ሕጉ እስከሚወጣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ማሻሻያ በማዘጋጀት በፍርድ ቤቱ የወንጀል ዳኝነት ሥልጣን ሥር የፖሊሲውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ፣ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የሚታይበትን ሁኔታ በማካተት፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ በአማራጭ ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ በማዘጋጀት በስህተት የተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ እንደገና የሚታይበትን ሥርዓት በማካተት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህን በአማራጭ የተጠቀሱትን ረቂቅ የማሻሻያ ሕጎች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፍትህ ሚኒስቴር በጋራ ወይም በተናጠል ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡
ከዚህም ሌላ ዐቃቤ ሕግ በስህተት የተሰጠ የወንጀል ጉዳይ ፍርድ ሲያጋጥመው ለይቅርታ ቦርድ ከማቅረብ ይልቅ በስህተት የተሰጠ ፍርድ እንደገና እንዳይታይ የሚከለክል ሕግ አለመኖሩንና በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ የተፈቀደ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ የማይቀበል ከሆነ ደግሞ እስከ ሰበር ችሎት በማቅረብ ማስወሰን ይችላል፡፡ የሰበር ችሎቱ ጉዳዩን ተቀብሎ ካስተናገደ የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት፣ በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ስላለው ሕግ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በዚህ ብቻ ሳያበቃ በስህተት የተሰጠ ፍርድ የዜጎችን ሕገመንግሥታዊ መብት የሚጋፋ ስለሆነ፣ ሕገመንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ በማቅረብ ማስወሰን ይችላል፡፡ ይህን ዓይነት ሕጋዊ ሥርዓቶችን ወደ ጎን በመተው ጥፋተኛ ያልሆነ ሰው እንደጥፋተኛ ተቆጥሮ ይቅርታ እንዲደረግለት ጥያቄ ማቅረብ የህጉን ዓላማና ግብ የሚያሳካ አይሆንም፡፡
በስህተት ከሕግ ያመለጡ ሰዎች ጉዳይ እንደገና እንዲታይ የሚያስችል ድንጋጌ በፖሊሲው እንዳይካተት የተፈለገው ለምንድነው?
ይህ ጉዳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው ነው፡፡ አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ በቦሌም ይሁን በባሌ ከተጠያቂነት ያምልጥ የሚል የሕግ መንፈስ የለም፡፡ የሌሎች ሀገሮች ልምድም ይህን አያሳይም፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የተረቀቀውና በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም ለፍትህ አካላት ጉባኤ የቀረበው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ፣ በሐሰት ማስረጃ ነጻ የሆኑ ሰዎች ጉዳይ እንደገና ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ የቀረበ ቢሆንም በአብዛኛው ሰው ድምጽ ውድቅ ተደርጓል፡፡
በ2003 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፖሊሲም እንዳይካተት ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም፡፡ እንኳንስ የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ደካማ በሆነበት እና በተንኮል የተተበተበ ጉዳይ በሚያስተናግድ አገር ቀርቶ፣ የፍትህ ሥርዓታቸው አድጓል በሚባሉ አገሮች ስህተት እንደሚፈጠር ታምኖ የሚታረምበት ሥርዓት ተበጅቷል፡፡ በሀገራችን እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት እንዳይዘረጋ የተፈለገው ማጭበርበር እየበረከተ ስለሄደና አጭበርብረው ከሕግ የሚያመልጡትን መከታተል አዳጋች በመሆኑ እንደወጡ እንዲቀሩ ስለተፈለገ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ በቦሌም ሆነ በባሌ ነጻ የወጣውን ሰው ጉዳይ እንደገና ማየት ድጋሚ ክስ ስለሆነ ሕገመንግሥቱንና የወንጀል ሕጉን ይቃረናል ይላሉ፡፡ ሁሉም የተሳሳቱ መከራከሪያዎች ናቸው፡፡በረቂቅ ፖሊሲው ተካቶ የነበረው መደበኛ በሆነ አሰራር ነጻ የወጡ ተከሳሾችን የሚመለከት ሳይሆን አጭበርብረው የወጡትን ብቻ የሚመለከት ነበር፡፡
ስለሆነም ሊያጋጥም የሚችል ችግር መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ አጭበርባሪዎች ከሕግ እንዳያመልጡ በሀሰተኛ ማስረጃ ነጻ የሆኑ ሰዎች ጉዳይ እንደገና ታይቶ ፍትሐዊ ውሳኔ የሚሰጥበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

 

br /

Read 10123 times Last modified on Saturday, 24 November 2012 12:01