Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 12:04

አርሰናል 3 ፉልሃም 3 ፉልሃም

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ምስራቅ በለሳ/ሰሜን ጐንደር/
መቼም ሰው ለስራ ጉዳይ ብሎ የማይገባበት ቦታ የለምና፤ እኔም ለዚሁ እንጀራዬ ብዬ ወደ ሰሜን ጐንደር ካቀናሁ ሶስተኛ ሳምንቴን ያስቆጠርኩ ሲሆን የምስራቅ በለሳ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው ጉሃላ የስራዬ መደምደሚያ ወረዳ ስትሆን ወረዳዋ ከምእራብ በለሳ ተገንጥላ ራሷን የቻለች ወረዳ እንድትሆን የተደረገው በቅርቡ ሲሆን ወረዳዋ ከተማ ከተማ እንድትሸት መንግስት፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ነጋዴውና ህዝቡ የበኩሉን እየጣረላት የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
አንድ ቅዳሜ ቀን የመስክ ስራዬን አጠናቅቄ ሆቴል ውስጥ አረፍ ብዬ መጽሐፍ በማንበብ ላይ ሳለሁ ሁለት እጅግ የተበሳጩ የሚመስሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ቡድናቸው አርሰናል ከፉልሃም ጋር 3-3 በመለያየቱ ምክንያት የ90 ደቂቃውን ኳስ እየገመገሙ ሲያወሩ ጆሮዬን ጣል አድርጌ ሰማሁና፣ ከጨዋታቸው ውስጥ ብዙ የሚያዝናኑና የሚያስተምሩ ነገሮች አገኘሁና እስኪ ለአንባቢ ላካፍል ብዬ አሰብኩ፡፡ አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ግን የጐንደርኛ ዘዬን ይልቅ ሲሰሙት ይበልጥ ሊያዝናና እንደሚችል ይሰማኛል፡፡

አንዱ፡-ኧረ አፈር ይብላ አንተ እንደው ቬንገር የሚባል ሰው መጫወቻ አርጐን ቀረ እኮ?
ሁለተኛው፡- እረዲያ ተዎው እሱማ እንደው እንደከብት እያደለበ መሸጥ ብቻ!
አንዱ፡-ደሞ እኮ ሚገርመው ተናደድሁ ብሎ ያነን ሀይላንድ እየጠጣ መወርወር እየጠጣ መወርወር አረ የዞዝ አምባው ጊዮርጊስ!!
ሁለተኛው፡- እሱንማ እኮ ማነው የሃይላንድ ፋብሪካው ከሶታልን (ከሶታል እኮ)፤
አንዱ፡-ምን ብሎ?
ሁለተኛው፡- ውሀውን እየጠጣ ሃይላንዱን እየጠመዘዘ የሚጥል ምን ቆርጦት ነው ብሎ፤ በዚህ መሃል የተናደዱበትን ምክንያት ለማወቅ አርሰናል ተሸነፈ እንዴ” ጠየኳቸው
አንዱ፡-ኧረ ምን ይሸነፋል እንተው! ያ ገዳፋ አርቴታ እንደው ባለቀ ሰዓት ኢሊጐሬ ስቶ አቻ ወጣ ንጂ
ሁለተኛው፡-ኧረ ለመሆኑ አርቴታ ምን ኩኖ ነው ግን ልሙስሙስ አርጐ የመታው?
አንዱ፡-እንደው ያነን ቫንፐርሲን ባይሸጠው ኑሮ እኮ እሱ ደህና አድርጐ ይመታው ኑሯል?
ሁለተኛው፡- ኧረ ቫንፐርሲማ መቶት ቢሆንማ ኑሮ ከቴም በረኛው እይዛለሁም አይል እንጂ! ቫንፐርሲማ መናጢ ነበር? አመርዝዞ (መርዘኛ እንደማለት) ነበር የሚመታው፤
አሁንም በመሃል ገብቼ እንዴት አገኙ አልኩኝ?
ሁለተኛው፡-ያቺ ማናት አርሻቪ በላይ ገጥ ይዛው መጣችና ተከላካዩ ሁለት እጁን ክርፍፍ አርጐ ቢመጣ ጊዜና እንደው እጁ ላይ አኑራው ሄደች፡፡ ምን ዋጋ አለው አንተ አርቴታ ተጫወተብን እንጂ፡፡ አንተዬ ኢሊጐሬው ሲሳት እኮ ነው ዳኛ ፊሽካ ነፍቶ ጨዋታው ያለቀ
አንዱ፡-እኔ እኮ አርጐ የሚነደኝ ቪንገር የት ያውቀኝ ብዬ ነው መናደዴ? በለሳ ወዜት (ወዴት) ነው? እብናት ወዜት ነው? ቢሉት ህዚህ አሉ የማይለንንስ ምን አገባኝ ብዬ ምናደድ? እረረረ!!!
አንዱ፡-በል ና አሁን እራት እንብላ?
ሁለተኛው፡-ኧረ ተቃጥያለሁ አንተ እኔ አልበላም
አንዱ፡-ተው ግድየለም ብላ ኋላ ደግሞ ያቺ ወባ በራበው አንጀትህ ገብታ ስታንጠራውዝህ እንዳታድር?
ሁለተኛው፡-ኧረ ተወኝማ ወባ አብሬያት ኑሬ ምን ታረገኝ ብለህ ቪንገር ተጫወተብን እንጂ፡፡ በምን ቀን ይህን አርሰናል ሚባል ቡድን መደገፍ እንደጀመርኩ …
አንዱ፡-ይህማ እርግማን ነው!! እናቴ ረግማኝ ኑራ ነው ሚሆንጂ ማንቸስተርን፤ ቼልሲን ደግፌ ዝም ብዬ እየሳቅሁ አልኖርም ኑሯል?
ሁለተኛው ፡- ኧረ እንደው አንተ ሌላ ቡድን ከምደግፍስ እንደው ሞቴ ይቅረብ (የአካባቢው ህዝብ ቃሉን በመጠበቅ ይታወቃል)
አሁንም በድጋሚ መሃል ገባሁና “በለሳ ላይ የአርሰናል ደጋፊ ይበዛል? እኔ እንኳን “አርሰናል ዳቦ ቤት፤ አርሰናል ፎቶ ቤት” የሚል አይቻለሁ ብዬ ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡
አንዱ፤ “ኧረ ተወኝ አንተ ሙላው የበለሳ ሰውና ኩታራው አርሰናል ነው፡፡ ኧረ ደጋፊውን ትተህ ሰው የሚጭነው አይሱዙ መጠሪያው ዋልኮት፤ ቫንፐርሲ ነው ሚባል፡፡ ፈዳላዎቹ ገና ከሩቅ አይሱዙው ሲመጣ አይተው ዋልኮት ገብቷል፤ አርሻቪ ወጥቷል እኮ ነው ሚሉ” አሉኝና ግርምትን ጭረውብኝ አለፉ፡፡
ሁለተኛው፡- “ኧረ ኩታራውና ፈዳላው አርጐ እንደበሰጨ (እንደተበሳጨ)!!! አንተዬ እንዲያው ወገቡ ስብር ብሎ እኮ ነው የወጣ፡፡
አንዱ፡-“ናስኪ ያነ ማንችስተር ከአስቶንቪላ ጋር 2፡30 ይጫወታል፤ እስከ እረፍት እንኳን ቢሆን አይተነው ቤታችን እንግባ” ሲባባሉ እኔም የማንችስተር ደጋፊ እንደመሆኔ ጨዋታውን ልይ ብዬ… “ወንድም ይቅርታ እራት እስክበላ እንዳይሞላ እባክህ ቦታ ያዝልኝ” ስለው በግራ መጋባት መንፈስ አየኝና “እህ ላውቶብሱን ነው ቦታ ያዝልኝ የምትል” ሲለኝ ሳቄን እንደምንም ተቆጣጥሬ ላስረዳው ስል ሃሳቤ የገባቸው ጓደኞቹ እሱን ፋራ በማድረግ “እረ ይህ ባላገር ለኳሱ ነው ቦታ ያዝልኝ ሚልህ፡፡” ብለው ተሳለቁበት፡፡ ኋላ ሳጣራ ሰውየው ለካ የአይሱዙ አውቶብስ ሹፌር (ኑሯል) ነበር፡፡ ዲኤስ ቲቪ ቤቱ ግን ከጠበቅሁት በላይ ሆኖብኛል፡፡ እውነት ለመናገር አዲስ አበባ ካሉ አንዳንድ ቤቶች በእጥፍ ይበልጣል የመቀመጫዎቹ ስፋት፤ ዋጋው 2 ብር ነው፡፡ በቂ ንፋስ አለው ወዘተ፡፡ ምስጋና ለሸዋየ ሆቴል፡፡
ሌላው ትኩረቴን የሳበው ነገር የማንችስተርና የአስቶንቪላ ጨዋታ በቪላ 1-0 መሪነት እረፍት ወጥተው የተወሰነው ሰው ወደ ውጭ ሲወጣ የተወሰነው ባለበት ቆየና የኳስ ተንታኞችን አስተያየት በጽሞና ሲየዳምጥ ሳይ ወይ የአዲስ አበባ ተልካች ያ በእረፍት ሰአት ከወንበር ወንበር እየዘሎላችሁ የምታወሩት ወሬና ጩኸት ምነው እዚህ መጥታችሁ ብትማሩ እንድል አርጐኛል፡፡
ከእረፍት መልስ ፈርጉሰን አሽሊ ያንግን አስወጥተው ቺዥከሪቶን ቀይረው አስገብተውት ሁለተኛው 45 ሲጀመር ኳሱን ከቫንፐርሲ ጋር የጀመረው እርሱ ነበር፡፡
ከጥቂት ደቂቃ በኋላም ስኮልስ በሰራው ስህተት በካውንተር አታክ ቪላ 2ኛውን ጐል አስቆጠረና ውጤቱ 2-0 ሆነና የቪላው አሰልጣኝ ጭፈራ ልዩ ነበርና ከጐኔ የነበረው፤
አንዱ ፡-እረ ይቺ አሰልጣኝ ኋላ የት ትገባ ይሆን? እንደው ቅልብጥ ቅልብጥ አበዛች’ሳ
ብዙም ሳይቆይ ግን ስኮልስ ስህተቱን ክሷል በሚያስብል ሁኔታ ለቺካሪቶ ያሻገረለትን ኳስ ቺካሪቶ በድንቅ ብቃት ኳሷን ወደ ጐል ቀየረና በደስታ ጨፍረን ቁጭ ከማለታችን ካሜራው የቺካሪቶን ምስል ሲሳየን ያው ሰውዬ “እረገኝ ደግሞ ቺካሪቶ መች ነው የገባ” ሲል መቼም በሰው ሀገር ብስቅ አደጋ እንዳይኖረው ሰጋሁና በውስጤ ሳቅሁ እንጂ ወሬውስ እንኳን ሳቅን ትንታንም የሚያመጣ ነበር፡፡ እስኪ ይታያችሁ ስለቺካሪቶ ከላይ ያወራሁት ሁሉ ሲደረግ ይህ ሰው ከጐኔ ቁጭ ብሎ እያየ ነው፡፡ እሺ እንግሊዝኛ አይችልም እንበልና ኳስ ዘጋቢዎቹን ያለመስማት ውስንነት ሊኖር ይችል ይሆናል ነገር ግን 2ኛው 45 ሲጀመርና ጐሉን ማን እንዳገባው በአይን ብቻ ማየት በቂ አልነበር፡፡ እንደው በድንገት ጥያቄው ሲነሳ ግን ከማሳቅም አልፎ ማስገረሙ አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተጠናቀቀው ቺካሪቶ ሃትሪክ ሰርቶ በማንችስተር 3-2 አሸናፊነት ሲሆን፡፡ ታዲያ ማንችስተር እየመራ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቪላ በከፍተኛ ጫና ያጠቃ ነበርና ያው ሰው ጭንቀቱን ሲገልጽ “እረ የዞዝ አምባው ጊዮርጊስ ፈጁነ ፈጁነ ፈጁነ” እያለ ነበር፡፡ በመጨረሻ ጨዋታው አልቆ ተጫዋቾች ሁሉ ቺካሪቶን እያቀፉ ሲሰሙ ከፊት አካባቢ የተቀመጠ አንድ ደጋፊ “እረ በወዜት (በየት) መጥቼ ልሳምሽ እረ በወዜት ላግኝሽ እረ ደህና አርገህ ሳምልኝማ እቺን ጀግና” ይሄን ፈዳላ ሁሉ አፉን አስያዘችልኝም አይደል እያለ ወጣ፡፡ መቼም ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ከአዲስ አበባ 700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሆነው በአለም ከፍተኛ ህዝብ የሚከታተለውን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ላይቭ እግር ኳስ ማየት መቻላቸው አስገራሚ ቢሆንም በለሳ ላይ ሆነው የእረፍት ሰዓቱ ማስታወቂያ ሲያዩት ግን ወይ አለቦታው የመጣ ማስታወቂያ ያሰኛል እውነት አሁን የ4 ኦሎምፒኮች ውሃ ዋና ሻምፒዮናው የማይክል ፍሌፕስ የhead and shoulder ሻንፖ ማስታወቂያና፤ የመኪናውን መሪ በእጅ ሳያዞሩት ራሱን እያሽከረከረ ፓርክ ማድረግ ሚችለውን ዘመናዊውን ford መኪና ማስታወቂያ ለበለሳ ሰው ምኑ ነው? አጃኢብ ያሰኛል፡፡ እኔም ዛሬ የሰማሁትን እንዴት አድርጌ እንደምተይበው እያሰብኩ ወደ ማደሪያ ሆቴሌ አቀናሁ፡፡

 

Read 6485 times Last modified on Saturday, 24 November 2012 12:13