Saturday, 24 November 2012 12:12

የማህጸን መውጣት ...ለማህበራዊ ችግርም ያጋልጣል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

.....እኔ ሴት ሁኜ መፈጠሬን እስከምረግም ድረስ የደረስኩበት ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ ችግሩ የደረሰው በእህ.. ላይ ነው፡፡ የምትኖረው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል በገጠር በምትኖርበት ጊዜ ዘጠኝ ልጅ ወልዳለች፡፡ አሁን ወደአዲስ አበባ የመጣችው ልጆችዋ ለሚሰሙዋት ሕመሞች መፍትሔ እንሻለን በሚለው ስለአመጡአት ነው፡፡ መቼም ከልጆቹ ደግሞ በእድሜም ከፍ የምለው እኔ እህትዋ ስለሆንኩ አንድ ቀን በድንገት ድረሽ ይሉኛል፡፡ እኔም እህ..ን ምን አገኛት ብዬ ሄድኩ ፡፡ ስደርስ ግን እኔ እህ..ን ላስታምም ሳይሆን እነ እርሱ እኔን ማስታመም ነበር የገጠማቸው፡፡ በቃ...ባየሁት ነገር በመደናገጤ በድንገት ነበር ስውር ያደረገኝ እና ከተቀመጥኩበት ሸርተት ያልኩት፡፡ የእህ..ን ልብስ ገለጥ አድርገው ከብልትዋ አካባቢ የተፈጠረው ነገር ምንድነው በሚል ሲጠይቁኝ እኔ ያየሁትን ማመን አቃተኝ፡፡ ለካንስ እኛ ሴቶች ስንፈጠር ስንት ችግር አለብን? ...ህክምና ደግ ነገር ነውና አሁን ታክማለች፡፡ ነገር ግን ማህጸን የሚባለው አካል እንዲህ ውልቅ ሊል የሚችል ነገር መሆኑን በአይኔ ስላየሁ ፕሮግራማችሁን ስሰማ አላስችል ብሎኝ ነው ይህንን መልእክት የላኩላችሁ፡፡... ..
እጅጋየሁ መኮንን ከኮልፌ፡፡

ባለፈው ሳምንት የማህጸን መልቀቅን ምንነትና ምክንያት ከባለሙያ ጋር ቃለምልልስ በማድረግ ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡ በችግሩ ዙሪያ የሚሰጠውን መፍትሔ ለዚህ እትም አቆይተን ነበር ፡፡ የማህጸን መውጣት ማለት ማህጸን በዙሪያው ያሉ ጅማቶች መላሸቅ ሲደርስባቸው ማህጸኑን አንጠልጥሎ ወይንም አቅፎ የሚይዘው አካል ስለማይኖር የሚፈጠር ችግር መሆኑን ባለሙያው ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት እትም አብራርተዋል ፡፡ ይህ ችግር ሊከሰት የሚችለውም ብዙ ልጅ በመውለድ...ለረጅም ጊዜ ምጥ ላይ በመቆየት... በተለይም እድሜአቸው በወር አበባ መቆም ክልል የሆኑ ሴቶች ይበልጡኑ እንደሚጎዱ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ ጠቁመው ነበር፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ...በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ...የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ለዚህም ህትመት መፍትሔ ነው ያሉትን ሙያዊ ምክር ለግሰዋል፡፡ 
ኢሶግ/ የማህጸን መውጣትን ለመከላከል መፍትሔው ምንድነው?
ዶ/ር እንግዲህ ስለህክምናው ስናወራ ብዙ ጊዜ እኛ የምንመክረው ችግሩ ከመድረሱ በፊት የመከላከል ተግባር እንዲቀድም ነው፡፡ ችግሩ ከደረሰ በኋላ ከመሯሯጥ አስቀድሞ መከላከሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስለሆነ ነው፡፡ ስለመከላከል ስንነጋገር የመጀመሪያው ደረጃ ፡-
ለችግሩ የሚያጋልጡ ነገሮችን መከላከል ነው ...ለምሳሌም ውፍረት አንዱ ለችግሩ የሚያጋልጥ ስለሆነ ማንኛዋም ሴት በዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባታል፡፡ ሌላው በመውለድ ጊዜ በተቻለ መጠን ወደጤና ኤክስ..ንሽን ወይንም ጤና ተቋም ሄዶ መውለድ እንጂ በቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ በምጥ መቆየት ተገቢ አይሆንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሆድ እቃ ላይ ክብደት የሚያመጡ እንደሳል የመሳሰሉ ነገሮችን በፍጥነት ማስወገድ ይገባል፡፡ እንዲሁም ብዙ ልጅን መውለድ በራሱ ለማህጸን መውጣት ምክንያት ስለሚሆን የልጅ ቁጥርን በመጠኑ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የልጅን ቁጥር መወሰኑ ለማህጸን መውጣት ብቻም ሳይሆን ለሌሎች ብዙ ተያያዥ ነገሮች ጠቀሜታ እንዳለው ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ/ ለተለያዩ አካላዊ ጤንነቶች የሚረዳውን እስፖርት መስራት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ ስፖርት መስራት በማህጸን አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን በማጠንከር ረገድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የእስፖርቱ አይነት የተለያየ ሲሆን ለማህጸን መውጣት ምክንያት ከሚባሉት ሕመሞች መካከል እንደስኩዋር ...የወገብ አከርካሪ እና ስፓይናል ኮርድ አካባቢ የህመም ስሜት ካለ እስፖርት በመስራት ችግሩን ማስወገድና ለማህጸን መውጣት ምክንያት እንዳይሆን እና ሕመም እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ/ ማንኛዋም ሴት አስቀድማ ወደህክምና ባለሙያ በመቅረብ የማህጸን ምርመራ የምታደርግ ከሆነ አስቀድሞውኑ ችግሩ እንዳይፈጠር ማድረግ ትችላለች፡፡ከዚህም በተጨማሪ ምናልባት የህመም ስሜት እንኩዋን ቢኖራት በማህጸን አካባቢ በሚሰራ የአካል ማጠንከሪያ መከላከል ይቻላል፡፡ ይህ እስፖርት ኬግልስ የሚባል ሲሆን የሚሰራውም ልክ አንድ ሰው ሽንት ወይንም አየር ሊያመልጠው ሲሞክር ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ሰውነትን እንደ ማኮማተር ነው፡፡ በማህጸን አካባቢ የሚደረገው ሰውነትን ቆንጠጥ እያደረጉ እየቋጠሩ መልቀቅ ጅማቱን ስለሚያጠነክረው መላላቱን ይከላከላል፡፡ ይህ አካልዊ እንቅስቃሴ ልክ አንድን ነገር ከመሬት ላይ ቆንጥጦ እንደመነሳት ወይንም አንድ ሰው ከቀዝቃዛ መሬት ..ሴራሚክስ.. ላይ ባዶ ገላውን ቢቀመጥ ሊያደርገው የሚችለውን የጡንቻ መኮማተር እያሰቡ ወደውጭ መግፋት ሳይሆን ወደውስጥ በመሳብ ነው የሚሰራው፡፡ ይህ እስፖርት ...ማለትም በማህጸንና በብልት አካባቢ አኮማትሮ መቆየት ከስምንት እስከ አስር ሴኮንድ መቆየት ሲገባ ድግግሞሹ ደግሞ ቢያንስ በአንድ ጊዜ ከአስር እስከ አስራሁለት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን እንቅስቃሴ በአንድ ቀን እስከ ሶስት ጊዜ ማድረግ እና በትንሹ እስከሶስት ወር ድረስ መስራት ይጠበቃል፡፡ በዚህ መልክ አካላዊ እንቅስቃሴ ከተደረገ የማህጸን መውጣትን ብቻም ሳይሆን ሽንትና ሰገራን የመቆጣጠር ችግር ያለበት ሰውም ወደጤነኛ ሁኔታ ሊመለስ ያስችለዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ሴቶችን በተለይ የምንመክረው በተለይም የወለዱና ለመውለድ ያሰቡ ከሆኑ ውሎ አድሮ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞውኑ ብልትና ማህጸናቸው አካባቢ መቆንጠጥ ወይንም ማኮማተርና መልቀቅን እንደልማድ አድርገው በተደጋጋሚ ቢሰሩ አስቀድመው ችግሩን መከላከል ይችላሉ፡፡
ኢሶግ/ ሴትየዋ ከምትሰራው አካላዊ እንቅስቃሴ ባሸገር በህክምናው ዘር የሚደረገው እርዳታ
ምን ይመስላል?
ዶ/ር ችግሩ በህክምና ሊረዳ ከሚገባው ደረጃ የደረሰ ከሆነ ማህጸን እስከብልት ጭምር ወደውጭ ተዘርግፎ ወጥቶአል ማለት ነው፡፡
ይህ በጣም አደገኛው ሰአት ነው፡፡ ማህጸኑ ወደ ውጭ በመውጣቱ ምክንያት በንክኪ መቁሰል ይመጣል፡፡ ሴትየዋ እንደልቡዋ መንቀሳቀስም ሆነ መቀመጥ አትችልም፡፡ ስለዚህ በሕክምናው የሚደረገው እርዳታ በኦፕራሲዮን የታገዘ ነው፡፡ ከኦፕራሲዮን በፊት ግን የሚሰጠው የህክምና አይነት እራሱን የቻለ መሳሪያ ያለው ሲሆን መሳሪያው ማህጸን ውስጥ የሚገባ ነው ፡፡ መሳሪያው በማህጸን ውስጥ በመግባቱ ማህጸኑ ያጣውን ድጋፍ አርተፊሻል በሆነ መንገድ ሲሰጠ ማህጸን ባለበት ደረጃ ሊያቆየው ይችላል ፡፡
ይህ የህክምና አይነት ግን በእኛ አገር የለም ፡፡ ሌላው ሕክምና እንግዲህ ኦፕራሲዮን መስራት ነው ፡፡ የነበረውን የጅማት መላላትና የጡንቻ መድከም እንዲሁም የነበሩትን የፊኛ እና የሰገራም መውጫ ቦታውን መልቀቅ የመሳሰሉት ሁሉ በኦፕራሲዮን እንደገና ይጠገናል፡፡ በዚህ ስራ እያንዳንዱን የቆሰለውን ቦታ የት ቦታ እንዳለ ስለሚታወቅ ያንን ነገር መልሶ የመጠገን ስራ ሲሆን በዚህ ሂደት ማህጸኑ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ በእርግጥ ያንን ማውጣት ሕክምና ሆኖ ሳይን ማህጸን ሲወጣ ለሌሎቹ ለተበላሹት ወይንም ስራቸውን ላዳከሙት ጅማቶች ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል በግልጽ ችግሩ እንዲታይ ሲባል ነው ማህጸኑ እንዲወጣ የሚደረገው፡፡ ኢሶግ / ማህጸኑ ከወጣ ሕክምናው ይበልጥ ትኩረት የሚያደርገው ከየትኛው አካል ላይ ነው?
ዶ/ር ማህጸን መውጣት ሲባል በአካባቢው ያሉትን እንደ ብልት ...የሽንት ፊኛ የመሳሰሉትን አካል ያካተተ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሸካሚ ጅማቶቹ መላላት የሚያስከትለው ችግር ዙሪያውን ባሉ አካላት ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ በተለይም ማህጸኑ ሲወጣ አብሮት የወጣው ብልት ወደነበረበት መመለሱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ሰለዚህ እነዚህን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ አካላትን ወደነበሩበት በተገቢው ለመመለስ ሲባል ማህጸኑን ማውጣት ምርጫ ይሆናል፡፡ አንዲት ሴት ከሕክምናው በሁዋላ በነበረችበት የሴትነት ባህርይ እንድትቀጥል ብልትዋ የሚያስፈልጋት ስለሆነ ለህክምናው የሚያስፈልጉትን ምርምሮች አድርጎ ጥቃቅን የደም ስሮችን ሳይቀር ለመጠገን እንዲቻል ማህጸኑ መወገዱ ግድ ይሆናል፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ሌሎቹ አካላት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ የሽንት ፊኛው በደንብ ቦታው ላይ እንዲሆንና ሽንት እንዳያመልጥ ሰገራ መውጫው ሁሉም ቦታው ላይ እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፡፡
ኢሶግ/ ከህክምናው በሁዋላ ሴቶች ጤናቸውን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለባቸው?
ዶ/ር ጥሩ ጥያቄ ነው ፡፡ ዋናው ነገር ከህክምናው በፊት ወይም ኦፕራሲዮን ከመሰራቱ በፊት አንዲት ሴት በደንብ ምክሩን መውሰድ አለባት ፡፡ ሴቶች በተለይም በገጠሩ አካባቢ ከበድ ባለ ስራ የሚጠመዱ ሲሆን በመውለድም ጭምር ይበልጡኑ የሚጎዱ ናቸው፡፡
በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የማህጸን መውጣት ችግር ቢደርስባቸው በማህበራዊና በስነልቡናዊ ሁኔታቸው ከቤተሰባቸው እንዲሁም ከአካባቢያቸው የተገለሉ ይሆናሉ፡፡ ከባሎቻቸውም ጋር ድብቅ በሆነ መንገድ ለመኖር የሚገደዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶች አስቀድሞውኑ እራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ችግር የተከሰተ መስሎ ሲሰማቸው ወደሕክምና ተቋም በመሄድ ከሐኪማቸው ጋር መማከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ችግሩ ከተከሰተ በሁዋላ ሊያደርጉት የሚገባውን ጥንቃቄ በሐኪም የሚነገራቸው ሲሆን ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ምንግዜም ግልጽ መሆንና ጤናቸው ከከፋ ደረጃ እስኪደርስ ደብቀው መቆየት እንደሌለባቸው እንዲሁም ወደህክምናው መሄድን እንዳይዘነጉ እመክራለሁ፡፡

Read 7114 times