Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 13:02

የሴቶች “ካቴና!” አገኘሁ አሰግድ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ብዙ ሴቶችን አይቻለሁ፡፡ አንዷ ከአንዷ በቁመት፣ በመልክ፣ በሰውነት ቅርጽ ቢለያዩ እንጂ በተረፈ አንድ ናቸው፡፡ ለፍቅር ስሱ ነኝ፡፡ ቶሎ እወዳለሁ፡፡ ፍቅሬን የምታበረክት ሴት ግን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ወድጃት፣ ወዳኝ…ሙዳችን፣ ኮከባችንና ከንፈራችን ገጥሞ ባለንበት ሰዓት፣ መሳሳማችንን አቋርጣ፣ አይኗን በአይኔ ላይ እያንከባለለች “ትወደኛለህ?” ትላለች፡፡ይኸኔ ደሜ ይፈላል፡፡ አንዲት ሴት እንዲህ ካለችኝ በቃ እጠላታለሁ፡፡ አብረን መቆየት አንችልም፡፡ ወይ እኔ እሄዳለሁ፣ ወይ እሷ ትሄዳለች፡፡ እድሌ ሆኖ ይሁን አላውቅም የማገኛቸው ሴቶች ሁሉ ሄደው ሄደው “ትወደኛለህ?” ማለታቸው አይቀርም፡፡

ሁሉ ነገሯን ሰጥታኝ፣ ሁሉ ነገሬን ሰጥቻት ምንድነው እንደማይተማመን ባልንጀራ “ትወደኛለህ፣ አትወደኝም?” እያሉ በየመሳሳሙ መሃል መማማል? ብዙ ሴቶች አውቃለሁ፡፡ ግን ሁሉም አንድ ናቸው፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ! 
“እውነት ግን ትወደኛለህ?” ለእኔ የቀሽሞች ቀሽም ጥያቄ ነው፡፡ ቆይ እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄ ይጠየቃል?...እሺ ልውደዳት፣ ግን እሷን መውደድ የእኔ እንጂ እንዴት የእሷ ጉዳይ ይሆናል? እኔ ብወዳት ባልወዳት ምን ያገባታል? ይልቅ ለምን ራሷን አትጠይቅም “እወደዋለሁ?” ብላ፡፡ እኔ እኮ “ትወጅኛለሽ?” ብዬ ጠይቄ አላውቅም፡፡
ይቅርታ አድርጉልኝና “ትወደኛለህ?” የሚሉ ሴቶች ፈፅሞ አይመቹኝም፡፡ እንደውም በአለም ላይ ቦታ ያላቸው የማይመስላቸው፣ ማነስ የሚሰማቸው፣ በሌላው ውስጥ እራሳቸውን ለመትከል የሚፍጨረጨሩ አምባገነኖች ይመስሉኛል፤ ይሄን ጥያቄ የሚጠይቁ ሴቶች፡፡
“ከልብህ ትወደኛለህ?” ይሄ ለኔ ጥያቄ አይደለም፤ ካቴና ነው፡፡ የሴቶች ካቴና! እኔ ደግሞ ነፃነቴን እወዳለሁ፡፡ ባቀፍኳት፣ ባጫወትኳት፣ በሳምኳት… ታሰር እባላለሁ እንዴ?
ሴቶች እንዲህ ሲጠይቁኝ ግለ ሂስ አውርድ የተባልኩ ያህል ምቾት ይነሳኛል፡፡በቃ የፍቅር ግምገማ አይደላኝም፡፡
በመጨረሻም ሶስናን ተዋወቅኋት፡፡ እንደ ሌሎቹ “ትወደኛለህ?” ብላ እስክትጠይቀኝ ድረስ አሪፍ ጊዜ አብሬያት እንደማሳልፍ አመንኩ፡፡ ጉደኛ ውበት አላት፡፡
እኔ ነኝ ያለች ቆንጆ ለሰዓታት ተኳኩላ ብትመጣ፣ ሶሲ ከእንቅልፏ ስትነሳ ካላት ውበት አትበልጥም፡፡ በዛ ላይ “ብሬይን” አላት፡፡
ደስ አይልም? ብሬይንም ውበትም ታድላለች፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፣ አንድ ቀን “ትወደኛለህ?” ብላ መጠየቋ አይቀርም፡፡ ያኔ እህል ውሃችን ያበቃለታል፡፡
ጊዜያት አለፉ፡፡ ያንን የምጠላውን ጥያቄ አልጠየቀችኝም፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ሶሲ ደስ አለችኝ፡፡ ከኔ ጋር ብዙ ጊዜ የመቆየትን ክብረ ወሰን ሰበረች፡፡ ስጋቴ ግን ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም፡፡
አሁንም ጊዜያት ከነፉ፡፡ ሶሲ አልጠየቀችኝም፡፡
አንድ ቀን…አልጋ ውስጥ ሆነን፣ እቅፌ ውስጥ እንዳለች በፍቅር ትክ ብዬ አየኋት፡፡ የሷም አስተያየት የፍቅር ነው፤ ታሳሳለች፡፡
ያን የምጠላውን ጥያቄ ከደሟ ውስጥ ባስወግድላት የዘላለሜ ትሆን ነበር ብዬ ተመኘሁ፡፡
ይሄን ያህል ጊዜ አብራኝ ቆይታ “ትወደኛለህ?” ብትለኝስ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እንደገና ፍርሃት ያዘኝ፡፡ በጣም ፈራሁ!! የማጣት የማጣት መሰለኝ፡፡
ውስጤ ተረባበሸ፡፡ ልቤ አካባቢ ምቾት የሚነሳ ስሜት ወረረኝ፡፡ ይሄን ስሜቴን ለማባረር ላወራት ፈለግሁ፡፡
“ሶሲ? ጠራኋት፡፡
“እ…እ…?” አለችኝ አይን አይኔን እያየች፡፡ ምን ላወራት እንደጠራኋት አላውቅም፡፡ “ወዬ…?” አለችኝ፣ ዝምታዬ ሲረዝምባት፡፡ እንዴት ከአፌ እንደወጣ አላውቅም…”ትወጅኛለሽ?” አልኳት፡፡ ወዲያው ክው አልኩኝ! “እ…እ..?” አለችኝ፤ በቀዘቀዘ ድምጽ፡፡ “ትወጅኛለሽ ወይ?”…እንደ ድምጿ አይኖቿም ቀዘቀዙ፡፡
ልቧም የቀዘቀዘ መሰለኝ፡፡ የምገባበት ጠፋኝ፡፡ አተነፋፈሴ ተዛባ፡፡ ዝምታ ነገሰ፡፡ የልቤ ምት ብቻ ነው የሚሰማኝ፡፡ - ድው…ድው…ድው…!

Read 9328 times