Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 13:07

ወጣቷ የፊልም ባለሙያ ምን ትላለች?

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ብዙ የፊልም ጽሑፎች እንዳሉሽ ሰምቻለሁ “ሰምና ወርቅ”ን በቅድሚያ ለመስራት ለምን መረጥሽ?
ስትፅፍ አንዱን ጀምረህ ሳትጨርስ ሌላውን ልትጀምር ትችላለህ፡፡ አጠገብህ ያሉት ሰዎች ስክሪፕቱን አይተውት ሊወዱት ይችላሉ፡፡ የት ደረሰ ብለው ሲጨቀጭቁህ ማለቅ አለበት ብለህ ለመጨረስ ትጣደፋለህ፡፡
ወንድሞቼና እህቶቼ እያነበቡ የሙሴ (ካሳሁን ፍስሀ የተጫወተው) እንዴት ሆነ? ሴቶቹን ገፀባህርያት ለምን እንደዚህ አደረግሻቸው ሲሉኝ ለ “ሰም እና ወርቅ” ቅድሚያ ሰጠሁ፡፡
ምን ያህል ስክሪፕቶች አሉሽ?

ያለቁ ያላለቁ? ሙሉ በሙሉ ያለቁ ሦስት ስክሪፕቶች አሉኝ፡፡ ሌሎች በርካታ ጅምር ስክሪፕቶችም አሉ፤ በፅንስ ደረጃ፡፡ 
ፊልሙ ተጀምሮ እስኪያልቅ ያለውን ሂደት ብትነግሪኝ
በፅሑፍ ሥራው ሳይሆን በተሟላ የፊልም ሥራ ደረጃ “ሰምና ወርቅ” የመጀመርያ ሥራዬ ነው፡፡ ከመጀመርያ ጀምሮ ነገን እየጓጓሁ ዛሬ ሊያልቅ ነው፣ ነገ ምንድ ነው የምሠራው እያልኩ ነው የጨረስኩት፡፡ ስክሪፕቱን ስፅፍ እስኪያልቅ ጓጉቼ፣ ቀረፃ ሲጀመር እስኪያልቅ ጓጉቼ፣ ኤዲቲንግ (አርትኦት) ሲጀመር እስኪያልቅ ጓጉቼ በምርቃቱም እስኪያልቅ ጓጉቼ ነው የተሠራው፡፡
ከመጀመርያም ስፅፍ “ሰምና ወርቅ” አልኩት፡፡ ጽሑፉ አልቆ በስድስት ወር ሥራ ተጀምሯል፡፡ ስክሪፕቱ ከሁለት ዓመት በፊት ነው የተሰራው ማለት ነው፡፡
ፕሮዱዩሰር ማግኘቱ ከባድ ይመስለኛል …
አዎ ግን አሳማኝ ስክሪፕት ካለህ ፕሮዲዩሰር ማግኘት ሊቀል ይችላል፡፡ የፊልሜ ፕሮዱዩሰር የኔ ድርጅት ነው ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር ግን አለው፡፡ ጥበቡን ወደው መስራት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ የኔንም ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዱዩሰሩ ስለወደደው ወዲያውኑ ሰራነው፡፡ የሩቅ ሰው አይደለም፡፡ ቤተሰብ ነው፡፡ ስክሪፕቱን አሳይቼው ፕሮዱዩሰር ፈልግልኝ አልኩት፡፡
በጣም ባተሌ ሰው ነው፡፡ ስክሪፕቱን ጠዋት ሰጥቼው 101 ገፅ አንብቦ ስምንት ሰአት አካባቢ ደውሎ ሥራውን ጀምሪ፤ ራሴ ፕሮዲዩስ አደርገዋለሁ አለኝ፡፡
እንዴት ፊልሙን በዳይሬክተርነት ልትሰሪው ቻልሽ? ከተዋናይነት ጋር ደርቦ መስራቱ አይከብድም?
የፊልም አዘጋጅ /ዳይሬክተር/ ለመሆን መጀመርያ አካባቢ አላሰብኩም ነበር፡፡ አዘጋጀነት ትልቅ ሙያ ነው፡፡
አንድ ነገር ለመስራት ስትዘጋጅ መንደርደርያ ይኖርሃል፡፡ የዳይሬክቲንግ ኮርሶች አሉኝ፡፡ መጻሕፍት ታነባለህ፡፡ ስለ ሙያው የምታውቅ ከሆነ ለመግባት ትፈራለህ፡፡ ለአራት አዘጋጆች ሰጥቼ ስክሪፕቱን የመቀየር፣ ያለውን ሀሳብ ከመስራት ይልቅ ሌላ ሀሳብ የማምጣት … ስትፅፈው የነበረህን ስሜት ያለመግለፅ ብቻ ባተሌ ስለሆኑብኝ በዝርዝር ፅፌው ስለነበር ራሴ ወደ አዘጋጅነቱ ገባሁ፡፡ አዘጋጆቹን ስታወራ የተሻለ ሀሳብ እና ልምድ ታገኛለህ፡፡ በድፍረት ገባሁበት ብዬ አላስብም፡፡
ምን ያቅታል በሚል በማቃለል ሳይሆን ይቻላል ብዬ ነው ወደ ሥራው የገባሁት፡፡
ቀረፃ ላይ የምትፈልገውን አስተካክለህ ከሲኒማቶግራፈሩ ጋር ተግባብተህ ካመቻቸህ አዘጋጅ ሆኖ መተወኑ አይከብድም፡፡ ተዋናዮቹም ልምምዱን በደንብ ሰርተው ለቀረፃ ከተዘጋጁ ይቻላል፡፡ ረዳት አዘጋጁም ያግዝሃል፡፡ አብረውኝ የሠሩት ባለሙያዎችም ጥሩዎች ነበሩ፡፡ አንዳንዴ ግን ትወና አቋርጬ እንዲህ ቢደረግ ብዬ አውቃለሁ፡፡ ዋና የማይችል ሰው እችላለሁ ብሎ ውሃ ከገባ ሊሰምጥ እንደሚችል ታውቃለህ፡፡
ፊልም ማዘጋጀቱም ሆነ ትወናው የመጀመሪያሽ ነው ማለት ነው?
አልተወንኩም፡፡ ግን መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ አንድ ፊልም ላይ ለመተወን ሞክሬ ነበር፡፡ ፊልሙ አልወጣም፡፡ ስለዚህ ስክሪፕቱም ሆነ ትወናው የመጀመሪያዬ ነው፡፡
በመጀመርያ ሥራ ውጤታማ መሆን… በተለይ በትወናው በኩል አያስቸግርም?
ነገርኩህ እኮ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ቢሆንም ጥሩ ሥራ መስራት እችላለሁ ብለህ ስትነሳ ትችላለህ፡፡ ሥራህ ጥሩ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብህ ታውቃለህ፡፡ ለዚያም ተዘጋጅተህ ትሠራለህ፡፡ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል አልተሳካም የሚለው ተመልካች ነው፡፡ እኔ ግን በተቻለኝ መጠን ተመልካቹን ላለማስከፋት ጥሬአለሁ ባይ ነኝ፡፡
አሁን በሲኒማ ቤቶች ከሚታዩ ፊልሞች “ሰም እና ወርቅ” በምን ይለያል?
“ሰም እና ወርቅ” እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያዊ ፊልም ነው፡፡ አማርኛን በደንብ ተጠቅመንበታል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከሌሎቹ በቋንቋ እንለያለን ማለቴ አይደለም፡፡ ማንኛውም ፊልም ጥሩ ነው፡፡ ከመነሻችን ጀምሮ ርዕሱ እንዲሁም በፊልሙ የተነሳው ሃሳብ ኢትዮጵያዊነት አለው፡፡ “ልጅህን ለልጄ” በሚል ባህላችን ላይ ተመርኩዞ ቃል ኪዳን በማክበርና ቃል በመጠበቅ ዙሪያ የተሰራ ነው፡፡ እነዚህ ሀሳቦች ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ኮሜዲ ክፍሉ ተመልካች እዚህ ጋ መሳቅ አለበት ተብሎ የገባ አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ኑሮአችን ቀልድ ብቻ አይደለም የሚያስቀን፡፡ በእውነተኛ ሕይወታችን ነው የሳቅነው፤ በሚያጋጥሙን፡፡
በሳምንት ምን ያህል ፊልም ታያለሽ?
ፊልም በጣም አያለሁ፡፡ ትያትርም በጣም አያለሁ፡፡ የሀገር ውስጥና የሆሊውድ ፊልሞች ማየት በጣም እወዳለሁ፡፡ በሳምንት ይኼን ያህል ብዬ በቁጥር ልገልፅልህ አልችልም ከብዙ ነገሮች የበለጠ የሚያዝናናኝ ፊልም ነው፡፡
“ነፃ ትግል” የተሰኘውን የአማርኛ ፊልም አይተሽዋል?
አይቼዋለሁ
ከአንቺ ፊልም ጋር ምን ያህል ይቀራረባል?
ወንድና ሴት ሕይወት ላይ ተሰሩ ካልክ ይመሳሰላሉ፡፡
አንድ ምድር ላይ አንድ ቦታ እየኖርክ ተመሳሳይ ሀሳቦች አይነሱ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሀሳቦች ሊመሳሰሉ ይችላሉ፡፡ ሀሳቦችን የምትገልፅበት መንገድ ይለያያል፡፡ “ነፃ ትግል” እንዴት ገለፀ? “ሰምና ወርቅ”ስ እንዴት ገለፀ ነው? ካሁን በኋላ በወንድነትና እና ሴትነት ጽንሀ ሀሳብ ላይ ብዙ ፊልሞች ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እንደ “አቫተር” ዓይነት እጅግ የተለየ ፊልም ካላመጣህ መመሳሰሉ ግድ ነው፡፡
አንዳንድ ፊልሞች ቃለተውኔትና ትዕይንት ይወራረሳሉ ይባላል?
እንደኔ እንደኔ እንዳለ ገልብጦ ማሳየት ተመልካችን መናቅ ነው፡፡ የትም ሀገር ይሁን፡፡ ፊልምና መጽሐፍ በዚህ ይለያያሉ፡፡ መጽሐፍ ላይ አንዱ የተጠቀመውን ሃሳብ ቃል በቃል ገልብጠህ ማስፈሩ ልክ ላይሆን ይችላል፡፡
ፊልም ላይ ግን ይለያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፊልም እያየህ አንዲት የፊልሙ ቁንጽል ሀሳብ ማርካህ እሷን ሙሉ ሀሳብ አድርገህ መስራት ትችላለህ፡፡ ይኼ ነገር ሙሉ ታሪክ ሊወጣው ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
እናም ሙሉ ታሪክ አድርጌ ብሠራው የሰው ፊልም ሰረቅሁ ማለት አይደለም፡፡ ካሳሁን (ማንዴላ) ከሌሎች እሱ ከሰራባቸው ፊልሞች አኳያ ወደ ውሱን ገፀ ባህርይ (Type actor) ተሸጋገረ የሚሉ ባለሙያዎች ገጥመውኛል…
ማንዴላ ማለት በጣም ትልቅ አቅም እና ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ልጅ ነው፡፡ አንድ ገፀ ባህርይ ብቻ ነው የሚተውነው ብለህ መበየን አትችልም፡፡ “ባላገሩ”ን አይተህ ከሆነ ወጣ ያለ ነገር ነው ብቻ ማንዴላ እንደምትፈልገው የሚሆንልህ ባለሙያ ነው፡፡ ግን የሆነ ነገር ስታስብ ከምታያቸው ሰዎች ነው የምትነሳው፡፡ ኮሜዲ ክፍሉን ስጽፍ ማንዴላን እያሰብኩ ጽፌው ሊሆን ይችላል፡፡ ከመጀመርያ ስጽፍ ጋሽ ፍቃዱ ተክለማርያምንና ማንዴላን አስቤ ነው የፃፍኩት፡፡ የማንዴላን አነጋገር አኳሁዋን ታይና ከዚያ ጋር የሚመጣጠን ነገር ልትፈጥር ትችላለህ፡፡ የማንዴላ ገፀ ባህርይ እዚህኛው ፊልም ላይ ሴቶችን የሚጠላ ከሆነ ሌላኛው ላይ የግድ ሴቶችን የሚወድ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ሁኔታዎች…አሳሳቅ፣ አነጋገር፣ የእጅ እንቅስቃሴ ወዘተ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ማንዴላ ባይሆን ኖሮ ከዚህ ፊልም ጋር አይመሳሰልም ልትል ትችል ይሆናል፡፡ ከአንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ፊልም ላይ እዚህ ቦታ ላይ ከሌላ ፊልም ጋር ተመሳስሏል ማለት አትችልም፡፡
አንባቢ ነሽ?
ብዙም አንባቢ ነኝ ማለት ይከብደኛል፡፡ ግን አነባለሁ፡፡
ንባብ ለፊልም ስራ ፋይዳው ምን ያህል ነው?
የምታነበው ነገር ለምትሠራው ሥራ ይጠቅማል፡፡ ያነበብከውን ፊልሙ ላይ አምጥተህ ቁጭ ታደርጋለህ ማለት ግን አይደለም፡፡ የምታነባቸው ነገሮች የመረዳት ችሎታህን ከፍ ያደርጉታል፡፡ ብዙ ጊዜ የማነበው ለስኬት መንገድ የሚከፍቱ መጽሐፎችን ነው፡፡
ሳልሳ ዳንስ የለመድሽው ለፊልሙ ብለሽ ነው ወይስ በፊትም ትችያለሽ?
አዎ እችላለሁ፡፡ በትምህርት ያገኘሁት ነው፡፡ ዳንሱ ደስ ስለሚለኝ ገንዘብ ከፍዬ ከሁለት አመት በፊት የተማርኩት ጥበብ ነው፡፡
በአንድ በኩል ፊልሙ ኢትዮጵያዊ ነው ተብሏል ሆኖም የውጭ አገር ባህል የሆነውን ሳልሳ ዳንስ ስትደንሺ ይታያል፡፡ ይሄ አይቃረንም?
አንዳንዴ ሉላዊነትን (globalization) መቀበል አለብህ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነህ ማለት በሌሎች አለማት ባህል ተካፋይ አትሆንም ማለት አይደለም፡፡ ሉላዊነት ከእስክስታ፣ ከሳልሳ፣ ከሂፖፕና ከሌሎች የአፍሪቃ ሙዚቃዎች እንድትመርጥ ዕድል ይሰጥሃል፡፡ ስትፈልግ ሳልሳና እስክስታ ትመርጣለህ፡፡ ነገሩ ፍላጎትን የመወሰን የመፈለግ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሌም እስክስ ካላልክ ኢትዮጵያዊ ጣእም የለህም ልትባል አትችልም፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሂፖፕ፣ ሳልሳ … ቢጨፍር መብቱ ነው፡፡ ማንነትህን አይበርዝበትም፡፡ እስክታ አልወድም፤ ሳልሳ እወዳለሁ ብልህ ሉላዊነት ጎድቶሻል ልትል ትችላለህ፡፡ ደስ ባለኝ ሠዓት እስክስታ እጨፍራለሁ፤ ደስ ባለኝ ሰዓት ሳልሳ እጨፍራለሁ፡፡ ይሄ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ግንኙነት የለውም፤ የፍላጎት፣ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡
ብዙዎቹ ፊልሞች አዲስ አበባ ላይ የሚያተኩሩና ቪላና ውድ አውቶሞቢል የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይሄ ተጨባጩን እውነታ ያሳያል ትያለሽ?
እንዲህ አይነት ኑሮ የሚኖሩትም እኮ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይህንን ፊልም ስንቀርፅ አሜሪካዊ ቤት ሄደን አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎችም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
አንድ ፊልም ስትሠራ እነዚህ ሰዎች ለምን የተንደላቀቀ ሕይወት ኖሩ ብለህ ማሰብ አትችልም፤ ኢትዮጵያውያን እስከሆኑ ድረስ፡፡ ፊልሙ የተሰራው በኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በአማርኛ ነው፡፡
አንዳንዴ ለምን ቦታው ወይም ቤቱ አማረ በሚል ኢትዮጵያዊነትን አይገልፅም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ፊልሙን የቀረፅነው ኢትዮጵያውያን ቤት ባይሆን ኖሮ ጥያቄው ተገቢ ሲሆን ይችላል፡፡ በኔ ፊልም በሁለቱ ቤተሰቦች መሃል ብር ቦታ የለውም ብዬ ነው የተነሳሁት፡፡ እሱ ለሷ ብር ስለሰጣት እሺ ትለዋለች ማለት አይደለም፡፡ ወይ ደግሞ እሷ ለሱ ብር ስለሰጠችው እሺ ይላታል ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱም ብር አላቸው፡፡ ቁም ነገሩ ብር አይደለም በቃ አለቀ፡፡ እሷም ጥሩ ቤተሰብ እሱም ጥሩ ቤተሰብ አላቸው፡፡ ታሪክህን መካከለኛ ኑሮ ያላቸው ቤተሰቦች ላይ ተመስርተህ ከፃፍከው እንደዚያ ታዘጋጃለህ፡፡ የፊልሙ ታሪክህ ነው የሚመራህ፡፡ የፃፍከው ፊልም ነው የሚመራህ፡፡ ሀብታም ቤት ብቻ ነው ፊልም እየተሰራ ያለው ብዬ አላስብም፡፡ መኪና፣ ቪላ፣ ፎቅ ቤት ኢትዮጵያዊነትን አይገልፅም ያለው ማን ነው? ኢትዮጵያ ፎቅ የላትም እንዴ?!
ወደ ቅጂ መብት ጉዳይ እንምጣ፡፡ ባሁኑ ጊዜ ፊልሙ በዲቪዲ ተባዝቶ ባንድ ጊዜ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ይታያል፡፡ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
አንድ ሰው በደንብ አስቦበት መጥቶ ያንተን ፊልም ላጥፋ ብሎ ከተነሳ የማንኛውም ሰው ፊልም ጥበቃ አለው ብዬ አላስብም፡፡ የምንሰጠው ለምናምነው ሰው ነው፡፡ የምታምነው ሰው ይዞልህ ሄዶ ያሳያል፡፡ ሰው ስለሆንክ ባንድ ጊዜ ብዙ ቦታ አትገኝም፡፡ የእኔም ፊልም ጋ ስትመጣ የማምናቸውን ሰዎች እየላኩ ነው አሳይተው ሲዲውን የሚመልሱልኝ፡፡ እርግጠኛ ሆኜ ላልናገር እችላለሁ፡፡ ብዙዎቻችን ተመሳሳይ ነገር ስለምንጠቀም እግዚአብሔር ይጠብቀን ነው የሚባለው፡፡ ቴክኖሎጂውም ይጠብቀን ማለት ይቻል ይሆናል፤ ግን እኛ ጋ የማይገለበጥ ሲዲ አልተስፋፋም፡፡ አንድ ሰው ኮፒ መደረግ የማይችል ሲዲ በትኖ በየሲኒማ ቤቶቹ ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑን ሰምቻለሁ፤ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
በፊልምሽ ላይ የቤት ሠራተኛዋ አነጋገር ከተለመደው ወጣ ብሏል የሚሉ ተመልካቾች ገጥመውኛል …
ይኼም ስለ ቤቱ ስናነሳ እንዳልኩት ነው፡፡ ሠራተኛዋ ለምንድነው እንደዚያ ማሰብና መናገር የማትችለው? ሠራተኛዋ እኮ ይህንን የምትናገረው ትምህርት ቤት ገብታ አይደለም፡፡ የሰውን ስሜት ማንበብ የምትችለው ትምህርት ቤት ስለገባህ አይደለም፡፡ አንዳንዴ እኮ ለኔቢጤ ገንዘብህን ሰጥተህ ስታልፍ ሕይወትህን የሚቀይር ነገር ሊነግርህ ይችላል፡፡ ሠራተኛዋም በአስተሳሰብ ደረጃዋ ልክ የመሠላትን ልትናገር ትችላለች፡፡
የፊልም ሥራና ቤተሰባዊ ሕይወት እንዴት ተጣጣመልሽ? ፊልምሽ ላይ ከንፈር ለከንፈር ሲሳሳሙ ይታያል…ከባህል አንፃር ተቃውሞ አልገጠመሽም?
በአንድ ነገር አምነህ ስትገባ አጠገብህ ያሉት ሰዎች ያምኑበታል፡፡ ቤተሰቤ እንዲረዳኝ መጀመሪያ ነው ያደረግዙት፡፡ ከዚያ ማምሸት፣ ማርፈድ፣ ሌሊት ቀረፃ ለነሱ ጭንቀት ነው፡፡ ደከመሽ ወይ፣ ምን እንርዳሽ ነው እንጂ የት ዋልሽ የት አደርሽ አይሉም፡፡ ምክንያቱም ሥራው ገብቷቸዋል፡፡ ፊልማችን ላይ መሳሳም የለም፡፡ መሳሳም የሚመስል ትእይንት ግን አለ፡፡ ሳትሳሳም ሰው የተሳሳምኩ ያህል እንዲሰማው ካደረግሁ የፊልሙን ብቃት ነው የሚያሳየው፡፡ ፊልም የትክክለኛው ዓለም ነፀብራቅ እስከሆነ ድረስ በትክክለኛው ዓለም እንደዚህ አይነት ሰዎች መሳሳማቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዴ’ኮ ሰው ይጠብቃል፡፡ እንዴት አይሳሳሙም? ምን ሆነው ነው ሊል ይችላል፡፡ መሳሳም ቢኖር እንኳ ሰው ሊከፋው ይችላል ብዬ አላስብም፡፡
“ሰምና ወርቅ” አሪፍ ፊልም እንደሆነ የሚመሰክሩ እንዳሉ ሁሉ አሪፍ አይደለም የሚል ቢገጥሙሽስ?
ምን አለ መሠለህ፡፡ አንተ ፊልም ስትሠራና ስታሳይ ሲኒማ ቤት በገባው ሰው ልክ የተለያየ ስሜት ይንፀባረቃል፡፡
ላንዱ ጥሩ ስሜት ሲሰጠው ሌላው ደግሞ ምን ማለት ነው ሊል ይችላል፡፡ ከተለያዩ ሥሜቶች ጋር ሊያገናኘው ይችላል፡፡ ስለዚህ ያኛው ሰው ፊልምሽ አልተመቸኝም ካለኝ ምንም አይነት ቅሬታ ሊፈጠርብኝ አይገባም፡፡ አይቶት ነው ጥሩ አይደለም ያለኝ፡፡ ለማስተካከል ሀሳብ ትሰበስባለህ፡፡ ወጡ ከተሰራ በኋላ ያልጣፈጠው ጨው በዝቶበት ነው፣ ዘይት አንሶት ነው ብትል ምክንያት አይሆንም፡፡ አይጣፍጥም ከተባለ አይጣፍጥም ነው፡፡
ማስረዳት ሳይሆን የሚጠበቅብህ ቀጣዩን ለማጣፈጥ መሞከር ብቻ ነው፡፡ ምክንያት ግን እጠይቃለሁ፡፡ አልከራከርም፡፡ ብዙ ሰው የወደደውን ፊልም ላልወድ እችላለሁ ወይም ደግሞ ብዙ ሰው ያልወደደውን ፊልም ልወድ እችላለሁ፡፡ ይህ የግል ስሜት ነው፡፡
“ሰምና ወርቅ” ምን ያህል ጊዜ ይታያል ብለሽ ታስቢያለሽ?
እኔ … ዘለዓለም ቢታይ ቅር አይለኝም፡፡ እንዲህ እንዲሰማኝ ያደረጉትን በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች አመሠግናለሁ፡፡
በምታመሰግኚአቸው ሰዎች እንቋጭ…
እጅግ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ሥራ ስትሠራ አጠገብህ ያሉ ሰዎች ስማቸው ላይጠቀስ ይችላል፡፡ ስማቸው አያሳስብህም ሊያሳስብህም ይችላል፡፡ ሙሴ የሚባል ወንድም አለኝ፡፡ ባርዬ ነው የምለው፡፡ እኔና እሱ ማለት እዚህ ሥራ ላይ ተጀምሮ እስኪያልቅ አብረን ነበርን፡፡ ዛሬ ስንት ገፅ ፃፍሽ ይለኛል፡፡ ዛሬ አልፅፍም ደብሮኛል ስለው እያነቃቃ ፊልሙ እንዲያልቅ የተጣጣረ ወንድሜ ነው፡፡ የሱ የተለየ ቢሆንም ሁሉንም ቤተሰቦቼን እና ሌሎችንም አመሠግናለሁ፡፡ ከሰዎች በላይ ደግሞ ታላቅ ሥራ ላደረገልኝ እግዚአብሔርን አመስግንልኝ፤ እግዚአብሔርን በጣም አመሠግናለሁ፡፡

Read 4480 times