Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 13:21

12ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድግስ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብይ ስፖንሰር የሆነለት 12ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬና ነገ በሚካሄዱ ውድድሮች በድምቀት ሊካሄድ ነው፡፡ የሩጫ ድግሱ ከአዲስ አበባ 125ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጋር በመያያዙ ታሪካዊ ሲሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰሞኑን ለ5 ቀናት የቆየ እና እስከ 12ሺ ጎብኝዎች ያገኘ ኤክስፖ በማዘጋጀት ውድድሩን ሲያሟሙቅ ሰንብቷል፡፡ ዛሬ በጃንሜዳ ፕላን ኢንተርናሽናል ‹ሴት በመሆኔ› በሚል መፈክር ስፖንሰር ያደረገውና 3500 ህፃናትን የሚያሳትፍ የ2 ኪ.ሜ ሩጫ ይደረጋል፡፡ ነገ ደግሞ በመስቀል አደባባይ 36ሺ ተወዳዳሪዎችን የሚያሳትፈው 12ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ እንደሚደረግ ሲጠበቅ ከዚሁ ውድድር በፊት ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአካል ጉዳተኞች የዊልቼር ሽቅድምድም እንደሚኖርም ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ 15 ወንድ እና ሴት የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች የሚሳተፉበት ልዩ ውድድርም ተዘጋጅቷል፡፡ ከዘንድሮው የታላቁ ሩጫ ውድድር ጋር በተያያዘ ‹ለህፃናት እሮጣለሁ› በሚለው የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ 1.2 ሚሊዮን ብር ሲገኝ 650ሺ ብሩን ክናርቪኪሚላ የተባለ የኖርዌይ ድርጅት እንዳሰባሰበው ተገልጿል፡፡ 1.2 ሚሊዮን ብሩ ከ4 ክልልሎች ለተውጣጡ 4 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚከፋፈል ሲሆን እነሱም የአዳማ እንረዳዳ እድሮች ማህበር፤ የሃዋሳ እድሮች ማህበር፤ የአማራ እና የትግራይ የማህበረሰብ እንክብካቤ እና ድጋፍ ቅንጅቶች ናቸው፡፡
ዘንድሮ በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ሩጫው ላይ በዋናው የአዋቂ አትሌቶች ውድድር የግል ክለቦች ተሳትፎ መጨመሩን ያመለከቱት የውድድሩ አዘጋጆች በርካታ የአትሌቶች ማናጀሮች የውድድሩን ታላቅነት በመገንዘብ አትሌቶችን ፍለጋ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በነገው ውድድር በአዋቂ አትሌቶች የሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ ደረጃ እንደሚኖረው የገለፁት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ሱር ኮንስትራክሽን፤ ራኒንግ አክሮስ ቦርደርስ፤ ተስፋ ቡድን፤ ሉሲ እና ካራማራ የተባሉት የግል ክለቦች አትሌቶቻቸውን ለማሳተፍ ከበቁት መካከል እንደሚጠቀሱ አስታውቀዋል፡፡ በወንዶች ምድብ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክለቦች የተውጣጡ 340 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ሲታወቅ ፤ ከእነዚህ አትሌቶች መካከል በ2012 የዱባይ ማራቶንን ያሸነፈው አየለ አብሽሮ፤ በግማሽ ማራቶን ሯጭነቱ የሚታወቀው ሌሊሳ ዲሳሳ እና በ5ሺ ሜትር ለለንደን ኦሎምፒክ ለፍፃሜ ውድድር የበቃው የኔው አላምረው ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ከአዲስ አበባ ክለቦች የተውጣጡ 200 አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ ከመካከላቸው የ2012 የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ፤ በለንደን ኦሎምፒክ በ3ሺ መሰናክል 5ኛ ደረጃ ያገኘችው ህይወት አያሌው እና በታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ የኮካኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የዘንድሮ አሸናፊዋ ፅጌሬዳ ግርማ ይጠቀሳሉ፡፡ በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች ከ1 እስከ 3 ደረጃ በማግኘት ለሚያሸነፉ አትሌቶች 40ሺ ብር ለሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡
አምና በ11ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወንዶች ሙሰነት ገረመው እንዲሁም በሴቶች አበበች አፈወርቅ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ በ12ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ሎራህ ኪፕላጋት፤ ጆን ትሬሲ እና ጁሊያብሊስዴሌ የክብር እንግዶች ናቸው፡፡ በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ሩጫው ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የውጭ አገራት ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ ሲታወቅ 3 የኬንያ አትሌቶች፤ አንዲት እንግሊዛዊ አትሌት እና ሁለት የስኮትላንድ አትሌቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡ ለ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ሽፋን ለመስጠት በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ሱፕር ስፖርት ከደቡብ አፍሪካ፤ ኢኤስፒኤን ከስፔን፤ ቻናል 4 ከዩናይትድ ኪንግደም፤ ዩሮ ስፖርት እና ከካናዳ የቴሌቭዥ ጣቢያ የመጡ አራት ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትናንት በሂልተን ሆቴል ዝግጅቱን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ ላይ ኃይሌ ገ/ስላሴ ባደረገው ንግግር አዲስ አበባ 125 አመቷን እያከበረች ባለችበት ወቅት የሚደረገው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው የአገራችንን መልካም ገፅታ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ መሆኑ ገልፆ፤ በነገው ውድድር ላይ ብቻ 36,000 ተወዳዳሪዎች ቢሮጡም በመላው ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ ኢትዮጵያውያን እየሮጡ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአንድነት መተሳሰብ ከቻሉ መላው ሕዝብ አንድ ግቢ እንደሚኖር ቤተሰብ መቀራረብ እንደሚችል የገለፀው ኃይሌ የነገው ሩጫ በስነ-ምግባር የታገዘና ህግን የተከተለ እንዲሆን መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ታዋቂው ጃፓናዊው የአትሌቲክስ ስፖርት ፎቶግራፈር ጂሮ ሞቺዚኪ “Haile Gebre Selassie The Emperor of Long Distance.” የሚል የሃይሌን የ20 ዓመታት የሩጫ ስኬት የሚያሳይ መፅሃፍ በስጦታ አበርክቶለታል፡፡
መፅሃፉ ከ230 በላይ ፎቶዎችን የያዘ ሲሆን አትሌቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያደረጋቸው ውድድሮች፤ ያስመዘገባቸው ውጤቶች፤ ሰዓቶችና ሪከርዶች የቀረቡበት ነው፡፡
የነገው 12ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ታሪክ በአዘጋጁ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተካሄዱ ውድድሮችን ብዛት 82 አድርሶታል፡፡ በእነዚህ የታላቁ ሩጫ ውድድሮች ከ400ሺ በላይ ስፖርተኞችን ተሳትፈዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዋናው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ከ10 በላይ የኦሎምፒክ ወይም የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ አትሌቶችን አፍርቷል፡፡ ከእነሱም መካከል የመጀመርያውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ 2ኛውን ያሸነፈው ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፤ በ3ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሴቶች ምድብ ያሸነፈችው ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ7ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሸነፈው ማራቶኒስቱ ፀጋዬ ከበደ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ምርጥ የማራቶን ሯጮች መካከል በሴቶች ድሬ ቱኔ እና ጠይባ ኢርኬሶ እንዲሁም በወንዶች ቻላ ደቻሳ እና ጌቱ ፈለቀ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪካቸው ወደ ስኬት ለመውጣት ከቻሉት አትሌቶች ይገኙበታል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመርያው አንደኛ ደረጃ የማራቶን ውድድር ኃይሌ ማራቶን በሚል ስያሜ በቀጣይ ዓመት በሃዋሳ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተቻለ፡፡ ውድደሩ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ካደረገው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ጋር ባደረገው ትብብር የሚዘጋጅ ነው፡፡ ኃይሌ ማራቶን 5ሺ ጫማ ከፍታ ባላት ሃዋሳ ከተማ ሲደረግ ውድድር ጎን ለጎን የግማሽ ማራቶንና የ5ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ ኃይሌ ማራቶን በኢትዮጵያ ህዝብ አሳታፊ የሩጫ ውድድሮችን ማስፋፋት እና ዓለም አቀፍ የቱሪስት ገበያን ለማጠናከር በተወጠነ ሃሳብ የሚካሄድ ነው፡፡
እስከ 1200 ማራቶኒስቶች በሚያሳትፈው የኃይሌ ማራቶን ለውድድሩ በተዘጋጀው ኦፊሴላዊ ድረገፅ www.hailemarathon.com ምዝገባው እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተባባሪ ሪፖርተር- ግሩም ተሰማ

Read 5593 times Last modified on Monday, 03 December 2012 13:44