Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 11:48

የሲግደን ሐይቅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 

 

ትርጉም - ነቢይ መኮንንአሌክሳንደር ሶልዘንስቲን

ስለዚህ ሐይቅ የሚጽፍ ሰው ፈፅሞ የለም፡፡ እንደው በሹክሹክታ ይወራለታል፡፡ በአስማት እንደተሠራ መቅደስ ወደዚህ ሀይቅ የሚወስዱት መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋል፡፡ በየአንዳንዱ መንገድ ላይ ቀጥ ያለ አግዳሚ ተጋድሟል፡፡ እንዲህ ያለ አግዳሚ ያጋጠመው ሰውም ሆነ እንስሳ ማለፍ አይችልም፡፡ መመለስ ይገባዋል፡፡ አንድ ምድራዊ ኃይል ያንን የእገዳ ምልክት አኑሯል፡፡

ያን ምልክት አልፎ መንዳት፣ ያን ምልክት አልፎ በእግር መጓዝም ሆነ መዳህ አሊያም በክንፍ መብረር በጭራሽ ክልክል ነው፡፡ 
በመንገዱ አቅራቢያ በሚገኙት የአናናስ ዛፎች ጥላ-ሥር ጐራዴና ሽጉጥ የያዙ ዘበኞች አሉ፡፡
በአካባቢው ባሉት ጫካዎች ውስጥ ዙሪያውን ስትዞር ትውላታለህ እንጂ ወደዚያ ሐይቅ የሚያደርስህ አንድም መንገድ አታገኝም፡፡ ደሞ ማንም ሰው በዚያ ጫካ ውስጥ ስለማይሔድ መንገድ ለመጠየቅም ችግር ነው፡፡ ሁሉ ሰው ፈርቶ ሸሽቷል፡፡ ያለው አንድ አማራጭ መንገድ አንድ ዝናባማ ከሰዓት በኋላ መርጠህ፣ የከብት-መንገድ ተከትለህ፣ የከብቶቹን የአንገት ቃጭል ሽፋን አድርገህ፤ መጓዝ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ስትጓዝ ገና በትላልቆቹ ዛፎች የተሞላውን ሰፊ ጫካ ስታይ፣ ወደ ሐይቁ ዳርቻ ስትደርስ የዚያ ቦታ የዘለዓለም እሥረኛና የዕድሜ ልክ ቁራኛ እንደምትሆንና መመለስ እንደማትችል ትረዳለህ፡፡
የሴግዴን ሐይቅ በኮምፓስ-መርፌ ዙሪያውን ተሰምሮ፣ በዚያ ውስጥ ውሃ የተሞላ ይመስል ፍፁም ክብ ነው፡፡ ካንደኛው ዳርቻ ላይ ቆመህ ብትጮህ (መጮህ ግን የለብህም፤ አለዛ የሚሰማ ይሰማሃል) በጣም ድክምክም ያለ የገደል ማሚቶ ድምፅ ብቻ ነው ወደሌላኛው ዳርቻ የሚዘልቀው፡፡ ካንዱ ዳርቻ በቀጥታ ወደሌላው ዳርቻ ለመድረስ በጣም ረዥም መንገድ ነው፡፡ ሐይቁን ሙሉ በሙሉ ጫካ ከቦታል፡፡ ረጃጅም ግዙፍ-ግዙፍ ዛፎች ግጥግጥ ብለው ዙሪያውን ቆመው ቁልቁል ያዩታል፡፡ ከዚህ ጫካ ስትወጣና አንዱ የውሃ ጫፍ ዘንድ ስትደርስ የተከለከለውን የሐይቁን ዳርቻ ሙሉ በሙሉ ታያለህ - እዚህ ጋ ቢጫ አሸዋ የለበሰ ቁራጭ መሬት፣ እዚህ ችፍግ ያለ ሸምበቆ፣ አለፍ ብሎ ረግረግ ላይ የበቀለ እርጥብ ጨፌ ታገኛለህ፡፡ ውሃው ጥርት ያለና የረጋ፤ ምንም የሚያንቀሳቅሰው ነገር የሌለበት ነው፡፡ ዳርቻው ላይ ከሚታየው ጥቁር አራሙቻ በቀር የውሃው ግርጌ ማለትም የሀይቁ አልጋ ነጭ ነፀብራቁን በውሃው ብርሃን-አሳላፊ ገላ ውስጥ ያሳያል፡፡
በምስጢራዊ ጫካ ውስጥ የተኛ ምስጢራዊ ሐይቅ፡፡ ውሃው ሽቅብ አንጋጦ ያያል፡፡ ሰማዩ ቁልቁል አቀርቅሮ ያስተውላል፡፡ ከዚህ ጫካ ባሻገር ሌላ ዓለም ቢኖር በጭራሽ አይታወቅም፡፡ በጭራሽ ሊታይ አይችልም፡፡ ድንገት ያለ ቢሆን እንኳ እዚህ ውስጥ ቦታ አይኖረውም፡፡ ከዚህ ጋር አይመሳሰልም፡፡
ይህ ቦታ ለዓለም ለዘለዓለም የሚኖሩበት፣ ዕድሜ ልክ የሚመንኑበት ነው፡፡ በአካባቢው ካለው ከማናቸውም የተፈጥሮ አካል ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ዓለም ነው፡፡ መንፈስን በዙሪያው ባሉት ነገር እያደሱ የሚኖርበት ክልል፡፡
ታዲያ ምን ያደርጋል? ይህንን መመኘት እንጂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንድ እርኩስ ልዑል፣ በጠንጋራ ዐይኑ አይቶ እርስተ-ጉልቱ አድርጐታል፡፡ ቤት ሠርቶበታል፡፡ የመታጠቢያ ቤት አመቻችቶበታል፡፡ እቡይ የአደን ባህሪው አሣ እንዲያጠምድ ይገፋፋዋል፡፡ እጀልባው ላይ ሆኖ እያነጣጠረ ዳክዬ ያድናል፡፡ በሀይቁ ላይ ጠመዝማዛ ሰማያዊ ጭስ ቡልቅ ይላል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ተኩስ ይሰማል፡፡
ከዚህ ጫካ ርቆ ያሉ ሰዎች ላብ በላብ እስኪሆኑ እየሠሩ፣ ቁና-ቁና እየተነፈሱ ይኖራሉ፡፡ ወደዚህ ለመምጣት መንገዱ ሁሉ ታጥሮባቸዋልና አቋርጠው አይመጡም፡፡ አሣ ማጥመድና አደን መዋል የዚያ ልዑል መደሰቻ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ አንድ ሰው እሳት አቀጣጥሎ እንደነበር ምልክት የሆነ የጠፋ እሳት ረመጥ ይታያል፡፡ ያንን እሳት የለኮሰ ሰው ተባሯል፡፡ እሳቱም ጠፍቷል፡፡
ነዋሪዎቿን የተራቆተች ውድ ሐይቅ፡፡
ዋ የትውልድ አገሬ …

Read 4297 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 12:11