Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 11:56

ከ30ዓመት በላይ በቢስክሌት አከራይነት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በወሊሶ ከተማ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እስከ 11ኛ ክፍል በቆዩበት ዘመን ለትራንስፖርት የሚጠቀሙበት ቢስክሌት ነበራቸው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ቢስክሌት በማከራየት ሲሰሩ ከ30 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ “የሥራዬ ልዩ ገጠመኝ ቢስኪሌት በተደጋጋሚ መሰረቄና ያንን ለማስመለስ ያደረግሁት ትግል ነው” የሚሉት አቶ መቻል ቦሪ፤ በህይወታቸው፣ በሥራቸውና በገጠመኞቻቸው ዙሪያ ከብርሃኑ ሰሙ ጋር አውግተዋል፡፡
ትምህርትዎትን ከ11ኛ ክፍል ለምን አቋረጡ? 
ጥላሁን ግዛው ከተገደለ ጊዜ ጀምሮ በወሊሶ፣ እንድብርና አምቦ በየዓመቱ በየትምህርት ቤቱ ሙት ዓመቱን ለማስታወስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እናደርግ ነበር፡፡ የወጣትነት እንቅስቃሴያችን በተለይ ከኢህአፓ በኋላ ለሕይወታችን አስጊ ስለነበር ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ በጭነት ማመላለሻ ድርጅት (ጭማድ) ውስጥ የሚሰራ ወንድም ነበረኝ፡፡ እንደመጣሁ በሱ ቤት መኖር ጀመርኩ፡፡
የሥራ ታሪክዎ ምን ይመስላል?

በወሊሶ እያለሁ በራስ ጎበና ዳጨውና በደጃዝማች ገረሱ ዱካ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ 
ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገባሁ በኋላ፣ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር በማስፈቀድ በማታው ክፍለ ጊዜ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በመሰብሰብና በማስተማር ገቢ አገኝ ነበር፡፡ 50 የሚደርሱ ተማሪዎች ነበሩኝ፤ እያንዳንዳቸው በወር 1 ብር ይከፍላሉ፡፡ የእኔ የመጀመሪያ ሥራ ማስተማር ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ነው ቢስኪሌት በማከራየት ሥራ ላይ ከ35 ዓመታት በላይ የቆየሁት፡፡
ወደ ሥራው እንዴት ነው የገቡት?
አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ በወንድሜ ቤት በጥገኝነት መኖሬን ያየው በላይ ኃይሌ የሚባል ጓደኛዬ፤ እሱ በወቅቱ አማኑኤል መሳለሚያ አካባቢ ቢስኪሌት ያከራይ ነበር፤ “ወሊሶ ቢስኪሌት አለኝ” ስለው “አምጣና እያከራየህ ራስህን ቻል” ብሎ ስለመከረኝ፣ ቢስኪሌቴን አምጥቼ መርካቶ ከጣና ገበያ በስተጀርባ በማቆም ሥራውን ጀመርኩ፡፡
በወቅቱ በሥራው ላይ የተሰማሩ እነማን ነበሩ?
በመርካቶ፣ መሳለሚያና አማኑኤል አካባቢ ቢረጋ፣ በላይና ሸዋ የሚባሉ ቢስኪሌት አከራዮች የነበሩ ሲሆን በፒያሳና ስታዲየም በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ የስታዲየሙ አቶ ሸሪፍና ልጃቸው አሁንም በሥራው ላይ አሉ፡፡
መርካቶ ውስጥ አቶ ኃይሉ መታፈሪያ የሚባሉ ታዋቂ ቢስኪሌት አከራይ ነበሩ ይባላል?
እሳቸው ላይ አልደረስኩም፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ወደ ሥራው ስገባ መርካቶ ውስጥ ታዋቂው ቢስኪሌት አከራይ አቶ ቢረጋ ነበሩ፡፡ እሳቸው ከማከራየትም አልፈው በቢስኪሌት ውድድር ይሳተፉ ነበር፡፡
የቢስኪሌት ዋጋ የቀድሞው ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?
በዓይነትና መጠኑ ቢስኪሌት የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ 12፣ 14፣ 16 እያለ እስከ 28 የሚደርስ መጠሪያ ያላቸው ቢስኪሌቶች አሉ፡፡ በተለምዶ አጠራር ማውንቴን፣ ከርስ … እየተባሉም ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ እኔ በወሊሶ ከተማ እጠቀምበት የነበረው ማውንቴን ቢስኪሌት በዘመኑ በ50 ብር ነው የገዛሁት፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደዚያ ዓይነቱ ቢስኪሌት እስከ 900 ብር ይከፈልበታል፡፡ እንደየደረጃቸው እስከ 5ሺህ ብር የሚሸጡ አሉ፡፡ የውድድር ቢስኪሌቶች ደግሞ ከዚያም በላይ ያወጣሉ፡፡
ቢስኪሌት የማከራያ ዋጋስ? ስንት ደረሰ?
ሥራውን ስጀምር ለ5 ደቂቃ 25 ሳንቲም እናስከፍል ነበር፡፡ አሁን እንደ ቢስኪሌቱ ዓይነት ለተመሳሳዩ ደቂቃ ከአንድ ብር እስከ አንድ ብር ከሃምሳ እናስከፍላለን፡
በአንድ ቢስኪሌት የጀመሩት ሥራ ወዴት አደገ?
ቁጥራቸው 16 ደርሰውልኝ ነበር፡፡ አሁን ያሉኝ ቢስኪሌቶች ስምንት ብቻ ናቸው፡፡ ሥራውንም በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነው የምሰራው፡፡ መርካቶ በአዳዲስ የግንባታ ሥራና በሰዎች እየተጨናነቀች ስለመጣች እንደ ቀድሞ ዘመን በአዘቦት ቀን ቢስኪሌት ማከራየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በሳምንት አንድ ቀን እሁድ ብቻ ነው የማከራየው፡፡ በሌሎቹ ቀናት የሰው ክብደት መለኪያ ሚዛን እሰራለሁ፡፡
እርሶ ጋ የተለማመደና አሁን ቢስኪሌት ተወዳዳሪ የሆነ አለ?
በዚህ መልኩ የማውቀው ማንም የለም፡፡ ግን ብዙ ሰዎች፣ አንዳንዶቹ መኪና ይዘው እየመጡ ቢስኪሌት አለማምደኸናል ይሉኛል፡፡
ቢስኪሌት አከራይ ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው?
ለልምምድ የሚመጡትን ልጆች እጃቸውን ይዞና ደግፎ ያስተምራል፡፡ ቢስኪሌት ሲጋልቡ ለአደጋ እንዳይጋለጡ የትራፊክ ደንብና ሥነ ስርዓትን ማሳወቅ አለበት፡፡
አንድ ተለማማጅ ልጅ ግራውን ይዞ ባይጋልብና ለአደጋ ቢጋለጥ ተጠያቂ ልሆን እችላለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እግዚአብሔር ይመስገን እስካሁን ችግር አልገጠመኝም፡፡
በሥራው ላይ የሚገጥምዎት ችግሮች ምንድን ናቸው?
በሥራው ላይ የሚከሰተው ትልቁ ችግር ሌብነቱ ነው፡፡ ከቢስክሌት መሰረቅ ጋር በተያያዘ ብዙ ገጠመኞች አሉኝ፡፡ ከአዲስ አበባ የሰረቀብኝን ቢስኪሌት ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ወስዶ የሸጠብኝን ልጅ ተከታትዬ በመሄድ ለማስመለስ የሞከርኩበት ጊዜ አለ፡፡ ጎጃም (ደጀን) ተወስዶ የተሸጠብኝንም ቢስክሌት ተከታትዬ በመሄድ ማስመለስ ችያለሁ፡፡ ተሰርቆብኝ ያልተመለሰለኝም ብዙ ነው፡፡
ሌቦቹ ላይ ክትትል የሚያደርጉት እንዴት ነው?
ቢስኪሌት ስናከራይ መታወቂያቸውን በመያዣነት እየተቀበልን ነው፡፡ ቢስክሌት ይዘው ሲጠፉ ለፖሊስ አመለክታለሁ፡፡ ፖሊስ የድጋፍና የትብብር ደብዳቤ ይጽፍልኛል፡፡
የሌባውን ፎቶ የማሳያቸው ልጆች የሚሰጡኝን ጥቆማ መሠረት በማድረግም ጭምር ነው ወደ ክትትል የምገባው፡፡ እንዲህም ሆኖ ወይም ሌባውን ይዤም በፖሊስም በፍርድ ቤት አካባቢም ለተጨማሪ እንግልት የተዳረኩበት ብዙ አጋጣሚ አለ፡፡
አሁን ዕድሜዎ ስንት ደረሰ?
56 ዓመቴ ነው፡፡ የትውልድ ዘመኔን አንተ አስላው፡፡
ቤተሰብ መስርተዋል?
ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነኝ፡፡
ወደፊት ሕይወትዎ ምን ይመኛሉ?
የወደፊቱን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ ዕድሜና ጤና እንዲሰጠኝ እፀልያለሁ፡፡

Read 17437 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 12:45