Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 June 2011 12:51

ነዋሪዎች በዋጋ መናር ተማርረዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በግል ድርጅት ውስጥ በማሽኒስትነት ትሰራ እንደነበርና ድርጅቱ ምርት ቀንሷል በሚል 20 ሠራተኞች ሲያባርር አብራ እንደተባረረች የተናገረችው ወ/ት ሀና ይልማ፤ የእህልና ሸቀጣሸቀጥ ዋጋ በመናሩ ኑሮው አልተቻለም ትላለች፡፡

 

..አሁን ሥራ የለኝም፤ ከእህቶቼ ጋር ነው የምኖረው፡፡ ድሮ ባቄላም በቆሎም ስኳር ድንችም እንበላ ነበር፤ አሁን መወደድ ብቻ ሳይሆን ምርቱም የለም፡፡ እነዚህ ምርቶች ደግሞ ሀገራችን የሚበቅሉ ናቸው፤ እንደዘይት ከውጭ አይመጡም.. የምትለው ወ/ት ሀና፤ ድሮ ከሱቅ ዱቤ መውሰድ ይቻል እንደነበር አስታውሳ፤ አሁን ግን ዱቤ አይሰጡም፤ ዋጋ በየቀኑ ስለሚቀያየር አንሰጥም ይሉናል ብላለች፡፡ በዋጋ ንረቱ ግራ የገባት የምትመስለው ሀና ..መንግስት የተራበ የሚመግብበት ቦታ ቢያዘጋጅ ጥሩ ነው.. ትላለች - በጭንቀት፡፡

 በግል ስራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ዮዲት አሸናፊ በበኩላቸው፤ በእግዚአብሔር ቸርነት ስለቆምን እንጂ እንደ ዋጋ መናሩ ቢሆን ድሃ የሚባል አይኖርም ነበር ብለዋል፡፡ ..ስኳር እንኳን ትንሽ ቀንሷል፤ ዘይት ግን በጣም ተጫወቱብን፡፡ እኛ እኮ ምንም የሌለን ድሆች ነን.. ሲሉ በማማረርም አራስ እናት የምትበላው ምግብ በማጣቷ ልጇን የምታጠባው ወተት የላትም ህፃናት ት/ቤት እየተራቡ ይወድቃሉ፤ ሲሉ የችግሩን ስፋት በማሳየት ለችግሩ መንግስትን ይወቅሳሉ፡፡

..መቼም መንግስት ሌላ አገር የሚመግበው ኢትዮጵያዊ የለም፤ ምን እንድንሆን እንደሚፈልግ አላውቅም.. ያሉት ወ/ሮ ዮዲት፤ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ መንግስት ስለሆነ መላ ያብጅለት ብለዋል፡፡

የአትክልትና የእህል ዋጋ ሰማይ ደርሷል የሚሉት የቤት እመቤቷ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይሉ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ሽንብራ መብላት አልተቻለም፤ ሽሮማ ለአምሮትም አልተገኘም፤ ተወዷል ይላሉ፡፡ ከሶስት ወር በፊት 12 ብር የገዛሁትን የሽሮ እህል ባለፈው ሳምንት 25 ብር ገዝቻለሁ ያሉት ወ/ሮ ትዕግስት፤ በርበሬም እንዲሁ ጨምሯል፤ በተለይ የባል እጅ ለምንጠብቅ ሴቶች ኑሮው ከብዷል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ..የቤት ኪራይና የልጆች ት/ቤትም አለ፤ አብዛኛው ሰው በግለሰቦች ቤት ተከራይቶ ነው የሚኖረው... ትንሽ ገቢ ያለን እንኳን ተካፍለን እናድራለን፡፡ ምንም የሌለው ምን ሊሆን ነው?.. በማለት የጠየቁት ወ/ሮዋ፤ መንግስት በዚህ እሳት ጊዜ የተራበ የለም ብሎ መግለጫ እንደማያወጣ እርግጠኛ ነኝ ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ሸምሲያ ከድር ደግሞ የዋጋ ንረቱ የሸቀጥ ግዢዬን ፕሮግራም አስቀይሮኛል ብለዋል፡፡ በፊት በወር አንዴ ሸመታ ይወጡ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በየሳምንቱ እገዛለሁ፤ በየቀኑ ዋጋ ስለሚጨምር ተጠራቅሞ እንዳይበዛብኝ እሰጋለሁ ብለዋል - የቤት እመቤቷ ወ/ሮ ሸምሲያ፡፡ ..ቀድሞ 100 ብር ይፈጅብኝ የነበረው የሸቀጥ ሸመታ አሁን በ300 ብርም አልተቻለም.. ያሉት የቤት እመቤቷ፤ የወር ደሞዝ ጠብቆ ለሚኖር ሰው ኑሮው የሚቻል አይደለም ባይ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነጋዴዎችም በዋጋ ንረቱ ተማረናል እያሉ ነው፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ነጋዴ የሆነው ሸምሱ መሐመድ የዋጋ በየጊዜው መጨመር እያሸማቀቀን ነው ይላል፡፡ አከፋፋዮች ከፈለክ ግዛ ያለበለዚያ ተወው ይሉናል፤ የዋጋ ተመኑ ለምን እንደቆመ አናውቅም ብሏል፡፡ ..እኛም እኮ ብንነግድም እህል መብላታችን አይቀርም፤ እህል ሲወደድ ትርፉ ከምግብ ወጪ አያልፍም.. ሲል የኑሮ ውድነቱ ንግዱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይገልጻል፡፡

የአገር ውስጥ ምርቶች በጣም መወደዳቸውን የሚናገረው ሸምሱ፤ ድሮ በአራት ብር የሚገዛው ፓስታ፤ አሁን በሶስት እጥፍ አድጓል፤ ትላንት የነበረ ዋጋ ዛሬ የለም፤ ሲል ስለዋጋ ንረቱ ያስረዳል፡፡ ..የተወደደው ሁሉም ነገር ስለሆነ የሚመረጥ የለም.. የሚለው ባለሱቁ፤ ዋጋ በየጊዜው መጨመሩ ደንበኞች ፊት እያሸማቀቀን ነው ብሏል፡፡

..የጤፍ ዋጋ የጨመረው የዝናብ ወቅቱ ተዛብቶ በነበረ ጊዜ ቢሆንም አሁንም ምርት ተትረፍርፎ እንኳን እንደተወደደ ነው.. ያለው የእህል ነጋዴው ሰይፈ ይሁኔ፤ ደብረ ማርቆስ የሚኖሩ አጎቱ እህል የተወደደው የማዳበሪያ ዋጋ በመወደዱ እንደሆነ ነግሮኛል ይላል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚመገበው ሽሮ እንኳ ተወድዶ ኪሎው 25 ብር እንደገባ ይናገራል፡፡

ነጋዴውም ሸማቹም በእህልና በሸቀጦች ዋጋ መናር ይስማማል፡፡ ለዋጋ መናሩ ጣቱን የሚጠቁመውም ወደ መንግስት ሆኗል፡፡ መንግስት ለኑሮ ውድነቱ ምን መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

 

Read 6388 times Last modified on Saturday, 18 June 2011 13:34