Tuesday, 28 June 2011 14:39

..እምነት ነክ ጥያቄዎች..፣ መልስ ያገኛሉ? - ..አርነት የወጡ ሃሳቦች..

Written by  ፋሲል ሊ.
Rate this item
(1 Vote)

ሃይማኖት (እምነት) በክርክር አይሆንም

ለአንተ ስል

ሰዎች በረሃብ ሲያልቁ

አፋቸውን በአንተ እንዳያላቅቁ፤

ፍትሕ በምድር ሲጠፋ

ብስጭታቸው እንዳይከፋ

እምነታቸው እንዳይላላ

ነፍሳቸው አንተን እንዳትጠላ፣

..እግዚአብሔር የለም እንዴ?.. ሲሉ፣

..አዎ የለም.. የምለው

ስለ አንተ ብዬ ነው፡፡

 

ዳዊት ፀጋዬ፤ ..አርነት የወጡ ሐሳቦች.. በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፍ ውስጥ፤ ካቀረባቸው 60 ግጥሞች መካከል አንዱን ነው ያስነበብኳችሁ፡፡ በመፅሃፉ መግቢያ ላይ፤ ..ሰው በሃሳብ ይለመልማል.. የሚለን ዳዊት ፀጋዬ፤ ያለ ሃሳብ መኖር እንማይፈልግ በመግለፅ ወደ ግጥሞቹ ይሻገራል - አርነት ወጥተዋል ወደተባሉት ሃሳቦች፡፡

በእርግጥ፤ ..ሃሳቦቸ ከየትኛው ባርነት አምልጠው፣ የትኛውን አፈና ሰብረው አርነት እንደወጡ በመፅሃፉ አልተጠቀሰም፡፡ አንዳንዶቹ ግጥሞችም፤ ባርነትና አፈና ያን ያህል የሚያሰጋቸው አይደሉም፡፡ ፍቅርና ትዳርን፣ ልጅና ወላጅን፣ ሰውና አገርን የሚዳስሱ በርካታ የዳዊት ግጥሞች፤ ይዘትና አቀራረባቸው ሲታይ፤ በአገራችን ጎልቶ ከሚታየው የዘመናችን የግጥም ዘይቤ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡

እዚህ ላይ ስለዘመናችን ግጥሞች የይዘትና የአቀራረብ አዝማሚያ፤ የታዘብኩትን መግለፅ ይኖርብኛል፡፡ ሁሉንም ግጥሞችና ገጣሚዎች አንድ ላይ ለመፈረጅ አይደለም፡፡ በብዙ ነገር ይለያያሉ፡፡ ነገር ግን በብዙዎቹ የዘመናችን ግጥሞች ላይ በተደጋጋሚ ያስተዋልኩትንና ጎልቶ የታየኝን አዝማሚያ ብገልፅ የውይይት መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለት ነጥቦችን በመጥቀስ ለመግለፅ ልሞክር፡፡

አንደኛ፤ ነባር ሃሳቦችን አዟዙሮና አገላብጦ የሚያገጣጥም ቀልድ ቀመስ አቀራረብ ይታይባቸዋል፡፡ (ከዚሁ ጋር፤ ..እንዴ!.. ወይም ..አሃ!.. የሚል ስሜት የሚፈጥር፤ አንዳች ያልተጠበቀ ለውጥና ግጥጥሞሽ የያዙ ናቸው - ብዙውን ጊዜ፡፡ በተጨማሪም፤ የማላገጥና የማሾፍ፣ የስላቅና የተረብ ስሜት ያመዝንባቸዋል፡፡ ያው፤ ቀልድ ብዙውን ጊዜ ከማላገጥ ጋር የተያያዘ ነው)፡፡

ሁለተኛው አዝማሚያ፤ የቃላት ወይም የሃረጋት አጠቃቀም ጨዋታ ነው፡፡ በአጠቃላይ የዘመናችን ግጥሞች፤ ውዥተተዥቸዥሰመ ጎልቶ የሚታይበት ይዘትና አቀራረብ ያመዝንባቸዋል እላለሁ - ከታዘብኩት በመነሳት፡፡ ከዳዊት ፀጋዬ የግጥም መፅሃፍ ውስጥ፤ ..ወደ ኋላ ቅደም.. የሚለውን የግጥም ርእስ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ልጅና ወላጅን በሚመለከት ከቀረቡት ግጥሞች መካከልም፤ ..የተገላቢጦሽ.. በሚለው ግጥም ውስጥ የምናገኛቸውን ሃሳቦች ተመልከቱ፡፡

...የወላጆችን ሳቅና ደስታ ተከትሎ ነው ልጅ የሚወለደው - እያለቀሰ፡፡ ወላጆች የሚያለቅሱት ልጃቸውን ሲያሳድጉ ነው - ልጃቸው በእንክብካቤ እየሳቀ፡፡ የወላጆቹን ችግር ስለማያውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ ሲስቅ ሌላው ያለቅሳል፡፡ እንዲህ ናቸው ብዙዎቹ የዘመናችን ግጥሞች -  ..ነባር ሃሳቦችን ላይና ታች አዟዙረውና ግራና ቀኝ አገላብጠው በማገጣጠም፤ ከቃላት ጨዋታና አክሮባት ጋር በቀልድ ቀመስ ዘዴ ማቅረብ..፡፡ ፍቅር በሚል ርእስ በገፅ 50 የሰፈረው ግጥም ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡

ፍቅር

ከውጭ ያሉ፣

..ፍቅር እስከ መቃብር ነው..

ብለው ተናገሩ፤

ከውስጥ ያሉ፣

..ፍቅር እንደ መቃብር ነው..

ብለው መሰከሩ፡፡

ዳዊት ፀጋዬ በተለያዩ ሃሳቦችና ርእሶች ዙሪያ ያቀረባቸውን በርካታ ግጥሞች በማንበብ፤ ስለ ዘመናችን የግጥሞች ዘይቤና አዝማሚያ ለመወያየት መነሻና ማገናዘቢያ ማግኘት ይቻላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ..ፍቅር ዘላለማዊ ነው - እስከ መቃብር..፤ ..ትዳር እስር ቤት ነው - እንደመቃብር.. የሚሉ ሃሳቦች፤ በአፈናና በባርነት ተይዘው በነፃነት ናፍቆት ሲብሰለሰሉ ቆይተዋል የሚባልላቸው አይመስለኝም፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ የመፅሃፉ ርእስ ከግጥሞቹ ይዘትና ሃሳብ ጋር አይገናኝም እያልኩ አይደለም፡፡

..አርነት የወጡ ሃሳቦች.. የሚለው ርእስ፤ በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት ሃይማኖት ነክ ወይም እምነት ነክ ግጥሞችና ሃሳቦች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ እውነትም፤ በሃይማኖት (ወይም በእምነት) ዙሪያ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን በነፃነት ማንሳት፤ በአገራችን ገና አልተለመደም፡፡ የነፃነት መንፈስ፣ የመጠየቅና የመመርመር ባህል ገና አልዳበረም፡፡ ድሮ ጥንት ከነበረም፤ ዛሬ እንደ ልብ የሚገኝ አይደለም፡፡

የስልጣኔ ባህል እና የነፃነት መንፈስ የራቀው፤ የኋላቀርነት ባህል እና የአፈና መንፈስ የተጫጫነው  ነው አገራችን የሺ አመት ታሪክ፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ብዙ ሰዎች፤ በእምነት ዙሪያ (ሃይማኖት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ) አእምሯቸውን እየተጠቀሙ የሚያሰላስሉትን ሃሳብና የሚያነሱትን ጥያቄ በይፋ ለመግለፅ ስጋት ቢያድርባቸው፤ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ይሉኝታ ቢያስራቸው አይገርምም፡፡ ዳዊት ፀጋዬ፤ እምነትነክ ሃሳቦቹንና ጥያቄዎቹን ከእንደዚህ አይነት ባርነትና አፈና አላቅቆ፤ በግጥም ከገለፃቸውና በመፅሃፍ ካሳተማቸው... ..አርነት የወጡ ሃሳቦች.. ሊባሉ ይችላሉ፡፡

በእርግጥም፤ በዚሁ መፅሃፍ ውስጥ የምናገኛቸው እምነትነክ ግጥሞች ጥቂት አይደሉም (ከሃይማኖት ጋር የተገናኙ ማለቴ ነው)፡፡ ከ60ዎቹ የዳዊት ግጥሞች መካከል፤ አንድ ሶስተኛ ያህሎቹ፤ በሃይማኖት ዙሪያ ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ እምነትነክ ሃሳቦችን ያቀፉ ናቸው - ከፅሁፌ መግቢያ ላይ ያነበባችሁትን ግጥም ጨምሮ፡፡

..ለአንተ ስል.. የሚለው ይሄው ግጥም፤ እምነትን በሚመለከት ከሚነሳ የብዙ ዘመናትና የብዙ ሰዎች ጥያቄ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ኪዳን በሚል ርእስ የቀረበውንም ተመልከቱ፡፡

ኪዳን!

አምላክ፤

ምድርን በውሃ ሙላት አላጠፋም አለ፡፡

እግዚአብሔር፣ ቃሉን አከበረ

በምድራችን ላይ፣ ዝናብ ከለከለ፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄ

..ምንም በማይሳነው ቅዱስ አምላክ ወይም ቅዱስ ፈጣሪ.. የሚያምኑ የየዘመኑ ሰዎች፤ መጥፎ ነገሮችን ሁሉ ከአለማችን አጥፍቶ፣ ብልፅግናና ምቾት፣ ጤናና ደስታ፣ ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚችል ያምናሉ፡፡ ግን ጥያቄ ይፈጠርባቸዋል - ..ታዲያ የምናምንበት አምላክ፤ ረሃብና ችግር፣ ስቃይና ጭንቀት፣ ወንጀልና ጦርነት እንዲኖር ለምን ያደርጋል? ራሱ ባያደርግ እንኳ እንዴት ይፈቅዳል?.. የሚል፡፡

ይሄ የመጀመሪያው ጥያቄ ነው፡፡ መልካም ነገሮችን፣ ጥሩ ህይወትን፣ ውብ አለምን በእውን ለማየት ከመመኘት የሚመጣ ጥያቄ ሊሆን ይችላል - ..ሁሉም ሰው አስተዋይ፣ ቅን እና ታታሪ ለመሆን ቢመርጥኮ፣ በዚህ መንገድ ራሱን ለመምራት ቢመርጥኮ፣ እንደየአቅሙና እንደየጥረቱ የብልፅግናና የደስታ ህይወት ይጎናፀፍ ነበር.. ... ብሎ እንደመመኘት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ፡፡

ግን ደግሞ ..መምረጥ.. የሚባል ነገር ካለ፤ ይህን መልካም መንገድ የሚመርጡና የማይመርጡ ይኖራሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወላወሉ ምርጫቸውን በመቀያየር እዚህና እዚያ በዡዋዥዌ የሚባክኑ፣  መንገዳቸውን ለማስተካከል ወይም ለማበላሸት ምርጫቸውን የሚለውጡ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ምርጫ ነዋ፡፡

..ምርጫ ሳይኖር ሁሉም ሰዎች መልካም መንገድን እንዲከተሉ ማድረግ ቢቻልኮ.. ብንልስ?... ያኔማ ሰው መሆናቸው ይቀርና ህይወት የለሽ ሮቦት ይሆናሉ፡፡ ጥያቄው ግን፤ በታዘዘው መንገድ ከሚጓዝ ሮቦት ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ሮቦት ለመሆንም አይደለም፡፡ ነገሮችን አስተውሎና አገናዝቦ መንገዱን መምረጥ የሚችል ድንቅ ተፈጥሮን (ሰውን) የሚመለከት ነው - ጥያቄው፡፡ ስለዚህ አምላክ በአንዳች መንገድ ሁሉም ሰዎች መልካም እንዲሆኑ ያድርጋቸው ብሎ መመኘት፤ ..ሁላችንንም ሮቦት ያድርገን.. እንደማለት ይሆናል፡፡ ነገር ግን፤ አምላክ ከመነሻው፤ ሰው ማስተዋልና መምረጥ እንዲችል አድርጎ ከድንቅ አእምሮ ጋር ፈጥሮታል የሚባል ከሆነ፤ ..ለምን መጥፎ መንገድ የመረጡ ሰዎች በወንጀልና በጦርነት ሌሎች ሰዎችን እንዲያሰቃዩ ይፈቅዳል?.. ይዚህን ጥያቄ አስቸጋሪነት የሚገል ይመስላል የዳዊት ግጥም፡፡

ሕዝብ፣ እግዜር፣ መንግስት!

እግዚአብሔር፣ ... ምን ብሎ ይመልስ የሕዝብን እሮሮ?

መንግስትን፣... እንዲናገር እንጂ እንዳይሰማ ፈጥሮ!

ድህነትና ረሃብ፣ ጦርነትና እልቂት የነገሰው በአጠቃላይ በሰዎች ተፈጥሯዊ ደካማነትና ተፈጥሯዊ ጉድለት ምክንያት ነው የሚባል ከሆነም፤ ..ለምን ከመነሻው ደካማና ጎደሎ ተፈጥሮ እንዲኖራቸው ያደርጋል?.. የሚል ጥያቄ ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ዞሮ ዞሮ ..ለምን መጥፎ ነገሮች እንዲበዙና እንዲነግሱ ያደርጋል? (ባያደርግ እንኳ ለምን ይፈቅዳል)?.. የሚል ነው የመጀመሪያው ጥያቄ፡፡

ምላሽ ለመስጠት አትቸገሩ

ጥያቄው ለብዙ ዘመናት ተደጋግሞ የተነሳ ጥያቄ እንደመሆኑ፤ ለብዙ ዘመናት በርካታ መልሶችና መከራከሪያዎች ቀርበውበታል - ..እንዲህ ወይም እንዲያ ስለሆነ ነው፤ ለእንዲህና ለእንዲያ ምክንያት ነው.. ከሚሉ ... ብዙ ብዙ መልሶች ጋር ብዙ ጥቅሶችንና ክርክሮችን አስተናግዷል፡፡ ግን አሁንም ጥያቄው መነሳቱ አይቀርም፡፡ ..እኮ ለምን?.. የሚለው ጥያቄ ተመልሶ ይመጣል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ለጥያቄው የሚቀርቡ በርካታ መልሶች ይለያያሉ፤ ከመለያየትም አልፈው ይቃረናሉ፡፡ ..የዚህን አለም ሳይሆን የቀጣዩን አለም መልካምነት ነው ማሰብ ያለብን.. በማለት ከመፅሃፍ ጥቅሶች ጋር አያይዘው የሚከራከሩ ይኖራሉ - ..ከዚህ አለም አይደለንም.. በማለት፡፡ ግን ደግሞ፤ ..በዚህ አለም፣ ልባችሁን በደስታ እሞላዋለሁ፣ ሃብታችሁን አበዛዋለሁ፣ ህይወታችሁን አረዝመዋለሁ.. የሚል ሃሳብ የሚያስተላልፉና ሌሎች ጥቅሶችን በመከራከሪያነት ይዘው ምላሽ የሚሰጡም ሞልተዋል - ..የሃጥያት ደሞዝ ሞት ነው.. በማለት፡፡

ለጥያቄው ዛሬም ተጨማሪ ምላሾችን ለመስጠት ፍቃደኛ ከመሆንም አልፈው በጉጉት መከራከሪያዎችን ለማቅረብ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ ግን የምላሽና የመከራከሪያ እጥረት የለም፤ እንዲያውም እጅግ ብዙ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ይሄውላችሁ - ..የትኛውን ምላሽ፤ የትኛውን የእምነት ሃሳብ እንምረጥ? የትኛው መከራከሪያና የትኛውም ምላሽ ትክክለኛ እንደሆነ ለመለየት በምን እንመዝናቸው?..

ሁለተኛው ጥያቄ - የመመዘኛ እጦት

መመዘኛችን ምንድነው? ይላል ጥያቄው፡፡ የትኛው መከራከሪያና የትኛውም ምላሽ ትክክለኛ እንደሆነ ለመለየት በምን እንመዝናቸው?..፡፡ ከሃይማኖት መፅሃፍ ጋር በማመሳከር መከራከሪያዎቹን መመዘንና መምረጥ እንችላለን የሚሉ ሃሳቦች እንደሚቀርቡ አውቃለሁ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው! ብዙዎቹ ተቃራኒ ምላሾችና ተቃራኒ መከራከሪያዎችኮ ከተመሳሳይ መፅሃፍ በተገኙ በርካታ ጥቅሶች ተደግፈው ነው የሚቀርቡት፡፡

እስካሁን ለዘመናት የተሰነዘሩትን ምላሾች የምንመዝንበትና የምንመርጥበት መላ ካልተገኘ፤ ተጨማሪ ምላሽና መከራከሪያ ማቅረብ ዋጋ የለውም፡፡ በዚያ ላይ ብዙ የሃይማኖት መፃህፍት አሉ፡፡ ከመፃህፍቱ መካከልስ የትኛውን በምን መመዘኛ እንመርጣለን? እንዲሁ አንዱን በእምነት ካልተቀበልን ሌላ አማራጭ ይኖረናል? አንዳንዶቹ ..ያኛውን እንጂ ይሄኛውን መፅሃፍ.. በእምነት አልተቀበሉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በተቃራኒው፡፡ እናም በየፊናቸው ጥቅስና ምላሽ እያቀረቡ ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ መንገድ ክርክሩ መቋጫ አይኖረውም፡፡

ሌላኛው አማራጭ፤  ክርክሮችን፣ ምላሾችንና የእምነት ሃሳቦችን፤ ከተፈጥሮና ከህይወት ጋር በማነፃፀር መመዘን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እምነትን በሳይንስ ለመመዘን መሞከር ይሆናል - ..ማንኛውም ሃሳብና ምላሽ ትክክለኛነቱ የሚመዘነው፤ ከተፈጥሮ ጋር በማመሳከር (በመረጃና በማስረጃ በማረጋገጥ) ነው የሚለውን ሳይንሳዊ አስተሳሰብ የምንቀበል ከሆነ፤ ያኔ ክርክሩ መቋጫ ሊኖረው ይችላል፡፡ ያው፤ ..እምነት ወይስ ሳይንስ.. የሚለው የብዙ ዘመናት ጥያቄ ውስጥ ገባን ማለት ነው፡፡

አይ፤ ..እምነት በሳይንስ መመዘን የለበትም.. ካልን ደግሞ፤ ለእምነት ጥያቄዎች የተለያዩ ምላሾችን በመስጠት መከራከር ዋጋ አይኖረውም፡፡ ከተለያዩ የሃይማኖት መፃህፍት እየተጣቀሱ የሚቀርቡ ምላሾችን ልንመዝን ቀርቶ፤ ከአንድ መፅሃፍ እየተጣቀሱ የሚቀርቡ ተቃራኒ ምላሾችንም ለመምረጥ የምንችልበት መመዘኛ አይኖረንም - ..ልባችን የፈቀደውን ምላሽ.. በእምነት መቀበል እንጂ፡፡

..አምላክ እንዴት መጥፎ ነገሮችን በዚህ አለም እንዲነግሱ ይፈቅዳል? ክፋትን የመረጡ ሰዎች ንፁሃንን እንዲያሰቃዩ ለምን ይፈቅዳል?.. ለሚለው ጥያቄ ከሚቀርቡ በርካታ ምላሾች መካከል ሁለቱን ብቻ እንመልከት፡፡ ..በዚህ አለም የተሰቃዩ ሰዎች፣ በአምላክ የተመረጡ ስለሆነ በቀጣዩ አለም ይካካስላቸዋል.. በማለት በጥቅሶች የተደገፈ መከራከሪያ የሚያቀርቡ እንዳሉ ሁሉ፤ ..በአምላክ የመረጠ ሰው በዚህ አለም በደስታና በብልፅግና እንደሚኖር.. ለማሳመን የሚከራከሩም ሞልተዋል - ታናሽዬውን ልጅ መረጥኩ፤ ታላቅ ወንድም ታናሽዬውን ያገለግላል የሚል የጥቅስ ሃሳብና ሌሎችንም እያነሱ፡፡

..ለምን ታናሽዬው ተመረጠ? በየትኛው መልካም ስራው ተመረጠ?.. ብሎ መጠየቅ እንደማይቻልና አምላክ የፈቀደውን እንደሚያደርግ በበርካታ ጥቅሶች አስደግፈው የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ፤ ማንኛውም ሰው በመልካም ስራው እየተመዘነ በፍትሃዊነት የስራውን ያህል እንደሚያገኝ የሚናገሩም አሉ - ብዙ ጥቅሶችን አክለው፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ይመስላል ኮብላዩ የተሰኘው የዳዊት ፀጋዬ ግጥም፡፡

ኮብላዩ

ያ ኮብላዩ ልጅ፣

ቤቱን ጥሎ በመጥፋቱ

በዝቶለታል በረከቱ ፡፡

ወንድሜ!

ክብርህን ከቤትህ፣ ለማግኘት አትልፋ

እዚህ ነኝ ይልሃል አንተ ስትጠፋ፡፡

በአለማችን የሚፈፀም ማንኛውም ነገር በሰው ፈቃድና ፍላጎት ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ እንደሆነ የሚገልፁ ሰዎች፤ አምላክ አይዋሽም፣ ሰው ስላልሆነም አይፀፀትም የሚሉ ጥቅሶችን አስተሳስረው ይከራከራሉ - ሰዎች ቢሮጡ፣ ቢያለሙ፣ ቢያጠፉ፤ ከእጣ ፈንታቸው አያመልጡም በማለት፡፡ ..አይ፤ ሰዎች ከሃጥያታቸው ለመመለስ ቢፈቅዱና ቢተገብሩ፤ አምላክ ያሰብኩባችሁን ክፉ ነገር ተፀፅቼ እተወዋለሁ ብሏል.. በማለት ሌሎች ጥቅሶችንም ጨማምረው የሚከራከሩም አሉ - የሰዎች ህይወት በእጣፈንታ ሳይሆን በራሳቸው በሰዎች ምርጫና ተግባር የሚወሰን እንደሆነ በመግለፅ፡፡

ለእንዲህ አይነት ጥያቄዎች፤ ..አምላክ አምሳያ አለው ወይስ የለውም? ፍቅር ነው ወይስ ቀናተኛ.. ለሚሉ ጥያቄዎች ጭምር በሚቀርቡ ተቃራኒ ምላሾች ከመብሰልሰል ጋር የተያያዙ ይመስላሉ የዳዊት ግጥሞች፡፡ ከሁለት ግጥሞች ቀንጨብ አድርጌ ላክልላችሁ፡፡

ቢረሳን ምናለ!

እኛ ሁላችንም ... የእግዜር ጸጸቶች ነን፤

ትዝ ባልነው ቁጥር ... ሁል ጊዜ የሚገድለን፡፡

መምሰል

የቀና የተበቀለ፣

የጠመመ የገደለ፣

ሰው ብቻ ነው ያልዋለለ፣

እግዚአብሔርን የመሰለ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምላሾችና መከራከሪያ ሃሳቦች ላይ፤ ተጨማሪ ለማቅረብ፣ አስታራቂ ሃሳብ ለማምጣት፣ አንደኛውን ሃሳብ ለመደገፍ ወይም ሌላኛውን ምላሽ ለማጣጣል፤ በዚህም ለመከራከር የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ምላሾችና የእምነት ሃሳቦች እስከዛሬ በብዛት ተሰንዝረዋል፤ ተጨማሪ ምላሾች ሊመጡ አይችሉም ማለቴ ባይሆንም፡፡ ይልቅ መምረጥና መመዘን ነው አስቸጋሪ የሆነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ..አንደኛው መከራከሪያ ጠንካራ ነው፤ ሌላኛው ደካማ ነው.. የሚል ብያኔ አልወጣኝም፡፡ ጠንካራና ደካማ፣ ትክክልና ስህተት ብሎ ለመበየን፤ በቅድሚያ አስተማማኝና መሰረታዊ መመዘኛ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ከሄድን፤ አስተማማኙና መሰረታዊው መመዘኛ፤ ..እውኑ ተፈጥሮ.. ነው፡፡ ከእውኑን ተፈጥሮ ጋር በማመሳከር (በመረጃና በማስረጃ በማረጋገጥ) ነው የአንድ ሃሳብ ትክክለኛነትና ስህተትነት የሚመዘነው፡፡ ይሄ አንድ አማራጭ ነው፡፡ በሁለተኛው አማራጭ፤ ..ሳይንሳዊ መንገድ ዋነኛ የትክክለኛነት መመዘኛ አይደለም.. ካልን ደግሞ፤ እንዲሁ ..ቀልባችን የፈቀደውን.. አምነን መቀበል እንጂ መከራከር አያስፈልገንም፡፡ ክርክር ማለት እንዲሁ ለመሰዳደብና ጊዜ ለማጥፋት ሳይሆን፤ መረጃና ማስረጃ እያቀረብን ትክክለኛ ሃሳቦችን በመመዘኛ እየለየን ለመማማር አይደለም እንዴ? መመዘኛ ከሌለ፤ ክርክር ዋጋ የለውም፡፡

 

 

Read 6837 times Last modified on Saturday, 02 July 2011 15:34