Saturday, 16 July 2011 13:21

ባህላዊ አነስተኛ ጥቃቅን እና “Take away” ምሁራን

Written by  ሌሊሳ
Rate this item
(2 votes)

በመቀጠልየምታነብቡት መጣጥፍ የተወለደው ከሦስት የሀሳብ ጓደኞች     ጋር በቅርቡ ካደረግነው ውይይት ነው፡፡ ውይይቱን ያደረግነው በጭጋጋማ እና ብርድ በወረሰው ቀን ውስጥ ቢሆንም፤ ከጭጋጉ እና ብርዱ ውስጥ ሞቅ ያሉ እይታዎች መነጩ፡፡ የቀኑን ስሜትም ቀየሩት፤ እኔም ውይይታችንን ደርዝ ሰጥቼ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡በመንገድ የራሴን ሀሳብ እያሰብኩ በማዘግምበት ወቅት አንድ የጽሑፍ ባልደረባ እና የዓመታት የውይይት ጓደኛዬ በታክሲ ሲያልፍ አይቶኝ ኖሮ. . . ጉዞውን አቋርጦ ከእኔ ጋር በእግር ለማዝገም ወርዶ ተቀላቀለ፡፡

. . .እየተጨዋወትን ትንሽ እንደተጓዝን አንድ ሻይ ቤት ገብተን መጠነኛ ቁርስ ለማድረግ ተስማማን፡፡ . . .ከጐኔ ያለው ወዳጄ የመረጠው ቤት ትልቅ ትኬት የሚቆረጥበት ነው፡፡ ትልቅ ደረሰኝ የሚቆርጡ ቤቶች ቀጭን ደረሰኝ ከሚቆርጡት የበለጠ ሂሳብ ያስወጣሉ፡፡ እስካሁን የተቆረጠልኝ ደረሰኝ፤ ጫፍ ለጫፍ ቢቀጣጠል የምድርን ወገብ ይዞራል፡፡ የእኔን ወገብ አዙሮታል፡፡ የእኔ ወገብ እየቀጠነ የምድር ወገብ እየሰፋ መጥቷል፡፡ . . .ሁሉም ትኬት የሚቆጥር ሆኗል፡፡ ..ያለዎት ቀሪ ዕድሜ አነስተኛ ነው! . . .እባክዎት ተጨማሪ ዕድሜ ገዝተው ይጠቀሙ... . . የሚል አየር የሚያሳጥር የብዝበዛ ርብርብ አለ፡፡ ከመንግሥት እና ከነጋዴ፣ ከነጋዴና ከመንግሥት. . . ቃሉ ሲደጋገም ..ከ.. የምትለዋ ፊደል መንግሥት እና ነጋዴ ላይ ትጠፋለች፡፡
ከኃይሌ ገ/ስላሴ ህንፃ በታች ያለው ሳይ ኬክ ቤት ውስጥ ነን፡፡ ሁለት ዳኒሽ ኬክ እና ሁለት ቡና አዝዘን ከተጠቀምን ሳይሆን ከቀመስን በኋላ የመጣው ትኬት ላይ ያለው የዋጋ ዝርዝር መንግሥት አብሮን የ4.43 ብር ምግብ መብላቱን ይገልጻል፡፡ ለምደን የሰለቸን ነገር ስለሆነ ተሳስቀን ከፍለን ወጣን፡፡
እየወጣን የሚያልፍ የሚያገድም ታክሲን እያማተርን ..መንግሥት ታክስ በጣም አድርጐ መቁረጥን የተማረው ከምሁራን ነው አይደለም?.. ብሎ ጠየቀኝ፡፡
..አዎን መሆን አለበት.. አልኩት፡፡
መሞከር የተማረ ምሁር ሙከራን ሊያስተምር እንጂ ትግበራን ሊያከናውን አይችልም፤ የሚል ሀሳብ ድንገት በአእምሮዬ ነድዶ አለፈ፡፡
..የምሁር ትርጉም ምንድነው?.. ብዬ ጠየኩት፡፡ ጥያቄውን ሲያስብበት የቆየ ይመስል ፈጣን መልስ ሰጠኝ፡፡
..የሌላውን ዓለም ምሑር ሳይሆን የእኛ ሀገር ምሁር ትርጉም ምርጥ ዘመናዊ እና እይታን የሚያሻሽል መነጽር ሰክቶ ሰውን ሲመለከት ግን በመነጽሩ ሳይሆን መነጽሩን ወደ አፍንጫው ቂጥ ዝቅ አድርጐ በመነሩ እያጌጠ በዓይኑ የሚያይ ማለት ነው.. አለኝ፡፡ (. . .ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት እየሞከርን ያለነው ..ተጨማሪ ዕድሜ.. ለመሙላት ከምናደርገው መፍጨርጨር ምክንያት ነው፡፡ ዕድሜያችንን ምን እንደ..ቀጠረው.. ወይ እንደቆረጠው በመረዳት እየበላን ያለውን ለማወቅ፡፡)
የትርጉሙ ቅልብጭ እና ቁልጭ ማለት የግኝት ሳቅ አሳቀኝ፡፡ የምሁሩ መነጽር የሚወክለው ትምህርቱን ነው፡፡ አይኑ የሚወከለው ደግሞ፤ ከቅድመ ትምህርት በፊት የነበረውን ስሜታዊ ባህላዊ እይታውን ነው፡፡
በዚህ እይታው እየተገረምኩ የሀሳብ ከባቢ አየራችን አድርገን ወደምንገለገልበት ቢሮአችን ገባን፡፡ በደረስንበት ..የምሁር ትርጉም.. ላይ ተጨማሪ ወይም ተቀናሽ አስተያየት ለመፈለግ ሌላው አንጋፋ ወዳጃችን ወደሚኝበት ክፍል እየተከራከረን ገባን፡፡
ያገኘነውን የምሁር ትርጉም ሳንነግረው በፊት ጥያቄ አቀረብንለት ..አንተ የኢትዮጵያ ምሁር ነህ?..
..እኔ ማረሻ ለመሥራት ፕሮፖዛል አልነድፍም፡፡ . . .ማረሻ ለመሥራት ጥናት የሚያደርግ እና የተሠራው ማረሻ ለምን ማረስ እንዳቃተው የትንተና ሪፖርት የሚያቀርብ ነው ምሁር.. አለን አንጋፋው ወዳጃችን፡፡
እኔና አብሮኝ የመጣው ጓደኛ ወንበር ይዘን እየተቀመጥን፡፡ ምን ማለትህ ነው? አልገባንም አስረዳን አልነው፡፡
..አልሰማችሁም ማለት ነው? ባለ ሁለት ማረሻ ያለውን ጥማድ ለመሥራት በምሁሮች የተደረገውን ጥናት እና ፕሮጄክት?.. ብሎ ጠየቀን ከፍተኛ የሆነ ሳቅ በዓይኑ ላይ እየተመላለሰ ነበር፡፡ ብላሽ የሆነ ነገርን አይቶ ማኩረፍ ሲሰለች ቀልድ ፈጥሮ ሀዘንን ለመግደል የሚሳቀው ዓይነት ሳቅ ነበር፡፡ ስለ ምሁራኑ የማረሻ ጥናት እና ፕሮጄክት ይነግረን ጀመር፡፡
..እርሻውን ለማቀላጠፍ እና የባህላዊውን የአስተራረስ ዘዴ ሳይጠፋ ነገር ግን ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ ሲያስቡ የነበሩ ምሁራን፤ ባለ ሁለት መሬት መግመሻ ብረት ያለው ነገር ግን በሁለት በሬ የሚጐተት ማረሻ ንድፍ ያበጃሉ፡፡ ንድፉ ወደ ተግባር ይለወጥና አዲሱ ማረሻ ይፈበረካል፡፡ በጐጆ ኢንዱስትሪ፡፡ በሬ ተጠምዶ አዲሱ ማረሻ ሲሞከር በሬዎቹ ጭራሽ ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም፡፡ አንድ ማረሻ አፈር ላይ ተቸክሎ መጐተት ከባድ እንግልት የነበረው የቀድሞ ዘዴ፤ ሁለት ማረሻ ሆኖ ሲሻሻል ጭራሽ አልንቀሳቀስ አለ፡፡ ማረሻው ማሰሪያ ችካል ሆነ፡፡ ምሁራኑ (ሳይንቲስቶቹ) ግን የበሬው የመጐተት አቅም ማነስ የቀንበር እና ሞፈሩ እንጨት ከብዶት ነው በማለት እንዲቀልለው እንጨቱን በገመድ ቀየሩት፡፡ ተጨማሪ ማሻሻያ እናድርግ ብለው ገበሬው ቆሞ ከሚያርስ ቁጭ ብሎ የሚያርስበትን እንደ ጋሪ ፈረስ ዓይነት መቀመጫ እና ዝናብ እና ሐሩር እንዳይነካው ጭንቅላቱን የሚሸፍን ጥላም ሠሩለት፡፡ . . .አሁንም በሬው ሊያርስ አልቻለም፡፡ የጅራፍ ውርጅብኙ ሲበዛበት እንዲያውም አንገቱን አዙሮ በቀንዱ ቁጭ ብሎ የሚገርፈውን ገበሬ ወጋው፡፡ ምሁራኑ ለዚህ ላልተሳካ እርሻ ሙከራ የጻፉት ሪፖርት የሚደመደመው ..የእርሻው ተግባር ስኬት በበሬው ፈቃድ ላይ መሠረት ያደረገ ነው? በሚል አረፍተ ነገር ነው.. ብሎን አንጋፋው ወዳጃችን ትረካውን ጨረሰ፡፡ ከመነጽሩ ምሳሌ ይበልጥ የሀገራችንን ምሁር ለመግለጽ ይችን ቀልድ ታሪክ የሚያክል ሊገኝ እንደማይችል አሰብኩ፡፡ የድሮ አልከሚስቶች ብረትን ወደ ወርቅ ለመቀየር እንደሚንደፉት የማይመስል ሙከራ አይነት ነው፡፡ ሙከራው ሳይሳካ ሲቀር የሚያቀርቡት ሪፖርት ..ብረቱ በጅብ ቆዳ መታሸት አለበት.. የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ በጅብ ቆዳ ታሽቶም ሳይሠራ ሲቀር ደግሞ ..በጅብ ቆዳ የሚታሸው ጨረቃ ስትጠልቅ በምትፈነጥቀው ብርሃን ነው.. የሚል ምክንያት ይሰጣሉ፡፡ ምክንያቱ አያልቅም፤ ብረቱም ወደ ወርቅ አይቀየርም፡፡
አንጋፋው ወዳጅ ለጠየቅነው ጥያቄ የሰጠን መልስ በአጭሩ ሲቀመጥ ..የማይመስል ጥናት እና ሀሳብ ለመሞከር በምሁርነቱ በጀት አስመድቦ ካባከነ በኋላ ሙከራው ሳይሳካ ሲቀር፤ ያልተሳካበትን ምክንያት መተንተን ምሁር ስለሚያስብል፤ እኔ በዚህ መስፈርት ከታየ ምሁር አይደለሁም.. ማለቱ ነው፡፡
በሳቁ፤ በወሬው እና ፍቺ በመፈለጉ መሀል ከራሴ ጋር ደግሞ ጉባኤ እገባለሁ፡፡ እስከዛሬ በሀገሪቱ ላይ በተለዋወጠው ስርዓት ከፍተኛ ምሁር የመሪነቱ ቦታ ላይ ተቀምጦ የታየው በአሁኑ መንግሥት መሆኑ አያጠያያቅም፡፡
እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ ግን እሰየው የሚያስብለው በምሁር መሪነት ሀገሪቷ የምትመኛቸውን ዓይነት ለውጦች ለማምጣት ከቻለች ብቻ ይሆናል፡፡ ምሁር የበላይ ሲሆን ብልጽግናን አስጨብጦን ካልሆነ የትምህርትም ሆነ የተማሩት ሰዎች ጥቅም ምኑ ላይ ነው? . . .አጉል አዋቂነት አጉል ግራ መጋባት ውስጥ የሚከተን ከሆነ. . . አጉል አዋቂነታቸው ይቅርብን ወይም እውነተኛ አዋቂዎች ይምጡልን፡፡ የባህላዊ አስተሳሰባችን ራሱ እውነተኛ አዋቂነትን የመቀቢያ ከፍት ቦታ አለው? . . .የሰፈነውን ባህላዊ አስተሳሰባችንን መጀመሪያ ሙሉ ለሙሉ መቀየር እንዳለብን የሚነግረንን ምሁር በየትኛው ጆሯችን ልንሰማው እንችላለን? ለመስማት ከባህላዊ ማንነታችን ውጭ የሆነ ጆሮ ማብቀል አለብን፡፡ ወይም በደንብ ባህላዊ ሆነን ምሁርነት ወይም መሻሻል የሚሉ ህልሞቻችንን ማስወገድ አለብን፡፡ ባህላዊ አስተራረሱንም ሙሉ ለሙሉ በትራክተር መቀየር እንጂ ሞፈርን በማወፈር ወይንም በማቅጠን የምንፈልገው ለውጥ አይመጣም፡፡ ምሁርነት ዘመናዊ ቁሳቁስን ተሸክሞ ለባህላዊ አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ አይደለም፡፡
ከማስበው ሀሳብ ጋር የሚገጥም ምሳሌ ከመንገድ ጀምሮ አብሮኝ የመጣው ጓደኛዬ አቀረበ፤ የሀሳብ መንገድ ሲገጣጠም የአንዱ ሀሳብ በሌላው አፍ ወጥቶ ይደመጣል፡፡ ..ለምሳሌ ሞባይል ዘመናዊ እቃ ነው፡፡ እንዴት እንደተሠራ እና እንዴት እንደሚሠራ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የምንጠቀምበት ለባህላዊ የቀድሞ አገልግሎቶቻችን ብቻ ነው፡፡
ለማይንቀሳቀስ አስተሳሰብ የሚንቀሳቀስ ስልጣኔ ሽባ ተደርጐ ካልሆነ ለማቀበል አይቻልም፡፡ ምሁርነትን እንደ ሥልጣኔ ደረጃ ማየት እንችላለን፡፡ የእኛ ምሁራን በመሠረቱ የገዳም ቀሳውስት እና የመለኮት ሰዎች ነበሩ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ወደ ሌላ አለማት ስልጣኔ ከምንጠጋ ወደ ቄስ ትምህርት መውረዱ ነው የሚቀለን፡፡ የምሁራኑ የወቅቱ ሁኔታ የቄስ ትምህርት ቤቱንም ሆነ ስልጣኔውን አይመስልም፡፡ ስልጣኔውም ዘንድ እንዳይደርሱ መነሻቸው ከፍተኛ ስብት አለው፤ ወደነበሩበት ይመስላቸዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ እንዳይመለሱ ስልጣኔው ወደ ላይ YgÖT¬cêL፡፡ መሀል ላይ ተንጠልጥለው ይቀራሉ፡፡ ከሁለቱም ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ መለየት አልቻሉም፡፡ ምሁርም በሁለት ይከፈላል፤ ዘመናዊ ትምህርቱን አጠቃልሎ በዘመናዊ እይታ ወደ ባህላዊ ለመመለስ የሚሞክር፤ እና ባህላዊ ትምህርቱን ንቆ በሙሉ ርቀት ዘመናዊ ለመሆን የሚሞክር፡፡ ሁለቱም ኮንፊውዝድ ናቸው፡፡.. አለ፡፡
..ምሁር እንዲመራን የምንፈልገው ..የተማረ ይግደለኝ.. የምንለው ከባህላዊ ችግሮቻችን ድንቁርና፣ ርሐብ፣ ኋላ ቀርነት፣ በሽታ. . . ተመዋች ምስኪንነት እንዲገላግሉን ነው አይደለም? ወይስ በተማረ ዕይታ መልሶ መላልሶ ባህላዊ ችግሮቻችን ውስጥ እንዲዘፍቁን ስለተፈለገ ነው?. . ... ብዬ ጠየቅሁት፡፡
ጥያቄው ሁላችንም ዘንድ የቆየ፤ መልስ ግን ያላገኘንለት ስለነበር ..ምን አውቃለሁ.. እንደማለት ትከሻችንን ነቅንቀን ዝም አልን፡፡    
..ኢትዮጵያዊ ምሁር.. ማለት ..ባህላዊ ምሁር.. ማለት ነው የሚል ድምዳሜ መጣልኝ፡፡ ኢትዮጵያ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ሀገር ናት፡፡ በቅኝ የገዛት ማንም የለም፤ ከድህነት እና ኋላ ቀርነት bStqR፡፡xþ÷ñ¸SèC ከድህነት መውጫ መንገድ ሲቀር፣ ግብር አስከፋዮች የግብር መሰብሰቢያ ህግ ሲያድቁ ሌላውን ዓለም ሳይሆን ኢትዮጵያን በለቦና ይዘው፤ ስለዚህች ሀገር በተለይ ተገንዝበው መሆን ነበረበት፡፡ ለበሬ ማረሻ እና የእርሻ ተግባርን ለማሻሻል በሬው ላይ ተጨማሪ የሥራ ጫና መጣል ካለበት ሁለት የማረሻ ችካል በመቸከል፣ አንዱ በሬ ሁለት ጊዜ በአንዴ እንዲያርስ የማድረግ ንድፍ የሚሠራ ምሁር በሬውንም ሆነ ገበሬውን ልብ ብሎ ያልተረዳ ነው፤ ተረድቶ አውቆ ከሆነ ደግሞ፤ እንዲሻሻል የማይፈልግ ምሁር ነው፡፡ ገበሬው ከተሻሻለ፣ ችግረኛው ከችግር ከወጣ፣ መሀይሙ ከተማረ የምሁር አስፈላጊነት ይቀንሳል፡፡ የምሁርነት ዋጋ እንዳይረክስ ትምህርቱን እና መፍትሔውን መደበቅ፡፡ የምሁርነት ብቃት ማረጋገጫ ወረቀትን በተስፋ ፈላጊው መሀል ይዞ በመከበር፣ ትምህርቱን እንደ መነጽር አፍንጫ ጫፍ ላይ ሰክቶ በባህላዊ (ተራ) አይን ችግሩን ማየት እና መፍትሔ ሳይሆን ማወሳሰቢያ ትንታኔ መስጠት. . .፡፡በፍጥነት ተሠርቶ የሚደርስ የማዕዱን ክብር የቀነሰበትን ያህል ዋጋው የተወደደ ምግብን በብልጭልጭ ወረቀት አፍኖ ይዞ መሄድን የለመደ ትውልድ የሚመስል ምሁር Take away ብዬ መሰየም ፈለግሁ፡፡ በብልጭልጭ ወረቀት የታሸገ ውስጡን ግን ለቄስ የሚያሰኝ መናኛ ማንነትን ጠቅልሎ የታቀፈ፤ ቀለም የተቀባ መሐይምነት. . .፡፡
. . .y“Take away” ዘመን     “Take away” ምሁራን ላይ ያለንን ቅሬታ በዚህ መልክ ተሳስበን፤ ከሀሳብ ጓዶቼ ጋር ተለያየን፡፡ . . . ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጥ እየተጠበቀ ያለው የተማረ አካል ቢሆንስ! የችግሩ መንስኤ. . . የሚል አዝማሚያ ባለው መዝጊያ ቃለ ጉባኤያችንን አጽድቀን ተበታተንን፡፡

 

Read 6820 times Last modified on Saturday, 16 July 2011 13:54