Print this page
Sunday, 24 July 2011 07:14

በወንዶች ዓለም ውስጥ አንዲት ሴት

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(3 votes)

የአዲስ አበባ ወንድ የመልበሻ ቤት መስተዋትሆኗል፡፡ ሴቶቹ በሱ ፊት ላይ አለባበሳቸውን ያያሉ፤ የአዲስ አበባ መንገዶች፣ ካፌዎች፣ ባሮች፣ ቢሮዎች፣ ሆቴሎች፣ የፀሎት ቤቶች...     አለባበስ ማሳያ መድረኮች ሆነዋል፡፡ ወንዱየጥሞና ጊዜ ተነፍጓል፡፡ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲሰራ፣ሲፀልይ፣ ታክሲ ሲጠብቅ... በሞዴሎች ተከቦ ነው፡፡ ህይወቱ የናይት ክለብ ውስጥ እስረኛ ሆናለች፡፡ ሲወለድ ሳውና ባዝ የገባ ሲሞት ይወጣል፡፡ ኑሮው በላብ መጠመቂያ ሥፍራው ሆናለች፡፡ አይኑ ሸሽቶ የትም አይደርስም፡፡ እድሜ ልኩን መስክ መካከል እንደቆመ ሁሉ በአበባ ተሰላችቷል፡፡ ..ትቢያ.. ናፍቆታል፡፡

ሴቶች፣ የወንዶች አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ሆነዋል፡፡ አይኑን ያገለግላሉ፣ ልቡን ያገለግላሉ፣ ስሜቱን ያገለግላሉ... የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ ..የወንዶች ገበያ.. እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ህይወታቸው በወንዶች ህልም የተፈበረከ ነው፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ከዘንድሮ ሴቶች አይገኝም፡፡ ወንድ የሚፈልገውን ግን አያጣም፡፡ አይኑ፣ ጆሮው፣ አፍንጫው፣ ምላሱ... በሴቶች ትጋት ሥር ተጠምዶ ተደናቅፏል፡፡ አንዲት ሴት ከአንዲት አበባ ጋር በንር ቆማለች፡፡ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጭ ሌላ ህልም የላትም፡፡
እንግሊዛዊው ደራሲ ዲ.ኤች ላውረንስ ይሄንን ታዝቦ አንዲት የመረረች መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ “Give her a pattern” ይላል ርእሱ “The real trouble about women is that they must always go on trying to adapt themselves to men’s theories of women, as they always have done.” ብሏል፡፡ (የሴቶች ዋነኛ ችግር ወንዶች ስለሴቶች የሚኖራቸውን ንሰ ሃሳብ አሟልተው ለመገኘት ሁልጊዜም መጣራቸው ነው)
የዘንድሮ ሴቶች ሴት የመሆን መብት የላቸውም፤ ወንድ የሚፈልገው አይነት ሴት እንጂ፡፡ ሴቶች የወንዶችን ህልም ለመተርጐም ህይወታቸውን የሚሰው ጭዳዎች ናቸው፡፡ በመሰልጠን ሥም እራሳቸውን ለፆታ ባርነት አጋልጠዋል፡፡ ኧረ እንዳውም ከባርነት ወርደው ለአሻንጉሊትነት ተዳርገዋል፡፡ ሁኔታውን “living Doll” ይለዋል Cliff Richard የተባለ አቀንቃኝ፡፡ ..ህያው አሻንጉሊት.. እንደማለት ነው፡፡ “I got myself a sleeping, walking, crying, talking Doll” (እራሴን የምትተኛ፣ የምትሄድ፣ የምታለቅስ፣ የምታወራ አሻንጉሊት ሆኜ አገኘሁት) የዘንድሮ ሴቶች ሰው መሆናቸው የሚረጋገጠው ስለሚተኙ፣ ስለሚሄዱ፣ ስለሚያለቅሱና ስለሚያወሩ ብቻ ነው፡፡ እንደ አበባ ..ንብ.. መጥራት የህይወት ትርጉማቸው ሆኗል፡፡ ከላውረንስ መጣጥፍ እንጥቀስ፤
“When a woman is throughly herself, she is being what her type of man wants her to be, when a women is hysterical its because she doesn’t quite know what to be, which pattern to follow, which man’s picture of woman to live up to.”
(አንዲት ሴት በትክክል እራሷን እንደሆነች የሚቆጠረው በእሷ አንፃር ያሉ ወንዶች እንድትሆን የሚፈልጉትን ሆና ስትገኝ ነው፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የምትጨነቀው ደግሞ በወንዶቹ ፍላጐት መሆን የሚገባት ሳይከሰትላት ሲቀር፤ የትኛውን ሴት የመሆን ሞዴል መከተል እንዳለባት ሲጠፋትና በእንዴት ያለው ወንዶች በሚወዱት የሴቶች ምስል መሰረት መኖር እንዳለበት አልገባት ሲል ነው፡፡)
የሴቶች ፍላጐት የት ነው? ግብ? ምርጫ? ህልም? ህይወት? ኑሮ? ...ከወንዶች አንፃር የሚቆመው እኩልነታቸው የታል? ሰውነታቸውስ? ክብራቸውስ? ነፃነታቸውስ? ...የራሳቸው የሆነው ፍርሃታቸው የትኛው ነው? ሼላ ሮውቦታም የተባለች የሴቶች መብት አቀንቃኝ ..ሌላው ቀርቶ ፍርሃታችን እንኳን የእነሱ (የወንዶች) ነው.. ትላለች፡፡ ከፍርሃት አቅም የተውሶ የሆነበት ህይወት እንዴት ያለው ነው?
የዘንድሮ ሴቶች ግባችሁን መርምሩ፣ ምርጫችሁን መርምሩ፣ ህይወታችሁን መርምሩ፣ ኑሮአችሁን መርምሩ፣ ከወንዶች አንፃር የሚቆመው እኩልነታችሁን መርምሩ፣ ሰውነታችሁን መርምሩ፣ ክብራችሁን መርምሩ፣ ነፃነታችሁን መርምሩ... ፍርሃታችሁን እንኳ የእናንተ መሆኑን መርምሩ...
የኖርዌይ ተወላጁ ፀሐፌ ተውኔት ሔነሪክ ኢብሰን ለሴቶች ተቆርቋሪነቱ ይታወቃል፡፡ ከስምንት አመት ትዳር በኋላ ህይወትና ኑሮዋን የምትመረምር አንዲት ገፀ ባህርይ አለችው፡፡ ኖራ ሔልመር ትሰኛለች፡፡ ከልጅነቷ አንስቶ የነበረው ህይወቷ የአሻንጉሊት እንደነበር ትደርስበታለች፡፡ የተውኔቱ ርእስም “Dolls house” ነው (..የአሻንጉሊቷ ቤት..) የምትተኛ፣ የምትሄድ፣ የምታለቅስ፣ የምታወራ... እንዲሁም የምትወልድና የወለደችውን የምታሳድግ ህያው አሻንጉሊት፡፡ ዓለምና ሥርዓቷ ለሴቶች ገሃነምና የገሃነም ድንጋጌ እንደሆኑ ትደርስበታለች፡፡ ግጭት ውስጥ ትገባለች፡፡ በስተመጨረሻ ወላጆቿን፣ ባሏን፣ ልጇን፣ ቤቷን፣ አካባቢዋን... ለቃ ትሰደዳለች፡፡ ..ማነው ትክክል? እኔ? ወይንስ የተቀረው አለም?.. የመጨረሻ ቃሏ ነው፡፡
የእኛ ሴቶች ጋ የሚጐድለው ይሄ ነው፡፡ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪነት በተቀየረው የወንዶች ፍላጐት ውስጥ መዳከራቸውን አይጠይቁም፡፡ የወንዶች አቅርቦት መሆናቸውን አይመረምሩም፡፡ ዳሌአቸው እንዲኮራ፣ ጡታቸው እንዲቀለበስ፣ አንጀታቸው እንዲሞት፣ አካሄዳቸው እንዲቀየር (ካትዎክ)... ሲጠየቁ ያለ ተጨማሪ ማብራሪያ ያደርጉታል፡፡ ያልተመረመረ ኑሮ ውስጥ የነፃነት ህይወት እንዳሌለ አይረዱም፡፡ ሲወገዝ የነበረው አሮጌው ዓለም በአዲሱ ዓለም ውስጥ አድፍጦ ቀጥሏል፡፡
አሮጌው አለም ከወንዶች አንፃር ሴቶች ምን መምሰል እንዳለባቸው ናሙና ሲፈጥርና ሲያስፈም ቆይቷል፡፡ ጥንታዊዎቹ ሮማውያን ከሐብት ማካበት ፍላጐታቸው አንፃር ተነስተው ሴት ምራቋን ዋጥ ያደረገች ብትሆን የተሻለ እንደሚሆን ያስቡ ነበር፡፡ ከተቻለ ፈት ብትገኝ የካበተው ሃብት አይባክንም ይላሉ፡፡ በመሆኑም የዚያ ዘመን ወጣት ሴቶች በባህርይ ብቻ ሳይሆን በአቋምና በአለባበስም ፈት ለመምሰል ክፉኛ ይጥሩ እንደነበር ላውረንስ ይነግረናል፡፡ ቄሳሩ ኔሮ ለሴቶች የሚያወጣውን መስፈርት ቶሎ ቶሎ እየቀያየረ፣ የአገሪቱን ሴቶች በማደናገሩ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ የዘመኑ ሴቶች በተለዋዋጩ የቄሳር መስፈርት ልክ ..የተንጦለጦለ.. ለውጥ በማድረግ እራሳቸውን በተፈላጊነት ሲያወዳድሩ ነበር፡፡
በዳግም ልደት ዘመን (Renaissances) ደግሞ የተማረች ሴት ተፈላጊነት እንዳላት መታሰብ ተጀመረ፡፡ ለዚህ እንደ ዳንቴ ያሉ ደራሲያን ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳላቸው ይወራል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሴቶች ህይወት ከመፃህፍት ጋር የተጣመረ፣ ከግጥሞች ጋር የተዳበለ፣ የመተንተን ኑሮ ሆነ፡፡ ቻርልስ ዲከንስ የተባለው እንግሊዛዊ ደራሲ በ..ዴቪድ ኮፐርፊልድ.. ልቦለዱ ውስጥ ነፍስ ያላወቀች ሚስት ይዞ ብቅ አለ፡፡ ዶራ ትባላለች፡፡ ምዕራባዊው ወንድ ይቺን ሴት ናሙና አድርጐ ወሰደ፡፡ እንደ ውሃ ላይ ኩበት የሚዋልለው የሴቶች ህይወት፤ ሕፃን ልጅ መስሎ ወደ መታየት አዘነበለ፡፡ ቢራቢሮ ማባረር፣ ለአበባ ቀልብን ማጣት፣ በጨዋታ እራስን መሳት... የሴቶቹ የማስመሰል ውሎ ሆነ፡፡
በኤልሳቤጣዊው ዘመን (16ኛው ክ/ዘመን) ደግሞ አንዳች አስፈሪ መስፈርት ለሴቶች ቀረበ፡፡ ዘመኑ ሐብት ለማሰስ እረጅም ጉዞ የሚኬድ ስለነበር፣ ባሎች የሚስቶቻቸው ነገር አሳሳቢ ሆነባቸው፡፡ በመሆኑም የወሲብ ፍላጐታቸውን ለመገደብ የሴት ልጅ ግርዘት መፍትሄ ሆኖ ቀረበ፡፡ በመሆኑም ሴቶቹ ያለ አንድ ተቃውሞ የሴቶች ግርዘት አስፈፃሚ ሆነው ተገኙ፡፡ ዘመናችን ይሄንን የሴቶች ግርዘት አውግዞታል፡፡ ውግዘቱ ዘመን ስለፈቀደለት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ለመሆኑ ወደፊት የሴት ልጅ ግርዘት አስፈላጊ የሚሆንበት ዘመን ቢመጣና የተፈላጊ ሴት መስፈርት ቢደረግ ሴቶቻችን ይቃወሙ ይሆን? አሁን ባለው ሁኔታቸው አይመስለኝም!! እራቁት አደባባይ እስከመውጣት የቀበጠውን የወንዶች መስፈርት አስተግብረው የለም? ለሚሸፋፈነው ገመና መልሳቸው እንቢ ይሆናል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው፡፡

Read 14691 times