Sunday, 24 July 2011 07:55

የባለቅኔ ምህላና ሠርጐ ገቦቹ

Written by  ከአዘጋጁ
Rate this item
(5 votes)

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ባለፈው ሳምንት ስለ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ህይወት የሚያውቀውን አስነብቦን ነበር፡፡ በዛሬው ጽሁፉ ደግሞ ..የባለቅኔ ምህላ.. በሚል ርዕስ የታተመውን የግጥም መድብል የተመለከተ መጣጥፍ እነሆ ብሎናል፡፡

ፋሲካ ከበደ
..የባለቅኔ ምህላ.. መጽሐፍ በ135 ገፆቹ 51 ግጥሞችን አካቶ ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በስንዱ አሳታሚ በገበያ የዋለውና በባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ በቁም ሁፍ የተፃፉት ግጥሞች አንድነትና ልዩነታቸውን በማጣቀስ እቃኛለሁ፡፡
..የባለቅኔ ምህላ እንደሰዶም?!.. የሚለው ግጥም የትክክለኛውን ግጥም አንድ ሦስተኛ (ሲሶውን) ብቻ አካቶ በተፋለሰ መልክ የቀረበ ነው፡፡ ያም ሆኖ 15 ቃላቶች ተወግደው በምትካቸው ሌላ ቃላቶች ተሰድረውበታል፡፡
..መስፍኔ.. የሚል ስያሜ የተቸረው ግጥም ዋናው ላይ ..መመረጣችሁንና መጠራታችሁን ታፀኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ.. (መሐፍ ቅዱስ) የሚል እንጂ መስፍኔ የሚል ስያሜ የለውም፡፡ ግጥሙም እራሱን የቻለ አንድ ግጥም ሲሆን 17ኛው ገ መጨረሻ ላይ ተቋርጦ ..አሁን ደሞ አንተ አልኩት ቅድም አንቺ ብዬ.. ከሚለው እስከ መጨረሻው ያለው ግጥም በገ 93 ..ጥበበኛውን አለማወቅ ገደለው.. ውስጥ በመውሰድ የተጋጠመ የሁለት ያልተቋጩ ግጥሞች ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡
በገ 112 ስያሜና መጀመሪያ የሌለው በግጥሙ መጨረሻ ..የሰከነች ሰፊና..  የሚል ባልተሟሉ ግጥሞች ከመገለፁ በተጨማሪ ገ 117 ..አንድምታ.. በሚለው ግጥም ውስጥ ..ሰፊና.. ተቀላቅላ ህብር የሌለው የተደበላለቀ ግጥም አድርጐታል፡፡
በመጽሐፉ የተካተቱት ግጥሞች የፊደል ግድፈቶችና የተለወጡ ቃላቶች ከብዛታቸው የተነሳ ሁሉንም ባልገልፃቸውም በጥቅሉ ወርቅን በጠጠር የመተካትና ወፎች የጠረጠሩት የወይን ፍሬ ዘለላ አስመስሎታል፡፡
በግጥሞቹ ውስጥ የፊደሎቹ መወናከር ይዘታቸውን ወደ ሌላ መልክ ከመቀየሩም በላይ እርስ በርስ እንዲጣረሱ አድርጓቸዋል፡፡ ..እነሆ ገ.. ላይ 23 ቃላቶች ፊደላቸው በመደንቆሉ ብቻ ..ሁሌም.. የሚለውን ..ሁኔዋ.. ..አልልም.. የሚለውን ..አልያም.. ..ተወለደ.. የሚለውን ..ተወሰደ.. ..ባንክህን.. የሚለውን ..ባክህን.. በመሳሰሉ ቃላቶች ተገልፀዋል፡፡
..ከወሎ ልጅ ወሎ.. ግጥም ላይ ..በዘሩ የፀና.. የሚለውን ..በዘሩ የፀዳ.. ተብሏል ..አክሱም የብቃት ስም.. ላይ ..አፈኛን.. የሚለውን ..አፈናን.. ተብሏል ..የንጉስ ዳዊት የገና ስጦታ እነሆ.. ላይ ..ጋጡና.. የሚለውን ..ኃጡና.. ..እነሆተ ማዱ.. የሚለውን ..እንሆልህ ሜዳው..፣ ..ልብህ ሲመዝንህ.. የሚለውን ..የልብህ ሲመዘን..፣ ..ዋሻህ.. የሚለውን ..ዋስህ.. አይነቶች ተቀይጠውበታል፡፡
ከዘመን አይሽሬ ረቂቅ ግጥሞቹ መካከል ..እኔ መዩ.. ላይ ..መፍላትንኳ.. የሚለውን ..መፍሳትንኳ..፣ ..ጋርጄ.. የሚለውን ..አርጄ..፣ ..ለቀንበር.. የሚለውን ..ለጐበር..፣ ..ልሆን.. የሚለውን ..ስሆን.. በመሳሰሉ ግድፈቶች ተገልፀዋል፡፡
ከመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ ..እግዜርንም ሸይጣንንም በእኩል ንቀት እየገረመመ ሲያናግራቸው እንደ ዳኛ ነው.. በማለት በስብሐት ለአብ ገብረእግዚአብሔር የተፃፈው (የመጽሐፉን እንጂ የእጅ ጽሁፋቸውን አላየሁትም) ከባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሰብዕና ጋራ አይዛመድም፤ እንዲያውም የግጥሞቹ ዋንኛ መለያው የመስቀል ምስል በመስራት በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የሚል ሳይፍ የገጠመው ግጥም አለመኖሩ ነው፡፡
የመሐፉ መጠሪያ የሆነው ..የባለቅኔ ምህላ.. ግጥም፤ በገ 98 ላይ ..ጌታ ሆይ ነፍሴን ባርካት.. ከሚለው ግጥም ውስጥ በትንሽ በትንሹ እየተመዘዘ ግማሹን ቃላቱን በሌላ በመተካት፣ ግማሹን እንዳለ በማስፈር የታጐረበት ሲሆን በመጽሐፉ ላይ ያልወጣ ..የባለቅኔ ኑዛዜ.. ከሚለው ግጥሞች ውስጥ እየተቀነጨቡ ታክለውበታል፡፡
ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ዱካው ያላረፈችበት ቦታ የለም፡፡ የፃፋቸው ግጥሞች እጅግ ብዙ በሆኑ ሰዎች ዘንድ በክብር ተቀምጠዋል፡፡ መጽሐፉ ብዙዎቹን ከማስደንገጥ ባለፈ አሳዝኗል፡፡ አያ ሙሴን ለማያውቁት ደግሞ መጽሐፉ ከሚያውቁት በላይ ክፉ ተዕኖ እንዳላደረሰባቸው በትንሹም ቢሆን ተስፋ አለኝ፡፡
መጽሐፉ አራት ከደሙ ንፁህ ነኝ ያሉ ባዶ ገፆች አሉት፡፡ ከባለቅኔ ኑዛዜ መጀመሪያውን ቀንጨብ በማድረግ ..ለጉኑዬ ግልባጭ ለብሔሬ ህይዋን ራማ.. የሚለውን ጽሁፉንና እነሆ መልካም እንሁን፡፡
..ለንጉስ ዳዊት መታሰቢያ
ለኔ ቀልብ መሰብሰቢያ ትሁን..
ትንሳኤ ዘዳግም
የባለቅኔ ኑዛዜ
..እንግዲህ አትፍሯቸው...
የማይገለጥ የተከበደ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና.....
ወንጌላዊው ማቲዎስ ወንድሜ
አዬ ሞቴ... አዬኔ...
ከሞቴ ደግሞ አሟሟቴ?
ዳማከሴ ይመስል በማንም መታሸቴ?
ሰው አፍ ገብቼ መሟሟቴ...
አዬ ሞቴ...?
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
 አምላክ
ዓሜን
ዘሚካኤል አረጋዊ
መስከረም 96
ይድረስ ለላይኛው ፍርድ ቤት
የነጉኖ ዘበናይ ችሎት...
አቤት ባይ... እኔና ዓይኔ...
ቀራቢ... ያቺ የልቧን በልቧ አራቢ...
ዝርዝሩ እነሆ
እንደ እያሱ... እንደ አሮን እንደ ሙሴ... አንድ ላይ በራሷ ውስጥ ተቋጥራ ወደ ከንአን የምትደርስ ታማኝ ፈረሰኛ ለመሆኗ አያጠያይቅም - ባይሆን እልህ እንደምርቅ ያነቃት ለት እንባዋ ሁለተኛው ልሳኗ ቢሆንም - ሁለቱም ቢደመሩ ግን ፈገግታዋን አያህሉም... የሆዷን ያንጀቷን ነገር እጇ ሲመሰክር አይቼዋለሁ ለዓመታት...
በክፉም በደጉም በአብሮነት አያሌ ቅዱስ ዮሐንስ ፈሷል... እናም እኔን ስንፍና እንዳጐበጠኝ ስላየሁት እሷ ላይም እንዳያረብብ ሰጋሁ...
ከስጋት በላይ ውጋት... ከንጋት በላይ ትጋት አለ እሚል ቢኖር... በራሱ ውሳኔ... ያውለት ክንድ ተጋት... እንዲል ሃዬ ባይ...
እኔም የዛሬ ተጣብቶኝ ነው መሰል - ለምን ከዚህ በላይ አትበርም... ለምን ናስ ማሰር ቅልጥም ያለኝ ብሎ የሚወለውለውን የመንደር ጉርባ ክንድ አትሰብርም
ለምን ከዚህ በላይ አትማርም... ለምን ለንፈ ዓለም አትዘምርም... እኔ ጭንቅ... እሷ ጥብብ... እኔ ጥብብ እሷ ጭንቅ... ትንቅንቅ ላይ ስላለን...
ክቡር ፍርድ ቤቱ... ብይኑ እንደካህናት ጉባኤ... እርቁ ማህበረ ሥላሴ ሆኖ ግራ ቀኝ እንዲያስማማ ክርስቶስን ዋስ ጠራሁ...
ወስብሐት ለእግዚአብሄር
ከአክብሮት ጋር
ሙሉጌታ ተስፋይ
ግልባጭ
ለብሔረ ህይዋን
ራማ

 

Read 8379 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 07:57