Print this page
Sunday, 24 July 2011 07:59

በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር ፍፃሜ

Written by  ግሩም
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ክለቦች የ2003 ውድድር ዘመን ከትናንት በስቲያ አርባ ምንጭ ከነማ ከአየር ኃይል ባደረጉት የብሔራዊ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ተፈፀመ፡፡ አርባ ምንጭ ከነማ በብሔራዊ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ በመለያ ምቶች አየር ኃይልን አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል፡፡ 48 ክለቦችን በማሳተፍ በተካሄደው የብሔራዊ ሊግ ውድድር በመጨረሻ ዙር በአስር ክለቦች መካከል በተደረገ የምድብ ጥሎ ማለፍ ከቀጠለ በኋላ አርባ ምንጭ ከነማና አየር ኃይል ለዋንጫ ደርሰው ለ2004 ፕሪሚዬር ሊጉን እንደተቀላቀሉ ይታወቃል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያያዞ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የ2004 የውድድር ዘመን ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት 14 ክለቦች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በፕሪሚዬር ሊጉ ላይ አዲስ አበባ ከተማን በመወከል የሚሳተፉት 6 ክለቦች ሲሆኑ እነሱም ደደቢት፣ መከላከያ፣ መብራት ኃይል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ቅ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ የይርጋለም ከተማን በመወከል ደግሞ ሃዋሣ ከነማና ሲዳማ ቡና ይሳተፋሉ፡፡
አዳማ ከነማ ከአዳማ፣ ሙገር ሲሚንቶ ከአሰላ፣ አርባምንጭ ከነማ ከአርባምንጭ፣ አየር ኃይል ከቢሸፍቱ፣ ድሬደዋ ከነማ ከድሬዳዋ እንዲሁም ሃረር ቢራ ከሃረር ከተሞች የተወከሉ የሊጉ ክለቦች ናቸው፡፡
የ2003 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከወር በፊት ሲጠናቀቅ ሊጉን ከመሰረቱት ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በ61 ነጥብ መሪ ሆኖ በመጨረስ ከ13 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ሻምፒዮን ሊሆን እንደበቃ አይዘነጋም፡፡ ቡና በዚህ ውጤቱ በቀጣይ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና በሴካፋው ካጋሜ ካፕ ላይ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ ደደቢት በ58 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ ሰበታ ከነማ፤ ትራንስ፤ ልደታ ኒያላና ፊንጫ ስኳር ከሊጉ እንደወረዱም ይታወሳል፡፡
በኮከቦች ምርጫ የኢትዮጵያው ቡናው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኮከብ ተብሎ 10ሺ ብር ሲሸለም የጊዮርጊስ አጥቂ አዳነ ግርማ የዘንድሮ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ በመመረጡ የ10ሺ ብር ሽልማት አግኝቷል፡፡ በርካታ የስታድዬም ተመልካች አሉላ መመረጥ ነበረበት ብሎ ምርጫውን ተቃውሟል፡፡ በኮከብ ጐል አግቢነቱ ምርጫ ላይ ኮከብ ተጫዋች የሆነው የጊዮርጊሱ አዳነ ግርማና የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በእኩል 20 ጎል ጨርሰው የ10ሺ ብር ሽልማቱን ተጋርተዋል፡፡
የኢትዮጵያን እግር ኳስ አስተዳደር፣ ውድድር፣ ክለቦችና ስፖርተኞችን ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ ማድረስና በስፖርቱ የዕድገትና የለውጥ እንቅስቃሴ መፍጠር የወቅቱ አስፈላጊ አቅጣጫ ነው፡፡ በዚህም ተግባራዊነት የአገሪቱን እግር ኳስ በአህጉራዊ ደረጃ ለተወዳዳሪነት ማብቃትን ማለም ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በሚያደርጉት የውድድር እንቅስቃሴ በፊፋ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ደንብና የውድድር መስፈርቶች እንዲመሩ ከ5 ወራት ያነሰ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ፊፋ የዓለም እግር ኳስ በፕሮፌሽናል የውድድር መስፈርትና መዋቅር እንዲመራ ለአባል ፌዴሬሽኖቹ መመሪያውን ካሰራጨ 2 ዓመት ያለፈው ሲሆን ይህንኑ መመሪያ ፌዴሬሽኖቹ እንዲያስፈፀሙ ደግሞ እስከ ኖቬምበር 2011 እ.ኤ.አ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ መስፈርቶችን በሚያሟላ ሊግና ክለቦች የተወዳደሩ ብቻ በአህጉራዊ ውድድሮች የመካፈል ፈቃድ ይኖራቸዋል በሚልም ጥብቅ ትዛዙን አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ እንዲያድግ ፊፋ ካስቀመጠው ቀነ ገደብ መቃረብ አንፃር በባለድርሻ አካላቱ አንዳንድ በርካታ ስራዎች አለመስራታቸው ያሳስባል፡፡ ይሁንና ባለው ጊዜ ፌዴሬሽኑ፤ ክለቦችም ሆነ ሌሎች የእግር ኳስ ስፖርት ባለ ድርሻ አካላት ወደ ፕሮፌሽናል አቅጣጫ ለመግባት ተስፋ በማድረግ ስርነቀል የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም በሊግ ደረጃ በሚደረግ ውድድር ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች በአማካይ ዓመታዊ በጀታቸው እስከ 4 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ እስከ 100 ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ እያደረጉ ሲወዳደሩ ቆይተዋል፡፡ ይሄው ከፍተኛ ገንዘብ ክለቦች በፕሮፌሽናል የሊግ መዋቅርና አቅጣጫ እንዲሠሩ በቂ መነሻ በጀት ሊሆን ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ በፕሮፌሽናል አደራጃጀትና መዋቅር ሲመራ በመጀመሪያ እርምጃው ለምሳሌ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሊቲድ ተብሎ በራሱ ንግድ ፍቃድ ኃላፊነቱ የግል ኩባንያ ሆኖ ሊሰራ ይችላል፡፡ ይሄው ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ ባለቤትነቱ በተወዳዳሪ የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች የተያዘ ይሆናል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በበላይነት የእግር ኳሱን የልማት እንቅስቃሴ በማከናወን በሊጉ ኩባንያ የአክሲዮን ድርሻ ኖሮት በሊጉ አመራር ቦርድ አባልነት ይሰጠዋል፡፡ እግር ኳሱን ሊመሩ የሚገባቸው በስፖርቱ በቂ ተሞክሮና ልምድ ያላቸው እንዲሁም በቂ እውቀትና ትምህርት ያያዙና በሙለ ጊዜ የሚሰሩ ፕሮፌሽናል ግለሰቦች መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህም በሌሎች የሴካፋ ዞን አገራት በሚካሄዱ ሊጐች የታዩ የለውጥና የእድገት ብልጭታዎችን እንደመነሻ መከተል ያስፈልጋል፡፡ እንዴት? በቀጣይ ሳምንታት የምንመለስበት ይሆናል፡፡

 

Read 4631 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 08:06