Sunday, 31 July 2011 13:58

የማንጐ ጐዳናው ቤት

Written by  ደራሲ - ሳንድራ ሲስኒሮስ ተርጓሚ - ቃልኪዳን ይበልጣል
Rate this item
(3 votes)

ስለፀሐፊዋ
ከሜክሲኮ ተነስተው አሜሪካ ሺካጐ ከደረሱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ወላጆች የተገኘችው ሳንድራ ሲስኒሮስ እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም ነው ሁለት ሚሊዮን ቅጂ ተሸጧል የሚባለውና መወድስ የሚዘንብለት The House on Mango Street የሚሰኝ እጥር ምጥን ያለ መጽሐፏን ያሳተመችው፡፡ የመጽሐፉ ስኬት እንዲሁም ከዚያ በኋላ አደባባይን ያወቁ የስንኝና ዝርው ስራዎቿ ተደምረው በሀገሯ ከአነስተኛ ማህበረሰብ መሃል ፈልቀው የስነ-ሁፍን ከፍታ ከተቆናጠጡ እንስት ፀሐፍት እንደ አንዷ እንድትቆጠር አስችለዋታል፡፡

መጽሐፉ አርባ አራት አጭርና ራሳቸውን ችለው የሚነበቡ ትረካዎችን ይዟል፡፡ ትረካዎቹ እርስ በርስ ስለተሰናሰሉ መደዳውን ለተወጣቸው የተሟላ ታሪክ ያቀብላሉ፡፡
ሺካጐ ከተማ ውስጥ ድሃ የላቲን አሜሪካ ስደተኞች ከሚኖሩባት ጭርቁንስ መንደር ወይም ባሪዮ (barrio) ሊያመልጥ የሚባትል አንድ ቤተሰብ አለ፡፡ የቤተሰቡን ውጣ ወረድ ቀለል አድርጋ የምትነግረን ትንሿ ልጅ እስፕራንዛ ኮርዴሮ ነች፡፡ ከትረካዎቹ የመጀመርያውና ለመጽሐፉ ርዕስ የሆነው እንዲህ ተተርጉሟል፡፡
***
ማንጐ ጐዳናን ዝንተ ዓለም አልኖርበትም፡፡ ቀድሞ ሉሚስ ኖረናል፡፡ ሦስተኛ ፎቅ ላይ፡፡ ከእርሱ በፊት ደግሞ ኪለር ነበርን፡፡ ከኪለር በፊት ፓውሊና፡፡ ከፓውሊና በፊት እንኳ አይታወሰኝም፡፡ በደንብ የማስታውሰው በየጊዜው መኖርያ እንደምንቀያይር ነው፡፡ ታዲያ ጓዛችንን ሸክፈን ለአዲስ ህይወት የምንንደረደረው አንድ አዲስ ሰው እየጨመርን ይመስላል፡፡ ማንጐ ጐዳና ስንሰፍር ራሱ ስድስት ደርሰናል፡፡ እማማ፣ አባባ፣ ወንድሞቼ ካርሎስና ኪኪ፣ እህቴ ኔኒ እና እኔ፡፡
የማንጐ ጐዳናው ቤት የኛ ነው፡፡ ለማንም ኪራይ የማንከፍልበት፣ የመጫወቻ ሜዳውን ከበታቻችን ከሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ጋር የማንጋራው፣ እየተሳቀቅን የድምፃችንን መጠን የማንቆጥብበት፣ ጣራችንን በመጥረጊያ የሚደለቅ የቤት አከራይ የሌለበት የራሳችን ታዛ፡፡ እንዲያም ሆኖ ይኖራል እያልን ከማሰልንለት የሃሳባችን ቤት ጋር በምኑም አይገጥምም፡፡
የሉሚሱን መኖሪያችንን የለቀቅነው በጥድፊያ ነው፡፡ እጅጉን ከማርጀቱ የተነሳ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦው ቢሰበርም አከራዩ ሊያስጠግኑት አልወደዱም፡፡ መፍጠን ነበረብን፡፡ ከጐናችን የሚገኙ ጐረቤታችንን የመታጠቢያ ክፍል ለመጠቀም፣ ውሃ በባዶ የወተት ማከማቻዎች ለመቅዳት ተገደናላ፡፡ ለዚያም ነው እማማ እና አባባ የተሻለ ቤት ማሰሱን የተያያዙት እና ወደዚህኛው የከተማዋ ጫፍ የመጣነው፡፡
ሁሌም አበክረው የሚነግሩን አንድ ቀን እስከመቼውም የግላችን ወደሚሆን ሁነኛ ቤት እንደምንገባና ከአመት አመት መንከራተቱን እንደምንገላገለው ነው፡፡ ያኔ ውሃ እንደ ልባችን እንቀዳለን፡፡ ቧንቧዎቻችን አይበላሹም፡፡ የውስጥ ደረጃዎቻችን በቴሌቪዥን እንደምናየቸው አይነት ምርጥ ደረጃዎች እንጂ ዝም ብሎ ተራ መተላለፊያዎች አይሆኑም፡፡ አንድ ክፍል ከምድር በታች እና ቢያንስ ሦስት የመታጠቢያ ቤቶች ስለሚኖሩን ገላችንን ልንለቃለቅ ስንፈልግ ለቤተሰቡ አባላት በሙሉ ማወጅ አይኖርብንም፡፡ ቀለሙ ነጭ፣ በዛፎች የተከበበ፣ ሰፊ የአትክልት ስፍራን የታደለና አጥር ባልከለለው ሳር የለመለመ ግሩም ቤት፡፡ አባባ የሎተሪ ቲኬት ጨብጦ ማውራት የሚቀናው፣ እማማ ወደ እንቅልፍ ቅጥር የሚሸኙንን ተረቶች ስትነግረን የምታልመው ያንን ነው፡፡
የአሁኑ ቤታችን ግን በጭራሽ እንደነገሩን አይነት አይደለም፡፡ እንዲያውም ትንሽ፣ ቀለሙም ቀይ ነው፡፡ በፊቱ በኩል ጠባብና የተጠባበቁ ደረጃዎች አሉት፡፡ የመስኮቶቹ ማነስ ትንፋሻቸውን ዋጥ ያደረጉ ያስመስላቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ጡቦቹ መፈራረስ ጀምረዋል፡፡ የመግቢያው በር አብጦ ስለተነፋፋ በሃይል ካልተገፋ አይከፈትም፡፡ የከተማው ማዘጋጃ የተከላቸው ጥቂት ዛፎች ከወደ ቅያሱ ከመቆማቸው በቀር አፀድ ብሎ ነገር ድራሹም የለ፡፡ ከበስተጀርባ ገና ላልገዛነው መኪና ማቆሚያ ተዘጋጅቷል፡፡ በሁለት ትልልቅ ህንፃዎች መካከል በመሸጐጧ የበለጠ አንሳ የምትታይ ሚጢጢ ጓሮም እንደ አቅሚቲ አለችን፡፡ በርግጥ ቤቱ ከውስጥ ደረጃዎች አሉት፡፡ ግን ተራ ደረጃዎች ተራ፤ መውጫና መውረጃዎች ናቸው፡፡ አንድ ለእናቱ የሆነው መታጠቢያው ጥበቱ አይጣል ነው፡፡ በዚያ ላይ ሁላችንም መኝታ ቤት ተጋርተን ነው የምናድረው፡፡ እማማ እና አባባ፣ ካርሎስና ኪኪ፣ እኔና ሄኒ፡፡
አንዴ ሉሚስ እያለን ነው፡፡ ውጪ ስጫወት ት/ቤታችን የማውቃቸው መነኩሲት አዩኝ፡፡ ከኛ አንድ ፎቅ ዝቅ ብሎ ያለው ላውንደሪ ከሁለት ቀናት በፊት በመዘረፉ ቢታሸግም፣ ባለቤቱ ገበያውን ላለማጣት በአንዲት እንጨት ላይ ..አዎ ስራ ላይ ነን.. የምትል ማስታወቂያ ቢጤ ሰክቶ አቁሟል፡፡
መነኩሲቷ ..የት ነው የምትኖረው?.. ሲሉ ጠየቁኝ፡፡
..እዚያ.. ወደ ሦስተኛው ፎቅ እየጠቆምኩ መለስኩ፡፡
..የምትኖረው እዚያ ነው?.. አይኖቻቸውን ተከትዬ ሦስተኛውን ፎቅ አሻግሬ ስመለከት፣ ደርቆ እየተፈረካከሰ የሚወድቀውን የግድግዳ ቀለም፣ በመስኮት ሾልከን እንዳንወድቅበት አባባ የሰራውን የእንጨት ፍርግርግ በደንብ አጤንኩት፡፡ የመነኩሲቷ አነጋገር በውስጤ የባዶነት ስሜት ፈጠረብኝ፡፡
..እ...ዚያ፤ የምኖረው እዚያ ነው፡..
ያኔ ነው ያወቅኩት ሁነኛ ቤት እንደ¸ÃSfLgŸ”” ጣቴን ቀስሬ በኩራት የማመላክተው እውነተኛ ቤት፡፡ ይሄ ግን ፈሞ አይደለም፡፡ ማንጐ ጐዳና ላይ አንድ ቀን የሚኖረን ቤት ከቶውንም እንዲህ አይነቱ ሊሆን አይችልም፡፡ ..ግድ የለም ለጊዜው ያህል ነው.. ትላለች እማማ፡፡ ..አንዘልቅበትም.. ይላል አባባ፡፡ እኔ ግን እንዲህ ያሉትን ነገሮች መረዳት ብዙም አልከበደኝ፡፡

 

Read 6518 times Last modified on Sunday, 31 July 2011 14:01